Friday, June 9, 2023
- Advertisment -
- Advertisment -

ኢትዮጵያ እየቆሰለችና እየደማች ዝም አይባልም!

ኢትዮጵያ በተደጋጋሚ እየቆሰለችና እየደማች ነው፡፡ ኢትዮጵያዊያን በማንነታቸው ምክንያት እንደ አውሬ እየታደኑ እየተገደሉ ነው፡፡ ኢትዮጵያን ከገባችበት ፈተና በፍጥነት ለማውጣት ልጆቿ በጋራ ብሔራዊ ጉዳዮች ላይ ተቀምጠው መነጋገር አለባቸው፡፡ አሁን የተያዘው ጎዳና አደገኛ ስለሆነ በፍጥነት መላ ማለት ይበጃል፡፡ ኢትዮጵያን የሰላም፣ የዴሞክራሲና የነፃነት አገር ማድረግ የሚቻለው በሕጋዊና በሰላማዊ የፖለቲካ ፉክክር እንጂ፣ አሁን እንደሚታየው በሁከትና በግጭት አይደለም፡፡ የኢትዮጵያ ሕዝብ የሚፈልገው ሰላም፣ ነፃነት፣ ፍትሕና እኩልነት ነው፡፡ በኢትዮጵያ ሕዝብ ስም የምትነግዱ ከሰላማዊ የፖለቲካ ትግል አፈንግጣችሁ የማንን ዓላማ ነው የምታሳኩት? ሕዝቡን ከድህነት ማጥ ውስጥ ለማውጣት የሚያስፈልገው ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ነው፡፡ ስለትናንቱ አይረቤ ሥርዓት ከመነታረክ ነገ የሚፈጠረውን የተሻለ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ማለም ነው የሚበጀው፡፡ ይህ ሥርዓት ዕውን የሚሆነው በሕዝብ ድምፅ ብቻ እንደሆነ ግልጽ ነው፡፡  ለዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ በማይመጥን ባህሪ ለሕዝብ ቆሜያለሁ ማለት ቀልድ ነው፡፡ ዓይንና እጅን በሕገወጥ መንገድ የሚገኝ ሥልጣንና ጥቅም ላይ አድርጎ በሕዝብ ስም መነገድ የለየለት ቁማርተኝነት ነው፡፡ ለአገርና ለሕዝብ የሚያስቡ ሥልጣንና ገንዘብ አያማልላቸውም፡፡ የእነሱ ፍላጎት ከአገር ብሔራዊ ጥቅምና ደኅንነት በታች እንደሆነ ይገነዘባሉ፡፡ ሕዝብ በሕዝብ ላይ እያነሳሱ አያጋድሉም፡፡ የአገርን ሰላም እያደፈረሱ ቀውስ አይፈጥሩም፡፡ ከሴራና ከአሻጥር የፀዱ በመሆናቸው ተግባራቸው ግልጽ ነው፡፡ ጨለማ ውስጥ መሽገው አገር አይበጠብጡም፡፡ ሕዝብ በተቃውሞ አደባባይ ወጥቶ በቃ ሲል ማዳመጥ የግድ ነው፡፡ ኢትዮጵያ እየቆሰለችና እየደማች ነው፡፡

የጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (/) መንግሥት የሕዝቡን ሰላምና ደኅንነት የማስከበር ኃላፊነት ሲኖርበት፣ የአገርን ብሔራዊ ደኅነነት የማስጠበቅ ግዴታም አለበት፡፡ ይህንን ግዴታና ኃላፊነት ለመወጣት ደግሞ በሕግ የተሰጠው ሥልጣን አለው፡፡ በዚህ ሥልጣኑ ሕግና ሥርዓት ማስከበር አለበት፡፡ ምንም እንኳ መንግሥት ኃላፊነቱን በአግባቡ ለመወጣት ብልኃትና ጥበብ ቢያስፈልገውም፣ ሕግ የማስከበር ተግባሩ ግን ፈጽሞ ለድርድር መቅረብ የለበትም፡፡ የዜጎችን መብቶችና ነፃነት የማክበር ሥራው ሳይዘነጋ፣ ሕገወጥ ድርጊቶችን አደብ ማስገዛት የግድ ነው፡፡ በተለይ የአገርን ሰላም የሚያናውፅ፣ የዜጎችን ሕይወትና ንብረት አደገኛ ሁኔታ ውስጥ የሚከት ድርጊት በተደጋጋሚ ሲያጋጥም ኃላፊነትን መዘንጋት ያስጠይቃል፡፡ በዚህ ጊዜ በርካቶች መንግሥት ለምን ሕግ አያስከብርም ሲሉ ይጠይቃሉ፡፡ መንግሥት ሕግ ማስከበር ተስኖት ተከታታይ ጥቃቶች እየተፈጸሙ ንፁኃን ሲገደሉ፣ ለአካል ጉዳት ሲዳረጉ፣ ሲፈናቀሉና ሲዘረፉ፣ እንዲሁም የአገር ንብረት ሲወድም በስፋት ተስተውሏል፡፡ ጥቃቶቹ አድማሳቸውን እያሰፉ አገር ወደ ማፍረስ እያመሩ ነው፡፡ የአገር ሰላም ከድጡ ወደ ማጡ ሆኖ የመንግሥት ያለህ ሲባል፣ መንግሥት ደግሞ በሙሉ አቅሙ መኖሩን ማሳየት አለበት፡፡ ሕዝብ በቃ እያለ ነው፡፡ ኢትዮጵያ እየቆሰለችና እየደማች ነው፡፡

ኢትዮጵያ ጠንካራ አገር ሆና ፀንታ መቆም የምትችለው ማንኛውም ሰው ከሕግ በታች ሲሆን ነው፡፡ ይህንን ማድረግ አለመቻል ግን አደገኛ የሆነ ቀውስ ውስጥ ይከታል፡፡ በተለያዩ ክልሎች ውስጥ እየታዩ ያሉ ግጭቶች፣ የቤተ እምነቶች ቃጠሎ፣ የንፁኃን ዕልቂትና መፈናቀል፣ በየቦታው መንገድ በመዝጋት የሰዎችንና የምርቶችን እንቅስቃሴ ማወክ፣ በአጠቃላይ አገርን ቀውስ ውስጥ የሚከቱ ቅስቀሳዎች መበራከትና የመሳሰሉት በሕግ ማስከበር ማቆም ካልተቻለ ቀውሱ እየተጠናከረ ነው የሚሄደው፡፡ ጠንካራ ተቋማትና አስፈጻሚዎች ማግኝት ብርቅ በሆነበት አገር ውስጥ አጉራ ዘለሎች እንዳሻቸው የሚፈነጩበት ዕድል ከተስፋፋ፣ እንኳንስ ምርጫ ማከናወንና በሕዝብ የተመረጠ መንግሥት መመሥረት ቀርቶ የአገር ህልውናም ያጠራጥራል፡፡ የአገሪቱን ህልውና እየተገዳደሩ ካሉ ኃይሎች በተጨማሪ ከውጭ ሆነው አደጋ የደቀኑም አሉ፡፡ አልሸባብን የመሰለ ለምንም ነገር የማይመለስ ሽብርተኛ ኃይል በቅርብ ርቀት እያለ፣ በዓባይ ውኃ የመጠቀም ተፈጥሯዊ መብትን የሚጋፋ አደገኛ ጠላትነት ተጋርጦ፣ የውስጥ ክፍፍሉ ሰፊና ጥልቅ እየሆነ ቸልታ ማብዛት አደጋው የከፋ ነው፡፡ ኢትዮጵያ በሥርዓት መኖር የምትችለው፣ መንግሥት ሕግ የማስከበር ኃላፊነቱን በብቃት መወጣት ሲችል ብቻ ነው፡፡ ኢትዮጵያውያን በገዛ አገራቸው እየታረዱ ሥርዓተ አልበኝነት እየተንሰራፋ፣ የውጭ ጠላትን መመከት አይቻልም፡፡ ሕዝብ በቃ ሲል ማዳመጥ ያስፈልጋል፡፡ ኢትዮጵያ እየቆሰለችና እየደማች ነው፡፡

ኢትዮጵያውያን ፖለቲከኞች፣ የሰብዓዊ መብት ተቆርቋሪዎች፣ የነፃነት አፈ ቀላጤዎች፣ ለሕግ የበላይነት፣ ለአገርና ለወገን ቆመናል የምትሉና ኃላፊነት እንዳለባችሁ የምትረዱ ወገኖች በሙሉ፣ ኢትዮጵያን ካለችበት ተስፋ አስቆራጭ ሁኔታ ውስጥ ተባብራችሁ አውጧት፡፡ ኢትዮጵያ ስትደክም ባዕዳን እጅ ጠምዛዦች ብሔራዊ ጥቅሟንና ደኅንነቷን አደጋ ውስጥ ይከታሉ፡፡ ኢትዮጵያ በሁለት እግሯ መቆም ካልቻለች እንኳንስ የህዳሴ ግድብ ግንባታን ማስቆም፣ የዓባይን መነሻዎች ሳይቀር እንቆጣጠር ይላሉ፡፡ ኢትዮጵያዊያን ሲከፋፈሉና እርስ በርስ ሲጋጩ ኢትዮጵያ በዝታባችኋል ብለው፣ እንደ ዩጎዝላቪያና ሶቪዬት ኅብረት ትንንሽ አገሮች እንድንፈጥር ያስገድዱናል፡፡ እንኳንስ የሰው ኃይላችንንና የተፈጥሮ ሀብቶቻችን ለመጠቀምና ለማልማት፣ ኢትዮጵያን በቁጥጥራቸው ሥር አውለው ቅኝ እንግዛችሁ ማለታቸው አይቀርም፡፡ ሌላው ቀርቶ መጪውን ምርጫ እርስ በርስ ተባልተን አገር እንድናፈርስበት ይጠቀሙበታል፡፡ ምርጫው በትክክል ተካሂዶ ሕዝብ የመረጣቸውን በሰላም ሥልጣን ማስያዝ እንዳይቻል፣ ምርጫውን የእርስ በርስ ጦርነት ማስነሻ ለማድረግ የሚቋምጡ ኃይሎች አይኖሩም ብሎ መዘናጋት የዋህነት ነው፡፡ ኢትዮጵያ ተስፋ ያላት ትልቅ አገር ናት፡፡ ነገር ግን ይህንን ተስፋ ማለምለም የሚቻለው ከሴረኞችና ከመሰሪዎች በመጠበቅ ነው፡፡ ይህንን ተስፋ ብሩህ ማድረግ የሚቻለው ከዘመናት ስንፍና በመላቀቅ ነው፡፡ የኢትዮጵያ ተስፋ ዕውን መሆን የሚችለው ከወሬና ከአሉባልታ ይልቅ፣ ምክንያታዊ የሆነ ትውልድ ኮትኩቶ በማሳደግ ጭምር ነው፡፡ የኢትዮጵያ ተስፋ የሚያንሰራራው ልጆቿ በሙሉ ሲተባበሩ ነው፡፡ ሕዝብ በቃ ብሎ አስጠንቅቋል፡፡ ኢትዮጵያ እየቆሰለችና እየደማች ነው፡፡ 

የኢትዮጵያ ሕዝብ በረዥሙ ታሪኩ የሚታወቀው በአስተዋይነቱና በአርቆ  አሳቢነቱ ቢሆንም፣ ከውስጡ ወጥተው ሥልጣን የሚቆናጠጡ ብዙዎቹ ግን ለዚህ ያልታደሉ ነበሩ፡፡ ቢታደሉማ ኖሮ የኢትዮጵያ ሕዝብ ለዘመናት የድህነት መጫወቻ ባልሆነ ነበር፡፡ አርቆ አሳቢዎች ቢሆኑ ኖሮ ኢትዮጵያ የተፈጥሮ ሀብቶቿ ለምተው ካደጉት አገሮች ተርታ ትሠለፍ ነበር፡፡ ስንዴ ማብቀል የሚችሉ ሰፋፊ ሁዳዶቿ ፆማቸውን አድረው ምፅዋት ጠባቂ አትሆንም ነበር፡፡ የኢትዮጵያ ሕዝብ የሚታወቅባቸው የግጭት አፈታትና የሽምግልና ሥርዓቶቹ ወደ ጎን ተብለው፣ የግጭት መናኸሪያ አትሆንም ነበር፡፡ የተለያዩ እምነቶች በሰላም መኖርን ለዓለም ባሳዩባት ኢትዮጵያ፣ የፖለቲካ ልሂቃን እርስ በርስ አይበላሉም ነበር፡፡ የዴሞክራሲን እሴቶች ከማንም ቀድማ ተግባራዊ ባደረገች አገር ውስጥ፣ አምባገነኖች እየተፈራረቁ ሕዝቡን አሳሩን አያበሉትም ነበር፡፡ ይሉኝታና ኃፍረት የሞራል ጥግ በሆኑበት ማኅበረሰብ ውስጥ፣ አገር የዘራፊዎች መፈንጫ አትሆንም ነበር፡፡ ጨዋነትና ቁጥብነት በሚያስከብሩባት አገር ውስጥ፣ መረኖችና ባለጌዎች አይፈነጩም ነበር፡፡ ሌሎች በርካታ ንፅፅሮችን ማንሳት ይቻላል፡፡ ነገር ግን ሁሌም ለፀፀት የሚዳርጉ ነገሮች እየበዙ ተስፋ ያስቆርጣሉ፡፡ ተስፋ መቁረጥ ደግሞ ከበርካታ መልካም አጋጣሚዎች ጋር ያለያያል፡፡ ሕዝብ በቃ እያለ ነው፡፡ ኢትዮጵያ እየቆሰለችና እየደማች ነውና፡፡

በዚህ ዘመን ትዕግሥት፣ ማስተዋልና አርቆ አሳቢነት በጎደላቸው ፖለቲከኞችና ልሂቃን ምክንያት ከፍተኛ ጥፋት እየደረሰ ነው፡፡ ለሕዝብና ለአገር ኃላፊነት የማይሰማቸው በሕዝብ መካከል መጠራጠርና ጥላቻ ይዘራሉ፡፡ በብሔርና በሃይማኖት ለማጋጨት ያደባሉ፡፡ በእነሱ የተቀሰቀሱ ኃላፊነት የማይሰማቸው ወገኖች ግጭት በማስነሳት የንፁኃንን ሕይወት ያጠፋሉ፣ ንብረት ያወድማሉ፣ ቤተ እምነቶችን ያቃጥላሉ፡፡ ከዚህም አልፈው ተርፈው የአገርን ህልውና እየተፈታተኑ የሕዝብን ደኅንነት ያቃውሳሉ፡፡ ከእንዲህ ዓይነት ችግሮች በስተጀርባ ያሉ ኃይሎች ዓላማሥልጣንና ጥቅም ማጋበስ በተጨማሪ፣ አገር ለማፍረስ መሆኑ ግልጽ ከሆነ ሰነባብቷል፡፡ ሕዝቡ ለዘመናት አብሮ የገነባቸውን ታሪካዊ እሴቶችመናድ የታሪካዊ ጠላቶችን ፍላጎት ለማስፈጸም እየሠሩ ነው፡፡ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ኢትዮጵያ ውስጥ ያጋጠመው ፈተና አገር አፍራሽነት ነው፡፡ ሕዝብ አደባባይ ወጥቶ በቃ ብሏል፡፡ ኢትዮጵያ እየቆሰለችና እየደማች ዝም አይባልም መባል አለበት!

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

የተጨማሪ እሴት ታክስ አዋጅን የሚተካ ረቂቅ ተዘጋጀ

ከቫት ነፃ የነበረው የኤሌክትሪክ ኃይል ገደብ ተቀመጠለት የገንዘብ ሚኒስቴር ከሃያ...

መንበሩ ካለመወረሱ በስተቀር መፈንቅለ ሲኖዶስ መደረጉን ቤተ ክህነት አስታወቀ

ቅዱስ ሲኖዶስ ከነገ ጀምሮ ውይይት እንደሚጀምር ተነገረ ‹‹እኛ ወታደርም ሆነ...

ኢትዮጵያን ከሱዳን የሚያገናኝ የባቡር መስመር ለመገንባት የሚያስችል የአዋጭነት ጥናት ተጠናቆ ለውይይት ቀረበ

ኢትዮጵያን ከሱዳን የሚያገናኝ የባቡር መስመር ለመገንባት በሁለቱ አገሮች የተያዘውን...

ብሔራዊ ባንክ ለጥቃቅንና አነስተኛ ብድሮች ዋስትና መስጠት ሊጀምር ነው

ኢንተርፕራይዞችን ብቻ የሚያገለግል የፋይናንስ ማዕከል ሥራ ጀመረ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ...
- Advertisment -

ትኩስ ፅሁፎች

ወልቃይትን ማዕከል ያደረገው የምዕራባዊያን ጫና

በትግራይ ክልል የተከሰተው የዕርዳታ እህል ዘረፋ የዓለም አቀፍ ተቋማት...

ከቀጣዩ ዓመት በጀት ውስጥ 281 ቢሊዮን ብሩ የበጀት ጉደለት ነው ተባለ

ለቀጣዩ በጀት ዓመት ከቀረበው 801.65 ቢሊዮን ብር አጠቃላይ በጀት...

የኢትዮጵያ ምርት ገበያ ከተለመደው አሠራር ወጣ ያለውን ‹‹የወደፊት ግብይት›› ሥርዓት በይፋ አስጀመረ

የኢትዮጵያ ምርት ገበያ ከተለመደው የማገበያየት ተግባሩ ወጣ ያለና በኢትዮጵያ...

የባንክ ማቋቋሚያ መሥፈርት እንደሚጠነክር ሚኒስትሩ ተናገሩ

 ባንኮች ስለውህደት እንዲያስቡም መክረዋል በኢትዮጵያ ውስጥ ባንክ ለማቋቋም የሚያስፈልገው መሥፈርት...
spot_img

ተዛማጅ ፅሁፎች

አገር አጥፊ ድርጊቶች በአገር ገንቢ ተግባራት ይተኩ!

ኢትዮጵያ ውስጥ በስፋት የሚስተዋሉ ችግሮችን ለመፍታት በመንስዔዎች ላይ መግባባት ያስፈልጋል፡፡ መግባባት ሊኖር የሚችለው ደግሞ በሠለጠነ መንገድ ለመነጋገር የሚያስችል ዓውድ ሲፈጠር ነው፡፡ ለዚህ ስኬት ዕውን...

ሕገ መንግሥት ለማሻሻል ባህሪን መግራት ያስፈልጋል!

በሥራ ላይ ያለው አወዛጋቢ ሕገ መንግሥት ከፀደቀበት ከ1987 ዓ.ም. ጀምሮ እስካሁን ድረስ ከተለያዩ አቅጣጫዎች ወቀሳዎችና ተቃውሞዎች ይቀርቡበታል፡፡ ከተቃውሞዎቹ መካከል በሕገ መንግሥቱ መግቢያ ላይ ኢትዮጵያዊነትን...

የፖለቲካ ምኅዳሩ መላሸቅ ለአገር ህልውና ጠንቅ እየሆነ ነው!

የኢትዮጵያ ፖለቲካ ምኅዳር ከዕለት ወደ ዕለት የቁልቁለት ጉዞውን አባብሶ እየቀጠለ ነው፡፡ በፖለቲካ ፓርቲዎች የእርስ በርስ ግንኙነትም ሆነ በውስጠ ፓርቲ ዴሞክራሲ የሚታየው መስተጋብር፣ ውል አልባና...