Wednesday, February 28, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

የቴሌኮሚኒኬሽን አገልግሎት ፈቃድ የጨረታ ሰነድ ሰኞ እንደሚከፈት ተገለጸ

ተዛማጅ ፅሁፎች

መንግስት የቴሌኮሙኒኬሽን ዘርፉን ለውድድር ክፍት ለማድረግ ያሳለፈውን ውሳኔ ተከትሎ የኢትዮጵያ ኮሚኒኬሽን ባለስጣን ባወጣው ዓለም አቀፍ ጨረታ የተሳተፋ የውጭ ኩባንያዎች ሰነድ ሰኞ ሚያዚያ 18 ቀን 2013 ዓም እንደሚከፈት ተገለጸ።

መንግስት ለውድድር ክፍት ያደረገውን የቴሌኮሙኒኬሽን ገበያ እንዲመራ እና እንዲቆጣጠር ያቋቋመው የኢትዮጵያ ቴሌኮሚኒኬሽን ባለስልጣን ለሁለት የግል የቴሌኮም ኩባንያዎች ለሀገሪቱ የመጀመሪያ የሆነውን የግል የቴሌኮሙኒኬሽን አገልግሎት ፈቃድ ለመስጠት በ ህዳር ወር 2013 ዓም ዓለም አቀፍ ጨረታ ማውጣቱ የሚታወቅ ሲሆን የአገልግሎት ፈቃድ ለማግኘት በመጠየቅ የፋናንስ ፕሮፖዛላቸውን ያስገቡ ኩባንያዎች ሰነድ ሰኞ ሚያዚያ 18 ቀን ይፋ ለማድረግ መሰናዳቱን ሪፖርተር የደረሰው መረጃ ያመለክታል። 

በጨረታው የተሳተፉ ኩባንያዎች የአገልግሎት ፈቃዱን ለማግኘት ያስገቡት የዋጋ መጠን ሰኞ ከታወቀ በኋላ ወደ ቴክኒክ ግምገማ እንደሚገባ ታውቋል።

መንግስት የጨረታ ግምገማ ሂደቱን እጅግ ጥብቅ በሆነ ሚስጥር እንደሚመራው የገለጸ ሲሆን ፤ ለዚህም ሲባል ለጠቅላይ ሚንስትሩ ተጠሪ የሆነ ኮሚቴ በጠቅላይ ሚንስትር ጽ/ቤት ስር ተደራጅቶ ሂደቱ ክትትል እየተደረገበት እንደሆነ መረጃዎች ያመለክታሉ።

ዓለም አቀፍ ጨረታው ከመውጣቱ አስቀድሞ የኢትዮጵያ ቴሌኮሚኒኬሽን ባለስልጣን ወደ ኢትዮጵያ የቴሌኮሚኒኬሽን ገበያ መግባት የሚፈልጉ ዓለም አቀፍ ኩባንያዎች የፍላጎት መግለጫ እንዲያስገቡ በይፋ ባቀረበው ጥሪ መሠረት 12 ዓለም አቀፍ ኩባንያዎች ፍላጎታቸውን መግለጻቸው ይታወቃል። 

ከ12ቱ መካከል በቴሌኮሙኒኬሽን አግልግሎት ለመሳተፍ ፍላጎት ያሳዩት ዘጠኝ ኩባንያዎች ሲሆኑ ፤ ከእነዚህ መካከል ዓለም አቀፍ ጥምረት ለኢትዮጵያ ቴሌኮም አገልግሎት በሚል አንድ ጥላ ስር ሆነው ፍላጎታቸውን የገለጹት ቮዳፎን ፣ ቮዳኮም እና ሳፋሪኮም የተባሉት እህትማማች ድርጅቶች አንድ ተብለው የሚጠቀሱ እና በርካታ የዘርፉ ተንታኞች የማሸነፍም ቀዳሚ ግምት ለሦስቱ ኩባንያዎች ጥምረት ሰጥተዋል።

ከነዚህ በተጨማሪ ፤ ኢቲሳልት ፣ ኤዢያን ፣ ኤም ቲ ኤን ፣ ኦሬንጅ ፣ ሳውዲ ቴሌኮም ፣ ቴልኮም ፣ ስኔል ሞባይል ፣ ካንዱ ግሎባል ፍላጎታቸውን የገለጹ ታዋቂ ኩባንያዎች ናቸው።

የጨረታ ግምገማ ሂደቱ ገና ያልተጠናቀቀ ቢሆንም ታዋቂ የቴሌኮም ዘርፍ ተንታኞች በኢትዮጵያ የቴሌኮም ፈቃድ ለማግኘት እየተወዳደረ የሚገኘው ሦስት ዓለም አቀፍ ኩባንያዎችን ያቀፈው እና ዓለም አቀፍ ጥምረት ለኢትዮጵያ በሚል ጥላ ስር የሚወዳደረው ጥምረት አንዱን ፈቃድ ሊያሸነፍ እንደሚችል እየገለጹ ይገኛሉ። ተንታኞች ለዚህ ግምታቸው ማጠናከሪያ ይሆን ዘንድም የአሜሪካ እና የእንግሊዝ መንግስታት በዚህ ጥምረት ውስጥ ተሳትፎ እያደረጉ መሆናቸውን ይገልጻሉ።

የአሜሪካን የውጭ ግንኙነት ፖሊሲ በዓለም አቀፍ ደረጃ ለማራመድ እና ለማሳለጥ ዓላማ ይዞ እ.ኤ.አ. በ2019 የተቋቋመው ዓለም አቀፍ የልማት ፋይናንስ ኮርፖሬሽን ( International Development Finance Corporation ) ለዚህ ጥምረት የ 500 ሚሊዮን ዶላር ብረድ አቅርቧል። 

ይህ የአሜሪካ ተቋም በዋናነት ቻይና እና ራሺያ በአፍሪካ ያላቸውን ጉልህ ተጽእኖ ማዳከም ፣ ከተቻለም መገደብ እና በአሜሪካን የውጭ ፖሊሲ ፍላጎት መተካት እንደሆነ በተቋሙ ድረገጽ ላይ በግልጽ ተቀምጧል።

የአሜሪካው ተቋም አቻ የሆነው የእንግሊዙ ሲዲሲ (CDC) የተባለው ሌላው ኩባንያ ወደ ኢትዮጵያ የቴሌኮም ገበያ ለመግባት በሚወዳደሩት የሦስቱ ኩባንያዎች ጥምረት ወስጥ ከፍተኛ ድርሻ መግዛቱም ታውቋል። 

የእንግሊዙ ተቋም በሦስቱ ኩባንያዎች ጥምረት ወስጥ ድርሻ ለመያዝ እና በኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ውስጥ በተጨማሪ ለሚኖረው ተሳትፍ አንድ ቢሊዮን ዶላር መመደቡን እና በኢትዮጵያም ቅርንጫፍ መክፈቱን መረጃዎች ያመለክታሉ። 

ዓለም አቀፍ የቴሌኮም ዘርፍ ተንታኞች ለውድድር ክፍት በሆነው የኢትዮጵያ የቴሌኮም ዘርፍ አንድ የአገልግሎት ፈቃድ ለማግኘት በአማካኝ አንድ ቢሊዮን ዶላር የፈቃድ ክፍያ ሊከፈልበት እንደሚችል ገምተዋል። 

ይህ የተንታኞቹ ግምት ትክክል ከሆነ በቅርቡ ይጠናቀቃል ተብሎ ከሚጠበቀው ጨረታ ሁለት አሸናፊ ኩባንያዎች የሚከፍሉት የቴሌኬም አገልግሎት ፈቃድ ክፍያ የኢትዮጵያ መንግስት በአማካኝ ሁለት ቢሊዮን ዶላር ገቢ ሊያገኝ ይችላል።

አሸናፊ የሚሆኑት ሁለት ኩባንያዎች እያንዳንዳቸው ለ15 ዓመት የሚያገልግል ፈቃድ የሚሰጣቸው እንደሆነ የኢትዮጵያ ቴሌኮሚኒኬሽን ባለስልጣን ቀደም ብሎ ማሳወቁ ይታወሳል።

የኢትዮጵያ መንግስት ከሁለቱ የቴሌኮም ፈቃድ ክፍያዎች እና በቅርቡ ጨረታ ከሚወጣበት የኢትዮጵያ ቴሌኮም 40 በመቶ ድርሻ ሽያጭ ከሚገኘው አጠቃላይ ገቢ ውስጥ አመዛኙን ሀገሪቱ ያለባትን እዳ ለመክፈል እንዲውል የሚንስትሮች ምክር ቤት መወሰኑ ይታወቃል።

ለዚህም ሲባል ከቴሌኮም ዘርፍ ፈቃድ እና ከፊል ሽያጭ የሚገኘው ሀብት አመዛኙ የሚንስትሮች ምክር ቤት እንዲቋቋም ለወሰነው የመንግስት ልማት ድርጅቶች ዕዳ እና ሀብት አስተዳደር ኮርፖሬሽን ( Liability and Asset Management Corporation ) ፈሰስ እነደሚደረግ ታውቋል። 

በተያያዘ ዜና መንግስት የሀገሪቱን የውጭ ዕዳ ጫናን ለማቅለል በቀየሰው ስትራቴጂ መሠረት ከውጭ መንግስታት እና ከውጭ የግል አበዳሪዎች የዕዳ ክፍያ ማራዘሚያ ለመጠየቅ በመጪው ሳምንት ከአበዳሪዎች ጋር ውይይት እንደሚያደርግ የዓለም አቀፋ የገንዘብ ተቋም ሰሞኑን ያወጣው መረጃ ያመለክታል።

ለውጭ የቴሌኮም ኩባንያዎች የፈቃድ ክፍያ የሚገኘው የውጭ ምንዛሪ ገቢ እና መንግስምትም ከዚህ ገቢ ውስጥ አመዛኙን ለእዳ ክፍያ ለማዋል መወሰኑ የውጭ አበዳሪዎች ኢትዮጵያ የምታቀርበውን የዕዳ ክፍያ ማራዘሚያ ለመፍቀድ ድፍረት እንደሚሰጣቸው ተንታኞች የገልጻሉ።

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች