በሁለተኛው የዓለም ጦርነት የለንደን ከተማ በጀርመን የጦር አውሮፕላኖች እየተደበደበች ነበር፡፡
በዚያኑ ቀን ጠቅላይ ሚኒስትር ቸርችል ለሕዝባቸው የሬዲዮ ንግግር ለማድረግ ቀጠሮ ይዘዋል፡፡ ሰዓቱ እየተቃረበ ሲሄድ የጀርመን አውሮፕላኖች ድንገት ደርሰው የቦንብ ድብደባቸውን ጀመሩ፡፡ ስለዚህም ቸርችል ለጥበቃው ሲባል ሳይታወቁ ወደ ሬዲዮ ጣቢያ በታክሲ መሄድን መረጡ፡፡
ቸርችል ባለታክሲውን አስቁመው ወደ ቢቢሲ ሬዲዮ ጣቢያ እንዲወስዳቸው ጠየቁት፡፡ ‹‹ወንድሜ ሌላ ብትፈልግ ይሻልሃል፡፡ እኔ የቸርችልን የሬዲዮ ንግግር ማዳመጥ ስለምፈልግ ቤቴ መግባት አለብኝ…›› አላቸው፡፡ ቢለምኑትም የሞኝ ያህል ቆጠራቸው፡፡ ‹‹ምንም ገንዘብ ከቸርችልና ከቸርችል ንግግር አይበልጥብኝም…›› አላቸው፡፡ ሰዓት እየተቃረበ የሄደባቸው ቸርችል አሥር ፓውንድ አውጥተው ሰጡት፡፡
ባለታክሲው ያን ከፍተኛ ገንዘብ ሲያይ ግራ ገባው፤ አሰበና፡- ‹‹ወንድሜ ደህና ሰው ትመስላለህ፡፡ የቸርችል ንግግርስ ቢሆን ከዚህ በላይ ምን ያመጣልኛል፡፡ ቢፈልግ ራሱ ቸርችልም ገደል ይግባ…›› አላቸውና አሳፈራቸው፡፡