አንድ ስኮትላንዳዊና አንድ እንግሊዛዊ በጉርብትና ይኖሩ ነበር፡፡ ስኮትላንዳዊው ዶሮ ስላለችው በየዕለቱ ጠዋት ተነስቶ እርሻው ውሰጥ ሲንጐራደድ እንቁላሎች ስለማያጣ ያንን ጠብሶ ቁርሱን ይበላል፡፡ አንድ ጠዋት ግን በእርሻው ስፍራ አንድም እንቁላል በማጣቱ በጥንቃቄ ሲፈትሽ ዶሮዪቱ ጐረቤቱ እርሻ ውስጥ እንቁላል ስትጥል አየ፡፡ ዘሎ ገብቶ ሊወስድ ሲል ግን እንግሊዛዊው እንቁላሉን ሲያነሳ ተመለከተ፡፡ ስኮትላንዳዊው ተንደርድሮ በመሄድ እንግሊዛዊውን እንቁላሉን የጣለችው የርሱ ዶሮ ስለሆነች እንዲሰጠው ጠየቀው፡፡ እንግሊዛዊው ግን በዚህ አልተስማማም፡፡ ግቢው ውስጥ የተወለደ እንቁላል ንብረቱ ሊሆን እንደሚገባ ተናገረ፡፡ ለረጅም ጊዜ ከተጨቃጨቁ በኋላ ስኮትላንዳዊው በመጨረሻ “ባገራችን አለመግባባቶችን የምናስወግደው እንደሚከተለው ነው” አለ፡፡ “በመጀመሪያ እኔ ብልትህ ላይ እመታህና ለመንቃት የሚፈጅብህ ጊዜ ይመዘገባል፡፡ ቀጥሎ ደግሞ አንተ ትመታኝና የነቃሁበት ጊዜ ይያዝልኛል፡፡ ፈጥኖ የነቃው አሸናፊ በመሆን እንቁላሉን ይወስዳል፡፡”
እንግሊዛዊው በሐሳቡ ስለተስማማ ስኮትላንዳዊው ወደኋላው አፈግፍጐ ከተንደረደረ በኋላ ባጠለቀው ከባድ ከስክስ ጫማ መታው፡፡ እንግሊዛዊው ብልቱን ይዞ ወለሉ ላይ እየተንፈራፈረ ለግማሽ ሰዓት ያክል ሲጮህ ቆይቶ ነቃ፡፡
በዚህን ጊዜ ስኮትላንዳዊው እየሳቀ ‹‹ሆ፣ ሆ፤ ይገርማልኰ! በዚህ የተረገመ እንቁላል የተነሳ ልንጣላ?! ኧረ አናደርገውም፣ ጐረቤቴ፤ እንቁላሉን ልትወስደው ትችላለህ›› ብሎት ጥሎት ሄደ፡፡
- አረፈዓይኔ ሐጐስ “የስኮትላንዳውያን ቀልዶች” (2005)