Sunday, February 5, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ኪንና ባህልየብርሃን መንገድ የጀመረው የጢያ መካነ ቅርስ

የብርሃን መንገድ የጀመረው የጢያ መካነ ቅርስ

ቀን:

በዓለም አቀፍ የባህል ተቋም ዩኔስኮ አማካይነት ከአራት አሠርታት በፊት የዓለም የሚዳሰስ ቅርስ ሆኖ የተመዘገበው የጢያ መካነ ቅርስ፣ ከአሥር ዓመት ለበለጠ ጊዜ ትኩረት ተነፍጎት ‹‹የዓለም ቅርስ›› እንኳን ሊመስል ለአቅመ አገራዊ ቅርስ ባለመታደሉ በኅብረተሰቡም ሆነ ባለሙያዎች ቅሬታዎች ሲቀርቡበት ኖሯል፡፡

የዓለም ቱሪዝም ቀን በ2002 ዓ.ም. የደቡብ ብሔር ብሔረሰቦች ክልል ሲከበር ከኢትዮጵያ የተለያዩ አካባቢዎች የታደሙ የኅብረተሰብ ክፍሎች የመጀመርያው የጉብኝት መዳረሻ የነበረው፣ በጉራጌ ዞን ሶዶ ወረዳ የሚገኘው የጢያ ትክል ድንጋዮች መካነ ቅርስ ነበር፡፡ በወቅቱ በመካነ ቅርሱ አስጎብኚም ሆነ በዞኑ ኃላፊዎች የተንፀባረቀው ጢያ ‹‹ትኩረት ተነፍጓታል›› የሚል ነበር፡፡

በተከታታይ ዓመታት የተለያዩ ጥረቶች ቢደረጉም ከግብ አልደረሱም፡፡ ይሁን እንጂ የቅርስ ጥናትና ጥበቃ ባለሥልጣን (ቅጥጥባ) ሃቻምና እና ዓምና ዓለም አቀፍ መካነ ቅርሱ እንዲጠገን በያዘው በጀት፣ ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ጋር በመተባበር የቅርሱን ጥገና ለማከናወን የሚያስችል የጥናት ሰነድ አዘጋጅቶ ሥራውን አከናውኗል፡፡

መሰንበቻውን የጢያ ትክል ድንጋይ መካነ ቅርስ የመጀመርያ ምዕራፍ ከሦስት ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ ጥገናው ተጠናቆ ለጎብኚዎች ክፍት መሆኑ ተገልጿል።

በባለሥልጣኑ የቅርስ ጥገናና እንክብካቤ አርክቴክትና ኮንሰርቬተር ሀፍታሙ አብርሃ እንደገለጹት፣ የተከናወነው ሥራ ወደ አንድ አቅጣጫ ያጋደሉ ድንጋዮችን የማቃናትና የመትከል እንዲሁም በመካነ ቅርሱ የነበረውን ሣር የመመንጠር፣ ቦታውን የመደልደልና አፈሩን በኖራ የማከም ነው፡፡

ቀደም ሲል ትክል ድንጋዩ ባለበት ቦታ ዝናብ ሲዘንብ ውኃ ያቁር እንደነበረ፣ ቅርሶቹ ግማሾቹ ተንጋደው ሌሎቹ ደግሞ ወድቀው ስለነበረ ቅጥር ግቢውም ጭምር ለመስህብነት የሚመች እንዳልነበረ ያስታወሱት አርክቴክቱ፣ በአሁኑ ወቅት የውኃ መውረጃ ቦይ በመሠራቱ ችግሩ መፈታቱን ገልጸዋል።

ከቅጥጥባ የተገኘው መረጃ እንደሚሳየው፣ ሥራው ሲሠራ በሁለት መልኩ ሲሆን አንደኛው ግቢውን የማስዋብ፣ የማስጌጥ፣ ለዓይን ሳቢና ማራኪ ማድረግ ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ በተፈጥሮና በሰው ሠራሽ ተፅዕኖዎች ቅርሱ አደጋ ውስጥ ስለገባ ያንን ለመከላለል የሚያስችሉ ሥራዎች እየተከናወኑ ይገኛል፡፡

የጢያ መካነ ቅርስ ለጎብኚዎች ሲከፈት የባህልና ቱሪዝም ሚኒስትር ሂሩት ካሳው (ዶ/ር)፣ የቅርስ ጥናትና ጥበቃ ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር ሙሉጌታ ፍሥሐ (ዶ/ር)፣ የጉራጌ ዞን ኃላፊዎችና ሌሎች ታዳሚዎች መገኘታቸው ታውቋል።

የጢያ መካነ ቅርስ ሲገለጽ

የጢያ ትክል ድንጋይ መካነ ቅርስ በደቡብ ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ክልል በጉራጌ ዞን ከአዲስ አበባ ወደ ቡታጂራ በሚወስደው መንገድ 88 ኪሎ ሜትር ርቃ ከምትገኘው ሶዶ ወረዳ በጢያ ከተማ ይገኛል፡፡

ከቅጥጥባና ከዩኔስኮ ድረ ገጾች የተገኙት መረጃዎች እንደሚገልጹት፣ የጢያ ታሪካዊ ድንጋዮች በቁጥር 44 የሚደርሱ ሲሆን፣ ከነዚህም ውስጥ 32ቱ ልዩ ልዩ ቅርጾችና ምስሎች ያሉባቸው ናቸው፡፡ ሁሉም ድንጋዮች የተለያየ ርዝመት፣ ስፋትና ውፍረት አላቸው፡፡ ይሁንና በሌሎቹ ሥፍራዎች ማለትም በአገር ውስጥ ሆነ በውጭ እንደሚታዩት የመቃብር ድንጋዮች አንድም አራት ማዕዘን ወይም ድቡልቡል አይደሉም፡፡ በአብዛኛው ከታች ሰፋ ብለው ወደ ላይ እየሾጠጡ የሚሄዱ ናቸው፡፡

የአንዳንዶቹ ትክል ድንጋዮች ቁመትም 1-5 ሜትር ሊረዝም እንደሚችል የአርኪዮሎጂ አጥኚዎች ሥራዎች ያመለክታሉ፡፡  በድንጋዮቹ ላይ የተቀረጹት ምስሎችም የጎራዴ ወይም የሰይፍ ወይም የጩቤ፣ የጦር፣ የትራስ እንጨት፣ ክብ ዳቦ ወይም ፀሐይ መሰል ቅርጾች፣ የግማሽ ጨረቃ ምስሎች እጆቹን ወደላይ የዘረጋ ሰው ክንዶች ናቸው፡፡

በቅድመ ታሪክ ይኖሩ የነበሩት ኢትዮጵያውያን ድንጋዮቹን ለምን እንደተከሏቸው ባይታወቅም ትልቅ የጦር መሪዎች፣ ገዥዎችና ታላላቅ ሰዎች የተቀበሩባቸው ሥፍራዎች ሊሆኑ እንደሚችሉ ይገመታል፡፡ ተመራማሪዎቹ ይህን ግምት የወሰዱት በአሁኑ ጊዜ በሶዶ፣ በስልጤና  በጌድኦ ካሉት የመቃብር ድንጋዮች እንደሆነም ያስረዳሉ፡፡

ምንም እንኳን ትክል ድንጋዮቹ መች እንደተተከሉ በትክክል ማወቅ ባይቻልም አንዳንድ አጥኝዎች 800 ዓመት በፊት እንደተተከሉ ይገምታሉ፡፡ ሌሎቹ ደግሞ ከቅድመ ታሪክ በፊት የነበሩ ኢትዮጵያውያን የተሠሩ ሊሆኑ እንደሚችሉ ይገምታሉ፡፡ የተወሰኑ ትክል ድንጋዮቹ ለብዙ ዓመት ሳይወድቁ የቀሩበትን ምክንያት ሲያብራሩም ከመሬት በታች ስምንት ሜትር ርዝመት ስላላቸው እንደሆነ ይገልጻሉ፡፡ በድንጋዮቹ ላይ ያለው የሰይፍ ብዛት ሟች ምን ያህል ልጆች እንዳሉት እና ምን ያህል አውሬ እንደገደለ ያሳያሉ ይላሉ፡፡

የጢያ ትክል ድንጋይ የአውሮፓውያንን ዓይን መሳብ ከጀመረ ብዙ ዓመትን ያስቆጠረ ሲሆን ኢጣሊያውያን የአርኪዮሎጂ ባለሙያዎች ጥልቅ ጥናት ባያካሂዱም 70 ዓመት በፊት ኢትዮጵያን ወርራ በነበረችበት ጊዜ የመጡ ተመራማሪዎች ስለድንጋዮቹ መኖር ዘግበዋል፡፡ የዛሬ 84 ዓመት ወደኢትዮጵያ መጥቶ የነበረው ጀርመናዊ አጥኚም በዚህ ሥፍራ በኩል አልፎ እንደነበረና የጎራዴ ምስል ያላቸው የድንጋይ ትክሎች እንዳየ በጥናቱ አመልክቷል፡፡ ከዚህ አጥኚ ቀደም ሲልም ኑቪለ እና ፔር ዛይስ (Neuville and Pere Azais.) የተባሉ አውሮፓውያን ጢያን መጎብኘታቸውን የዩኔስኮ ጥናቶች ያመለክታሉ፡፡

ትራቭል አፍሪካ በተሰኘው የጎብኝዎች የኢንተርኔት መረጃ ምንጭም ጢያ የሚገኙት ትክል ድንጋዮች አዳዲ ማርያም ከተባለው ከድንጋይ ፍልፍል የተሠራው ቤተ ክርስቲያን፣ ሀረ ሸይጣን ከተባለው ክሬተር ሐይቅ፣ ከመልካ አዋሽ መስመር ጋር ስለሚገኙ ለጎብኝዎች በአንድ ጉዞ ብዙ ታሪካዊ ቦታዎችን ለመጎብኘት ያስችለዋል በማለት አስፍሯል፡፡

ፊሊፕ በሪግ የተሰኙት አጥኚም የጢያ ትክል ድንጋይ ጥንታዊነትን ለዓለም በማስተዋወቅ አዎንታዊ አስተዋጽኦ ማበርከታቸው ይታወቃል፡፡ የፈረንሳይ አርኪዮሎጂ ባለሙያዎች መረጃ እንደሚያመለክተው የጢያ ትክል ድንጋይ ባለበት ቦታ ዕድሜያቸው 18-30 የሚገመቱ ብዙ ወጣቶች በአንድ ላይ የተቀበሩበት ሥፍራ ነው፡፡

ትራቭል አፍሪካ የተሰኘው መጽሐፍ እንደሚያወሳው፣ ከጢያ ጋር የሚመሳሰሉ ትክል ድንጋዮች በሶዶ ወረዳ 160 ሥፍራዎች ሲኖሩ ከነዚህም ድንጋዮች በኢማም አህመድ ኢብራሂም (‹‹አህመድ ግራኝ››) እንደተተከሉ በአፈ ታሪክ ቢነገርም በትክክል ማን እንደተከላቸው ግን አይታወቅም፡፡

የአርኪዮሎጂ አጥኚዎች እንደሚሉት የጢያ ትክል ድንጋዮች ከሰሐራ በታች ካሉ ትክል ድንጋዮች ከአክሱም በስተቀር በዕድሜ የሚበልጣቸው የለም፡፡

ከላይ የተጠቀሱትን ምክንያቶች መሠረት በማድረግ ቦታው .. 1980 ጀምሮ በዓለም የቅርስ መዝገብ ሰፍሮ ይገኛል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያንና የመንግሥት ውዝግብ

የጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) መንግሥት ባለፉት አራት ዓመታት...

የኢትዮጵያ ካፒታል ገበያ ምሥረታ ዝግጅቶችና ከገበያው የሚጠበቁ ዕድሎች

ኢትዮጵያ ከ50 ዓመት በኋላ ዳግም የምታስጀምረውን የካፒታል ገበያ ዘመኑን...

አዲሱ የብሔራዊ ባንክ ገዥ ትኩረት የሚያደርጉባቸውን ቀዳሚ ጉዳዮች ይፋ አደረጉ

አዲሱ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ገዥ ትኩረት አድርገው የሚሠሩባቸውን ቀዳሚ...

መንግሥት የደቡብ ሱዳን ታጣቂዎች ድንበር ጥሰው የሚያደርሱትን ጥቃት እንዲያስቆም ተጠየቀ

የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የውጭ ግንኙነትና የሰላም ጉዳዮች ቋሚ...