Friday, June 2, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ዜናፌዴሬሽን ምክር ቤት ለክልሎች በዓላማ ላይ የተገደበ የድጎማ በጀት ተግባራዊ እንደሚያደርግ አስታወቀ

ፌዴሬሽን ምክር ቤት ለክልሎች በዓላማ ላይ የተገደበ የድጎማ በጀት ተግባራዊ እንደሚያደርግ አስታወቀ

ቀን:

የፌዴሬሽን ምክር ቤት ሲሠራበት የነበረው ለክልሎች የሚሰጥ ጥቅል የድጎማ በጀት ቀመር፣ የመሠረተ ልማት ተጠቃሚነት ላይ ክፍተት የሚፈጥር መሆኑ በጥናት በመረጋገጡ፣ በ2014 በጀት ዓመት የተመጣጠነ ዕድገት መፍጠር የሚያስችልና ፍትሐዊ የሀብት አጠቃቀም ማሥፈንን መሠረት ያደረገ፣ በዓላማ የተገደበ የድጎማ በጀት ቀመር ተግባራዊ እንደሚሆን አስታወቀ፡፡

ፌዴሬሽኑ እንዳብራራው፣ በዓላማ የተገደበ የድጎማ በጀት ቀመር እስካሁን ሲሠራበት በነበረው ማዳረስ ያልተቻለውን የመሠረተ ልማት ተጠቃሚነት ክፍተት በመሙላት ወደኋላ የቀሩትን ወደ ፊት ማምጣት ያስችላል፡፡

የፌዴሬሽን ምክር ቤት በጥቅል ዓላማ የድጎማ በጀት፣ የፌዴራል መንግሥት የመሠረተ ልማት ሥርጭት ፍትሐዊነት፣ ድጋፍና ክትትል ሥርዓት ዙሪያ ያስጠናውን ጥናት የክልል ርዕሳነ መስተዳድሮች በተገኙበት ሰሞኑን አቅርቧል፡፡

የምክር ቤቱ አፈ ጉባዔ አቶ አደም ፋራህ እንደተናገሩት፣ ከክልል ወደ ወረዳዎች የሚደረገውን የፊስቫል ሽግግር ሥርዓት ጥናት ለማካሄድ የተዘጋጀ የጥናት መነሻ ሐሳብ ቀርቦ ውይይት ተደርጎበታል፡፡ እስካሁን በነበረው ሒደት ሲሠራበት የነበረው ጥቅል ዓላማ ያለው የድጎማ በጀት ቀመር ብቻ ነበር፡፡ በዚህም በክልሎች መካከል የተመጣጠነ ዕድገት ለማምጣትና በልማት ወደኋላ የቀሩ ክልሎችን በግልጽ አሠራር ለመደገፍ አለመቻሉን አስረድተዋል፡፡

በሁሉም ክልሎች ፍትሐዊ የሀብት ተጠቃሚነት ለማሥፈንና የተመጣጠነ ዕድገት ለማምጣት፣ በዓላማ የተገደበ የድጎማ በጀት ቀመር በአሠራር ማበጀት እንደሚያስፈልግም አክለዋል፡፡

በዓላማ የተገደበ የድጎማ በጀት በተለያዩ ተቋማት በዘፈቀደ ሲሠራበት እንደነበር ያስታወሱት አፈ ጉባዔው፣ ልቅ የነበረው አሠራር ግልጽነትና ተጠያቂነት በሠፈነበት መንገድ እንዲከናወን መዘጋጀቱን ገልጸዋል፡፡ በመሆኑም ‹‹ከ2014 በጀት ዓመት ጀምሮ በዓላማ የተገደበ የድጎማ በጀት አሠራር ሥርዓት ወጥ በሆነ መንገድ ተግባራዊ ይደረጋል፤›› ብለዋል፡፡ ጥቅል ዓላማ ባለው የድጎማ በጀት ብቻ ተወስኖ የነበረውን የክልሎች ፍትሐዊ ተጠቃሚነት በማረጋገጥ አገራዊ ዕድገት እንዲመዘገብ እንደሚያደርግም ጠቁመዋል፡፡

በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የአገር ልማት መካነ ጥናት ተቋም ዳይሬክተር ጌትነት ዓለሙ (ዶ/ር)፣ ክልሎች ገቢ የመሰብሰብ መብታቸው ዝቅተኛ፣ ወጪያቸው ደግሞ ከፍተኛ መሆኑን ገልጸዋል። ባለፈው ዓመት ብቻ በተወሰደ መረጃ ክልሎች ያመነጩት ገቢ 41 በመቶ ሲሆን፣ ቀሪው 59 በመቶ የተሸፈነው በፌዴራል መንግሥት መሆኑንም ገልጸዋል፡፡

በመሆኑም በዓላማ የተገደበ የድጎማ በጀት፣ በጥቅል ድጎማ በጀት ያልተሸፈኑ ክፍተቶችን በመሙላት፣ የክልሎችን ፍትሐዊ ተጠቃሚነትና ልማት ያሳድጋል ብለዋል፡፡ የክልሎች የድጎማ በጀት ከአገራዊው ጥቅል ገቢ ምን ያህል እንደሆነ በመቶኛ በግልጽ የተቀመጠ ባለመሆኑ መስተካከል እንዳለበትም አክለዋል፡፡

በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የኢኮኖሚክስ ትምህርት ክፍል ኃይሉ ኤልያስ (ረዳት ፕሮፌሰር)፣ በክልሎች መካከል ፍትሐዊ ተጠቃሚነትና ዕድገት እንዲኖር የሚመለከታቸው አካላት ተናበው መሥራት አለባቸው ብለዋል፡፡ በተለይም በቀጥታ የሚመለከታቸው የፌዴሬሽንና የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤቶች ተቋማት፣ በሕገ መንግሥቱና በአዋጅ በተሰጣቸው ሥልጣን መሠረት ኃላፊነታቸውን መወጣት እንደሚገባቸው ጠቁመዋል፡፡

የፌዴሬሽን ምክር ቤት የተጠያቂነት ሥርዓት ለማስፈን ሥራዎች መቼ፣ እንዴትና ለምን እንደሚሠሩና እንደሚጠናቀቁ ማወቅ እንዳለበትም ገልጸዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የአዛርባጃንን ብሄራዊ ቀን በአዲስ አበባ በድምቀት ተከበረ

የአዛርባጃን ኤምባሲ  የአዛርባጃንን ብሄራዊ ቀን በትላንትናው ዕለት አከበረ። ሰኞ...

የመንግሥትና የሃይማኖት ልዩነት መርህ በኢትዮጵያ

እንደ ኢትዮጵያ ባሉ አገሮች የሃይማኖት ተቋማት አዎንታዊ ሚና የጎላ...

ሐበሻ ቢራ ባለፈው በጀት ዓመት 310 ሚሊዮን ብር የተጣራ ትርፍ ማግኘቱን አስታወቀ

የአንድ አክሲዮን ሽያጭ ዋጋ 2,900 ብር እንዲሆን ተወስኗል የሐበሻ ቢራ...