በአዲስ አበባ ከተማ በተለይም ያለፉትን ሁለት ወራት የግብር ተቆጣጣሪ መሥሪያ ቤት ሠራተኞችን በመምሰል ግብር ከፋዮችን የሚያደናግሩ ግለሰቦች ቁጥር እየተበራከተ እንደመጣ ተገለጸ፡፡
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ገቢዎች ቢሮ ኃላፊ አቶ ሙሉጌታ ተፈራ ለሪፖርተር እንዳስታወቁት፣ ከሕግ ተገዢነት አንፃር የገቢዎች ቢሮው ባለሙያዎች በተመረጡ ቦታዎች ላይ ድንገተኛ ቁጥጥርና ክትትል እያደረጉ ይገኛሉ፡፡ ሆኖም በቅርቡ በተለይም ያለፉትን ሁለት ወራት በአዲስ ከተማ ክፍለ ከተማ መርካቶ አካባቢ፣ እንዲሁም በንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማ ንፋስ ስልክ አካባቢዎች ላይ የተለያዩ ግለሰቦች የገቢዎች ቢሮ ሠራተኞች በመምሰል ግብር ከፋዮችን በደረሰኝ አልሸጣችሁም በሚል ግብር ከፋዩ ላይ ጫና የመፍጠርና የማዋከብ ተግባር እንደሚስተዋል ለማረጋገጥ መቻሉን ገልጸዋል፡፡
ግለሰቦችና የተደራጁ ቡድኖች የገቢ ሰብሳቢ መሥሪያ ቤቱን ሠራተኞች በመምሰል፣ በሚጠቀሟቸው የማጭበርበሪያ መንገዶች ግብር ከፋዮችን ላልተገባ እንግልት ከመዳረጋቸው ባሻገር በገቢ አሰባሰብ ሥርዓቱ ላይ አሉታዊ ተፅዕዎችን በመፍጠር ላይ እንደሚገኙ የተገለጸ ሲሆን፡፡ በተለይም ሐሰተኛ መታወቂያዎችን በማሠራት የሽያጭ መመዝገቢያ መሣሪያ ተቆጣጣሪ ሠራተኞች መስለው የተለያዩ የንግድ ተቋማት ውስጥ በመግባት፣ የተዛቡ መረጃዎችን በማሠራጨት፣ በግብር ከፋዩ ላይ የተገኘ የአሠራር ክፍተትን መነሻ በማድረግ በአዋጅና መመርያዎች አስፈራርተው፣ ከታክስ ከፋዩ ጋር በመደራደር ገንዘብ የመሰብሰብ ሥራ ላይ የተሰማሩ ግለሰቦች መኖራቸውን፣ የችግሩ ሰለባ የሆኑ ግብር ከፋዮች ለቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤቶች በስልክና በአካል ቀርበው ከገለጹት ጥቆማ ለመረዳት ተችሏል ሲል ቢሮው አስታውቋል፡፡
እነዚህን የግብር ከፋዩን የሥራ እንቅስቃሴ በማጤን የሚደረጉ ክስተቶችን ለመከላከል የንግዱ ማኅበረሰብ ራሱን ከእነዚህ ጭንብል ለባሾች ሊጠብቅ እንደሚገባም ተናግረዋል፡፡ በተለይም በስምሪት ሥራው ላይ የሚገኙ ሠራተኞች ከመሥሪያ ቤቱ የተሰጣቸውን ተገቢውን የመረጃ መሰብሰቢያ ቅጽ የያዙ መሆናቸውን ማረጋገጥና ምናልባትም በመመርያ የሚያስጠይቅ የአሠራር ጥሰት ተፈጽሞ ከሆነ መሥሪያ ቤቱ ያስቀመጠው ቅጣት ተግባራዊ እንዳይሆን ከመደራደር ይልቅ፣ ተገቢውን የቅጣት ገንዘብ ለመሥሪያ ቤቱ ገቢ በማድረግ ደረሰኝ መቀበል እንደሚገባ ቢሮ አስታውቋል፡፡
ከታክስ ጋር የተገናኘ የሕግ ማስከበር ሥራን ለመሥራትና ለማጠናከር ‹‹በመጀመሪያ መሠራት አለበት ብለን የምንንቀሳቀሰው ግብር ከፋዮች ስለ ታክስ ግንዛቤ እንዲኖራቸው ማድረግ ነው›› ያሉት አቶ ሙሉጌታ፣ ከዚህ ባሻገርም ቢሮው ያሉትን ሠራተኞች ከፋይናንስ ደኅንነት ማዕከልና ሰላም ሚኒስቴር ጋር በመተባበር የታክስ ክትትል ምርመራ መቼና እንዴት ይደረጋል? የሚለው ላይ እየሠራ ይገኛል ብለዋል፡፡
የገቢዎች ቢሮው በተያዘው የበጀት ዓመት 42.4 ቢሊዮን ብር ገቢ ለመሰብሰብ አቅዶ፣ አስከ ተያዘው ወር ድረስ 32 ቢሊዮን ብር ሰብስቧል፣ ይህም ከዓመቱ ዕቅድ 76 ከመቶ ነው፡፡ ገቢን ባቀደው ልክ እየሰበሰበ እንደሚገኝ ያስታወቀው ቢሮው፣ ከዚህ በፊት የነበሩ ውዝፍ ሥራዎችን ጭምር መስመር በማስያዝ በተነፃፃሪ ከተማዋ የተሻለ ገቢ እንድታገኝ እየተሠራ እንደሚገኝ ተገልጿል፡፡