የቅዱስ ጊዮርጊስ ስፖርት ማኅበር በቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ እየተሳተፈ የሚገኘው የእግር ኳሱ ቡድኑ በሚደረግለት ድጋፍና ክትትል ልክ ውጤት ሊያስመዘግብ እንዳልቻለ፣ ለዚህ ደግሞ ተጠያቂ ባላቸው አራት ነባር ተጨዋቾች ላይ የዲሲፕሊን ዕርምጃ መውሰዱን አስታወቀ፡፡ ዕገዳው የተላለፈባቸው ተጨዋቾች ከቡድኑ ውጪ መደረጋቸውም ታውቋል፡፡
የስፖርት ማኅበሩ በማኅበራዊ ትስስር ገጹ እንዳስታወቀው ከሆነ፣ ቅዱስ ጊዮርጊስ እየተደረገለት ካለው ሁሉን አቀፍ ድጋፍ አንፃር የሚጠበቅበትን ያህል አርኪ የሚባል እንቅስቃሴዎችን እያደረገ አይደለም፡፡ ይህም ሆኖ በቡድን ውስጥ ያሉ አንዳንድ ተጨዋቾች የሚያሳዩት ያልተገባ ባህሪና የሥነ ምግባር ጉድለት እጅጉን የሚያስቆጭ ስለመሆኑ ጭምር ክለቡ በመግለጫው አመልክቷል፡፡
ቡድኑ በድሬዳዋ ስታዲየም ባለፈው ሐሙስ ሚያዝያ 14 ቀን 2013 ዓ.ም. የ20ኛ ሳምንት ጨዋታውን ከጅማ አባ ጅፋር ጋር ካከናወነው ጨዋታ በኋላ፣ ከቡድኑ ነባር ተጨዋቾች መካከል ጌታነህ ከበደ፣ አስቻለው ታመነ፣ ጋዲሳ መብራቴና ሙሉዓለም መስፍን ከፍተኛ የዲሲፕሊን ግድፈት መፈጸማቸውን ጠቅሷል፡፡
እንደ ማኅበሩ መግለጫ ከሆነ አብዛኞቹ ተጨዋቾች ከዚህ ቀደም ቡድኑ በባህር ዳር በነበረው ቆይታ የሥነ ምግባር ጉድለት መፈጸማቸው፣ ይሁንና ለቡድኑ ውጤታማነትና አንድነት ሲባል በማስጠንቀቂያ እንዲታለፉ ተደርጓል፡፡ የክለቡ ሥራ አመራር ቦርድ ባደረገው አስቸኳይ ስብሰባ ተጨዋቾቹ በፈጸሟቸው የዲሲፕሊን ግድፈቶች ላይ የቡድን መሪው በዝርዝር በሚያቀርቡት ሪፖርት ላይ ቦርዱ ውሳኔ እስከሚሰጥ ድረስ ለጊዜው ከቡድኑ ታግደው እንዲቆዩ መወሰኑን አስታውቋል፡፡ አራቱ ተጨዋቾችም ከድሬዳዋ ወደ አዲስ አበባ እንዲመለሱ ስለመደረጋቸውም በመግለጫው ተካቷል፡፡