Saturday, June 22, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
እኔ የምለዉረባሽ ከብቶችን ለይቶ ማሰር ይቻላል!

ረባሽ ከብቶችን ለይቶ ማሰር ይቻላል!

ቀን:

በያዳ ኡመታ

ይህን ርዕስ የተጠቀምኩት ፕሮፌሰር በየነ ጴጥሮስ መጋቢት 24 ቀን 2013 .ም. በወጣው አዲስ ዘመን ጋዜጣ ላይ በሰጡት ቃለ መጠይቅ ኢትዮጵያን የሚበጠብጧትን ፖለቲከኞች በተመለከተ የተናገሩትን መነሻ በማድረግ ነው፡፡ ፕሮፌሰሩ ያሉት ‹‹እኔ የከብት እረኛ ነበርኩና አንድ በረት ውስጥ ካሉ ከብቶች መካከል አንድ ወይም ሁለት ረባሽ ከብቶች ካሉ የቀሩትን ሁሉ ዕረፍት ይነሳቸዋል፣ ይዋጋቸዋል፣ ያሸብራል፣ በረቱን ኢትዮጵያ በይው፡፡ አሁን እያየን ያለነውም ይህንኑ ነው፤›› ብለው ነበር፡፡ እኔም የአርሶ አደር ልጅ፣ በገጠር ያደግኩ እንደ መሆኔ አባቶቻችን እንደዚህ የሚያስቸግሩ ከብቶችን ለይተው ለብቻቸው ሲያስሩዋቸው አውቃለሁ፡፡ ስለዚህ አገራችንን ኢትዮጵያን የሚረብሹትን የውስጥ ኃይሎች በመለየትና በመነጠል ማሰር፣ ወይም ማግለል አይቻልም ወይም አይሻልም ወይ የሚሉትን ሐሳቦች ለማንሸራሸር ነው አንዱ የጽሑፌ ዓላማ፡፡

በአገራችን እንደ ባህል የተወሰደው ተቃዋሚ የፖለቲካ ድርጅቶች ሥልጣን ላይ ያለውን መንግሥት መገዳደር ወይም በጠላትነት ማየትና መንግሥቱን ለማፍረስ መታገል ነው፡፡ በእርግጥ በአሁኑ ጊዜ በርካታ የፖለቲካ ፓርቲዎች በሥልጣን ላይ ያለውን የለውጡን ኃይል በአዎንታዊነት በመውሰድ፣ በሰላማዊ መንገድ ለሥልጣን በመወዳደር ላይ ይገኛሉ፡፡ ግን የተወሰኑት ጥቂቶች እንደ በጥባጭ ከብቶቹ በቆየው የፖለቲካ ባህላቸው የለውጥ ኃይሉን መንግሥት መገዳደሩን ተያይዘውታል፡፡ እንደሚታወቀው በአሁኑ ጊዜ አገራችን በከፍተኛ ውጫዊና ውስጣዊ ተግዳሮቶች በውጥረት ውስጥ ናት፡፡ በትልልቅ ዕድሎችና ሥጋቶችም ውስጥ ናት፡፡ ከህዳሴ ግድቡ ጋር በተገናኘ ግብፅንና ሱዳን፣ እንዲሁም እነዚሁን በመደገፍ ከቆሙት ከአሜሪካከአንዳንድ የምዕራብ አውሮፓ፣ ከዓረቡ ዓለም የሚደርስባት ተፅዕኖ የጎላ ነበር፡፡ የሱዳን መንግሥት የኢትዮጵያን ድንበር ጥሶ መግባትና ወረራ በትግራይ በሕወሓት ላይ በተወሰደው የሕግ ማስከበር ዕርምጃ ጋር በተገናኘ ከአሜሪካና ከምዕራቡ የአውሮፓ አገሮች የሚደረጉባትላስፈላጊ ጫናዎችና ጣልቃ ገብነት ቀላል አልነበሩም፡፡ በኢትዮጵያ የሚካሄደው ለውጥ አፍሪካን ያዳርስና አፍሪካውያን ከቁጥጥራችን ውጪ ይሆናሉ በሚል ከላይ የቀረቡት አገሮች ሥጋትና ይህንኑ የመግታት ፍላጎት፣ እንዲሁም አገራችን ራሷን ችላ ቀና ብላ ከእነሱ ተፅዕኖና ዕርዳታ ተቀባይነት እንዳትወጣ ፍላጎት አላቸው፡፡ በሌላ በኩል የኢትዮጵያና የኤርትራ ወዳጅነትና ትብብር ሁለቱን አገሮች አጠናክሮ በአካባቢው ተፅዕኖ ፈጣሪ ያደርጋቸዋል የሚልም የምዕራባውያንናሌሎቹ ሥጋት መኖሩ፣ ይህን ለማደናቀፍ የሚሸርቡዋቸው ሴራዎች ጠንካራዎቹ ውጪያዊ ሥጋቶቻችን ናቸው፡፡ 

ከኮሮና ወረርሽኝ ጋር በተገናኘ በዓለም ደረጃ የአምራቾቹ ቁጥር መቀነስ፣ ከነዳጅ ዋጋ ጋር በተገናኘ ከውጪ በምናስመጣቸው ጥሬ ዕቃዎች ላይ የተደረገው ከፍተኛ የዋጋ ጭማሪ፣ ከውጭ ምንዛሪውጥረት ጋር ተደምሮ የምርቶችን ዋጋ እንዲጨምር በማድረጉ የኑሮ ውድነቱን ማባባሱ ሌላው ውጪያዊ ተፅዕኖ ተብሎ የሚወሰድ ነው፡፡ ውስጣዊ ሥጋቶችን በተመለከተ የኮሮና ወረርሽኝ እያስከተለ ያለው ተፅዕኖ እንደተጠበቀ ሆኖ፣ ከሥራ አጥነቱና ከኑሮ ውድነቱ ጋር የሚያያዙ እንደ ስርቆትናዝርፊያ የወንጀል ተግባራት መበራከት፣ በአብዛኛው በውጫዊ ኃይሎች ድጋፍ ሰጪነት የሚካሄዱ በንፁኃን ዜጎች ላይ የሚደርሰው ግድያና ማፈናቀል ጉልህ ችግሮች ናቸው፡፡ ከብሔር ጋር በተገናኘ የመንግሥት ኃይልን የመከፋፈል ሙከራዎችና በሰሜኑ የተደረገው ጦርነትና የትግራይን ሕዝብ ከረሃብ ለመታደግና መሠረተ ልማቶችን ለመገንባት የሚወጣው ወጪና የትኩረት መውሰድ ሌላው የኢኮኖሚ ጫና ነው፡፡ በዚህ ዓመት የሚካሄደውን ብሔራዊ ምርጫ ለማደናቀፍ የሚደረግ ጥረት የአገራችን ሥጋት ሆነው ይታያሉ፡፡ ስለሆነም ዜጎች  እነዚህን ሁኔታዎች በጥልቀት ተገንዝበው ይህንን ከባድ ችግር በጋራ በአንድነት እንዴት መወጣት እንደሚኖርብን መነጋገሩ በጣም አስፈላጊ ነው ብዬ አምናለሁ፡፡ በዚህ ሒደት በውጭ የሚገኙ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያን በአንድነት በመነሳት፣ ከኤርትራውያን አጋሮቻችን ጋር በአሜሪካ በተለያዩ ግዛቶችና በአውሮፓ በተለያዩ አገሮች ሲያደርጉ የቆዩት ሰላማዊ ሠልፍና በተለያዩ መንገዶች የፈጠሩትና እየፈጠሩ ያሉት ተፅዕኖ ተስፋ የሚሰጥ ነው፡፡ ይኸው በጎ ተግባር ይቀጥላል የሚል እምነት አለኝ፡፡ በአገር ውስጥ ምንም እንኳ ሕዝቡ ከለውጥ ኃይሉ ጋር ኢትዮጵያን ለማሻገር ቁርጠኛ ሆኖ በመሥራት ላይ የሚገኝ ቢሆንም፣ ቀደም ሲል እንደተገለጸው ጥቂቶች ሕዝቡን የማመስና አንድነቱን የመሸርሸር ሁኔታዎች በማሳየት ላይ ይገኛሉ፡፡ እነዚህ ጉዳዮች ሲነሱ የዚህ ጽሑፍ አቅራቢ እንደ በረት ከብቶች በጥባጮች የሚታዩ ኃይሎችን በአራት ምድቦች ይከፍላቸዋል፡፡

1. ኦፌኮ በአቶ ዳውድ ኢብሳ የሚመራ ኦነግና ከኦነግ ያፈነገጡ የኦሮሞ ነፃነት ሠራዊት ብለው ራሳቸውን የሚጠሩ፣

2. በአብን ውስጥ የሚገኙና የሌሎች የአማራ ብሔርተኛ ኃይሎች፣

3. የቀሩት የትሕነግ መሪዎች አባላትና ደጋፊዎቹ፣

4. በተለይ በኦሮሞ፣አማራናትግራይ ብሔረሰቦች ስም የሚነግዱ አንዳንድ ማኅበራዊ አንቂዎች /አክቲቪስቶች/ ናቸው፡፡ እነዚህ እንደሚከተለው በዝርዝር እንያቸው፡

የኦሮሞ ፌዴራላዊ ኮንግረስ (ኦፌኮ)

ኦፌኮመረራ ጉዲና (ፕሮፌሰር) ይመራ የነበረው የኦሮሞ ኮንግሬስና በአቶ ቡልቻ ደመቅሳ ሲመራ የነበረው የኦሮሞ ፌደራሊስቶች ተዋህደው የመሠረቱት የፖለቲካ ድርጅት ነው፡፡ ድርጅቱ በተለይ ባለፈው ዓመት የፖለቲካ አክቲቪስት የነበረውን አቶ ጃዋር መሐመድን በአባልነት ከተቀበለ በኋላ ያደረጋቸውና አሁንም የሚያደርጋቸው ክንውኖች ጤናማ አይደሉም፡፡ አቶ ቡልቻ እርጅና ባይጫጫናቸው ኖሮ ድርጅቱን ከፍለው፣ የተከፈለው ኃይል የለውጡ ኃይሉን ደግፎ በትክክለኛ መስመር እንዲሄድ ጥረት ያደርጉ ነበር፡፡ ምክንያቱም እሳቸው በሰላማዊ የድጋፍ ሠልፍ ጭምር በመሳተፍ / ዓብይን እንደግፍ የሚሉ መልዕክቶችን ሲያስተላልፉ እንደቆዩ የምናውቀው ነው፡፡ የኦፌኮ መሪ የሆኑት መረራ (ፕሮፌሰር) ከወር በፊት በማኅበራዊ ሚዲያ ‹‹ከፍርኃት ነፃ አድርገናቸው ከሆዳምነት ግን ማላቀቅ አልተቻለም›› የሚል መልዕክት አስተላልፈው ነበር፡፡ በፕሮፌሰር መረራ አስተሳሰብ ከእሳቸው፣ ከኦነግና ከሕወሓት አስተሳሰብ ውጪ ያለው የለውጥ ኃይሉን ማለት / ዓብይን የሚደግፉት በሙሉ ሆዳሞች ናቸው፡፡ እሳቸው የለውጥ ኃይሉን በመቃወማቸው ራሳቸውን ትልቅ ጀብዱ እንደፈጸመ ጀግና ቆጥረዋል፡፡ ሌላው የተሰማው ዜና ከመጪው የ2013 ምርጫ ኦፌኮ ራሱን አግልሎ አይሳተፍም የሚለው ነው፡፡ ለዚህ ምክንያቱ አባሎቼ ታስረውብኛል፣ ቢሮዎቻችንም ተዘግተውብናል ብለዋል፡፡ ይህ የታሰሩ የተወሰኑ የኦፌኮ አባላቱ ቀደም ሲል በረሃብ አድማ መንግሥትን በማስጨነቅ፣ ከሕግና ሥርዓት ውጪ ከእስር እንዲፈቱ ሲደረግ የነበረው ትግል ቅጥያም ይመስላል፡፡

በዚያን ጊዜ የኦሮሞ ሕዝብ ‹‹›› ብሎ ከእነሱ ጎን በመሠለፍ በመንግሥት ላይ ተፅዕኖ ፈጥሮ መንግሥት ተገዶ ይፈታናል ብለው ያሰቡት ከንቱ ሆኖ በመቅረቱ፣ ይህ በምርጫ አልሳተፍም ሥልት በምዕራቡ ዓለም በኢትዮጵያ ላይ እየሸረበ ካለው ሴራ፣ እነዚህ የታሰሩትን አባላት ማስፈታት የፖለቲካ ትርፍ ያስገኝ ይሆን ከሚል የተሳሳተ ዕሳቤ የመጣ ይመስላል፡፡ በእውነቱ የፕሮፌሰር መረራ የእስከ አሁን የፖለቲካ ታሪክ በአግባቡ ሲመረመር፣ ለኦሮሞ ሕዝብም ሆነ ለኢትዮጵያ የሰጠው ፋይዳ እምብዛም ነው፡፡ ከጥቅሙ ይልቅ ጉዳቱ ያመዝናል፡፡ ይህ የሆነበት ምክንያት የእርሳቸው የፖለቲካ ስትራቴጂ ተስፋ ሊሰጥ በማይችል በአሉታዊ አስተሳሰብ (Negative thinking) ላይ የተመሠረተ፣መቃወምና በመተቸት ተግባር ውስጥ የራስን ዝናና ክብር ከማሳደግ ውጪ ሌላ ፋይዳ የሌለው በመሆኑ ነው፡፡ እንዲያውም ኢሕአዴግን ዴሞክራት ለማሰኘነት ነው ሲያገለግሉ የኖሩት፡፡ ኢሕአዴግም የማይጎዱና ለአጫዋችነት ስለሚረዳቸው ሳይነኳቸው ቆይቷል፡፡

ፕሮፌሰሩ በኢሕአዴግ ከመታሰራቸው አሥር ቀናት አካባቢ ቀደም ብሎ በአዲስ ዘመን ጋዜጣ የሰጡት ቃለ መጠይቅ ምላሽ ነበር፡፡ በቃለ ምልልሱ ሲሰጡት የነበረው በውጭ የሚኖሩ ኢሕአዴግ በሽብርተኝነት የፈረጃቸው የፖለቲካ ድርጅቶች ከሚያወሩት ጋር ተመሳሳይ ነበር፡፡ ስለዚህ የታሰሩት በጀብደኝነታቸው እንጂ ከኦሮሞ ሕዝብም ሆነ ከአገር ጉዳይ ጋር በሚያያዝ ጉዳይ አይደለም፡፡ 2009 ዓ.ም. በተለይ በኦሮሚያ የቄሮና ቀሬ ትግል ሲፋፋም ይህን የኦሮሞ ወጣት ትግል ፕሮፌሰር መረራ ይመሩ ይሆን የሚል ፍርኃት ስለገጠመው ነው ኢሕአዴግ ሊያስራቸው የቻለው፡፡ በለውጥ ኃይል ወደ ሥልጣን ሲመጣ ከእስር ቤት ሲፈቱ፣ ከለውጥ ኃይሉ ጎን በመሆን የኦሮሞን ሕዝብ ጥያቄ በአግባቡ እንዲመለስ በማገዝ ፈንታ ወዲያው የዶ/ ዓብይን መንግሥት ወደ መቃወም ነው የገቡት፡፡ ይህ አሉታዊ ባህሪያቸውና የግል ዝናና ክብርን ከመፈለግ ውጪ ለአገር የተሻለ መሥራት በሚል አይደለም፡፡ ከእስር በተፈቱበት ሰሞን የአሜሪካ ድምፅ ሬዲዮ ቃለ መጠይቅ ሲያደረግላቸው፣ በእነ አቶ ለማና ሌሎች ኃይሎች ከእስር ቤት ተፈተዋል፣ ለወደፊት ከእነሱ ጋር ለመሥራት ተዘጋጅተዋል የሚል መንፈስ ያለው ጥያቄ ጋዜጠኛዋ ስታቀርብላቸው ምላሹን ለመስጠት ሲያቅማሙ ቆይተው፣ ጋዜጠኛዋ በተደጋጋሚ ጥያቄውን ስታቀርብላቸው፣ ‹‹ለማ እኮ የእኔ ተማሪ ነው›› ያሉት፡፡ ይህ ሁለት ትርጉም አለው፡፡ አንደኛው ይህን ያስተማርኩት እኔ በመሆኑ ከእኔ በላይ ዕውቀት የለውም ማለት ይሆናል፡፡ ሁለተኛው ግን የአቶ ለማን ትግል ውጤት የመጋራት በሚመስል እኔ እኮ ስለአስተማርኳቸው ነው ውጤታማ የሆኑት የሚል ነው፡፡ እንግዲያውስ የእሳቸው ውጤት ይሆን አቶ ለማ ትግሉን በመሀል አቋርጠው ወደ እሳቸው ቡድን ያዘነበሉት? ስለዚህፕሮፌሰር መረራ ባህሪ ቀረፃ ውጤት ይሆን እንዴ ተወዳጅና ለለውጡ ትልቅ አስተዋፅኦ የነበራቸውን አቶ ለማን ያጣነው? ይህ ከሆነ በፕሮፌሰሩ ማስተማር ሒደት በርካታ ዜጎች በእሳቸው አሉታዊ አስተሳሰብ ተቀርፀዋል ማለት ይቻላል፡፡

በሌላ በኩል የኦፌኮ አመራሮች በሙሉ ማለት ይቻላል በዚህ በአሉታዊ አስተሳሰብ የተካኑ ናቸው፡፡ በዚህም ምክንያት ነው አገራችን ኢትዮጵያን ለማዳን በውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን ከፍተኛ ትግል በሚያደርጉበት ወቅት የጠላት ተባባሪ በመሆን ለለውጡ መንግሥት ባላንጣ የሆኑት፡፡ ኦፌኮን ከመንግሥትና ከሕዝብ ተፃራሪ ሆኖ መቆሙን የሚያሳየው፣ በአቶ ዳውድ የሚመራው ኦነግን ጨምሮ በትግራይ የሕግ ማስከበር ዕርምጃን አይደግፉም፡፡ እነሱ ትሕነግ በሰሜን የነበረውን የአገር መከላከያ ኃይል በግፍ ሲጨፈጭፍ የፌዴራሉ መንግሥት በደስታ አበባ እንዲያቀብላቸው ፈልገው ይሆን? ይህ አቋማቸው ደግሞ ለሕግ ማስከበሩ ድጋፍ ከፍተኛ የሆነ ገንዘብና ሰንጋ ለመከላከያ ኃይል ካበረከተው የኦሮሞ ሕዝብ በተፃራሪ መቆማቸውን በገሃድ የሚያጋልጥ ነው፡፡ ሌላው ኦፌኮ በቅርቡ በሰሜን ሸዋ በተፈጠረው የኦሮሞና የአማራ የአካባቢ ግጭትና በሌሎቹ ጉዳዮች ያወጣው መግለጫ የተላለፈው ከካይሮ በግብፅ መንግሥት ድጋፍ በሚሰራጨው ኦኤምኤን ሚዲያ ነበር፡፡ ስለዚህ ኦፌኮ ከግብፅ መንግሥት በተዘዋዋሪ እየተጠቀመ ነው ማለት ነው፡፡ ይህ ደግሞ ባንዳነትንና የአገር ክህደትን በግልጽ የሚያሳመረጃ ነው፡፡ ፕሮፌሰር መረራ አሉታዊ አስተሳሰባቸውን የሚለካው ሌላ ጉዳይ ‹‹የተራበ ሕዝብ መሪዎቹን ይበላል›› የሚሉት ቀልድ ይሁን ቁምነገር ያልለየለት ፌዛዊ ንግግራቸው ነው፡፡ ስለዚህ እንደ እሳቸው አባባል ሕዝቡ ተርቦ መሪዎቹን በመብላት እንዲያስወግዳቸው የጎዳና ላይ ነውጥ ማካሄድ እንጂ፣ / ዓብይ እየመሩ ያለውን ሪፎርም ከማንኳሰስ በስተቀር ለአገር ዕድገት የሚበጅ የተሻለ ሐሳብ ይዘው በሰላማዊ መንገድ ለመፎካከር/ለመወዳደር ፍላጎቱ ወይም ብቃቱ የላቸውም፡፡

ኦፌኮ ከምርጫ ወጥተናል የሚለው ለመሆኑ በአሁኑ ጊዜ በምርጫ የት ነው ተወዳድረው የሚያሸንፉት? የድምፃዊ ሃጫሉን አስከሬን ባንገላቱበት አምቦ? በአርሲ?  በባሌ? በጂማ? በኢሉባቡር? የትም ማሸነፍ አይችሉም፡፡ እነዚህስ ከእስር ካልተፈታን የሚሉት ከእስር ቤት ተፈተውስ  ሕዝብ ውስጥ በንፁህ ህሊና መኖር ይችሉ ይሆን? በእነሱ አማካይነት ያለቀው ሕዝብ ደም እየጮኽ መሆኑንይረዱት ይሆን? ‹‹ደንቆሮ ያለው ዕውቀት እስከ ደነቆረበት ድረስ ያለው ነው፤›› ይባላል፡፡ እንደ ድሮ ቄሮ፣ ቄሮ በሚል ጥሪ የኦሮሞን ወጣት የሚነዱ መስሎዋቸው ከሆነ፣ ይህ አሁን የለም፡፡ ነጋ ጠባ በፌስቡክ ላይ የሚወሸክቱትን ጥቂት መሰሎቻቸውን እንደ ሕዝብ ድጋፍ ቆጥረውት  ከሆነም ባይሳሳቱ መልካም ነው፡፡ ከአሁን በኋላ ከእነሱ ጎን ተሠልፎ በደሙ ያመጣውን ለውጥ እንደ እነሱ የሚቃወም የኦሮሞ ሕዝብ የለም፡፡ የኦሮሞን ሕዝብ አዋርደዋል፡፡ ኦሮሞንም ጨምሮ በርካታ ሌሎች ዜጎች  በግፍ በጭካኔ እንዲገደሉ ምክንያት ሆነዋል፡፡  እንደዚሁም ሕዝቡ ተረጋግቶ የልማት ሥራ ላይ በመሳተፍ ከድህነት እንዳይወጣ በተለያዩ የሽብር ቅስቀሳዎች ያደናግሩታል፡፡ በተለይ ወጣቱ ተስፋ ቢስ እንዲሆንና ተስፋ ቆርጦ ለአመፅ እንዲነሳሳና ወገኖቹን እንዲገድል፣ ንብረት እንዲያወድም ብሎም ለእነሱ  ወደ ሥልጣን መወጣጫ መሣሪያ እንዲሆንላቸው ጥረዋል፡፡ የድምፃዊ ሃጫሉ ድንገተኛ ሞት ጊዜ በምዕራብና ደቡብ አርሲ፣ በባሌና በሻሸመኔ የደረሰው ጉዳት ለዚህ በቂ ማስረጃ ነው፡፡ በሌላ በኩል መሪዎች ፖለቲካን  እንደ ንግድና ሀብት ማካበት በድሎት ለመኖር የሚጠቀሙበት የሥራ አማራጭ ማድረጋቸው ነው፡፡ በእነዚህና በሌሎች ምክንያቶች ሕዝባችን በእነሱ ተሰላችቷል፣ በአሁኑ ጊዜ እነሱም ተተፍተዋል፡፡ አንዳንዶች ከመጪው ከምርጫ በኋላ በኦሮሚያ ብጥብጥ ይኖራል የሚል ሥጋት አላቸው፡፡ ነገር ግን የእነዚህ ኃይል ደጋፊዎች የተመናመኑና ሕዝብ ለይቶ የተፋቸው በመሆኑ፣ ሕዝቡን ለማንቀሳቀስና ለአመፅ ለማነሳሳት ምንም አቅም የሌላቸው ሆነዋል፡፡ እነሱ የሚተነፍሱት በባንዳ ቅጥረኞች በማኅበራዊ ሚዲያ፣ ኦኤምንና ኩሽ በመሳሰሉት ሚዲያዎች ላይ ብቻ ነው፡፡ በእነዚህ ሚዲያዎች ሲያለቀሱና ሲያስለቅሱ ይውላሉያድራሉየዕልቂት ሟርት እየተመኙና ሙሾ እያወረዱ ንግዳቸውን ያጧጡፋሉ፡፡

‹‹መልከ ጥፉን በስም ይደግፉ›› እንዲሉ በምርጫ ተወዳድረው ማሸነፍ ስለማይችሉ ሰበብ ፈጥረው ከምርጫ ራሳችንን አግለናል ማለት የተሻለ ክብር የሚሰጣቸው መስሏቸዋል፡፡ ይህ የመገዳደር የፖለቲካ ባህል እስካሁንም ከጉዳት በስተቀር የጠቀመን የሌለ በመሆኑና በአሁኑ ጊዜ በአብዛኛው ሕዝብ የሚደገፈውን ለውጥ ለማሰናከል መሥራት የዴሞክራሲ መብት ፈጽሞ ሊሆን አይችልም፡፡ እንዲህ ዓይነት ድርጊቶች ካሁን በኋላ በኢትዮጵያ ተቀባይነት ሊኖራቸው አይገባም፡፡ እነዚህ የሐሳብ ድርቀት ያጠቃቸውና ለአገር ምንም ራዕይ የሌላቸው ግለሰቦች የፖለቲካ ድርጅቶቹን እንደ ገቢ ምንጭ በመውሰድ፣ አገርን በማጥላላትና የኦሮሞን ወጣቶች ለመጠቀም የሚያደርጉት መፍጨርጨር በትዕግሥት መታየት የለበትም፡፡ እነ ፕሮፌሰር መረራና አንዳንድ የኦሮሞ ዳያስፖራ ምሁራን የሚባሉት ስለምክክር (Dialogue) ዘወትር ያነሳሉ፡፡ በምን ዓይነት ቋንቋ ነው እነሱ የሚከተሉት የአሉታ ፖለቲካ ከተጨባጩ ሁኔታ ጋር የሚስማማው ለማለት ካልሆነ በስተቀር፣ በውይይት ከእነሱ ጋር የለውጥ ኃይሉ የሚግባባበት ነጥብ የለውም፡፡ የለውጥ ኃይሉን ዓላማና አካሄድ ከተቀበሉ ይቻል ይሆናል፡፡ ግን እነሱ እኮ ሥልጣን ለማግኘት ሲሉ ሊሆን የማይችል የሽግግር መንግሥት ነው የሚጠይቁት፡፡

በአቶ ዳውድ ኢብሳ የሚመራው ኦነግ

ኦነግ ከሽግግሩ መንግሥት ከወጣና በአቶ ዳውድ መመራት ከጀመረ ጊዜ አንስቶ እየተከፋፈለ የመጣ ሲሆን፣ በቅርቡም የመከፋፈል ዕጣ ያጋጠመው ድርጅት ነው፡፡ ምናልባት ክፍፍሉ አቶ ዳውድ ለብቻቸው እስከሚቀሩ ድረስ ይቀጥል ይሆን? እነዚህ ሁኔታዎች የሚያሳዩት የግለሰቡሞክራት ያለመሆን፣ብዕናቸውንና የአመራር ድክመታቸውን የሚጠቁም በመሆኑ የኦሮሞ ሕዝብ ከዚህ ድርጅት ከአሁን በኋላ የሚጠብቀው በጎ ነገር አይኖርም፡፡ ድርጅቱ በአሁኑ ጊዜ ከእርሱ ተገንጥለው ወጡ ለሚባሉት ሽፍቶች በሞራል ደጋፊነት ከሚኖረው ጉዳት በስተቀር፣ በኦሮሞ ሕዝብ ላይ የሚኖረው ተፅዕኖ እዚህ ግባ የሚባል አይደለም፡፡

ከኦነግ ያፈነገጡ የትጥቅ ትግል የሚያካሄዱ ኃይሎች (የኦሮሞ ነፃነት ሠራዊት)

የእነዚህ ኃይሎች አፈጣጠር በሰላማዊ መንገድ የፖለቲካ ትግሉን እንዲያካሄድ ከኤርትራ ወደ አገር የገባው በአቶ ዳውድ የሚመራው ኦነግ፣ በአገር ውስጥ የነበሩትን ታጣቂዎች ትጥቅ አስፈትቶ ወደ ሰላማዊ ኑሮ እንዲመለሱ የተደረገውን ጥረት አቶ ዳውድ ‹‹ትጥቅ አስፈቺውና ፈቺው ማነው?›› የሚለውን ሐሳብ ከሰነዘሩ በኋላ፣ ኃይሉ ተጠናክሮ በደቡብና ምዕራብ ኦሮሚያ በርካታ ሥፍራዎችን መቆጣጠሩ ይታወሳል፡፡ በቅርብ ጊዜ እየወጡ ባሉ መረጃዎች በኦሮሚያ ውስጥ ሁለት የሽምቅ ተዋጊ ኃይሎች እንዳሉ ይነገራል፡፡ አንደኛው በተለምዶ ኦነግ ሸኔ የሚባለው የኦነግ ሠራዊት ብሎ ራሱን የሚጠራው ነው፡፡ ይህ ሕዝብን አይዘርፍም፣ የሰውንም ሕይወት አያጠፋም እየተባለ ይነገርለታል፡፡ ሁለተኛው ሥራ አጥና የሥነ ምግባር ጉድለት ያላቸውን ምናልባት የቅጥረኛ ጽንፈኛ ኃይሎች ለፖለቲካ ቁማርነት ለመጠቀም ፀረ ኢትዮጵያ ኃይሎች ያደራጁዋቸው ሊሆኑ ይችላሉ፡፡ እነዚህ በከተማዎች ጭምር የሚኖሩና እየተጠራሩ ዝርፊያ፣ ግድና ሴቶችን የመድፈር ተግባር የሚፈጸሙ ሽብርተኞች ናቸው፡፡ ይሁን እንጂ ሁለቱም ኃይሎች ለኦሮሞ ሕዝብ ጥቅም ምንም የማይፈይዱ በመሆናቸው አንዱ ከሌላው ይሻላል የሚያስብል አይደለም፡፡

እነዚህ ታጣቂዎች የሚዋጉለት ዓላማቸው ምንድነው? የኦሮሞን ሕዝብ በአሁኑ ጊዜ ከማን ነፃ ሊያወጡ ነው? ከዶ/ ዓብይ ነው? ከሆነ የሚያሳዝኑ ብቻ ሳይሆን የሚያስቁምቸው፡፡ አሁን በዚህ የሽፍትነት ሥራ ንፁኃን ግለሰቦችን በመግደልና መንግሥትንማሸነፍ ዓላማቸውን ከግብ ለማድረስ ይቻላል? የኦሮሞንሊስና ልዩ ኃይል መግደል ምን ትርጉም ይሰጣቸው ይሆን?  እነዚህ ኃይሎች የሚዋጉት ዶ/ር ዓብይ ኦሮሞን ከድቶ ከአማራ ጋር ሆኗል፣ ስለዚህ የአማራ የበላይነት ተመልሶ እንዳይመጣ ለመከላከል ነው የሚሉ አሉ፡፡ በዚህ አስተሳሰብ አንዳንድ ቀድሞ የኦነግ አባላትና ደጋፊዎች የነበሩና ኦነግን የሚያፈቅሩና እንደ ሃይማኖት የሚከተሉ የተማሩ ኦሮሞዎች ጭምር ሲቸገሩና ይኼንኑ ሐሳብ ሲያራምዱ ይታያሉ፡፡ የአማራ የበላይነትን ለመከላከል ኦሮሞ የትጥቅ ትግል ማካሄድ አያስፈልገውም፡፡ እስከ አፍንጫው የታጠቀውን በትሕነግ የሚዘወረውን ኢሕአዴግን በሰላማዊ ትግል ያሽመደመድው ሕዝባዊ ኃይል አሁንም አለ፡፡ ከዚህ በኋላ ሕዝባችን በመተባበር የጋራ እሴቶቹን እያዳበረ ሁሉም በእኩልነት የሚኖርባትን ኢትዮጵያን መገንባት እንጂ ሌላ የሚፈጠርበት ዕድል የለም፡፡ የኦሮሞ ሕዝብ አሁን በደረሰበት ንቃተ ህሊና የሌሎችን የበላይነት የሚቀበልበት ወይም የራሱን የበላይነት በሌሎች ላይ ለመጫን ሁኔታ ውስጥ አይደለም፡፡ መንግሥት በወሰደው ዕርምጃ እንዲሁም ሕዝቡ ላይ ባደረሰው ጉዳት የኦነግ ሸኔ በሕዝቡ በመተፋቱና በተለይ አባገዳዎች በዚሁ ታጣቂ ላይ በወሰዱት የውግዘት አቋም መዳከሙና ወደ ተራ ሽፍታነት መውረዱ የሚታወቅ ነው፡፡ ቡድኑ በኦሮሞ ሕዝብ ሥም እንቀሳቅሳለሁ ይበል እንጂ ዶ/ር ዓብይ እንዳሉት የኦሮሞ ሕዝብ ጭምር ጠላት በመሆኑ ሊወገዝና ሊወገድ የሚገባው ነው፡፡ ይህ ቡድን በወገኖቻችን ላይ ግድያ የሚፈጽመው አንደኛ አለን ለማለትና የገንዘብ ድጋፍ ለሚያደርጉለት የጠላት መንግሥታትና በውጭ የሚኖሩ ግራ የተጋቡ ወይም የተወናበዱ የአንዳንድ የኦሮሞያስፖራዎች ድጋፍ እንዳይቋረጥበትና እንዲጨምር ለማድረግ ነው፡፡ ሁለተኛው በአማራና በኦሮሞ ሕዝብ መካከል በተለይ አመራሮችን ለማጋጨትና ለመለያየት ነው፡፡ በዚህም ብዙ ሙከራዎች ተደርገዋል፡፡ ይሁን እንጂ ሕዝቡ ውስጥ ውዥንብር ማስከተሉ ባይቀርም አመራሮችን በመከፋፈሉ እስካሁን እምብዛም የተሳካላቸው አይመስልም፡፡

 በአብን ውስጥ የሚገኙና የሌሎች የአማራ ብሔርተኛ ኃይሎች

ለኢትዮጵያ አገራችን ግንባታና ቀጣይነት የአማርኛ ተናጋሪው ኅብረተሰብ የነበረውና ለወደፊትም የሚኖረው ሚና ከፍተኛ ነው፡፡ አንድነቷ የተጠበቀ አገር እንዲኖረን የሁለቱ የኦሮሞና የአማራ ሕዝብ በጋራ በቅንጅት ሌሎቹንም ብሔረሰቦች በማስተባበር፣ ኢትዮጵያን ዴሞክራሲየዊ በሆነ መንገድ የመምራት ትልቅ ኃላፊነት አለባቸው፡፡ የተጀመረው ለውጥም ውጤታማ የሆነው የሁለቱ ሕዝቦች የፖለቲካ ልሂቃን በፈጠሩት ቅንጅት መሆኑ የሚታወቅ ነው፡፡ በሌላ በኩል ከ1960ዎቹ ጀምሮ የሁለቱ ብሔረሰቦች ልሂቃን በአገራዊ ጉዳይ ከእርስ በርስ ጥርጣሬ፣ ከታሪክ ጉንጎና ተላቀው ልዩነትን በውይይት በመፍታት ተከባብረውና ተግባብተው አለመሥራት አገራችንን ትልቅ ዋጋ አስከፍሏል፡፡ ያለፉት ሃያ ሰባት ዓመታት በሕወሓት የሚዘወረው ኢሕአዴግ ሕዝቡን እየከፋፈለና እየበደለ ሥልጣን ላይመቆየት መቻሉ ዋነኛው ምክንያት፣ ይኼው የሁለቱ ብሔረሰቦች የፖለቲካ ልሂቃን ተቻችለውና ተግባብተው አብሮ መሥራት መቸገር ነው፡፡ ነገር ግን በለውጡ ዋዜማ በኢሕአዴግ ውስጥ በነበሩት የኦሕዴድ ተራማጅ ኃይሎች በሚስጥር ውስጥ ለውስጥ ከአማራሞክራሲያዊ ድርጅት መሪዎች ጋር ምክክር የመካሄዱ ሥራ እንደተጠበቀ ሆኖ ማለት ነው፡፡ በእነ አቶ ለማና / ዓብ አነሳሽነት በመጀመሪያ ‹‹ጣና ኬኛ››፣ ‹‹ጣና የእኛም ነው›› በሚል ወደ ባህር ዳር የማቅናት በኦሮሞ ወጣቶች የተጀመረው የሁለቱን ሕዝቦች መቀራረብበኋላም በኦሮሚያ ክልል መሪዎችና የአገር ሽማግሌዎች ባህር ዳር ጉብኝት በማድረግ የተፈጠረው የሁለቱ ሕዝቦች የፖለቲካ ልሂቃን መቀራረብ፣ ሕወሓትን ከሥልጣን ለማስነሳት የበቃ ተግባር መሆኑ የሚታወስ ነው፡፡ በዚህ ሒደት የክቡር አቶ ገዱ አንዳርጋቸውና የክቡር አቶ ደመቀ መኰንን እንዲሁም ፋኖ፣ ዛርማና ሌሎች የአገራችን ወጣቶችና የኅብረተሰቡ አካላት አስተዋጽኦ ድምር ለለውጡ መምጣት ከፍተኛ ሚና የነበረውም መሆኑ የሚታወቅ ነው፡፡ በቅርቡ በውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን የአሜሪካና የምዕራብ አውሮፓ አገሮች በኢትዮጵያ ላይ በመፍጠር ላይ የሚገኙትን አግባብ ያልሆነ ተፅዕኖ በመቃወም ሲያደርጉ የነበረው፣ የጋራ ኅብረትና ለለውጥ ኃይሉ በተለይ ለዶ/ ዓብይ የሚደረገው ድጋፍ ይኼንኑ የጋራ ኅብረት ሥራን የሚያመላክት ነው፡፡ ይሁን እንጂ ይህ የሕዝቡ ኅብረትና ቅንጅት ለዓላማቸው መሳካት ያሠጋቸው የውጭና የውስጥ ኃይሎች ከአገራቸው በላይ ሥልጣናቸውንና ክብራቸውን በማስበለጥ፣ ይኼንን የተፈጠረውን አገራዊ አንድነት ለማፍረስ በትጋት ሲሠሩ ይታያሉ፡፡

ጠንካራ ኢትዮጵያን ማየት የማይፈልጉ ግብፆችና ምዕራባውያን ኢትዮጵያውያንን በመከፋፈልና በማተራመስ ለማዳከም አቅደው፣ በጀት መድበው፣ ለዚህ አስፈጻሚ ቅጥረኞችን ገዝተው፣ በተለይ በቤኒሻንጉልና በምዕራብ ወለጋ ንፁኃን አርሶ አደሮችንና ሌሎች ዜጎቻችንን በመግደልና በተለይ የአማራና የኦሮሞን ሕዝብ በማጋጨት የተፈጠረውን ቅንጅትና ኅብረት ለማፍረስ ሌት ተቀን እየሠሩ ይገኛሉ፡፡ በሌላ በኩል ይህንን የመከፋፈል ዕቅድ አውቀውም ይህን ሳያውቁ በተዘጋጀው ቦይ ለመፍሰስ የሚያገለግሉ ኃይሎች እንደ የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄአብንእና ሌሎች ዘረኝነት የሚያጠቃቸው ዘረኛ ኃይሎች የቆጥቆጥ ሁኔታ ይታያል፡፡ የአማራን የቆየ ገናና ታሪክ እናድሳለን የሚል መንፈስ ያዘለ በኦሮሞ የፖለቲካ ልሂቃን ግንባር ቀደምትነት በመመራት ላይ ያለውን የለውጥ ኃይል ያለ መቀበል የሚመስሉ እንቅስቃሴዎችም በእነዚህ ኃይሎች ዘንድ ይስተዋላል፡፡ በአቶ እስክንድር የሚመራው የባልዳራስ ለፍትሕና ለዴሞክራሲ ፓርቲ መቋቋም የዚሁ በአዲስ አበባ አስተዳደር የኦሮሞ መሪዎችን በአማራ ብሔርተኞች የመተካት ፕሮጀክት ነው፡፡ በአብን ውስጥ የሚሰተዋሉት አክራሪና በሌሎች ማኅበራዊ ‹‹አክቲቪስቶች›› የሚቀነቀነው  ብሔርተኛ አቋም ቀደም ሲል እንደተገለጸው በጠንካራዎቹ የኦሮሞ መሪዎች፣ በተለይ በክቡር አቶ ሽመልስ አብዲሳ፣ በክብርት / አዳነች አቤቤና በአቶ ታዬ ደንደአ ላይ የሚደረገው የማኅበራዊ ሚዲያ ዘመቻ የኦሮሞ መሪዎችን በማሸማቀቅና ከተቻለም ከሥልጣን በማስወገድ ለእነርሱ ሊስማማ በሚችል ደካማ አመራር እንዲተኩ ለማስደረግ የሚሠራ ቅንጅታዊ ሥራ ይመስላል፡፡ እንደዚህ ዓይነት ድርጊቶች ብልፅግና ፓርቲው የኦሮሞን አክራሪ ኃይሎች ጠንክሮ እንዳይታገል፣ ብሎም ለእነሱ መጠናከር ይረዳ እንደሆነ እንጂ ለአማራ ሕዝብ የሚያመጣው በጎ ነገር የለም፡፡ እነዚህ የዘረኝነት መንፈስ የተፀናወታቸው ኃይሎች የሚገደሉትን ንፁኃን የአማራ አርሶ አደሮችን ለዓላማቸው መሳካት ለፖለቲካ ፍጆታ ሲጠቀሙባቸው ይስተዋላል፡፡ በየቀኑ የአማራ ተወላጆች በቤንሻንጉልና በወለጋ መገደልን ለፖለቲካቸው ግብ መሳካት እንደ ዕድል እየወሰዱ ችግሮቹን ያራግባሉ፡፡

የዓብይ መንግሥትና የኦሮሚያን ክልል ብሔራዊ መንግሥት የሕዝባችንን ደኅንነት መጠበቅ አልቻሉም፣ ስለዚህ በመጪው ምርጫ የአማራ ብልፅግና ፓርቲ  በተለይ / ዓብይ መመረጥ የለባቸውም የሚሉ መልዕክቶችን በተዘዋዋሪ በማስተላለፍ፣ የአማራ ሕዝብ ለዶ/ ዓብይ እየሰጠ ያለውን ድጋፍ ለማሳጣት በቅንጅት ከውጭ ኃይሎች ጋር ተቀናጅተው የሚሠሩ ይመስላል፡፡ በተጠናከረና በተደራጀ ቅንጅት በድንገት በአሳቻ መልክ በሽምቅ ውጊያ የማካሄድን ግድያ በየመንደሩ የመከላከያ ኃይልን በማሳለፍ መከላከልስ እንዴትስ ይቻላል? አክቲቪስቶቹ የሚያሠራጩት የኦሮሞ ብልፅግና ፓርቲ ነው የአማራን አርሶ አደሮች የሚገድለውና የሚያስገድለው የሚባለው ኦሮሞን ከአማራ ሕዝብ ጋር የማጋጨት ከእውነት የራቀ ተራ ፕሮፓጋንዳ በመሆኑ በዚህ ጉዳይ ጊዜ ልናጠፋ አይገባም፡፡ በእርግጥ በመንግሥት በተለይም በታችኛው አመራሮች ሆን ተብሎም ሆነ በመዘናጋት የሚፈጠሩ ድርጊቶች ሊኖሩ ይችላሉ፡፡ እነዚህን ችግሮች በገለልተኛ ኃይሎች አጣርቶ ዕርምጃ መውሰድ የፌደራል መንግሥት ኃላፊነትና ግዴታ ይሆናል፡፡

ከኦሮሞ ሕዝብ የተገኘ / ዓብይን የመሰለ የቴክኖሎጂ ዕውቀትን ጨምሮ  በሁለገብ ዕውቀትና የመጠቀ አስተሳሰብ የተካነ መሪ በአሁኑ ጊዜ ኢትዮጵያ ማግኘቷ ትልቅ ዕድል ነው፡፡ ሌሎች አገሮች በዚህ ምክንያት በኢትዮጵያ ይቀናሉ፡፡ ሕይወቱን ቀብድ አስይዞ ይህን ለውጥ በትዕግሥትና በብልህነት ከጓዶቹ ጋር እየመራና አሁንም ከምዕራባዊያን የሚደርስባትን ተፅዕኖ ተቋቁሞቆራጥነትና አገርን ለድርድርና ለተፅዕኖ ላለማድረግ የሚሠራውን መሪ ለመጣል መሥራት የሥልጣን ጥመኝነት የዘረኝነት፣ የምቀኝነትና የጥቅም ፍላጎት ከአገር ህልውና በላይ ምን ያህል እንደሄደ ከማሳየት ውጪ ሌላ ምን አለ? የእነዚህ ኃይሎች ምኞትና ጥረት / ዓብይ በአማራ ሕዝብ ያላቸውን ድጋፍ እንዲቀንስ በተለይ ብልፅግና ፓርቲ በአማራ ክልል እንዲሸነፍ ነው፡፡ የአማራ ሕዝብ አዋቂና የሚያገናዝብ በመሆኑ እነሱ ባዘጋጁት ወጥመድ የሚገባና ለብልፅግና ፓርቲም ሆነ ለዶ/ር ዓብይ ድጋፉን ይነሳል ተብሎ አይገመትም፡፡ አይሆንም እንጂ ቢሆንና የአማራ ሕዝብ ብልፅግናን ባይመርጥ / ዓብይ በኦሮሞና በሌሎቹ ኢትዮጵያውያን የሚመረጡ ስለመሆናቸው ምንም ጥርጥር አይኖርም፡፡ ከሞራልም ሆነ ከዕውቀት ዝግጅት አንፃር የኦሮሞ ሕዝብ የኢትዮጵያን ሕዝብ አስተባብሮ በዴሞክራሲያዊ ሥርዓት በእኩልነት ለመምራት ብቁ ነው፡፡ ሊታወቅና ግልጽ ሊሆን የሚገባው የአማራ ሕዝብ ዶ/ር ዓብይን በመሪነት ሲቀበልና ድጋፍ ሲያደርግ፣ የኦሮሞ የፖለቲካ ልሂቃን አመራርን የተቀበለ መሆኑ የተረጋገጠ ነው፡፡ በዚህ መሠረተ ሐሳብ ሕዝቡ የለውጥ ሒደቱን ደግፎ ሲሠራ ቆይቷል፡፡ የኢትዮጵያን አንድነት የሚያስከብር መንግሥት ከመጣ በማንም አመራር መተዳደር ይቻላል የሚለውን የአማራ ሕዝብና ሌላው መላ የኢትዮጵያ ሕዝብ የተቀበለው ነው፡፡ ስለዚህ እነዚህ ጽንፈኛ ኃይሎች ሁኔታዎችን ተገንዝበው አቋማቸውን እንደገና እንዲገመገሙና ወደ ትክክለኛው መንገድ እንዲመጡ ይመከራሉ፡፡ በአሁኑ ጊዜ በኢትዮጵያ አንዱ ብሔረሰብ ሌላውን የሚገዛበት ሁኔታ የለም፡፡ ለመገንባት ጥረት በመደረግ ላይ ባለው ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ሁሉም በእኩልነት የሚተዳደርበት ሥርዓት ስለሚሆን፣ አንዱ የበላይ ሌላው የበታች የሆነ ሁኔታ አይፈጠርም፣ አይኖርምም፡፡ መደመር ማለትም ሁሉም ተስማምቶና ተባብሮ አገር እየገነቡ በመከባበር በእኩልነት የሚኖርበት ሥርዓት ነው የሚል እምነት አለ፡፡

የቀሩት የትሕነግ መሪዎች አባላትና ደጋፊዎቹ

የትግራይ ሕዝብ ነፃነት ግንባርትሕነግ2010 ዓ.ም. በተካሄደው የመንግሥት ለውጥ በማዕከላዊ መንግሥት የነበረውን ሥልጣን ለቆ ወደ መቀሌ ትግራይ በመግባት ለጦርነት ሲዘጋጅ ቆይቷል፡፡ ጥቅምት 24 ቀን 2013 .ም. በሰሜን በሚገኘው  የመከላከያ ኃይል ላይ በወሰደው አሰቃቂ የማጥቃትና የመሣሪያዎች ዝርፊያ የተነሳ  የፌዴራሉ መንግሥት ዕርምጃ መውሰዱ ይታወቃል፡፡ ይሁን እንጂ በክልሉ አሁንም የትሕነግ ትርፍራፊ ኃይል ወደ ሽምቅ ውጊያ በመግባት በሚያደርገው እንቅስቃሴ የክልሉ ሰላም ሙሉ በሙሉ አልተመለሰም፡፡ በትግራይ በጦርነቱ ምክንያት የተፈጸሙት ጉዳቶች በርካታ መሆናቸው የታወቀ ነው፡፡ ይሁን እንጂ ጦርነቱ ያስከተላቸውን ችግሮች  አጉልቶ በማውጣት በውጤት ላይ ብቻ በመመሥረት የጎረቤት አገር ንብረት ወሰደ፣ ሰው ገደለ፣ ወዘተ የሚባሉትን መደረግ ባይኖርበትም ይህን ማራገብ ብቻ ሳይሆን ይህ ሁኔታ ለምን ተፈጠረ? ለምን ወደ ጦርነት ተገባ? ለዚህ ጥፋተኛውና ተጠያቂው ማነው? የሚሉት ጥያቄዎች ምላሽ ሊያገኙ ይገባል፡፡ በአንድ አገር ሁለት መንግሥት ሊኖር አይችልም፡፡ በአገራችን ላለፉት ወደ ሦስት ዓመት ለሚጠጋ ጊዜያት ግን በሰሜን የፌዴራል መንግሥትን የሚገዳደር ወይም ተግባብቶ የማይሠራ በሕወሓት የሚመራ የትግራይ ክልል መንግሥት ነበር፡፡ በሁለቱ መካከል የነበረውን ችግር በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት የፌዴራል መንግሥትና በግል ዶ/ር ዓብይ ብዙ ለፍተዋል፡፡ የሴቶች ተወካይ እናቶች፣ የአገር ሽማግሌዎች፣ በአዲስ አበባ የሚኖሩ ታዋቂ የትግራይ ባለሀብቶችና የውጭ አገር አምባሳደር ሳይቀር አማላጅ እስከ መላክ ድረስ ለምነዋቸዋል፡፡

ሕወሓቶችን ግን ይህን ሁሉ አሻፈረኝ ብለው ለውጡን ተቀብለው 1.8 ሚሊዮን በዕርዳታና በሴፍትኔት የሚኖረውን ሕዝባቸውን ሥራ በመፍጠር ከልመና ማላቀቅ ሲገቸባው፣ ለጦርነት በመቶ ሺሕ የሚቆጠሩ ልዩ ኃይልና ሚሊሻ በማሠልጠን ሲዘጋጁ ነበር የቆዩት፡፡ ጥቅምት 24 ቀን 2013 ዓ.ም. የትግራይን ሕዝብ በዘበኝነት ሲጠብቅ የነበረውና ብዙ ውለታ ለትግራይ ሕዝብ የዋለውን የአገር መከላከያ በመውረር ኢሰብዓዊ በሆነ ሁኔታ በመጨፍጨፍ ጦርነቱን ጀምረዋል፡፡ ከጦርነቱ በኋላ የኢትዮጵያ መንግሥት አንድ ቢሊዮን ዶላር የሚገመት የምግብ ዕርዳታ ለትግራይ ሕዝብ ሲያቀርብና ትሕነግ ያወደማቸውን የመሠረተ ልማት ሲሠራ፣ አሁንም ይኸው ሲቀጥል የአገሪቱ ኢንዱስትሪዎች በውጭ ምንዛሪ እጥረት ምርት እያቆሙ ነው፡፡ አገሪቱ ባላት ውስን የውጭ ምንዛሪ የሰውን ሕይወት ማዳን ይቀድማል ተብሎ ለስንዴ ግዥ ሲውል፣  በሌላው የኢትዮጵያ ሕዝብ ላይ የኑሮ ውድነትን እንዲጨምር ተደርጓል፡፡ የተለያዩ ማኅበረሰቦችና የክልል መንግሥታት ከሕዝባቸው ቀንሰው ለትግራይ ሕዝብ  ዕርዳታ እያቀረቡ የሕዝብን ሕይወት ለመታደግ ቀና ደፋ ይላሉ፡፡ ግን የትግራይ ወገኖች ሁሉም ናቸው ባይባልም በተለይ በውጭ አገር የሚኖሩ በሚዲያቸው ወጣቶችን ለጦርነት ይቀሰቅሳሉ፣ የዓለም መንግሥታት ኢትዮጵያ ላይ ማዕቀብ እንዲጥል ተግተው ይሠራሉ  የኢትዮጵያ ገጽታ እንዲበላሽ ይደክማሉ፡፡ ሕዝባቸው ከረሃብ መታደግ  ግን የለበትም፡፡ ለሕዝብ የሚያስብ ለየትኛው ነው ቅድሚያ መስጠት ያለበት? ሕዝባቸውን ከማዳን ይልቅ የመረጡት የሕወሓትን አልሸነፍ ባይነት ክብርን ማስመለስ ነው፡፡ በአገር ውስጥም ሕወሓትን በማውገዝ ከመንግሥት ጋር በመሠለፍ ፈንታ ወጣቶችን እያበረታቱ ወደ በረሃ ለሽምቅ ውጊያ ይልካሉ፣ ይሄዳሉ፡፡ እነዚህ ኃይሎች ምን እየሠሩ ነው? ዘረኝነት ጭፍን ነው የሚባለው እውነት ሊሆን ነው? ሌላው በጣም የሚያሳዝነውና የሚያሳምመው በውጭ የሚኖሩ ተወላጆች ከግብፅና ከሱዳን መንግሥታት ጋር በመሠለፍ የህዳሴ ግድብ እንዳይጠናቀቅ በሚሸርቡት ሴራ በከሃዲነትና በባንዳነት መሠለፍ ነው፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ በማስጀመራቸው የተወደሱበትን የህዳሴ ግድብ እንዳይሳካ ሴራ መሸረብ ለትግራይ ሕዝብ ጥቅም ነውን? በትግራይ የሚደረገው የሽምቅ ውጊያስ ዓላማው ምንድነው? ትሕነግን ወደ ሥልጣን መመለስ ነው? ይህስ ይቻላል? ቢቻልስ ለትግራይ ሕዝብ ይጠቅማል? ትሕነግ/ሕወሓት እስካሁን በትግራይ ሕዝብ ለደረሰው በደል፣ ውርደትና ዘርፈ ብዙ ችግሮች ተጠያቂ መሆኑን በሀቅ መገንዘብ ያስፈልጋል፡፡ ዛሬ የሞተና እስትንፋሱ ብቻ የቀረን የፖለቲካ ድርጅት የመደገፍ ምክንያቱ ምንድነው? በእልህ ትግራይንኃይል ከኢትዮጵያ ለመገንጠል በቀሩት የትሕነግ አባላትና ደጋፊዎች የሚቀነቀነው ሐሳብስ የትግራይ ሕዝብ ፍላጎት ነውን? ይህ ተግባር ፈጽሞ የሚሳካ አይሆንም፡፡ ቢሆንም ለሕዝቡ የሚጠቅም አይደለም፡፡ የትግራይ ሕዝብ እስካሁን ከተፈጸሙት ስህተቶች መማር አለበት፡፡ በእርግጥ በትግራይ ‹‹ተሳስቻለሁ ይቅርታ ማለት እንደ ውርደት ይታያል›› ይህ ባህል በአሁኑ በሠለጠነ ጊዜ ሊሠራ የሚችል አይደለም፡፡ ስለዚህ ሁሉም በአልሸነፍነትና በዕልህ ከመመራት ወደ ህሊና መምጣት ይጠቅማል፡፡

የማኅበራዊ አንቂዎች (አክቲቪስቶች)

እንደሚታወቀው በአብዛኛው ከትግራይ፣ ከአማራና ከኦሮሞ ብሔረሰቦች የወጡ አንዳንድ ማኅበራዊ አንቂዎች ሕዝብን ከሕዝብ፣ አንዱን ብሔር ከሌላው፣ ሕዝብን ከመንግሥት ጋር የሚያጋጩ መልዕክቶችን ሲያሰራጩ ይውላሉ፡፡ ብሔረሰባቸውን በመወከል ወይም የሌላው ብሔር ተቆርቋሪ በመምሰል የሚያሠራጩዋቸው መልዕክቶች እምብዛም ንቃትና የማመዛዘን ወይም ምክንያታዊ ያልሆነውን የኅብረተሰብ ኃይልና የወጣት ኃይል ወደፈለጉት ሲነዱት ቆይተዋል፡፡ ይህ ኃይል ለአገር አለመረጋጋትና ለሰላም መታወክ የሚጫወተው ሚና ቀላል አይደለም፡፡ ሰሞኑን የሚገደሉትን የአማራ ተወላጆች ለመታደግ በሚመስል አስፈላጊ ያልሆነ ሰላማዊ ሠልፍ በአሜሪካ ሲካሄድ የነበረው፣ የዚሁ የማኅበራዊ ሚዲያው ጉዳዩን የማራገብና የኦሮሚያ ክልል መሪዎችን በተጠያቂነት ለማቅረብ ብሎም ችግሮቹ የብሔር መልክ እንዲይዙ የተሠራው ሥራ ውጤት ነው፡፡

የችግሩ ዋነኛ ምንጮች

የ1966 ዓ.ም. አብዮት ይዟቸው ከተነሳው ዓበይት አጀንዳዎች አንዱ የብሔር እኩልነት ጥያቄ ነበር፡፡ ደርግ የመሬት ላራሹን ጥያቄ በመመለስ በዚያው የፊውዳሉ ሥርዓት እንዲገረሰስ ሲደረግ የብሔር ጥያቄን በአግባቡ አልመለስም፡፡ በዚህ ሳቢያ ለየብሔራቸው መብት የሚታገሉ ኢሕአዴግ ሲገባ በርካታ የፖለቲካ ድርጅቶች እንደነበሩ ይታወሳል፡፡ ኢሕአዴግ ይህን ጥያቄ በተሟላ መልኩም ባይሆን ለመመለስ ዕርምጃ ወስዷል፡፡ የብሔር ጭቆና በኢትዮጵያ አለ ወይም የለም በሚሉት ሐሳቦች ላይ መግባባት አልተደረሰም፡፡ የብሔር ጭቆና የሚባል የለም፡፡ የመደብ ጥቆና ብቻ ነበር የሚሉትና የብሔር ጭቆና ነበር በሚሉት መካከል አሁንም ልዩነት አለ፡፡ የደርግ ሥርዓት ዴሞክራሲያዊ ባለመሆኑና የብሔር ጥያቄን ለመመለስ ባለመቻሉ ከደርግ ጋር በሕዝብ ድርጅት ጥላ ሥር ሲሠሩ የነበሩት እንደ ኢጭአት በኋላ በኦነግ፣ ትሕነግ (ሕወሓት)  እንዲሁም ሌሎች ኦብነግ፣ የአፋር፣ የቤኒሻንጉል፣ የጋምቤላ ንቅናቄዎች፣ ወዘተ ለትጥቅ ትግል ወደ ጫካ ገቡ፡፡ ኢሕአዴግ በኢትዮጵያ ሕዝብና በእነዚህ ኃይሎች ትብብር ደርግን አሸንፎ  ሲገባ እነዚህን ኃይሎች አሰባስቦ ነው የሽግግር መንግሥት ያቋቋመው፡፡ ሕዝቡን ከፋፍሎ ለመግዛት እንዲመቸው ነው የብሔረሰብ ክፍፍሉን አስተዳደራዊ ቅርፅ ሰጥቶ በማደራጀት ጥያቄውን መመለስ የሞከረው፡፡ ይሁን እንጂ ሥርዓቱን ዴሞክራሲያዊ በማድረግና የዜጎችን መብቶች በሕግ በማስከበር ጥያቄውን መመለስ ይቻል ነበር የሚሉ በርካታዎች ናቸው፡፡ ኢሕአዴግ ከአነስተኛ የሕዝብ ቁጥር በተገኘ ትሕነግ የሚዘወር በመሆኑ ግልጽነትን በማስፈን ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት መመሥረት ስለሚቸገር፣ በሥልጣን ላይ ለመቆየት የብሔርተኝነቱ ክፍፍሉ እንዲጎላ ጉልህ ሚና ተጫውቷል ማለት ይቻላል፡፡

ዶ/ር ዓብይና ሌሎች ዴሞክራሲያዊ ኃይሎች አሁን እየታገሉ ያሉት ክፍፍሉን በማላላት የኢትዮጵያዊነት ስሜትን በኅብረ ብሔራዊነት ውስጥ በማጠናከር ቀስ በቀስ  የብሔረሰብ ሚናን በማሳነስ በእኩልነት የዜጎች የግልና የወል መብት የተከበረበት ጠንካራ ዴሞክራሲያዊ አገር መመሥረት ነው፡፡ የብሔር ጥያቄ የሚባለው የውሸት ትርክት ነው፣ ጥያቄውን የሚያነሱ ኃይሎችን ሰጥ ለጥ አድርጎ ዝም ማሰኘት ይቻላል የሚሉ አንዳንዶች በኅብረተሰቡ ውስጥ አሉ፡፡ በእርግጥ ይህ አመለካከታቸው የአማራን የፖለቲካ ልሂቃንን ሁሉ የሚወክል አይደለም፡፡ እነ ዶ/ር አምባቸውና ሌሎች በርካታ አሁንም የብልፅግና ፓርቲ አባል የሆኑ፣ እንዲሁም የሌሎች ፖለቲካ ድርጅቶች አባላትና የማንኛውም ፓርቲ አባል ያልሆኑ የአማራ ተወላጅ ምሁራን ከዚህ ትምክህተኛና አክራሪ አስተሳሰብ ነፃ የሆኑ ናቸው፡፡ ይህ ዋልታ ረገጥ ኃይል በርካታ የአብን አባላት ተከታይ የነበሩት፣ በአዲስ አበባ ከተማ ደግሞ የባልደራስ ለፍትሕና ለዴሞክራሲ ፓርቲ ያሉትን ያጠቃልላል፡፡ በአክቲቪስት ደረጃ በውጭ አገር የ‹‹Ethio 360›› ጋሻ ጃግሬዎች ሀብታሙ አያሌውና ኤርሚያስ ለገሠ የመሳሰሉትንም የያዘ ነው፡፡

የኦሮሞ ብሔርተኝነት እየተዳከመ ሲመጣ  የአማራ ብሔርተኝነት አብንና ነባሮቹ የእነ ሻለቃ ዳዊት ወልደ ጊዮርጊስ ቡድንና የእነዚሁ አቀንቃኝ እንደሆኑ የሚነገርላቸው የማኅበራዊ አንቂዋን መስከረም አበራን ተጣብቷል፡፡ ሌሎቹ እንኳን የኢትዮጵያዊነት ጭንብል አጥልቀው ነበር የአማራ ብሔርተኝነትን የሚያቀነቅኑት፡፡ አንዳንዶች ግን በቀጥታ በአማራነት ስም ነው የሕዝቡን አንድነት የሚቦረብሩት፡፡ የሻለቃ ዳዊት ወልደ ጊዮርጊስን ተልዕኮ በአገር ቤት ያስፈጽማሉ የሚባሉት መስከረም አበራ ከዘረኝነት ቅስቀሳቸው ባሻገር፣ ሁልጊዜ ዶ/ር ዓብይንና የአማራ ክልል የብልፅግናን የመንግሥት መሪዎችን በመንቀፍና በማንኳሰስ በሕዝብ ተቀባይነታቸው እንዲወርድ አጥብቀው ይሠራሉ፡፡ በአሁኑ የአገራችን ተጨባጭ ሁኔታ የለውጥ ኃይሉን መንግሥት በተፃራሪነት ቆሞ መቃወምና መገዳደር ማለት ለውጡ ወደፊት እንዳይራመድ እንቅፋት መሆን ነው፡፡ ስለሆነም በእንደዚህ ዓይነት ተግባራት የሚሳተፉት የፖለቲካ ኃይሎች አገርንና ሕዝብን የሚጎዱ እንጂ የሚያበረክቱት አስተዋጽኦ የለም፡፡ እንደዚህ ዓይነት የእልህና የግትር አካሄድ ላለፉት ዓመታት የኢትዮጵያንለቲካ አልጠቀመም፡፡ የተቃዋሚ ኃይሎችን ተፅዕኖ ለመቋቋም መንግሥት በሕዝብ ላይ ሸምቆቆ እንዲያጠብቅና ለበለጠ ሰብዓዊ መብት መጣስ ነው ዳረገው፡፡

ለምሳሌ ኦነግና ኦፌኮ በኦሮሚያ ውስጥ ከለውጥ ኃይሉ አካሄድ በተፃራሪ በመቆማቸው፣ ሥልጣን በእነዚህ ኃይሎች እጅ ይገባል በሚል ፍርኃትና ጥርጣሬ  ይመስላል መንግሥት ኅብረተሰቡን በማሳተፍ በታችኛው የአስተዳደር እርከን ከራሱ ፓርቲ አባላት ውጪ ያሉትን ሌሎች ዜጎችን አምኖ ወደ አመራር ለማምጣት አልቻለም ይሆን የሚል ጥርጣሬ አለ፡፡ ይህ ከሆነ በዚህ ሳቢያ ሕዝቡ በቀደሙት አመራሮች ለሙስናና ለመልካም አስተዳደር  ችግሮች ተጋልጦ እንዲቆይ ተደርጓል ማለት ነው፡፡ በሌሎችም ክልሎች ተመሳሳይ ሁኔታ የታየ ይመስለኛል፡፡ ስለዚህ እንዲህ ዓይነት ተቃዋሚዎች መኖራቸው ለኅብረተሰቡ ያተረፈው ጉዳት ብቻ ነው፡፡ በጽሑፌ መግቢያ ላይ አገራችን ኢትዮጵያ ያለችበትን ሁኔታ ስጠቅስ፣ ከዚህ መንግሥት የተለየና የሚገዳደር የፖለቲካ አቋም መያዝ ከግብፆችናምዕራባዊያንን ጋር መሠለፍ ነው ብዬ ነበር፡፡ ከዚህ በፊት በተሞክሮ እንደሚታወቀው እነዚህ ጠላቶች ኢትዮጵያን ለማጥቃት የሚጠቀሙት እንዲህ ዓይነት የውስጥ ተቃዋሚዎችን ነው፡፡ ይህ ደግሞ ባንዳነት ወይም አገር መክዳት ነው፡፡ ስለዚህ እነዚህን ዓይነት የባንዳነት ተግባር የሚፈጽሙትን ከበረቱ  (ኢትዮጵያ ሕዝብ) ለይቶ ለብቻ ማሰር ወይም ማግለል ነው መደረግ ያለበት፡፡ የዴሞክራሲ መብት የሚባሉት ሕግና ሥርዓትን ተከትለው መከናወን ያለባቸውና ከአገር ህልውና በታችም ያሉ ናቸው፡፡ እኛ ኢትዮጵያውያን ካሁን በኋላ በተቃዋሚነት አገር የሚበጠብጡትን፣ ከውጭ ጠላት መንግሥታት ጋር የሚሠለፉ ወይም ሊያግዙ በሚችል ተግባር ላይ በመሳተፍ ለአገር አደጋ የሚሆኑትን የፖለቲካ ኃይሎች መታገስ አይገባንም፡፡ እኛ ተቃዋሚዎች ነን በሚል ከውጭ የጠላት ኃይሎች ጋር ተመሳጥረው በመንግሥት ላይ ብሎም በአገር ጉዳት የሚያደርሱት ኃይሎች ደረታቸውን ነፍተው የሚፎልሉበት ዕድል ፈጽሞ ሊሰጣቸው አይገባም፡፡ ምናልባት በቅርቡ በአማራ ብሔራዊ ክልላዊ ዞን የተከሰተው መንግሥትን ለማሳጣት ሆን ተብሎ፣ የዞኑን ሕዝብ የሚያነሳሱና ወደ ግጭት ያመሩ የተንኮል ሥራዎች ተሠርተው ይሆን? የሚል ጥርጣሬንም ያጭራል፡፡

በኦሮሞ ብሔረሰብ ዞን የተፈጠሩ ክስተቶች

በአማራ ብሔራዊ ክልል የኦሮሞ ብሔረሰብ ዞን የተፈጠረው ችግርና የሰው ሕይወት መጥፋትና ንብረት መውደም ያሳዝናል፡፡ በዚህ አካባቢ ባለፈው ሁለት ዓመት ችግር ተከስቶ የግጭት መነሻውና መፍትሔው በወቅቱ በአግባቡ ባለመሰጠቱና ተሸፋፍኖ በማለፉ፣ ‹‹አለባብሰው ቢያርሱ በአረም ይመለሱ›› ዓይነት ዳግመኛ የዛሬ ወር አካባቢ የተፈጠረ ግጭት ሰሞኑን አገርሽቶባቸው በአጣዬ፣ በሸዋ ሮቢትና በአካባቢው ከባድ ጉዳት ማድረሱ ይታወቃል፡፡ ጉዳዩ የተለያዩ መረጃዎችን በማገጣጠም ሲተነተን የግጭቱ ምክንያት የአማራ ክልላዊ መንግሥት ዞኑን በአግባቡ ያለ መምራቱን የሚያመላክት ነው፡፡ በተወካዮች ምክር ቤት ሐሳብ ያቀረቡት የዞኑ የሕዝብ እንደራሴ ከተናገሩት ውስጥ ‹‹የዞኑ ሕዝብ እስር ቤት እንዳሉ የሚቆጠር ነው›› ሲሉና በኋላም የክልሉ ልዩ ኃይል ከዞኑ ይውጣ ሲባል በአማራ ክልል ሥር አልተዳደርም ማለት ነው፡፡ እንዲሁም የዞኑ ተወላጅ የሆኑት ለሕክምና የሚሄዱት በግፍ ተገድለዋል የሚባለው ሁሉ፣ በክልሉ አመራርና በዞኑ ሕዝብ መካከል የጎላ ቅራኔ መፈጠሩን የሚያሳይ ነው፡፡ በሌላ በኩል የክልሉ መንግሥት ተዋጊዎቹን ‹‹የኦነግ ሸኔ ነው፤›› ሲል የዞን አመራሮች፣ ‹‹ኦነግ ሸኔ የሚባል የለም፣ የተቆጡ አርሶ አደሮች ናቸው›› ይላሉ፡፡ ጉዳዩ ሕዝቡን ያስቆጡ ሁኔታዎች ተፈጥረው የዞኑ ወጣቶች የተሳተፉበት ከኋላ የሕዝቡ ድጋፍ ያለው የሚመስል ውጊያ ነው የተካሄደው፡፡ የመብት ጥያቄ ካለ በሰላማዊ ትግል ጥያቄውን ማቅረብ እንጂ፣ እንዲህ ዓይነት አውዳሚ ጦርነት ውስጥ መግባት ፈጽሞ ተቀባይነት የሌለውና ይህንን ያስተባበሩና የመሩ ለሕግ መቅረብ አለባቸው፡፡ ይሁን እንጂ ችግሩን በጦርነት ብቻ መፍታት ስለማይቻል መንግሥት ሁኔታውን የሚያረጋጋ ዕርምጃ ወስዶ የችግሩ ምንጭና የሕዝቡ ጥያቄ ካለ በአግባቡ ታይቶ ዘለቄታ ያለው መፍትሔ እንዲሰጥ መደረግ ይኖርበታል፡፡ ችግሩ ፖለቲካዊ ስለሚመስል የፖለቲካ መፍትሔ ይሻል፡፡

አጠቃላይ የመፍትሔ ሐሳቦች

የአማራና የኦሮሚያ ክልል አመራሮች በቅርቡ በወቅታዊ የሁለቱ ክልል የሰላምና የጋራ ልማት ዙሪያ ውይይት በማድረግ፣ በመግባባት ንግግሩን መቋጨታቸው የሚታወቅ ነው፡፡ ይህን መሰል ንግግሮችን በየጊዜው በማካሄድ በመካከላቸው የሚፈጠሩ ጉዳዮች ወደ ሚዲያ ሳይሄዱና ክፍተቱ ሳይጎላ፣ እዚያው በብልፅግና ፓርቲ በውስጥ እንደሚጨርሱም ስምምነት ላይ ደርሰዋል፡፡ ይህ በጎ ጅምር ነው፡፡ ቀደም ሲል የተጀመሩት የሁለቱ ክልል ምሁራንና የንግድ ማኅበረሰብ ውይይቶች እንደገና ተጠናክረው ቢቀጥሉ የሚል እምነትም አለ፡፡ የየክልሉ የወጣቶች ተወካዮች የየክልሉን ታሪካዊ ቦታዎችን የሚጎበኙበትና ውይይት የሚያካሂዱባቸው መድረኮች ቢፈጠሩና የሕዝብ ለሕዝብ ግንኙነቱ የበለጠ ቢጠናከር፣ አገራዊ አመለካከትን ለማጎልበትና ሕዝባዊ አንድነትን ለማጠንከር በጣም አስፈላጊ ናቸው፡፡ በወለጋ የሚታየውን ችግር  በዘለቄታው ለመፍታት የአካባቢዎቹን የመንግሥት አመራሮች በጉዳዩ ራሳቸውን የበለጠ አሳምነው፣ የአካባቢዎቹን የአማራ ተወላጆች ጎረቤት የሆኑትን ነባር የኦሮሞ ተወላጆችን በማሳመን ከአማራ ተወላጆቹ ጎን እንዲሠለፉ፣ ንብረታቸውን እንዲጠብቁ ሰፊ ሥራ መሥራት ይገባል፡፡ የአማራና የኦሮሞ ተወላጆች እንደ ሌሎቹ አካባቢዎች ሁሉ በወለጋም ተቀራርበውና ተጋብተው በፍቅር የሚኖሩ በመሆናቸው በሕዝብ መሀል ችግር የለም፡፡ ፖለቲከኞች ለሥልጣናቸው ሲሉ ሕዝቡን በማበጣበጥ ለአገር መፍረስ የሚዳርገውን እኩይ ተግባራቸውን በጊዜ ተው ሊባሉ ይገባል፡፡

የኦሮሞ ሕዝብ ሌሎች ወገኖቹን አቅፎ በሰላም አብሮ ሲኖር የቆየውን ባህል ወይም እሴት በወለጋም መተግበር ለኦሮሞ ሕዝብ ክብር በመሆኑ፣ በትንንሽ ጥቅሞችና በቅርቡ በተስፋፋው የዘረኝነት ስሜት ይህ አኩሪ እሴቱ ሊበላሽ አይገባም፡፡ ሁሉም የአካባቢው ተወላጆችም ሆኑ ሌሎች በተለይ በአዲስ አበባ የሚኖሩ የኦሮሞ ምሁራንና የንግድ ማኅበረሰብ ጭምር ተረባርበው በዚህ ጉዳይ ላይ መሥራት ይኖርባቸዋል፡፡ ይህ ሲደረግ ነው የኢትዮጵያ አንድነት ሊጠበቅ የሚችለው፣ ሰላምና መረጋጋትን ማስፈን የሚቻለው፡፡ ጥቃቅን በደሎችና ቁርሾዎች ጎልተው ቢነገሩም ነገሮችን በይቅርታና በትዕግሥት በማለፍ ካልሆነም ለወደፊት በማቆየት አሁን አገራችን ያለችበትን ትልቁን ሥዕል በማየት፣ የጋራ አገርን ለመገንባት መሥራት ይበልጥ ትኩረት ሊደረግበት ይገባል፡፡ የኦሮሞ ብሔረሰብ ዞን የተከሰተውንም ችግር ከአማራና ከኦሮሞ ውጪ በሆኑ በሌሎች ገለልተኛ የብሔረሰብ ተወካዮች ከደቡብ፣ ከሲዳማ፣ ከሱማሌ፣ ወዘተ ክልል በተወጣጡ የአገር ሽማግሌዎች የሁለቱን አጎራባች ሕዝቦችን በማሳተፍ የችግሩ ምንጭ ተጣርቶ ጥፋተኛውን በይቅርታና በምሕረት በመደራረግ ዘላቂ ሰላም መፈጠር ይኖርበታል፡፡ ያለፈው አልፏል፣ ከሁለቱም ወገን አሁን የሚፈለገው የዕርቅና የሰላም ሐሳብ እንጂ፣ ግጭቶችን የሚያባብስ ቅስቀሳና ውትወታ አይጠቅምም፡፡ በእርግጥ በግለሰብ ደረጃ ተጠያቂ የሚሆኑት በሕግ ሊጠየቁ ይገባል፡፡ የአካባቢ ወጣቶች በአስተሳሰብና በአመለካከት ለውጥም ላይ ብዙ ሊሠራ ይገባል፡፡

ሕዝብን ያሳተፈ አገርን የመታደግ ንቅናቄ በመላ አገሪቱ ማካሄድና እያንዳንዱ ዜጋ ምን እያደረገ እንደሆነ እንዲገነዘብ ሰፊ ሥራ ሊሠራ ይገባል፡፡ በኢትዮጵያ አንድነትና ለውጡን ዘላቂ ለማድረግ የውይይት መድረኮች በዩኒቨርሲቲዎች፣ በቀበሌዎች፣ በተለያዩ መሥሪያ ቤቶች፣ በሌላውም በስፋት ማካሄድ ይጠቅማል፡፡  በተቻለ መጠን አወያዮች የመንግሥት ሰዎች ሳይሆኑ ገለልተኛ ከሆኑ ምሁራንና የንግድ ማኅበረሰብ የተወጣጡ ሆነው የተወሰነ ሥልጠና ወስደው ሥራውን የሚሠሩበት ሁኔታ መመቻቸት አለበት፡፡  ቀደም ሲል እንደተገለጸው አገር ለሚበጠብጡ ኃይሎች ማሳሰቢያና ማስጠንቀቂያም ሊሆን ይችላል፡፡ ከዚህ አድራጎታቸው ተቆጥበው የለውጥ ኃይሉን በማገዝ አገራችን ከተደቀነባት ችግር በጋራ ለማሸጋገር እንዲቻል በመንግሥት የመጨረሻ ጥሪ  ቢደረግላቸው ይመረጣል፡፡ በጫካ ውስጥ በውጊያ ላይ  ተደብቀው የሚገኙት ይቅርታና ምሕረት ተደርጎላቸው በሰላም እጅ ሰጥተው፣ የተሃድሶ ትምህርት ተሰጥቶዋቸው ወደ ሕዝቡ ቢዋሀዱ ይበጃል፡፡ በጦርነት ማዳከምና አቅመ ቢስ ማድረግ ይቻል ይሆናል እንጂ ሰላምን ማስፈን የሚቻለው በዕርቅ ብቻ ነው፡፡ መበቃቀል፣ ላለፈው ጥፋት ተጠያቂ ለማድረግ መጠቃቃቱ አሁን አይጠቅመንም፡፡ ከሁለቱም ወገን የሚሞተው ኢትዮጵያን ለወደፊቱ የሚገነባ ኃይል ነው፡፡ የሚጠፋው የአገር ሀብት ነው፡፡ ዛሬ ጠላት የሚባለው ራሱን ካስተካከለ ነገ ወዳጅና ጥሩ ዜጋ መሆኑ አይቀርም፡፡

ጥሪውን ተቀብለው ከመንግሥት ጋር ለመሥራት ከተስማሙ፣ በከባድ ወንጀል ተጠርጥረው የታሰሩትን ሳይጨምር በጥርጣሬ የታሰሩ ሌሎች ካሉ ከእስር በምሕረት ተለቀውና የተሃድሶ ሥልጠና አግኝተው ወደ ኅብረተሰቡ እንዲቀላቀሉ ማድረግ ያስፈልጋል፡፡ ይኼው ጉዳይ በተለይ በኦሮሚያ በአባገዳዎችና በሌሎች አገር ሽማግሌዎች በድጋሚ እንዲያነጋግሩዋቸው ማስደረግና ይኼንኑ የማይቀበሉ ከሆነ፣ በአባ ገዳዎችና በአገር ሽማግሌዎችና በአገር ጠላትነት እንዲወገዙ፣ ከሕዝቡ እንዲገለሉና እነዚህ ኃይሎች ተለይተው መንግሥት ብቻ ሳይሆን ሕዝቡ እንዲከታተላቸው ማድረግ ይገባል፡፡ ሕጉ በሚፈቅደው መሠረት በአገር ከሃዲነትም ጭምር ለሕግ ማቅረብ ያስፈልጋል፡፡ በሁሉም ችግሩ በሚታይባቸው አካባቢ ይኼው ጥሪና በአገር ሽማግሌዎችና በሃይማኖት መሪዎች የማግባባት ሥራ በሁሉም ወገኖች እንዲሠራ ተደርጎ፣ ከዚህ የሚያፈነግጡት ላይ ሕጋዊ ዕርምጃ መወሰዱ አስፈላጊ ይሆናል፡፡ ቀደም ሲል አገርን በመበጥበጥ የተጠቀሱ የፖለቲካ ፓርቲ አባላት ራሳቸውን በመጠየቅ በመሪዎቻቸው ላይ ተፅዕኖ ፈጥረው፣ የድርጅታቸው አቋም እንዲስተካከል መታገል ይኖርባቸዋል፡፡ ይህ የማይሳካ ከሆነ ራሳቸውን ከፓርቲዎቹ አግልለው ወደ ሕዝቡ እንዲደባለቁ ሊሠሩ ይገባል፡፡ ፕሮፌሰር መረራና አቶ ዳውድ ኢብሳ ከፖለቲካው ራሳቸውን ጡረታ ቢያወጡ፣ ይበቃቸዋል፡፡ የአሁኑን ኢትዮጵያን ወይም የኦሮሞን ሕዝብ ለመምራት በዕድሜያቸውም ጭምር ብቁ አይደሉም፡፡ ዕድሉን ለተተኪው ወጣቶች ሰጥተው በክብር ቢኖሩ ይሻላቸዋል፡፡ ራሳቸውን ካላስተካከሉ ፕሮፌሰሩ ከተመደቡባቸው የመንግሥት ሥራዎችና ከዩኒቨርሲቲ መምህርነት ጭምር ማስነሳት ያስፈልጋል፡፡ የአማራ ሕዝብና በተለይ ምሁራን እንዲሁም በውጭ የሚኖሩ ተወላጆች ሁኔታዎችን ከዘር ስበት በፀዳ መንገድ ተንትነውና ተረድተው፣ በአገር ጉዳይ ላይ የሚረብሹትን ተወላጆቻቸውን አደብ ለማስገዛት ጠንካራ ሥራ ይጠብቃቸዋል፡፡ በክልሉ እያቆጠቆጡ ያሉትን ዋልታ ረገጦችን ሕዝቡ ተፅዕኖ ፈጥሮባቸው እንዲታገሱ በተደራጀና በተጠናከረ መንገድ ብዙ መሥራት ይኖርባቸዋል፡፡ በሚቀጥለው ምርጫም ሥልጣን በሚበጠብጡት እጅ እንዳይወድቅ ጥንቃቄ ሊደረግ ይገባል፡፡ ሁሉም ወገን ከተጠቂነትና ግልፍተኛ ስሜት በመላቀቅ ጉዳዮችን በዕርጋታና በትዕግሥት በማየት፣ ሌሎችን ወገኖች ስሜት ሳይነካ በመከባበር ላይ በተመሠረተ ይህን አገራዊ ችግር በሰላም ለመፍታት መረባረብ ይኖርብናል፡፡

ለወደፊቱ ያልተፈቱ ጉዳዮች ካሉ ከምርጫ በኋላ በዕርቅ ኮሚሽን አማካይነት ሊታዩ ይችላሉ፡፡ ተፈጠሩ የተባሉ ችግሮች በዝርዝር ቀርበው በብሔራዊ ዕርቅ አማካይነት በዳይ ወገን ላደረሰው ጥፋት አምኖ ይቅርታ በመጠየቅ፣ ይቅርታ በመደራረግና ከልብ የመነጨ ዕርቅ በመፍጠር በብሔራዊ ዕርቅ ይህን የተበዳይነትና የበዳይነት ታሪክ ምዕራፍ በሁሉም የኢትዮጵያ ብሔረሰቦች መካከል እንዲዘጋ ማድረግ ይቻላል፡፡ መሆንም ያለበት ይኼው ነው፡፡ ታሪክን  ከዳግመኛ ስህተት መዳኛ ለመማሪያ እንጂ ወደ ኋላ በመሄድ ለግጭትና ቁርሾ መፍጠሪያ መጠቀም አይገባም፡፡ በታሪክ የግድ መስማማትም አይኖርብንም፡፡ በምንስማማባቸው አገራዊ ጉዳዮች በጋራ እየሠራን ስንሄድ ልዩነቶቻችን እየጠበቡ ይመጣሉ፡፡ በአሁኑ ጊዜ የሚታዩትን ትናንሽ ጉዳዮችን ትተን አገራችንን ለሚያሠጉ ለትልልቅ ጉዳዮች ቅድሚያ ሰጥተን እንደ ቀድሞ ታሪካችን በጋራ በመረባረብ አገራችን ከተደቀነባት ችግር ማውጣት አለብን፡፡ በአገራችን በሚካሄደው ምርጫ ኅብረተሰቡ ተሳትፎውን በማሳደግ በመብቱ መጠቀም የሚያጠያይቅ አይደለም፡፡ በአብዛኛው በዋነኛ ተፎካካሪ ፓርቲዎችና በገዥው ፓርቲ መካከል የሚታዩ ልዩነቶች፣ በማንነት ማለትም በዜግነትና በኅብረ ብሔራዊነት ላይ መመሥረት ነው፡፡ በሌላ በኩል ከዚሁ ጋር በተያያዘ በፌዴራል ክልል አደረጃጀት/አወቃቀር ላይም የተመሠረተው ልዩነት ነው፡፡

አብዛኞቹ ተፎካካሪ ፓርቲዎች የክልሎች አደረጃጀት በቋንቋ ወይም በብሔረሰብ ላይ መመሥረቱ፣ ለግጭትና የእርስ በርስ መከፋፈል አገሪቱን ዳርጓታል የሚል ነው፡፡ ሌሎች የሚሉት ደግሞ የዴሞክራሲ እጥረትና ለመግዛት እንዲመች በልዩነት ላይ የተመሠረተና ከፋፋይና ጨቋኝ አገዛዝ ይህን ፈጠረ እንጂ፣ በብሔረሰብ ላይ በተመሠረተው አደረጃጀት አይደለም ብለው ይከራከራሉ፡፡  ይህ ይልቅ የብሔረሰቦችን መብት ያስከበረና መተማመንን የፈጠረ ነው ይላሉ፡፡ ይህ ጉዳይ ቀላል አለመሆኑና የኅብረተሰቡን ፍላጎትና አስተያየት ሁሉ የሚፈልግ በመሆኑ፣ በተረጋጋ መንፈስ ከሕገ መንግሥት መሻሻል ጋር የሚኬድበት ሰፊ ጊዜና ጥናትን የሚሻ ጉዳይ ነው፡፡ በጉዳዩ ላይ መግባባት ካስቸገረም በሕዝብ ድምፅ ውሳኔ ሊሰጥበት የሚችል በመሆኑ፣ በአሁኑ ጊዜ የልዩነት አጀንዳ ተደርጎ መወሰድ የለበትም፡፡ ስለሆነም ልዩነቱ እንደተጠበቀ ሆኖ ያለውን ተቀብሎ ማሻሻያዎችን በማካሄድ መቀጠል ነው የሚመከረው፡፡ የነበረውን ሁኔታ በአጭር ጊዜ ለመለወጥ መሄድ ለአገሪቱ የበለጠ ችግርን መጋበዝም ይሆናል፡፡

በዚህ ጽሑፍ አዘጋጅ እምነት በአሁኑ ጊዜ ኢትዮጵያን የገጠማት ወርቃማ ጊዜ ነው፡፡ የ1966 ዓ.ም. አብዮትና አንድ የተማረ ትውልድ ያለቀበት ትግል፣ አሁን ከሚታየው ለውጥ የተሻለ ምን ለማምጣት ነበር? ‹‹በእጅ የያዙት ወርቅ እንደ መዳብ ይቆጠራል›› ካልሆነ አንድነቷ የተጠበቀና በእኩልነት ላይ የተመሠረተ ዴሞክራሲያዊ አገር ለመመሥረት ይህ ሪፎርም ዕድል የከፈተ ነው፡፡ ይህን ችላ ካልን ሌላ ምንድነው የምንፈልገው? ሁሉም ራሱን መጠየቅ አለበት፡፡ የአሁኑ የ2013 ዓ.ም. ምርጫም ሒደቱ እስካሁን ደህና ነው፡፡ በመንግሥትም በኩል ምርጫውን ፍትሐዊና ተዓማኒ ለማድረግ ቁርጠኝነቱ ይታያል፡፡ ስለሆነም ተፎካካሪዎች መገንዘብና ምርጫውን መለካት ያለባቸው በማሸነፍና ድምፅ ባለማግኘት ብቻ ሊሆን አይገባም፡፡ በአገራችን የዴሞክራሲ መሠረቱ መጣሉና ሕዝብ መንግሥትን የማውረድና የመሾም ሥልጣን የሚተገበርበት ሥርዓት መፈጠሩ የሁላችንም ድል መሆኑ ላይ ነው፡፡ በዚህ ምርጫ የሚፈለገው በሙሉ ባይሳካና መጠነኛ ግድፈቶች (መታየት የለባቸውም) ቢታዩም፣ ለወደፊቱ የመማሪያና የሚስተካከል እንደሆነ በመውሰድ ሒደቱን በአዎንታዊነት መወሰዱ የተሻለ ነው፡፡ ሰሞኑን በሚታዩት ክርክሮች አንዳንድ ተፎካካሪዎች የብልፅግና ፓርቲን አናሸንፍም የሚል ተስፋ የመቁረጥ ስሜት ከፊታቸው ይነበባል፡፡ ይሁን እንጂ የሚያስቡትን ያህል ባያሸንፉም ሒደቱ ጤናማ ከሆነ፣ እነሱም ሆኑ ኢትዮጵያን እንዳሸነፈች መውሰድ ይገባቸዋል፡፡ በምርጫ ባያሸንፉም በቂ ዕውቀትና የትምህርት ዝግጅት ያላቸው የተፎካካሪ ፓርቲ አባላት የአሸናፊውን ፓርቲ ርዕዮተ ዓለምና ፕሮግራም ከተቀበሉ፣ በመንግሥታዊ ሥራ ተሾመው ወይም ተመድበው ሊሠሩ ይችላሉ፡፡ በመሀላቸው የርዕዮተ ዓለም ልዩነቶች እምብዛም ስለማይታይ አብሮ መሥራት ይቻላል፡፡ መደመር ማለት ይህ ይመስለኛል፡፡ የአገራችንን የሰው ኃይል በአግባቡ መጠቀምና በጋራ አገርን ለመገንባት እነዚህ ኃይሎች ከገዥው ፓርቲ ጋር በቅርበት የመሥራት አስፈላጊነት የሚያጠያይቅ አይደለም፡፡ ገዥው ፓርቲ ይህንን ይተገብራል የሚል እምነት አለኝ፡፡ ካልሆነም ሊያስብበት ይገባል፡፡ ተፎካካሪዎችና ገዥው ፓርቲ በጎሪጥ በመተያየትና አንዱ ሌላውን ለመጣል በማሴርና በመዶለት የፖለቲካ  ባህላችን ይለወጣል የሚል እምነት አለ፡፡ እስካሁን የታዩትም ይኼንን ያመለክታሉ፡፡ ሕዝቡም በዚህ መሠረተ ሐሳብ በመንግሥትም ላይ ሆነ በተፎካካሪዎችም ሆነ በተቃዋሚዎች/ለመቃወም ብቻ የሚሠሩት/ የበኩሉን ተፅዕኖ መፍጠር ይገባዋል፡፡

የትግራይ ሕዝብ በጦርነቱ የሥነ ልቦና ጉዳት ቢደርስበትም፣ ጉዳቱ የደረሰው በትሕነግ ምክንያት መሆኑን አምኖ ክልሉን ወደ ሰላምና መረጋጋት ለማምጣት መሥራት ይኖርበታል፡፡ የእልህና የበቀል ዕርምጃ ለማንም አይበጅም፡፡ የትግራይ ሕዝብ ዕድሜ ልክ ልጆቹን እየገበረ በጦርነት ውስጥ መኖር የለበትም፡፡ በተለይ የትግራይ ምሁራንና የንግድ ማኅበረሰብ በዚህ ጉዳይ ጥቅምና ጉዳቶችን ለይተው በመተንተን ሕዝቡ ነፃነቱን፣ መብቱንና ሰላሙን ለማስከበር ራሱ በመረጠው ለመተዳደር መብቱን ባገኘበት ለምን ወደ ሽምቅ ውጊያ መሄድ ያስፈልጋል የሚሉትን ሐሳቦች በማንሸራሸር፣ በየቀበሌውና በወረዳው በሚፈልጋቸው መሪዎች እንዲተዳደርና ለልማቱ እንዲነሳ መሥራት ይጠበቅባቸዋል፡፡ የትግራይ ሕዝብ  ከእልህና ከዘረኝነት በመፅዳት ተረጋግቶ፣ አስቦና አሰላስሎ፣ ጥቅምና ጉዳቱን አመዛዝኖ ሰላሙን  የሚያውኩትን አጋልጦ በመስጠት፣ ከክልሉ ጊዜያዊ አስተዳደር ጋር በመተባበር በሚፈበረኩ ውሸቶችና ፕሮፓጋንዳ ሳይታለል፣ በክልሉ ሰላም በማስፈን ለዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ መሠለፍ የሚያጠያይቅ ሊሆን አይገባም፡፡ ሕዝቡ ራሱን ከሕወሓት ነጥሎ በመውሰድ ለሕወሓት ሲወረወሩ የነበሩትን የፕሮፓጋንዳ ሥራዎችን በራሱ እንደደረሰ ሳይወስድ፣ በሞራልና በገንዘብ ከጎኑ የቆመውን የተቀረውን የኢትዮጵያ ሕዝብ አክብሮ ራሱን በማረጋጋት በክልሉ ሰላም ተፈጥሮ ወደ ልማት ለመግባት መሥራት ይጠበቅበታል፡፡ የትግራይ ሕዝብንም ሆነ አገራችንን የሚጠቅመው ይኼው ነው፡፡ የኢትዮጵያን መንግሥትና ሕዝብን በጥላቻ ሳይሆን በወዳጅነትና በአገርነት በማየት፣ በመረጋጋት ሰላም በሚሰፍንበትና ወገኖች በቂ ዕርዳታ አግኝተው ከዚህ ችግር በሚላቀቁበት ላይ ሁሉም በጋራ በቅንጅት መሥራት አስፈላጊ ነው፡፡

የኢትዮጵያ ሕዝብ በሙሉ በያገባኛል መንፈስ ተንቀሳቅሶ፣ የየአካባቢውን ሰላም ከመጠበቅ ባሻገር፣ በአገራዊ ጉዳዮች ድምፁን በማሰማት በመሸምገልም ሆነ ግንዛቤ ለወጣቶች በመስጠትና ያጠፉትን በመኮነንና እንዲስተካከሉ በማድረግ ጉልህ አስተዋጽኦ ማድረግ ይጠበቅበታል፡፡  ሁሉንም ነገር ለመንግሥት በተለይ ለመከላከያ ኃይል ሰጥቶ ውጤቱን መጠበቅ ብቻ በቂ አይሆንም፡፡ መንግሥትም ለዚህ በቂ መድረክ ማዘጋጀት ይኖርበታል፡፡ በኦሮሚያ፣ በአማራና በትግራይ በሚከናወኑ ድርጊቶች የሌሎች ብሔረሰቦች ሁሉ ድምፃቸውን ማሰማት ይኖርባቸዋል፡፡ በእነዚህ አካባቢዎች የሚፈጠሩ ሁኔታዎች ሁሉንም ኢትዮጵያ የሚነኩ በመሆናቸው፣ በሐሳብም ሆነ በአካላዊ እንቅስቃሴ የነቃ ተሳትፎ በየአካባቢው ሊያደርጉ ይገባል፡፡ በማኅበራዊ ሚዲያዎችና በአንዳንድ ከውጭ አገር በተለይ ከግብፅ ካይሮ በሚተላለፉት መደበኛ ሚዲያ የነገሡትን አሉታዊ መልዕክቶች የሚያስተላልፉ ማኅበራዊ አንቂዎችን በተመለከተ ሕዝቡ በተለይ ወጣቱ እንዳይከተላቸው በመሥራት፣ እነሱን ያለ መስማትና ያለ ማዳመጥ አድማ ሁሉ እስከ ማድረግ መሄድ ያሻል፡፡ በዕውቀት የተደገፈ ሰፊና ከፍተኛ ፀረ ፕሮፓጋንዳ ሥራ መጀመር ጊዜ የሚይሰጠው ተግባር መሆን አለበት፡፡ ተለይተው የሚታወቁ ማኅበራዊ አንቂዎች ከአጥፊ አድራጎታቸው ካልተቆጠቡ ሕጋዊ ዕርምጃም እንዲወሰድባቸው መሥራትም የግድ ነው፡፡ በሌላ በኩል ከመንግሥት መረጃዎችን በየወቅቱ ለኅብረተሰቡ አሟልቶ በማቅረብ የተጠናከረ የግንዛቤ ሥራም ሊሠራ ይገባል፡፡ የሚፈበረኩ የሐሰት ወሬዎች ሳይናቁ በየወቅቱ ማስተባበያና የመክሸፊያ ሥራ በመንግሥትም ሆነ በሌሎች የግል ሚዲያዎች ተጠናክሮ መሠራት አለበት፡፡ በማኅበራዊ ሚዲያ ፊት ለፊት ወጥተው በዘር ወይም ብሔር ላይ የተመሠረተ ስድብ የሚረጩትንና  ሕዝብን ከሕዝብ ጋር  የሚያሻክሩትን፣ መንግሥት ለሕግ ማቅረብና ተጠያቂ ማድረግ አለበት፡፡ ሕዝቡም ሊያጋልጥና ጥቆማ ሊሰጥ ይገባል፡፡ የአገራችን የሚዲያ ተቋማት የሚፈለግባቸውን እየሠሩ ባለመሆኑ ትኩረት ያስፈልጋቸዋል፡፡ በዚህ ጽሑፌ ብዙ ሰዎችን ማስቀየሜ ይገባኛል፡፡ ‹‹አካፋን አካፋ›› ማለቱ ዙሪያ ጥምጥም ከመሄድ የተሻለ አቀራረብ ስለሆነ ነው፡፡ ግን አገሬን ኢትዮጵያን ለመታደግ ያደረግኩት በመሆኑ የተወቀሱት የፖለቲካ ድርጅቶችና ግለሰቦች፣ እንዲሁም ሕዝባችን በአዎንታዊ ጎኑ የጽሑፉን መልዕክት እንዲረዱና ራሳቸውን እንዲጠይቁ ያደረግሁት በመሆኑ ከፍተኛ እርካታ ይሰማኛል፡፡

ማሳሰቢያ 

ይህ ጽሑፍ ለብዙኃኑ ተደራሽ እንዲሆን የሚዲያ ተቋማትና አካላት ሌሎች ትንተናዎችን በማቅረብና በማዳበር ሁሉም እንዲወያዩበት እንዲደረግ አጥብቄ እጠይቃሁ፡፡ ኢትዮጵያ በአንድነትና በሰላም ለዘለዓለም ትኑር፡፡

ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እየገለጽን፣ በኢሜይል አድራሻቸው [email protected] ማግኘት ይቻላል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የንብረት ማስመለስ ረቂቅ አዋጅና የሚስተጋቡ ሥጋቶች

ከሰሞኑ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የቀረበው የንብረት ማስመለስ ረቂቅ...

የመጨረሻ የተባለው የንግድ ምክር ቤቱ ምርጫና የሚኒስቴሩ ውሳኔ

በአገር አቀፍ ደረጃ ደረጃ የንግድ ኅብረተሰቡን በመወከል የሚጠቀሰው የኢትዮጵያ...

ሚስጥሩ!

ጉዞ ከካዛንቺስ ወደ ስድስት ኪሎ፡፡ የጥንቶቹ አራዶች መናኸሪያ ወዘናዋ...