183 ቢሊዮን ብር ለባንኮች ተሠራጭቷል
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ በቅርቡ ያካሄደው የገንዘብ ለውጥ ከተያዘለት የጊዜ ገደብ በአንድ ወር ዘግይቶ የተጠናቀቀ ቢሆንም፣ የብር ቅያሪው በሁሉም የአገሪቱ ክፍሎች በተሳካ ሁኔታ መከናወኑ ተገለጸ፡፡
በብር ቅያሪው ዙሪያ ያነጋገርናቸው የኢትዮጵያ የብሔራዊ ባንክ ከፍተኛ የሥራ ኃላፊ እንደጠቆሙት፣ የብር ለውጡን ለማካሄድ ከተሰጠው የሦስት ወራት ጊዜ በተጨማሪ አንድ ወር እንዲታከል የተደረገው በትግራይ ከነበረው የሕግ ማስከበር ሥራ ጋር ተያይዞ ነው፡፡
በዚህም ምክንያት በሌሎች ክልሎች የብር ቅያሪው ከተጠናቀቀ በኋላ በትግራይ ግን ተጨማሪ ጊዜ እንዲሰጥ በመደረጉ የብር የመቀየሪያው ጊዜ በአንድ ወር ሊዘገይ ቢችልም፣ አጠቃላይ የብር ቅያሪ ሒደቱ እጅግ የተሳካ መሆኑን እኚሁ ኃላፊ ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡
በኢትዮጵያ የብር ቅያሪ ሥራ ከፍተኛ ወጪ የወጣበትና ከፍተኛ ገንዘብ የተሠራጨት እንደሆነ የተነገረለት የዘንድሮ የብር ቅያሪ ሥራ ጥቃቅን ከሚባሉ ችግሮች ውጪ ይህ ነው የሚባል ችግር እንዳልነበረውም ጠቁሟል፡፡
የብር ቅያሪው የጊዜ ገደብ በአንድ ወር ዘግይቶ እንዲጠናቀቅ መደረጉ፣ የብር ቅያሪው ሥራ በይፋ ስለመጠናቀቁና ክንውኑን በተመለከተ መገለጽ የነበረበት ሪፖርት ማቅረቢያ ጊዜንም እንዳዘገየው ከኃላፊው ገለጻ ለመረዳት ተችሏል፡፡
ማክሰኞ ሚያዝያ 19 ቀን 2013 ዓ.ም. አጠቃላይ በብር ቅያሪ ለውጡ ዙሪያ ሪፖርት እንደሚቀርብም ከኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ የተገኘው መረጃ ያመለክታል፡፡
ሪፖርቱ ይፋ በሚደረግበት ፕሮግራም ላይም ለብር ለውጡ ስኬት ከፍተኛ አስተዋጽኦ ላበረከቱ አካላት ዕውቅና የሚሰጥበት ፕሮግራም ይካሄዳል ተብሎ ይጠበቃል፡፡
እንደ ባንኩ ሥራ ኃላፊ ገለጻ፣ 262 ቢሊዮን አዲስ ብር የታተመ ሲሆን፣ ከዚህ ውስጥ 183 ቢሊዮን ብር ለባንኮች የተላለፈ መሆኑን አመልክቷል፡፡ በአገሪቱ የብር ቅያሪ ታሪክ ከፍተኛ ነው የተባለው ይህ የገንዘብ መጠን ከስድስት ሺሕ በላይ በሚሆኑ የባንክ ቅርንፎች በኩል የተሠራጨ ነው፡፡
2.9 ቢሊዮን ብር ወጪ ተደረገበት አዲሱ የብር ኖት በተለያዩ አገሮች የታተመ ሲሆን፣ ከብር ለውጡ ጋር አዲስ የ200 የብር ኖት እንዲቀረፅ ያደረገ ነው፡፡
ከ1983 ዓ.ም. በኋላ የመጀመርው ብር ሲቀየር የተቀየረው የብር መጠን ስምንት ቢሊዮን ብር ብቻ እንደነበር ይነገራል፡፡ የብር ቅያሪው የተለያዩ ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታዎችን ያስገኘ ሲሆን፣ በተለይ ከብር ቅያሪ ጋር ተያይዘው በወጡ መመርያዎች መሠረት ከስድስት ሚሊዮን በላይ አዳዲስ ቆጣቢዎች ወደ ባንክ ሥርዓቱ እንዲገቡ ያስቻለ ነው፡፡ በእነዚህም አዳዲስ ቆጣቢዎች ከ89 ቢሊዮን ብር በላይ አዲስ ቁጠባ መሰባሰብ ስለመቻሉ መገለጹ ይታወሳል፡፡