Wednesday, February 28, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

የተመረጡ ፅሑፎች

ያለደንበኞች ኪስ ከማያገለግሉን ሠራተኞች መንግሥት ይታደገን

ሰሞኑን እኔ ከምኖርበት ኮንዶሚኒየም ግቢ ውስጥ ካሉ አምስት ብሎኮች  መካከል የሁለቱ ብሎኮች ተለይቶ የኤሌክትሪክ ኃይል ይቋርጧል፡፡ እነዚህ ብሎኮች ተለይተው አገልግሎት የተቋረጠበትን ምክንያት ባናውቅም፣ በሳምንቱ መጀመርያ ቀን የተቋረጠው የኤሌክትሪክ ኃይል እስከ አምስት ቀን ዘልቆ ሳይስተካከል ቆይቶም ነበር፡፡

የኤሌክትሪክ ኃይሉ እንደተቋረጠ ነዋሪዎች ለኤሌክትሪክ ኃይል ስልክ ደውለው አገልግሎት እንደተቋረጠባቸው አስታውቀው ነበርና ጥገና የሚያካሂዱ ሠራተኞች ይመጣሉ የሚል ምላሽ አግኝተው ነበር፡፡ ግን አልመጡም፡፡

አንዱን ቀን እንደምንም ታልፎ በሚቀጥለው ቀን ይሠራል የሚል ተስፋ ቢያዝም፣ በሁለተኛው ቀንም ሁለቱ ብሎኮች በጨለማ ተውጠው አደሩ፡፡ በሁለተኛው ቀን ምሽት ላይ ወደ ቤቴ ስገባ አብዛኛው የብሎኩ ነዋሪዎች ከሰልና ሻማ እየተጠቀሙ ነበር፡፡

ምሽቱን በረንዳቸው ላይ በከሰል የሚያበስሉ ጎረቤቶቼን ለምንድነው ያልተስተካከለው? ብዬ ጠየቅሁ፡፡ ከኤሌክትሪክ ኃይል መሥሪያ ቤት ሠራተኞች መጥተው እንደነበር፣ ሆኖም ጥገናውን ሳያካሂዱ ተመልሰው መሄዳቸውን ነገሩኝ፡፡ ለምን? ብዬ ስጠይቅ እነርሱም መልስ የሚሆን ነገር አልነበራቸውም፡፡ ከአንዷ ጎረቤቴ ግን፣ ‹‹ያው ምናምን ፈልገው ነው፤›› የሚል ቃል ወጥቶ ጆሮዬ ደረሰ፡፡ 

ነገሩ እየከነከነኝ ሻማዬን ይዤ ወደ ቤቱ ገባሁ፡፡ በመጀመርያዎቹ ሁለት ቀናት ቤት ውስጥ በስለው የተቀመጡ ምግቦች ተበላሽተዋል፡፡ ሌላ ምግብ ማብሰል አይቻልም፣ ቴሌቪዥን ከፍቶ መጠቀም፣ ስልክ ቻርጅ ማድረግ አይቻልም፡፡ ምሽት ላይ ልሠራቸው የነበሩ ሥራዎቼም በዚሁ ኃይል መቋረጥ ተስተጓጉለዋል፡፡ ለተማሪ ልጆቻቸው ምግብ መቋጠር የሚኖርባቸው የብሎኩ ነዋሪዎች ግን አንድ ሁለት ከሰል ማንደጃ አቀጣጥለው በየደጃፋቸው መሥራት ግድ ብሏቸዋልና ይኼው በየደጃፋቸው ይስተዋላል፡፡ ይህ ሁሉ የሆነው በቀላሉ ሊስተካከል የሚችል ሥራ ባለመስተካከሉ ነው፡፡

ቀጣዩም ምሽት በሻማ አለፈ፡፡ በከሰል ማብሰል ቀጠለ ማለት ነው፡፡ በእርግጥ የኤሌክትሪክ ኃይል ከዚህ ቀን በበለጠ የተቋረጠበት ጊዜ ቢኖርም፣ እኛን የገጠመን ግን በአነስተኛ ብልሽት ሳቢያ ጥገና ለማድረግ አለመቻሉና ለመጠገን በማንገራገራቸው ነው፡፡  

አንድ አገልግሎት ሰጪ ተቋም ከሕግና ከአሠራር ውጪ ደንበኞችን እንዲህ ባለው ሁኔታ ማጉላላቱ ተገቢ አለመሆኑ ግልጽ ቢሆንም፣ ፍራንካ ካልተሰጠ ጥገና አይካሄድም የመባሉ ነገር በእጅጉ የሚያስገርም ነው፡፡

በሦስተኛው ቀን ላይ የገጠመንን ሁኔታ ለቅርብ ወዳጆቼ ገለጽሁ፡፡ እንዲግህ ኤሌክትሪክ ተቋርጦብን የተቋረጠበትን ምክንያት የተመለከቱ የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ሠራተኞች ችግሩን ተናግረው ተመለሱ፡፡ እንደገናም መጥተው ሳያስተካክሉ ሄዱ አልኩ፡፡ ተመልሰው የሄዱበት ምክንያት ደግሞ የሻይ ፈልገው ሲሆን፣ ይህ ባለመሆኑ ተመለሱ የሚለውንም ገለጽኩ፡፡ ጥገና የሚደርገው እንዲህ ነው ወይ? ብዬ ስጠይቅ ያነጋገርኳቸው ሁሉ፣ ‹‹የተለመደ ነው›› በሚል አተያይ ይህ እኮ የተለመደ ከሆነ ቆየ አሉኝ፡፡

እነዚህ ሠራተኞች መንግሥት ደመወዝ የሚከፍላቸው አይመስልም፡፡ ጭራሽ እኛም ሰሞኑን እንዲህ ገጥሞን ገንዘብ ሰብስበን ሰጥተን ነው የቀጠሉልን የሚሉ ሦስት የተለያዩ አካባቢዎች የሚኖሩ ሰዎች ያጋጠማቸውን ሁኔታ አንድ በአንድ ነገሩኝ፡፡

እንዲህ ያለውን ብዥታ የፈጠረብኝ ሐሳብ ይዤ እንደተለመደው አመሻሽ ላይ ወደ ቤቴ ጉዞ ጀመርኩ፡፡ ዛሬም አይስተካከል ይሆን የሚል ጥያቄዬን እንደያዝኩ ከምኖርበት ኮንዶሚኒም ደጃፍ ስደርስ ከእኛ ሕንፃ ቤቶች የሚታየው ብርሃን የኤሌክትሪክ ሳይሆን ጭልጭል የሚል የሻማ ብርሃን ነበር፡፡ ይህ ለሦስተኛ ቀን መሆኑ ነው፡፡

መቼም መብራት የለም ተብሎ ውጭ አይታደርምና ወደ ቤቱ የሚወስደውን መወጣጫ ይዤ ጉዞ እንደጀመርኩ ሁለተኛው ወለል ላይ ስደርስ ከብሎኩ ነዋሪዎች የተወሰኑት ሰብሰብ ብለው አየሁ፡፡ ሁለቱ ወረቀት ይዘዋል፡፡ በእስክርቢቶ የሚጽፉትም ነገር አለ፡፡ ‹‹ሰላም ነው፤›› አልኩኝ፣ ‹ሰላም ነን› የሚል ምላሽ ሰጡኝ፡፡

አንድዋ ጎረቤቴ ‹‹ያው እንግዲህ ዛሬም አልሠሩልንም፡፡ ስለዚህ በግልጽ ተነግሮናል፡፡ ዛሬም መጥተው ጠዋት እንመጣለን ስላሉ ትንሽ ገንዘብ አዋጥተን ልንሰጣቸው ነው አሉ፡፡ ‹‹ጉቦ!›› አዎ የተለመደ ነው ተብሏል፡፡ ስለዚህ እንዲህ ከምንሰቃይ ሰላሳ ሰላሳ ብር እየሰበሰብን ነው ብለው አረዱኝ፡፡

መብትን በጉቦ ይሉሃል ይኼ ነው፡፡ እኔ አልፌያቸው ሄድኩ፡፡ እነዚያ እናቶች ግን በሦስት ቀን ውስጥ የገጠማቸውን ችግር በሚገባ ያውቃሉና ችግራቸው አስገድዷቸው ያደረጉት መሆኑ ገብቶኛል፡፡  እንዲህ ያለው ግልጽ ሙስና ያለንበትን ሁኔታ በግልጽ ያመለከተ ሲሆን፣ በጣም የገረሙኝ ደግሞ ገንዘቡን ለመክፈል  ያስተባበሩት ሴቶቹ መሆናቸው ነው፡፡

በአራተኛው ቀን ላይ አረፋፍጄ ነበር የወጣሁትና ግቢ ደጃፍ ላይ የኤሌክትሪክ ኃይልን ተሽከርካሪና ሠራኞችን አየሁ፡፡ ሊሠሩ መሆኑ ገባኝ፡፡ እነዚያን ጎረቤቶች ወርጄ አገኘኋቸው፡፡ እንዴት ሆናችሁ ስል የሰበሰብነውን ሰጠን እየሠሩት ነው አሉኝ፡፡ የሚገርመው ጥገናው ከ20 ደቂቃ በላይ አልፈጀም፡፡

እዚህ ላይ መታሰብ ያለበት ይህ ገጠመኝ የብዙዎች መሆኑን ነው፡፡ ሥራዬ ብዬ ብዙ ሰው ጠይቄ የተረዳሁትም ይህንኑ ነው፡፡ በእጅ ካልተባለ ምንም የማይሠራ መሆኑን ነው፡፡ ለምን ጉቦ ይሰጣል ብዬ በጠየቅሁ ቁጥር፣ ኧረ እንዲህ ከተባሉ ጭራሽ ላይመጡልን ይችላሉ፣ እንዲታወቅባቸው አይፈልጉም የሚለው ሥጋትም ነገሩ ምን ያህል ሥር የሰደደ መሆኑን አሳየኝ፡፡ እንግዲህ ሕግ ባለበት አገር ዜጎች የገዛ መብታቸውን እንዲህ ሲነጠቁ ማየት ያሳዝናል፡፡ እንዲህ ያለ ሙስና ሕጋዊ እስከመሆንም ደርሷል፡፡

አገልግሎት ሰጪ ተቋማት እንዲህ በግልጽ ሙስና ሲሠሩ ማየት ያማል፡፡ ከሁሉም በላይ ነገሩ እንደ ሕጋዊ ሥራ እየተቆጠረ ሁሉም የተለመደ ነው ብሎ መብራት ሲቋረጥበት እንዲህ ማድረጉ ነው፡፡ እንደ አገር የብልሽታችን መጠን ቅጥ አጥቷል፡፡ ምግባር ጠፍቷል፣ ኃላፊነትን በአግባቡ መወጣት ብርቅ እየሆነብን ነው፣ የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ባለሥልጣናት እንዲህ ያለውን ፀያፍ ተግባር አናውቅም ሊሉ አይችሉም፡፡ ግን ጥቂት የማይባሉ ሠራተኞቻቸው በየዕለቱ ደንበኞች ኪስ ውስጥ ያላግባብ እየገቡ ነው፡፡

መንግሥትና ሕዝብ ከሚከፍላቸው ደመወዝ በተጨማሪ ሌላ ሕገወጥ የገቢ ምንጭ እያፈሩ ስለመሆኑ የአደባባይ ሚስጥር ነው፡፡ ብልሽት ማስመዝገብ ለሠራተኞቹ ሠርግና ምላሽ ነው፡፡ እንዲህ መቀጠል ስለሌለበት ተቋሙ አሠራሩን ይፈትሽ፡፡ በብልሽት ስም ከብልሹ አሠራር ውስጥ የተዘፈቁትን ሠራተኞች ከንፁኃኑ ይለይ! መብት ጉቦ አያሻውም!

Latest Posts

- Advertisement -

ወቅታዊ ፅሑፎች

ትኩስ ዜናዎች ለማግኘት