ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች በሚነሱ ግጭቶች ምክንያት፣ ‹‹የበርካታ ዜጎች ሕይወት አለፈ፣ ዜጎች ለዓመታት ያፈሩት ሀብት ንብረት ወድመት ደረሰበት፣ እንዲሁም በርካታ ዜጎች ለዓመታት ከኖሩበት ቀዬ ተፈናቀሉ…›› የሚሉ ዜናዎችን መስማት እየተለመደ መጥቷል፡፡
ምንም እንኳን የዜጎች ሞት፣ የአካል ጉዳት፣ ለዘመናት ያፈሩት ሀብት ውድመትና መፈናቀል የአየር ሁኔታ ትንበያ ዘገባን ያህል የዕለት ተዕለት የዜና ፍጆታ የሆነ ቢሆንም፣ የሚመለከተው አካል በተለይም መንግሥት እነዚህን ሰቆቃዎች ሊቆጣጠርና ሊያስቆም ባለመቻሉ ዕልቂትና ሰቆቃው አሁንም ቀጥሏል፡፡
በተለይም የፖለቲካ ፓርቲ አመራሮችና ሌሎች ባለድርሻ አካላት መንግሥት የዜጎችን ሰላምና ደኅንነቱን የማረጋገጥ ሚናውን በአቸኳይና በአግባቡ እንዲወጣ የሚጠይቁ በርካታ መግጫዎችን በተለያየ ጊዜ ያወጡ ቢሆንም፣ ማቆሚያ አልባው የዜጎች ሰቆቃና ዕልቂት ግን አሁንም አላባራም፡፡
ግለሰቦች፣ የፖለቲካ ፓርቲ አመራሮች፣ የሰብዓዊ መብቶች ተሟጋች ቡድኖችና ሌሎች ባለድርሻ አካላት ለሚያቀርቡት ተደጋጋሚ ጥሪና ማስጠንቀቂያ የመንግሥት ምላሽ፣ ‹‹አገርን ለማፍረስ የሚጥሩ አካላት ያደረሱት ጥቃት ነው፣ አጥፊዎቹን በቁጥጥር ሥር ለማዋል መንግሥት በከፍተኛ ጥረት ላይ ይገኛል፣ …፤›› የሚሉና ተመሳሳይነት ያላቸው ናቸው፡፡
በዚህ መሀል ግን የዜጎች ሞት፣ መፈናቀልና ጉስቁልና መቆሚያ ያጣ ሲሆን፣ ‹‹የመፍትሔ ያለህ›› ጥያቄም እንዲሁ እየጎረፈ ነው፡፡ በዚህ መሀል በተለይ ባለፈው ሳምንት ማገባደጃ ላይ በአጣዬ ከተማ የደረሰው ጥቃት ብዙዎችን ያሳዘነ፣ እንዲሁም ያስቆጣ ክስተት ሆኗል፡፡
በተለይ ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ እየተበራከተ ከመጣው ዘርንና ሃይማኖትን መሠረት አድርገው ከሚካሄዱ ጥቃቶች አንፃር በርካቶች የደኅንነት ሥጋት ውስጥ መውደቃቸውን ከመግለጽ ባለፈ የጥቃት አድራሾቹ በደፈናው መገለጽ፣ ተይዘው ሕግ ፊት አለመቅረባቸው፣ የመንግሥት የፀጥታ መዋቅር እንዲህ ያሉ ጥቃቶች በተደጋጋሚ ሲፈጸሙ ቀድመው መከላከል አለመቻላቸው፣ እንዲሁም ከደረሱ በኋላ የከፋ ጉዳት ሳያደርሱ መቆጣጠር ካለመቻላቸው የተነሳ ሥጋታችውን ወደ ጭንቀት ከፍ እንዳደረገባቸው ይገልጻሉ፡፡
ለዚህም በኢትዮጵያ የተለያዩ ክፍሎች በተለይም በቤኒሻንጉል ጉምዝ ክልል መተከል፣ በኦሮሚያ ክልል ወለጋ፣ እንዲሁም በደቡብ ክልል ጉራፈርዳ በአማራ ተወላጆች ላይ የደረሱ ብሔርን መሠረት ያደረጉ ጥቃቶች ተወግዘው ሳያልቁና ጉዳት የደረሰባቸው ቤተሰቦች ተፅናንተው ሳይጨርሱ ከሰሞኑ አጣዬ፣ ኤፍራታ፣ ማጀቴና የመሳሰሉ አካባቢዎች የደረሰውን ጥቃትና ዕልቂት ለማነፃፀሪያነት ያነሳሉ፡፡
ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ እየተከሰቱ ያሉ የሰላምና የፀጥታ ችግሮች ተመሳሳይነት፣ እንዲሁም እያደረሱ ካሉት ተመሳሳይ ጉዳቶች የተነሳ መንግሥት መዋቅሩን እንዲፈትሽ የሚጠይቁና የሚመክሩ ድምፆች ተበራክተዋል፡፡ ከዚህ ባለፈም በመንግሥት መዋቅር ውስጥ ከሚገኙ የተለያዩ ኃላፊዎች ከሚሰጡት መግለጫና አንዱ አንዱን ከመኮነን አባዜ ወጥተው፣ ዜጎች ላይ አደጋ የሚያደርሱ አካላትን ለፍትሕ በማቅረብ የዜጎችን ዕንባ እንዲያብሱና ሰላምና ፀጥታ እንዲያሰፍኑ የሚጠይቁ በርካቶች ናቸው፡፡
ከሰሞኑ በአጣዬ ከተማ ከደረሰው ጥቃት አስቀድሞ ከወር በፊት ተመሳሳይ ጥቃት መፈጸሙ የሚታወስ ሲሆን፣ በአካባቢው የአገር መከላከያ ሠራዊት ባለበትና እንዲህ በአጭር ጊዜ ተመሳሳይ ጥቃት፣ ነገር ግን በመጠን የከፋና የሰፋ ጉዳት መድረሱ ለበርካቶች ጥያቄ ከማጫር አልፎ በርካታ የአማራ ክልል ከተማ ነዋሪዎች ለተቃውሞ ሠልፍ አደባባይ እንዲወጡ አስገድዷል፡፡
ከሰኞ ሚያዝያ 11 ቀን 2013 ዓ.ም ጀምሮ በአማራ ክልል ሰሜን ሸዋና በኦሮሚያ ልዩ ዞኖች በሚገኙ ከተሞች በንፁኃን ላይ የተፈጸመውን ጥቃት፣ ማፈናቀልና የንብረት ውድመትን የሚያወግዙና ‹‹ሞት ይብቃ›› በሚል የክልሉን ርዕሰ ከተማ ባህር ዳርን ጨምሮ በተለያዩ የክልሉ ከተሞች በተካሄዱ የተቃውሞ ሰላማዊ ሠልፎች ነዋሪው ብሦቱን አደባባይ ወጥቶ ገልጿል፡፡
ባህር ዳርን ጨምሮ በደሴ፣ በደብረ ማርቆስ፣ በወልዲያ፣ በሐይቅ፣ በላሊበላ፣ እንዲሁም ሌሎች የክልሉ ከተሞች ለተካሄዱት የተቃውሞ ሠልፎች መጠራት ምክንያት የሰሞኑ የአጣዬና አካባቢው ጥቃት ቢሆንም፣ ሠልፎቹ ላይ የተስተዋሉት መፈክሮች ግን ከዚህ ቀደም በመተከል፣ በወለጋ፣ እንዲሁም በጉራፈርዳ የደረሱና አማራን ዒላማ ያደረጉ ጥቃቶችን የሚያወግዙ፣ ‹‹በአማራ ተወላጆች ላይ እየተፈጸመ ያለውን ማንነትን መሠረት ያደረገ ግድያና መፈናቀል ይቁም›› የሚሉ ናቸው፡፡
የአጣዬው ጥቃት በክልሉ የተለያዩ ከተሞች ለተካሄደው ትዕይንተ ሕዝብ ገፊ ምክንያት ቢሆንም፣ በወቅቱ ከተስተዋሉ መፈክሮች ማስተዋል የሚቻለው ሕዝቡ በወቅታዊው የአገሪቱ ፖለቲካ አመራር ላይ በርካታ ጥያቄ እንዳለውና አጋጣሚውን ተጠቅሞ ይህን ተቃውሞውን ለማሰማት እንደተጠቀመበት ለማስተዋል ይቻላል፡፡
በሰላማዊ ሠልፎቹ ወቅት፣ ‹‹የአማራ ክልል አመራሮች አማራን አይወክሉም፣ በአማራዎች ላይ የሚፈጸም ግድያ ይቁም፣ አትንኩን፣ ስትነኩን እንበዛለን፣ ተላላኪዎች ልብ ግዙ፣ ሕፃናትን መግደልና ከተማን ማፍረስ ጀግንነት አይደለም፣ በአማራ ላይ እየተፈጸመ ያለው ግድያና መፈናቀል መንግሥትን ሊያሳስበው ይገባል፣ እንዲሁም ለአማራ መሰደድ መነሻ የሆነው ሕገ መንግሥት በአስቸኳይ ይሻሻል…›› የሚሉ በአጣዬና በሌሎች ሥፍራዎች ላይ የደረሰውን በደል ከማውገዝ ባለፈ፣ ሌሎች በዓውዳቸው ሰፋ ያሉ ጥያቄዎችም ተስተጋብተዋል፡፡
የክልሉ በርካታ ከተሞች በሰላማዊ ሠልፍ ከመጥለቅለቃቸው አስቀድሞ የአገር መከላከያ ሠራዊት በአካባቢው የኮማንድ ፖስት ወደ ሥራ በማስገባት፣ ከደብረ ሲና እስከ ኮምቦልቻ ከተማ ድረስ ባሉ አካባቢዎች ከዋናው መንገድ ወደ ውስጥ እስከ 20 ኪሎ ሜትር ድረስ መሣሪያ ይዞ መንቀሳቀስ እንደማይቻል ማስታወቁ የሚታወስ ነው፡፡
ጥቃቱን የሚያደርሰው ማን ነው?
በኢትዮጵያ የተለያዩ አካባቢዎች የሚፈጸሙ ጥቃቶች ብዛትና ስፋት ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ ከመሄዱ ባሻገር፣ ጥቃቱን የሚፈጽመው አካል በውል አለመታወቅ ለበርካቶች የሥጋት ምንጭ ሆኗል፡፡
ሚያዝያ 8 ቀን 2013 ዓ.ም. በአማራ ክልል ሰሜን ሸዋ፣ በደቡብ ወሎና በኦሮሞ ልዩ ዞን በሚገኙ በተለይም በአጣዬ፣ አንፆኪያ፣ ኤፍራታ ግድም፣ ሸዋ ሮቢት፣ ካራቆሬ፣ ጨፋ ሮቢት፣ ማጀቴና ሌሎች ከተሞች በሚገኙ ቀበሌዎች በሦስት ዓመታት ውስጥ ለአምስተኛ ጊዜ የተከሰተው ጥቃት አሁንም ጥቃት አድራሾቹ ‹‹ማንነታቸው በግልጽ ያልታወቁ የታጠቁ ኃይሎች›› ከሚል ጥቅል ስም ውጪ፣ በቡድንም ሆነ በግለሰብ ከእነዚህ ጥቃቶች ጋር ተያይዞ ለፍርድ ሲቀርቡም ሆነ አስተማሪ የሆነ ቅጣት ሲጣል አይስተዋልም፡፡
ምንም እንኳን ‹‹ማንነታቸው ያልታወቁ የታጠቁ ኃይሎች›› የሚለው የወል ስም ለብዙዎች መንግሥትን የሚቃወሙ አካላት የሚሰጥ ስያሜ ቢሆንም፣ ከሰሞኑ በአጣዬ ለደረሰው ጥቃት ግን የፌዴራሉም ሆነ የክልል መንግሥት ኦነግ ሸኔን ተጠያቂ አድርገዋል፡፡
ሆኖም ከሮይተርስ ዜና ተቋም ጋር የኢሜይል ልውውጥ ያደረጉት ራሱን ከኦሮሞ ነፃነት ግንባር (ኦነግ) የነጠለው የኦሮሞ ነፃነት ሠራዊት ቃል አቀባይ ኦዳ ታረቢ ሠራዊታቸው በሥፍራው እንዳልነበረ በመግለጽ፣ እንዲያውም ‹ኤኬ 47 ጠመንጃ በታጠቁ የኦሮሞ አርሶ አደሮች ላይ የአማራ ልዩ ኃይል ዕርምጃ ወስዷል፤›› በማለት የሚሰነዘርባቸውን ወቀሳና ክስ አጣጥለውታል፡፡
ምንም እንኳን የጥፋት አድራሾቹ ‹‹ማንነታቸው ያልታወቁ የታጠቁ ኃይሎች›› የሚለው አጠራር በአገሪቱ የተለያዩ ክፍሎች ለሚደርሱ ጥቃቶች በመንግሥት በኩል ጥቅም ላይ የሚውል ቢሆንም፣ ከሰሞኑ ጥቃት ጋር ደግሞ የኦነግ ሸኔ ጥቃት እንደሆነ ቢገለጽም፣ በርካቶች እንዲህ ተደራጅቶ ታጥቆ የመጣ ኃይል ጥቃት ፈፅሞ የሚሄደው የት ነው? ጥቃት አድራሾቹ የታጠቁትን የጦር መሣሪያ ከግምት በማስገባት፣ እንዲህ እስከ አፍንጫቸው ዘመናዊ መሣሪያ እስኪታጠቁ ድረስ የመንግሥት የፀጥታ መዋቅር ምን ይሠራ ነበር? እንዲሁም የአገሪቱን ህልውና የሚፈታተኑ መሰል ጥቃቶች በቁጥጥር ሥር ውለው የቀደመው ሰላምና ፀጥታ ወደ ነበረበት የሚመለሰው መቼ ነው? የሚሉ በበርካቶች ዘንድ የሚሰነዘሩና አፋጣኝ ምላሽ የሚሹ አንገብጋቢ ጥቄያዎች ሆነዋል፡፡
እንዲህ ዓይነት ማንነትን መሠረት ያደረጉ ጥቃቶችን ለመለየት ጥናት ያደረጉ በርካታ ምሁራን ባሳተሟቸው ድርሳናት እንደሚያትቱት፣ በአገሪቱ በተደጋጋሚ የሚስተዋሉት ማንነትን መሠረት ያደረጉ ጥቃቶች መንስዔያቸው በዘር ላይ የተመሠረተው፣ ብሔርን መሠረት ያደረገው ፌዴራሊዝም መሆኑን የሚጠቅሱ ሲሆን፣ ለዚህም ሁነኛ መፍትሔው ይህንን መፈተሽና አማራጭ የፌዴራሊዝም አተገባበር ወደ ሥራ ማስገባት እንደሆነ ይገልጻሉ፡፡
ከዚህ ሐሳብ ጋር የሚስማማ መግለጫ ያወጣው የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን ጥቃቱን የሚያወግዝና የሚኮንን መሆኑን ከመጥቀስ ባለፈ፣ መንግሥትም የዜጎችን ሰላምና ፀጥታ የመጠበቅ ኃላፊነቱን እንዲወጣ ጥሪ አቅርቧል፡፡
በአማራና በኦሮሚያ ክልሎች በተለይም በሰሜን ሸዋና በኦሮሚያ ልዩ ዞን በሲቪል ሰዎች ላይ ያነጣጠሩና ብሔርን መሠረት ያደረጉ ጥቃቶችና የአፀፋ ጥቃቶች የብዙ ሰዎች ሕይወት ያጠፉ ሲሆን፣ ‹‹አጥብቆ የሚወገዝ ነው፤›› በማለት ጥቃቱን ማውገዙን ኮሚሽኑ አስታውቋል፡፡
ከዚህ በተጨማሪም፣ ‹‹እነዚህ አሳዛኝ ክስተቶች ጥልቅ መሠረት ካላቸው ማኅበራዊ፣ ፖለቲካዊና ተቋማዊ ምክንያቶች የሚመነጩ ሲሆን፣ ያለ ተጠያቂነት እየተፈጸሙ ያሉ ዘግናኝ ጥቃቶችን በዘላቂነት ለማስቆም የሚያስችሉ ዕርምጃዎች መውሰድ ግድ ይላሉ፡፡ መንግሥትም የሰዎችን ደኅንነት የመጠበቅ ግዴታውን ሊወጣ ይገባል፤›› በማለት አሳስቧል፡፡
ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ የሚስተዋሉት ማንነትን መሠረት ያደረጉ ጥቃቶች ቁጥራቸውና ተደጋጋሚነታቸው ቢበረክትም፣ ብሔርን መሠረት ያደረገው ፌዴራሊዝም በኢትዮጵያ መተግበር ከጀመረ ወዲህ በማንነት ምክንያት የሚደርሱ ጥቃቶችን ማስተዋል የተለመደ መሆኑን የሚገልጹት በርካታ ድርሳናት የሚገኙ ሲሆን፣ በአብዛኛው መሰል ጥቃቶች ለችግሩ መበራከትና መስፋት የመንግሥት አፋጣኝ ምላሽ አለመስጠት እንደሆነ ያትታሉ፡፡
ከዚህ ጋር ተመሳሳይ በሆነ መንገድ በርካቶች ከአጣዬው ጥቃት በኋላ መንግሥት ሐዘኑን አለመግለጹን፣ እንዲሁም ጥቃቱን አለማውገዙን በማውሳት በመንግሥት ላይ ተቃውሞ አሰምተዋል፡፡
ሆኖም ሐሙስ ሚያዝያ 14 ቀን 2013 ዓ.ም. መጪው ምርጫን በተመለከተ፣ ከክልል ርዕሰ መስተዳድሮችና ከምርጫ ቦርድ አመራሮች ጋር የተወያዩት ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር)፣ ‹‹በኢትዮጵያ ከሰላማዊ ሥልት ውጪ ሌሎች አማራጮች የማያዋጡና ሊተገበሩ የማይችሉ ናቸው፤›› በማለት ለሰላማዊ ትግል ቅድሚያ እንዲሰጥ መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡
በተመሳሳይ ዕለት ለተወሰኑ የመገናኛ ብዙኃን መግለጫ የሰጡት የአማራ ክልል ፕሬዚዳንት አቶ አገኘሁ ተሻገር፣ በቅርቡ በአጣዬ ከተፈጠረው ችግር ጋር የክልሉን መንግሥት አደረጃጀት እየመረመሩ እንደሆነ ገልጸዋል፡፡ ‹‹በጥፋቱ አመራሮች መሳተፋቸው ጥቆማ ስለመጣ የማጣራት ሥራው እየተከናወነ ነው፤›› ብለዋል፡፡
ከዚህ ባለፈ ግን፣ ‹‹ጥቃት ሲፈጸም የፀጥታ መዋቅሩ አስቀድሞ ሊያውቅና ሊከላከል ያልቻለበትን ምክንያት እየመረመርን ነው፤›› የሚለው የክልሉ ፕሬዚዳንት ማብራሪያ፣ በርካቶች ለወራት ሲያነሱት የነበረ ጥያቄ ከመሆኑ አንፃር የምርመራውን ውጤት በጉጉት እንዲጠበቅ አድርጎታል፡፡
በተደጋጋሚ በአገሪቱ የተለያዩ ሥፍራዎች የሚከሰቱ ማንነትን መሠረት ባደረጉ ጥቃቶች ምክንያት፣ በርካቶች ስለአገሪቱ ህልውና አብዝተው እንዲጨነቁና እንዲያስቡ አስገድዷቸዋል፡፡ በዚህ ሳቢያ በርካቶች መንግሥት የፀጥታ መዋቅሩን እንዲፈትሽና እንዲያጠናክር አበክረው ያሳስባሉ፡፡ ከዚህ ባለፈም ሁሉም ያገባናል የሚሉ ባለድርሻ አካላትን ያሳተፈ ውይይት እንዲያዘጋጅም ይወተውታሉ፡፡