በአገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች ማንነትን መሠረት በማድረግ እየተፈጸሙ ያሉ ጥቃቶችን፣ መንግሥት በማውገዝ ሊከላከል እንደሚገባ ተገለጸ፡፡
ይህ የተገለጸው ‹‹ስለኢትዮጵያ ዝም አንልም፣ ትውልድን ከግብረ ሰዶም እናድን ማኅበር›› በአገሪቱ እየታየ ያለውን የሰላም ማጣት ችግርና ስድስተኛው አገራዊ ምርጫን በተመለከተ፣ ‹‹ሰላም ለኢትዮጵያ›› በሚል ርዕስ ማክሰኞ ሚያዝያ 19 ቀን 2013 ዓ.ም. በኢትዮጵያ ሆቴል መግለጫ በሰጠበት ወቅት ነው፡፡
የማኅበሩ ፕሬዚዳንት አቶ ደረጀ ነጋሽ በመግለጫው ወቅት እንደገለጹት፣ መንግሥት ስለሰላም አጥብቆ መሥራት አለበት፡፡ ሰዎች እየሞቱ መንግሥት ጉዳዩን እያዳፈነ በሄደ ቁጥር አደጋ ይመጣል ያሉት አቶ ደረጀ፣ የዜጎችን ሞት፣ ስደትና የንብረት ውድመቶችን እየተመለከቱ ምንም እንዳልተፈጠረ መቁጠር የበለጠ ችግሩን ማስፋፋት ነው ብለዋል፡፡
‹‹በተለያየ የአገሪቱ ቦታዎች ሰዎች ይገደላሉ፣ ደም ይፈሳል፣ ንብረት ይወድማል፣ እንዲሁም ወገን ወገኑን ማሳደዱና ማፈናቀሉ፣ በወገኑ ንብረት ውድመት መደሰቱ ኢሰብዓዊ ድርጊት ነው፤›› ያለው ማኅበሩ፣ ይህ የሰላም ዕጦት ስላሳሰበው ‹‹ሰላም ለኢትዮጵያ›› የሚለውን መግለጫ ለመስጠት መገደዱን አስታውቋል፡፡
‹‹መንግሥት በሰላም ጉዳይ ላይ በከፍተኛ ደረጃ እንዲሠራ ጥያቄ እናቀርባለን፤›› ያለው ማኅበሩ፣ ተፎካካሪ ፓርቲዎችም ሆኑ የግል ተወዳዳሪዎች ከምርጫው በፊት ሰላም መቅደም ስላለበት ስለኢትዮጵያ ሰላም አብዝተው እንዲሠሩ ጠይቋል፡፡
በአገሪቱ የሚስተዋለው ትርምስ እየተባባሰ እንዳይሄድ ስለሰላምና ስለኢትዮጵያ የሚገልጽና 19 ባለድርሻ አካላትን የሚያካትት ባለ 25 ገጽ ምክረ ሐሳብ (ቢጋር) ለሰላም ሚኒስቴር ካስገቡ ስምንት ወራት እንደተቆጠሩ አቶ ደረጀ ገልጸዋል፡፡ ሆኖም የሰላም ሚኒስቴር በምክረ ሐሳቡ ላይ ምክክር እንዲደረግ እስካሁን ጥሪ እንዳላቀረበ ገልጸዋል፡፡
ይህ በብዙ ባለሙያዎች ተሳትፎ የቀረበ ምክረ ሐሳብ ለአገሪቱ ትልቅ ሚና ስለሚጫወት፣ በግንቦት 2013 ዓ.ም. የሃይማኖት ተቋማት፣ መገናኛ ብዙኃን፣ የባህልና ቱሪዝም፣ የውጭ ጉዳይና የሰላም ሚኒስቴሮች በጠቅላላው 19 ባለድርሻ አካላት ባሉበት በሰነዱ ላይ ውይይት ለማድረግ መታቀዱን አስታውቀዋል፡፡
የማኅበሩ የሕግ ክፍል ባለሙያ አቶ መልካሙ ኡጎ በበኩላቸው፣ እንደ አገር በቀል ግብረ ሰናይ ድርጅት በዜጎች ላይ እየደረሱ ያሉ ጥቃቶችን መንግሥት እንዲከላከል ጥሪ ከማቅረብ በዘለለ፣ በሕግ የተሰጠ ድርሻ እንደሌላቸው አስታውቀዋል፡፡ ‹‹ሆኖም አሁንም በማኅበር ደረጃ መንግሥት በአገሪቱ በዜጎች ላይ እየደረሱ ያሉ ሞትና መፈናቀሎችን ተከትሎ እየወሰደ ያለው ዕርምጃ ክፍተት እንዳለበት ተረድተናል፤›› ብለዋል፡፡
‹‹ምንጊዜም ቢሆን በአንድ አገር የሰዎችን ነፃነት በምንም መንገድ ማስከበር ያለበት መንግሥት ነው፤›› ያሉት ባለሙያው፣ ከሚታዩት ጉዳቶች አንፃር ተገቢውን ኃላፊነት የመወጣት ተግባሩ ከመቼውም በላይ መቀጠል ይገባል ብለዋል፡፡