በመላው አውሮፓ ከሚኖሩ ትውልደ ኢትዮጵያውያን የተውጣጡ ምሁራን የኢትዮጵያን ጥቅም ለማስጠበቅና ለማስከበር የሚሠራ አግባቢ (lobbist) ቡድን ማቋቋማቸውን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡
የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ዲና ሙፍቲ (አምባሳደር) በሳምንታዊ ጋዜጣዊ መግለጫቸው ‹‹ዲፌንድ ኢትዮጵያ›› በሚል ስያሜ የተቋቋመው ቡድን፣ የኢትዮጵያን ብሔራዊ ጥቅምና መብት ለማስጠበቅና አገሪቱ ያለችበትን ሁኔታ ለመላው ዓለም በትክክለኛው መንገድ ለማሳወቅ የሚሠራ ነው ብለዋል፡፡
ቡድኑ በኢትዮጵያ ላይ በአንዳንድ ወገኖች የሚሰነዘረውን አሉባልታና ያልተገባ ጥቃት፣ ተገቢ በሆነ መንገድ ለመመከት የተቋቋመ እንደሆነም ቃል አቀባዩ ተናግረዋል፡፡
ከቅርብ ጊዜ ወዲህ መንግሥት በትግራይ ክልል እያደረገ ባለው የሕግ ማስከበር ዘመቻ፣ እንዲሁም ከህዳሴ ግድብ ግንባታ ጋር በተያያዘ ደግሞ በግብፅ አማካይነት የአሜሪካና የአውሮፓ ኅብረት መንግሥታት ጫና ለመፍጠር እንቅስቃሴ ሲያደርጉ እንደነበር መገለጹ ይታወሳል፡፡
በመጋቢት ወር አጋማሽ ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ወቅታዊ ጉዳዮችን አስመልክተው ከአባላት ለቀረቡላቸው ጥያቄዎች በሰጡት ምላሽ የሕዝባዊ ወያነ ሓርነት ትግራይ (ሕወሓት) ከስድስት ወራት በፊት አግባቢ (lobbist) ቀጥሯል ብለው ነበር፡፡
በተለያዩ ዓለም አቀፍ ተቋማት በተለይም በአምነስቲ ኢንተርናሽናል፣ በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ወይም በሌሎች ኤጀንሲዎች የተሰገሰጉ ለ30 ዓመታት ያህል በሕወሓት ሲደገፉ የነበሩ የካድሬ ቤተሰቦች ናቸው ማለታቸው አይዘነጋም፡፡
የሕወሓት አግባቢ ቡድን ለበርካታ ዓመታት በፈጠረው የቤተሰብና የዝምድና ትስስር በሚያደርገው ዓለም አቀፍ ጫና፣ አገሮች በኢትዮጵያ ላይ እንዲዘምቱ እያደረገ እንደሆነም ገልጸው ነበር፡፡
የሕወሓት አካል የተዘረፈ ሀብት ስላለውና ኢትዮጵያ ግን ምንም ሀብት እንደሌላትና እንደተዘረፈች፣ የተዘረፈውንም ለማስመለስ ገና ጥረት እያደረገች ያለች መሆኗን በመግለጽ፣ ነገር ግን አግባቢ የሚባለውን አካል መቅጠር እንደማትችል ተናግረዋል፡፡
ሕወሓት የቀጠራቸው የሚዲያና የፓርላማ አባላት እንደሚጮሁለት በመጥቀስ፣ መተከል ላይ ለሚሞቱት ግን አግባቢ መቅጠር አይደለም እንዴት እንደሚቀጠርም መረጃ የለም ብለው ነበር፡፡
ነገር ግን ሕወሓት አግባቢ ቡድን እንደሚቀጥረው ሁሉ፣ የኢትዮጵያ መንግሥት መቅጠር እንደማይችልና ዳያስፖራው ግን ገንዘብ ካለው ይህን አግባቢ ቢቀጥር መልካም እንደሆነ በመናገር በውሸት ላይ የተመሠረተውን ውንጀላ መከላከል እንደሚቻል ተናግረው ነበር፡፡