ክልሎችም የሦስት ሚሊዮን ብር ድጋፍ አገኙ
የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን በሚቀጥለው ዓመት በካሜሩን አስተናጋጅነት በሚካሄደው የአፍሪካ ዋንጫ ላይ ለሚሳተፈው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን (ዋሊያዎቹ) ስድስት ሚሊዮን ብር አበረከተ፡፡ በተጨማሪም ብሔራዊ ፌዴሬሽኑ ከ17 ዓመት በታች ውድድር ለሚያደርጉ ክልሎች የሦስት ሚሊዮን ብር ድጋፍ ማድረጉ ታውቋል፡፡
ብሔራዊ ፌዴሬሽኑ እንዳስታወቀው፣ በአሠልጣኝ ውበቱ አባተና ረዳቶቻቸው አሠልጣኝነት ከስምንት ዓመት በኋላ ለአፍሪካ ዋንጫ ተሳትፎ ለበቃው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን የገንዘብ ሽልማት ሥነ ሥርዓት የሚከናወነው ቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ፍጻሜውን በሚያገኝበት በሐዋሳ ከተማ ይሆናል፡፡
በድሬዳዋ አስተናጋጅነት ሲካሄድ የሰነበተው ቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ረቡዕ ሚያዝያ 19 ቀን 2013 ዓ.ም. ወላይታ ድቻ ከቅዱስ ጊዮርጊስ፣ በወራጅ ቀጣና ውስጥ የሚገኘው ጅማ አባ ጅፋር ከኢትዮጵያ ቡና በሚያደርጉት ጨዋታ የድሬዳዋ ቆይታው የሚጠናቀቅ ይሆናል፡፡
የፕሪሚየር ሊጉ የመጨረሻዎቹ የአምስት ሳምንት የጨዋታ መርሐ ግብር የምታስተናግደው የሐዋሳ ከተማ ስትሆን 30 ጨዋታዎችን የምታስተናግድ ይሆናል፡፡ የሊጉ መሪ ፋሲል ከነማ በሒሳብ ሥሌት የዋንጫው ባለቤት ሆኗል ባይባልም አሸናፊ መሆኑ እየተረጋገጠ ነው፡፡
በሌላ በኩል ዕድሜያቸው ከ17 ዓመት በታች በሁሉም ክልሎች እየተከናወነ ለሚገኘው የውድድር መርሐ ግብር፣ የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ለሁሉም ክልሎች የሦስት ሚሊዮን ብር ድጋፍ አድርጓል፡፡ እንደ ፌዴሬሽኑ መግለጫ ከሆነ እያንዳንዱ ክልል የ300 ሺሕ ብር የገንዘብ ድጋፍ ይደረግለታል፡፡