የፓርኪንሰን ሕመም ከቅርብ ዓመታት ወዲህ በኢትዮጵያ መታየት መጀመሩ ይወሳል፡፡ የሕመሙ ምልክቶች መንቀጥቀጥ፣ የጡንቻ መገታተር፣ የእንቅስቃሴ ፍጥነት፣ መፍዘዝና ሚዛንን አለመጠበቅና ሌሎቹም እንደሆኑ ሐኪሞች ይገልጻሉ፡፡
የፓርኪንሰን ታማሚዎች በአገር ውስጥ ሕክምናና መድኃኒት ከማግኘት አንስቶ በኅብረተሰቡ ዘንድ ያለው የግንዛቤ ማጣት ከበሽታው ባልተናነሰ እየጎዳቸው እንደሆነ መናገር ከጀመሩ ዓመታት ተቆጥረዋል፡፡ የተወሰኑ መሻሻሎች ቢኖሩም፣ ማኅበር ተቋቁሞ ችግሮቹ እንዲታውቁ እየተሠራ ቢሆንም ችግሩ ዛሬም አልተቀረፉም፡፡ በመሆኑም የፓርኪንሰን በሽታን ለመግታትና በዘርፉ ላይ ያሉትን ችግር ለመፍታት መንግሥትም ሆነ ሌሎች ባለድርሻ አካላት ኃላፊነታቸውን እንዲወጡ ጥሪ ቀርቧል፡፡
የፓርኪንሰንን ቀን ‹‹ትኩረት ለፓርኪንሰን ሕሙማን›› በሚል መሪ ቃል በኢትዮጵያ ለአሥረኛ ጊዜ ሲከበር የተገኙት፣ የፓርኪንሰን ፔሸንትስ ሰፖርት ኦርጋናይዜሽን ኢትዮጵያ መሥራች ወ/ሮ ክብራ ከበደ እንደገለጹት፣ በኮሮና ወረርሽኝ ምክንያት የአቅም ግንባታ ሥራዎች በታቀደው መሠረት ማከናወን አለመቻሉ ከዚህ በተጨማሪም የመድኃኒት አቅርቦት ትልቅ ችግር እንደሆነባቸው አብራርተዋል፡፡
በአዲስ አበባ ከ700 በላይ ለሚሆኑ የፓርኪንሰን ሕሙማን የአቅም ግንባታና የእንክብካቤ ሥራዎች መሠራታቸውን የገለጹት ወ/ሮ ክብራ፣ ከዚሁ ጎን ለጎን ማኅበረሰቡ ስለ በሽታው አውቆ ጥንቃቄ እንዲያደርግ የግንዛቤ ማስጨበጥ ሥራ እየተሠራ እንደሆነ አስረድተዋል፡፡
መንግሥት ለበሽታው ትኩረት በመስጠት ለሕሙማን በአፋጣኝና በተቀላጠፈ መንገድ መድኃኒት እንዲያገኙ እንዲያመቻችም ጥሪ አቅርበዋል፡፡
ከ100 በላይ ለሚሆኑ የፓርኪንሰን ሕሙማን ለስድስት ወራት የሚያገለግል መድኃኒት ቢያቀርቡም የመድኃኒት አቅርቦት ችግር መኖሩንና አገልግሎት አሰጣጡ ላይ ክፍተት እንደተፈጠረ የድርጅቱ የኢትዮጵያ ዳይሬክተር ወ/ሮ ጽዮን ተረፈ ተናግረዋል፡፡
ለ25 ሕሙማን ለስድስት ወራት የሚያገለግል መድኃኒት ለማቅረብ መንገድ ላይ መሆናቸውን የሚናገሩት ዳይሬክተሯ፣ ችግሩን ለመቅረፍ ትኩረት ተሰጥቶ መሥራት ያስፈልጋል ብለዋል፡፡
ሕሙማንን ተከታትሎ መድኃኒት እንዲወስዱና በቂ እንክብካቤ እንዲያገኙ ለማስቻል መንግሥት የቦታ ይዞታ እንዲያመቻችላቸው ቢጠይቁም፣ መልስ አለማግኘታቸውን ወ/ሮ ጽዮን አክለዋል፡፡
በአሁኑ ወቅት የሕክምና አገልግሎቱ ላይ ትልቅ ችግር እንዳለ፣ በተለይም የመድኃኒት አቅርቦቱ አነስተኛ መሆኑን በሕሙማኑ ኑሮ ላይ ቀውስ እንደፈጠረባችው አስረድተዋል፡፡
በሰው ልጅ አዕምሮ ውስጥ የሚገኘው ዶፓሚን የሚባል ኬሚካል ከዕለት ወደ ዕለት በሚቀንስበት ጊዜ የፓርኪንሰን በሽታ ሊከሰት እንደሚችል የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የነርቭ ስፔሻሊስት ቢኒያም ዓለማየሁ (ዶ/ር) ተናግረዋል፡፡
የፓርኪንሰን በሽታ የነርቭ ከሚባሉት በሽታዎች ተርታ የሚመደብ ሲሆን፣ ይህ ሕመም የዶፓሚን ኬሚካል በሚቀንስበት ጊዜ ሰዎቹ ሰውነታቸው የመንቀጥቀጥና ያለመታዘዝ ስሜት እንዲሰማቸው እንደሚያደርግ ዶ/ር ቢኒያም ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡
ማኅበረሰቡም ስለበሽታው ምንነት በማወቅ የበሽታውን ምልክት ሲያይ በአፋጣኝ ወደ ሕክምና ማዕከል መሄድ እንዳለበት አስገንዝበዋል፡፡
በፓርኪንሰን ሕመም መሰቃየት ከጀመሩ ስምንት ወራት የሆናቸው አቶ ሳሙኤል ኃይሌ፣ በየካቲት 12 ሪፈራል ሆስፒታል ምርመራ ሲያደርጉ ነው በሽታው እንዳለባቸው ያወቁት፡፡ ከዕለት ወደ ዕለት እየፀናባቸው እንደመጣም አስታውሰዋል፡፡
በሽታው ሰውነታቸውን ሙሉ ለሙሉ እንደተቆጣጠረው በዚህም የተነሳ ያሉበት ሁኔታ ትልቅ ችግር ውስጥ መሆኑን ገልጸው፣ መንግሥት የበኩሉን በመወጣት ለበሽታው ትኩረት ሰጥቶ መሥራት እንዳለበት አሳስበዋል፡፡
መድኃኒቱን ቶሎ ቶሎ ማግኘት አለመቻላቸውን የሚናገሩት አቶ ሳሙኤል፣ ሕመሙ እየፀናባቸው መምጣቱንና ከቦታ ቦታ መንቀሳቀስ እንደሚከብዳቸው ተቋሙ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የመድኃኒት ድጋፍ እያደረገላቸው መሆኑን ተናግረዋል፡፡
ለፓርኪንሰን ሕመም የሚውል መድኃኒት 11 ብር የሚሸጥ እንደሆነ፣ ሕሙማኑ በቀን ሦስት ጊዜ እንደሚወስዱ በወር 1,000 ብር እንደሚያወጡም ተገልጿል፡፡