Tuesday, May 30, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ልናገርጠቅላይ ሚኒስትሩን ማን ምክር ጠየቃቸው?

ጠቅላይ ሚኒስትሩን ማን ምክር ጠየቃቸው?

ቀን:

በመርሐ ፅድቅ መኮንን ዓባይነህ

ማክሰኞ መጋቢት 14 ቀን 2013 ዓ.ም. የሕዝብ እንደራሴዎች ምክር ቤት በስድስተኛው ዙር የሥራ ዘመን 11ኛ መደበኛ ስብሰባውን አካሂዶ ነበር፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) ደግሞ በዚሁ ስብሰባ ላይ ተገኝተው በአሥር ዓመቱ የልማት ዕቅድና በወቅታዊ ጉዳዮች ላይ ለተከበሩ የምክር ቤቱ አባላት ገለጻ ለማድረግና በአንፃሩም ከእንደራሴዎቹ ለሚቀርቡላቸው ጥያቄዎች ምላሽ ለመስጠት በዕለቱ ተሰይመዋል፡፡

ይሁን እንጂ ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትሩ በኢፌዴሪ ሕገ መንግሥት መሠረት ተጠሪ ለሆኑለት የሕዝብ እንደራሴዎች ምክር ቤትም ሆነ ለሚያስተዳድሩት ለመላው የኢትዮጵያ ሕዝብ ቀጥታ በቴሌቪዥን በተላለፈው መልዕክታቸው ያስደመጡን ረዥም ዲስኩር፣ አልፎ አልፎ ቀልድ መሳይ ነገር የተቀላቀለበትና ያልተጠየቀ ምክር ቢጤ ጭምር የበዛበት የየኔታ ፋንታሁን ዓይነት ሰፊ ቃለ ምዕዳን ሆኖ ታዝበነዋል፡፡

በእርግጥ ይህ አነስተኛ መጣጥፍ እንደ መጫኛ የረዘመውንና ጠቅላያችን ለፓርላማው ያቀረቡትን፣ የዚያን ሙሉ ዲስኩር ጠልቆ በዝርዝር የመተቸት ዓላማ የለውም፡፡

ከዚያ ይልቅ የታላቁ ምክር ቤት ስብሰባ ከመካሄዱ ጥቂት ቀናት አስቀድሞ በአማራ ክልል ተጎራባች ዞኖች፣ ማለትም በሰሜን ሸዋና በኦሮሞ ብሔረሰብ አስተዳደር ዘንድሮ ለዳግመኛ ተከስቶ ከነበረው ደም አፋሳሽ ሁከትና ብጥብጥ ጋር በተያያዘ ከምክር ቤቱ እንደራሴዎች ቀርቦላቸው ለነበረው ፖለቲካ ነክ ጥያቄ፣ በገደምዳሜም ቢሆን በሰጡት የግብር ይውጣ ምላሽና ማብራሪያ ላይ ማተኮርን ይመርጣል፡፡

ከፍ ብሎ በተጠቀሱት የክልሉ ዞኖች ውስጥ ከአጣዬ እስከ ማጀቴ፣ ከሸዋሮቢት እስከ ከሚሴ በሚዘልቁት ከተሞችና ዙሪያ የገጠር ቀበሌዎች ሳይቀር በአደገኛ ሁኔታ ተስፋፍቶ ከመጋቢት 9 ቀን 2013 ዓ.ም. እስከ መጋቢት 13 ዓ.ም. ድረስ በነበሩት ጊዜያት እንደ ስናይፐር፣ አርፒጂና መትረየስ በመሳሰሉ ከባድና የቡድን ጦር መሣሪያዎች ተደግፎ ባልታጠቁ ሰላማዊ ዜጎች ላይ የከፋ መዓት አውርዶባቸዋል፡፡

እንግዲህ ይህንኑ አስመልክቶ አቋማቸውን እንዲያብራሩና ዜጎችን ከእንዲህ ያለው ጥፋት ለመታደግ መንግሥታቸው እያሳየ ያለውን የበዛ ዳተኝነት ሀቀኛ ሆነው እንዲከላከሉ ነበር፣ ጉዳዩ ባሳሰባቸው በአንዳንድ ንቁ የሕዝብ እንደራሴዎች ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትሩ በመጀመርያ የተጠየቁት፡፡

እንደ እውነቱ ከሆነ ጠቅላዩን በጥያቄ ያፋጠጧቸው እንደ ሌላው ጊዜ በሌላ ክልል ውስጥ ብቻ ሳይሆን፣ በራሱ በአማራ ክልል ውስጥ ለሰሚም ሆነ ለተመልካች ፍፁም በሚዘገንን ሁኔታ የኦነግን ሰንደቅ ዓላማ አንግበው ሲንቀሳቀሱ በታዩ ታጣቂዎች ዕርምጃ በአማራው ብሔር አባላት ላይ የተካሄደው ዘርና ሃይማኖት ተኮር ጭፍጨፋ ክፉኛ ያስቆጣቸውና ያበሳጫቸው እንደራሴዎች ብቻ አልነበሩም፡፡ በተቃራኒው ከመካከላቸው ከአጣዬ እስከ ከሚሴ የዘለቀውን አውዳሚ ጥቃት የፈጸመውም ሆነ ያቀነባበረው ከርቀት የመጣ ሌላ ኃይል ሳይሆን፣ ኦሮሞ ጠልና ፀረ እስልምና የሆነው የአማራ ልዩ ኃይል በመሆኑ ከሁሉም ነገር በፊት ይኸው ኃይል ከኦሮሞ ብሔረሰብ ዞን ጠቅልሎ ይውጣልን በማለት፣ ሁከትና ግርግሩን ከሃይማኖትና ከብሔር ጽንፈኝነት ጋር በማስታከክ አደናጋሪ ጩኸት ያሰሙም ይገኙባቸዋል፡፡

ይሁን እንጂ በትልቁ ፓርላማ ዘንድ ከተሰማባቸው የሰላ ሂስና ከተደመጡባቸው ጠንካራ አስተያየቶች አኳያ የጠቅላይ ሚኒስትሩ ረዥም ዲስኩር ‹‹ፍየል ወዲህ ቅዝምዝም›› ወዲያ ሆኖ አግኝተነዋል፡፡ በችግሩ ዙሪያ ለቀረቡላቸው ጥያቄዎች የሰጡት ምላሽና ማብራሪያም ቢሆን ያን ያህል አሳማኝና ውኃ የሚቋጥር ሆኖ አልተገኘም፡፡

ይባስ ብለው ጠቅላያችን በዚያ መድረክ ከውሳኔ ሰጪነት ይልቅ የአሸማጋይነት ዝንባሌ ተስተውሎባቸዋል፡፡ እንዲያውም ረብ የለሽ ካድሬዎቻቸውን አምርረው ከመገሰጽና ከመካከላቸው ዕልቂቱን ሳያነሳሱ እንዳልቀሩ በሚገባ የተጠረጠሩትን የኦሮሞ ጽንፈኞች በኃላፊነት ከመጠየቅ ታቅበው አማራና ኦሮሞ በማኅበረሰብ ደረጃ የተጋጨና ቀድሞውኑ ተፃራሪ ጥቅሞች ያሉት ይመስል፣ እንደ እሳቸው አነጋገር ደጋጎቹ የሰሜን ሸዋ አማሮች አብረዋቸው በፍቅርና በወንድማማችነት ከኖሩት ከወሎ ኦሮሞዎች ጋር ጎራ ለይተው መገዳደላቸውን እንዲያቆሙ ሊመክሩ ሲዳዳቸው በአንክሮ አስተውለናል፡፡

ለነገሩ እሳቸው እኮ ድሮውንም ቢሆን መሪያችን እንጂ አማካሪያችን አልነበሩም፣ አይደሉምም፡፡ እንግዲህ የያኔዎቹ የወርኃ መጋቢት ሰለባዎች በከባድ መሣሪያ ተደግፎ የተፈጸመው ዳግም የጥይት እሩምታ ካደረሰባቸው ቀውስ ገና በቅጡ ሳያገግሙ ነበር አንድ ወር ባልሞላ ጊዜ ውስጥ፣ ማለትም ከሚያዚያ 6 ቀን 2013 ዓ.ም. አንስቶ አሸባሪው ቡድን ከመቼውም ጊዜ ይበልጥ በመታጠቅና በመደራጀት ወደ እነዚሁ የፈረደባቸው የሰሜን ሸዋ አካባቢዎች በመመለስ እንደ አጣዬ፣ ካራቆሬ፣ ማጀቴ፣ ቆሪሜዳ፣ አንጾኪያ፣ ሸዋሮቢት ያሉትን ከተሞችና በዙሪያቸው የሚገኙትን በርካታ የገጠር ቀበሌዎች ለሦስተኛ ጊዜ ያጠቃው፡፡

ቡድኑ በዚህ ጥቃት ሰላማዊ ዜጎችን በጠራራ ፀሐይ አርዷል፣ የመኖሪያም ሆነ የአምልኮ ቤቶቻቸውንና የንግድ ተቋሞቻቸውን በእሳት አጋይቷል፣ መሠረታዊ የዕለት ተለት መገልገያዎቻቸውን ጨምሮ በላብና በጥረታቸው ደክመው ያፈሩትንና ያጠራቀሙትን ሀብትና ንብረት ያለ አንዳች ሀይ ባይ አውድሟል፡፡

በተጠቀሱት አካባቢዎች ላይ የወረደው ይህ ድንገተኛ መከራ የአማራ ክልልንም ሆነ የፌደራል መንግሥቱን የፖሊስና የመከላከያ ኃይሎች ሳይቀር በብርቱ እስከ መገዳደር የደረሰ ነበር፡፡ በዚያ ድንገት ለዜጎች ደኅንነት ዋስትና ይሆናሉ ተብለው የተገመቱ የፖሊስና የመከላከያ አባላት አሸባሪው ቡድን ለጥፋት ካሰማራቸው ወራሪዎች ጋር ሲነፃፀር በመረጃ፣ በትጥቅም ሆነ በድርጅት አቅም አንሰው በመገኘታቸው ከሰላማዊው ሕዝብ ጋር እኩል ተጠቅተዋል፣ ተጨፍጭፈዋልም፡፡

ከጅምላ ጥቃቱና ከግድያው ለመትረፍ የቻለው የየከተሞቹ ነዋሪ ከወረራው የተነሳ ከየሚኖርበት ቀዬ ተፈናቅሎ እስከ መሀል ሜዳ፣ ደብረሲና ደብረ ብርሃን ከተሞች ድረስ በእግሩ ተጉዞ ለመሰደድ ተገዷል፡፡ እንዳለመታደል ሆኖ ረዥም ርቀት ለመሄድ የተሳናቸው ነፍሰ ጡር ሴቶች፣ ሕፃናት በጀርባቸው ያዘሉ እናቶች፣ አረጋውያንና አካል ጉዳተኞች ደግሞ ከአቅም ማነስ የተነሳ በየመንገዱ ወድቀው ቀርተዋል፡፡

እንደ ሰሜን ሸዋ ዞን አስተዳደር መግለጫ ከሆነ ለሦስተኛ ጊዜ በተፈጸመው በዚህ የታጣቂው ቡድን ወረራ የተፈናቀለው፣ እግሬ አውጪኝ በማለት ወደ ተለያዩ ሥፍራዎች የተበተነው ሕዝበ አዳም ቁጥሩ በጠቅላላው እስከ 250 ሺሕ ይደርሳል ነው የሚባለው፡፡

በተለይ በኤፍራታና ግድም ወረዳ ተደጋጋሚ የጥቃት በትር ያለ ርኅራኄ ያረፈባቸው  የአጣዬና የካራቆሬ ከተሞች ሙሉ ለሙሉ ሊባል በሚችል ደረጃ በእሳት ቃጠሎው ወድመዋል፡፡ የግልም ሆኑ የመንግሥት ተቋማት ተዘርፈዋል፣ ተቃጥለዋልም፡፡ የሕግ ታራሚዎች መጠለያ የሆነው የአጣዬ ማረሚያ ቤት ሳይቀር በኃይል ተሰብሮ እስረኞች ራሳቸውን ፈትተው እንዲወጡና ኃላፊነት በጎደለው አኳኋን እንዲያመልጡ ተደርጓል፡፡ ይህ እንግዲህ ለሰላማዊው ኅብረተሰብ ደኅንነት ምን ያህል አደገኛና አስፈሪ ኩነት እንደሆነ ለመገመት አያዳግትም፡፡

ለነገሩ እኮ አጎራባች ከሆነው ከኦሮሚያ ክልል እየተንደረደሩና ይልቁንም በራሱ በአማራ ክልል ውስጥ በታቀፈው የኦሮሞ ብሔረሰብ አስተዳደር አንዳንድ ወረዳዎችና ቀበሌዎች እየመሸጉ ሲሠለጥኑ ይቆዩና አሳቻ ጊዜ እየፈለጉ አድብ ተው በመውጣት፣ የአማራውን ማኅብረሰብ አባላት መርጠው በምልልስ የሚያጠቁት ወሮበሎች ዕርምጃ ለአካባቢው ያን ያህል እንግዳ ነገር አይደለም፡፡ በኦሮሞ ነፃነት ስም እንንቀሳቀሳለን የሚሉት አክራሪና ጽንፈኛ ብሔረተኞች ለዘመናት ፀንቶ የዘለቀውን የአማራና የኦሮሞ ማኅበረሰቦች አብሮ የመኖር ዕሴት አብዝቶ በሚገዳደርና ክፉኛ በሚያጠለሽ መንገድ፣ ዜጎችን በማንነታቸው ላይ አተኩረው ሲገድሉ፣ ሲያቆስሉና ሲያፈናቅሉ ቆይተዋል፡፡

ለምሳሌ የአጣዬና አካባቢው ነዋሪ ሕዝባችን በሚያዝያ ወር 2011 ዓ.ም. ተመሳሳይ ወረራ ተፈጽሞበት እንደነበር አንዘነጋውም፡፡ በእርግጥ ያንን ድፍረት የተመላበት የግፍ ወረራ የከፋ ጥፋት ከማድረሱ አስቀድሞ በተፋጠነ ዕርምጃ በመቀልበሱና አማፅያኑን በመጡበት አኳኋን አሳፍሮ በመመለሱ ረገድ፣ አፈሩ ይቅለላቸውና የወቅቱ የአማራ ክልል ሰላምና ደኅንነት ቢሮ ኃላፊና የታማኝ ጓዶቻቸው ቁልፍ ሚና ተጠቃሽና አይተኬ ነበር፡፡

እንግዲህ እንደ ቀደምት ጥቃቶች ሁሉ ሰሞነኛው ወረራም እስካሁን ድረስ ትክክለኛ ባለቤቱ በይፋ አይታወቅም፡፡ ጉዳዩ በቀጥታ የሚመለከታቸው የክልሉ ባለሥልጣናት የኦነግ ሸኔ ታጣቂዎች እያሉ ነው አዘውትረው የሚጠሯቸው፣ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ደግሞ በስም ከመጥራት በመቆጠብ አሸባሪውን ቡድን አንድ ጊዜ የጥፋት ኃይል፣ ሌላ ጊዜ ደግሞ ጠላት በሚሰኝ ቅጽል እየለዋወጡ ሲጠሩት እንሰማለን፡፡

በዚህ ረገድ ኦፊሴላዊ ያልሆነ የአፈንጋጭነት ዝንባሌ የሚታይበት የኦሮሞ ብሔረሰብ አስተዳደር ብቻ ከእንዲህ ያለው የተዥጎረጎረ ፍረጃና አጠራር የለሁበትም ሲል ራሱን ወደ አማፅያኑ ጎራ ለማስጠጋት የመረጠ ሆኖ እናየዋለን፡፡ አህመድ ሐሰን የተባሉት የብሔረሰብ ዞኑ ዋና አስተዳዳሪ በዚያን ሰሞን ወደ ሚዲያ ብቅ ብለው እኔ በበኩሌ ኦነግ ሸኔ የተሰኘ ታጣቂ ቡድን አላስጠለልኩም፣ እንዲያ የሚባል ቡድንም አላውቅም፣ ይህ የፈጠራ ወሬ ነው ሲሉ ሽንጣቸውን ገትረው ሲከራከሩ መደመጣቸው የዚህ ማሳያ ይመስላል፡፡

ይህ ሁሉ ሲሆን ታዲያ የፌደራሉ መንግሥት ጀሮዬን ይድፈነው በማለት ሊምልና ሊገዘት እስኪዳዳው ድረስ ስለሁከቱ ጨርሶ የሰማ እንኳን አይመስልም፡፡ አገር ቀውጢ ሆኖ ከተሞች እንደ ጧፍ ከነደዱ በኋላ ብቅ ብሎ  እባካችሁን ተረጋጉ በማለት፣ በመከላከያና በሰላም ሚኒስቴሮቹ አማካይነት የ‹‹ጅብ ከሄደ ውሻ ጮኸ›› ዓይነት መግለጫዎችን አዥጎድጉዶልናል፡፡

መከላከያውስ ከዚህም አልፎ ከደብረሲና እስከ ኮምቦልቻ የሚዘልቅ የኮማንድ ፖስት ቀጣና ዘርግቶልናል፡፡ ይህንን እንዲያደርግለት የአማራ ክልል መንግሥት አስቀድሞ ይጠይቀው አይጠይቀው፣ በእርግጥ በይፋ የሚታወቅ ነገር የለም፡፡

ኦነግና በስሙ የሚጠራው ኦነግ ሸኔ ምንና ምን ናቸው? ለዘመናት በደፈጣ ተዋጊነት ተሰማርቶና በመንግሥት በኩል ደግሞ በአሸባሪነት ተፈርጆ ከቆየ በኋላ ከለውጡ ማግሥት በሰላማዊ መንገድ ለመታገል እንደ ወሰነና ወደ አገር ቤት እንደገባ አጥብቆ ሲወተውት የሚሰማው የኦሮሞ ነፃነት ግንባር (ኦነግ)፣ ተፈጥሯዊ ውላጁ ከሚመስለውና ‹ኦነግ ሸኔ› እየተባለ ከሚጠራው ከዚህ የአመፅና የወንጀል ቡድን ጋር አንዳች ትስስር የለኝም ሲል ነው በየጊዜው ሲምልና ሲገዘት የምንታዘበው፡፡

በሌላ በኩል ደግሞ ትክክለኛው መጠሪያዬ መንግሥት እንደሚለው ‹ኦነግ ሸኔ› ሳይሆን ‹የኦሮሞ ነፃ አውጪ ሠራዊት› ነው ሲል በህቡዕ ከመሸገበት ሥፍራ ሆኖ በአሜሪካ ድምፅ የአማርኛውን አገልግሎት በስልክ ያገኘው ኩምሳ ድሪባ፣ ወለጋ ውስጥ ማንነትን መሠረት በማድረግ በንፁኃን የአማራ ብሔር ተወላጆች ላይ ያለ ማቋረጥ እየተፈጸመ ላለው ጥቃት ተጠያቂው እኔ ሳልሆን ራሱ መንግሥት ነው በማለት አምርሮ ይከሳል፡፡

ግራም ነፈሰ ቀኝ በልዩ ሁኔታ እስካፍንጫው ድረስ የታጠቀና የተደራጀ ነው እየተባለ የሚነገርለትና በህቡዕ የሚንቀሳቀሰው ኦሮሞ በቀል ቡድን ኦነግ ሸኔ የሚሰኘው ስሙ በተደጋጋሚ አየር ላይ ሲናኝ በአግራሞት መታዘባችንን ቀጥለናል፡፡ እስካሁን ድረስ ፍፁም ጉራማይሌ የሆነብንና በውል ለመረዳት የተሳነን ግን በዚሁ ቡድን ስም እየተንቀሳቀሱ የከተማም ሆነ የገጠር መንደሮችን ሲወሩና በንፁኃን ወገኖቻችን ላይ ማንነትን መሠረት ያደረጉ ጭፍጨፋዎችን በተከታታይ ሲፈጽሙ፣ የሰለባዎችን ሕይወት ሲቀጥፉና ንብረት ሲዘርፉ ወይም ሲያወድሙ የምናገኛቸው የጥፋት መልዕክተኞች አፋን ኦሮሞ የሚናገሩና አልፎ አልፎም በኦነግ ባንዲራ አሸብርቀው የሚታዩ መሆናቸው ነው፡፡

እንግዲህ ጉዳዩ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ መንገድ የሚመለከታቸው የኦሮሚያ ክልላዊ መንግሥትም ሆነ የራሱ የፌደራሉ መንግሥት የበላይ የፖለቲካ አመራሮች መፍታትና ማፍታታት የሚጠበቅባቸው ይህንን እንቆቅልሽ መሆን አለበት፡፡

የትኛውም ዓይነት ጥያቄ እንደቀረበበት ዓውድ ከአንድ በላይ የሆኑ መልሶች ይኖሩት ይሆናል፡፡ ትክክለኛ ምላሹ ግን ምንጊዜም ቢሆን አንድና አንድ ብቻ ነው የሚሆነው፡፡ ለግብር ይውጣ ያህል የሚሰጥ የማስታገሻ መልስና ኃላፊነት የሚወሰድበት ምላሽ በጠባያቸው ይለያያሉና፡፡

አበቃሁ፡፡

ከአዘጋጁ፡- ጸሐፊው በሕግ ሙያ የመጀመርያ ዲግሪያቸውን በ1981 ዓ.ም. ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የቀድሞው የሕግ ፋኩልቲ ያገኙ ሲሆን፣  በሐምሌ ወር 2001 ዓ.ም. ደግሞ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲና በተመድ የሰላም ዩኒቨርሲቲ ጣምራ ትብብር ይካሄድ ከነበረው የአፍሪካ ፕሮግራም በሰላምና በደኅንነት ጥናት የማስተርስ ዲግሪያቸውን ሠርተዋል፡፡ በአሁኑ ወቅት በአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት በቢሮ ኃላፊ ማዕረግ የርዕሰ መስተዳድሩ ዋና የሕግ አማካሪ ሆነው በማገልገል ላይ ናቸው፡፡ ጽሑፉ የእሳቸውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እየገለጽን፣ በኢሜይል አድራሻቸው [email protected] ማግኘት ይቻላል፡፡  

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የመስቀል አደባባይ የመግቢያ ክፍያ ለምን?

ወጣቶች፣ ሕፃናትና አረጋውያን ሳይቀሩ መንፈሳቸውን የሚያድሱበት እንዲሁም ሐሳባቸውን በነፃነት...

በሕገ መንግሥቱ የተዋቀረው ‹‹የብሔር ፖለቲካ›› እና ‹‹ሥርዓቱ›› ያስከተለው መዘዝና መፍትሔው

(ክፍል አራት) በዓቢዩ ብርሌ (ጌራ) ባለፈው ጽሑፌ (በክፍል ሦስት) አሁን ያለው...

የኢትዮጵያ ኅብረተሰብና የመንግሥት መሪ ምሥል

በበቀለ ሹሜ በ2015 ዓ.ም. መጋቢት ወር ውስጥ ይመስለኛል በ‹ሸገር ካፌ›...

ዩኒቨርሲቲዎችን ራስ ገዝ ያደረገው አዋጅ የፍትሐዊነት ጥያቄ አስነሳ

በቀጣዮቹ ሁለት ዓመታት ስምንት ዩኒቨርሲቲዎችን ራስ ገዝ በማድረግ ተቋማዊና...