Tuesday, February 27, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

በዋጋ ንረት የተፈተነው የበዓል ሸመታ

ተዛማጅ ፅሁፎች

የዋጋ ንረቱ ማየል ከጀመረ ሰነባብቷል፡፡ የዓውደ ዓመት መደረብ ደግሞ የዋጋ ንረቱን የበለጠ አማራሪ አድርጎታል፡፡

ከፊታችን ያሉ የትንሳዔና የኢድ አል አፈጥር በዓላት ዋዜማ ገበያም ይህንኑ የሚያሳይ ነው፡፡ በተለይ ለበዓል ተፈላጊ የሚባሉ ምርቶች የተወሰነ ጭማሪ ያሳያሉ፡፡ ዘንድሮ ግን ከወትሮ በተለየ የዋጋ ንረቱ ወደ ላይ ተሰቅሏል፡፡ በበዓላቱ ዋዜማ ላይ ያለው ገበያ ሲታይ ከወትሮው በተለየ የዋጋ ጭማሪ የታየበት መሆኑን ሪፖርተር ታዝቧል፡፡ ሸማቾችም እየገለጹ ነው፡፡  

የሰሞኑን የገበያ ለተመለከተም ነገሩ በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ ሆኗል፡፡ ወ/ሮ አስናቁ ገነቴ ለትንሳዔ በዓል ከወዲሁ የሚፈልጉትን ለመሸመት ገበያ የወጡት ቅዳሜ ሚያዝያ 16 ቀን 2013 ዓ.ም. ነበር፡፡ የቅርብ ገበያቸው ደግሞ ሳሪስ ገበያ ነበርና ለሸመታው ይበቃኛል ያሉትን ገንዘብ ይዘው ወጥተዋል፡፡ ሲመለሱ ግን እገዛዋለሁ ብለው ያሰቡትን አልገዙም፡፡ የተገዛውም ቢሆን ካሰቡት መጠን እየቀነሱ ነበር፡፡

‹‹ኧረ ምንድነው የምንሆነው›› የሚሉት አስናቁ አንድ ኪሎ ቅቤ በ470 ብር መግዛታቸውን ይገልጻሉ፡፡ በ18 ዓመት የትዳር ዘመናቸው፡፡ ለአንድ ኪሎ ቅቤ የዚህን ያህል ዋጋ አለማውጣታቸውን ያስታወሱት ሸማች፣ ከሁለትና ከሦስት ወራት በፊት አንድ ኪሎ ቅቤ 280 ብር መግዛታቸውን፣ በሦስት ወራት ውስጥ 190 ብር ጨምሮ ሲያገኙት እንደገረማቸው ተናግረዋል፡፡ ሪፖርተር ባደረገው ቅኝትም በአብዛኛዎቹ የአዲስ አበባ ገበያዎች አንድ ኪሎ ለጋ ቅቤ እስከ 500 ብር እየተሸጠ መሆኑን ታዝቧል፡፡

እንደ ወ/ሮ አስናቁ ገለጻ በየበዓላቱ የቅቤ ዋጋ ላይ የተወሰነ ለውጥ ቢኖርም፣ እንደ ዘንድሮ የቅቤ ዋጋ በዚህን ያህል ደረጃ የጨመረበት ጊዜ አልነበረም፡፡ ለምን በዚህን ያህል ደረጃ ዋጋ እንደጨመረ ሸማቾች ምንም የሚያውቁት ነገር የለም፡፡ ያነጋገርናቸው የቅቤ ሻጮች ግን ከምንጩ መጨመሩን ቢገልጹም፣ በዓልን አስታከው ያደረጉት የዋጋ ጭማሪ አነጋጋሪ መሆኑ አልቀረም፡፡

የቅቤ ገበያ የተጋነነ ጭማሪ የታየበት መሆኑን ማሳያ የሚሆነው ከገበያ ውጭ የሚሸጡ ነጋዴዎች እየሸጡ ያሉበት ዋጋ ሲታይ ነው፡፡ እነዚህ በተለያዩ ሠፈሮች፣  አልፎ አልፎም ወደ ተለያዩ ተቋማት እየሄዱ የሚሸጡ ቅቤ አቅራቢዎች አሁን እየሸጡበት ያለው ከፍተኛ ዋጋ 350 ብር ነው፡፡

እንዲህ ባለ ሁኔታ ሽያጭ የሚያከናውኑት የቅቤ ነጋዴዎችን ጠይቀን እንደተረዳነው ቅቤውን ከባህር ዳር እንደሚያስመጡና 350 ብር ያዋጣቸዋል፡፡ ከወደ ሰሜን ሸዋ ደብረ ብርሃን የሚያመጡት ደግሞ ዋጋው እንደሚጨምር ነግረውናል፡፡ በደብረ ብርሃን ከወር በፊት አንድ ኪሎ ቅቤ 420 ብር መሸጡን ሰምተናል፡፡ 

ከሰሞኑ የቅቤ ሽያጭ ዋጋ ተያይዞ በሠፈሯ የገጠማትን ያጫወተችን የቅቤ ነጋዴ፣ አንዱን ኪሎ 350 ብር ስትሸጥ አንዳንድ የሠፈሩ ሰዎች ቅቤው ጥሩ ባይሆን ነው እንጂ እንዴት በዚህ ዋጋ ይሸጣል? ብለዋት ለመሸጥ መቸገሯን ነግራናለች፡፡  ዋጋውን 400 ብር ስታደርገው ግን ገበያ አግኝታ መሸጧንም ገልጻለች፡፡

የዘንድሮውን የበዓል ዋዜማ ገበያ በተለየ የሚታይበት ታይቶ በማይታወቅ ሁኔታ የቅቤ ዋጋ እንዲህ መሰቀሉ ብቻ አይደለም፡፡ እንደ ወ/ሮ አስናቁ ያሉ የቤት እመቤቶችን አጀብ ካሰኛቸው ሰሞናዊ የዋጋ ጭማሪዎች ውስጥ በርበሬም አንዱ ነው፡፡ ለወትሮ ተወደደ ተብሎ አንዱን ኪሎ ዛላ በርበሬ ከ150 እስከ 170 ብር እንደሸመቱት የሚናገሩት ወ/ሮ አስናቁ፣ ቅዳሜ ለአንድ ኪሎ በርበሬ የተጠየቁት 250 ብር ነበር፡፡

15 ኪሎ በርበሬ ለመሸመት ሄደው አሥር ኪሎ በርበሬ ለመግዛት መገደዳቸውን በዓውደ ዓመት ሰበብ የተጨመረው ዋጋ አቅማቸውን መፈተኑን አክለዋል፡፡

ለበዓሉ ያስፈልጋሉ ከተባሉ ዕቃዎች ውስጥ ዶሮ ተጠቃሽ ነው፡፡ እስከ ቅዳሜ ባለው ገበያ ትልቅ የሚባል ዶሮ በሳሪስ ገበያ 450 ብር ይጠራል፡፡ በቄራ ገበያ ተመሳሳይ ዋጋ ይጠራል፡፡

አነስተኛ ዶሮ ከ250 እስከ 300 ብር እየተሸጠ ነው፡፡ የዶሮ ገበያ የሚደረገው የበዓሉ የመጨረሻ ዋዜማ ቀን ላይ በመሆኑ ዋጋው ሊጨምር ይችላል የሚል ሥጋት ግን ሸማቾች አላቸው፡፡ ምክንያቱም ብዙ ሸማቾች የዶሮ ገበያን የሚያከናውኑት በበዓሉ መዳረሻ የመጨረሻዎቹ ሁለት ቀናት በመሆኑ ነው፡፡

ከሰሞነ ህማማት ጀምሮ ምዕናኑ ለባዕለ ትንሳዔ ሽርጉድ የሚልበት ሳምንት ነው፡፡ ገበያውም በሰሞነ ህማማት ይደራል፡፡ የዘንድሮ የትንሳዔ በዓለ ዋዜማ እንደ አገር በብዙ መከራና ችግር የተፈተነ ነው፡፡ በየአካባቢው ያለው የፀጥታ ችግር፣ የአንበጣ መንጋ ያጠፋው ሰብል፣ ድርቅና ረሃብ ከተደቀኑት ችግሮች ውስጥ ይጠቀሳሉ፡፡ በተጨማሪም ሰዎችን አቅል ያሳጣው የሸቀጣ ሸቀጦችና የምግብ ፍጆታዎች የዋጋ ንረት በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ ሆኗል፡፡

በየቀኑ ከሚሰማው የሰው ሕይወት መጥፋትና የደኅንነት ሥጋቶች ላይ የዋጋ ንረቱ ተደማምሯል፡፡

መገናኛ ሾላ ገበያ፣ ከዱበር፣ ከወላይታ፣ ከጊንጪ፣ ከወሊሶና ከአርባ ጉጉ ተሸምተው የሚመጡ በጎች በአማካይ እስከ ስድስት ሺሕ ብር እየተሸጠ ይገኛሉ፡፡ በሸመታው ዝቅተኛው የበግ ዋጋ ከ3,000 ብር ሲሆን፣ መካከለኛ 3,500 እንዲሁም ትልቅ (ከፍተኛ) የሚባለው እስከ 9,500 ብር እየተሸጠ ይገኛል፡፡ አሥር ዓመት በላይ በግ ከተለያዩ የክልል ከተሞች እያመጣ የሚሸጡት አቶ መኩሪያ በቀለ ከሚሸምቱበት ቦታ እጅግ ውድ በሆነ ዋጋ እየገዙ መሆናቸውን ያስረዳሉ፡፡

ሪፖተር ሚያዝያ 18 ቀን 2013 ዓ.ም. ባደረገው የገበያ ቅኝት ሸማቾች በቦታው በብዛት አለመኖራቸውን ታዝቧል፡፡ ሸማቾች ቀደም ብሎ የመግዛት ልማድ አናሳ ቢሆንም፣ የዘንድሮ የትንሳዔ ገበያ እንደሚቀዘቅዝ ለዚህም የገዥ አቅም በመዳከሙ መሆኑን ነጋዴዎች ተናግረዋል፡፡

አሁን ባለው የገበያ ሁኔታ የተቀዛቀዘ ቢሆንም ከሰኞ በኋላ ባሉት ቀናት ገበያ ይደራል ተብሎ ይጠበቃል፡፡ በሾላ የቁም እንስሳት መሸጫ የበሬ ዋጋ ዝቅተኛው 40,000 መካከለኛ 60,000 እና ትልቁ ደግሞ እስከ 90 ሺሕ እና ከዚያ በላይ ለገበያ ቀርቧል፡፡

በገበያው የበሬ ዋጋ በአማካይ እስከ 60,000 እየተሸጠ መሆኑን ሪፖርተር ተመልክቷል፡፡ በክልል ከተሞች ከ30,000 እስከ 40,000 እና አዲስ አበባ ከሚጠራው ጥሪ በላይ እየተሸጠ እንደሚገኝ አቶ መኩሪያ ነግረውናል፡፡

የዋጋው ጭማሪ በውል ባይታወቅም የመኖ ዋጋ ጭማሪና ካለው የኑሮ ውድነት ጋር ተዳምሮ እንደሚሆን አቶ መኩሪያ ገልጸዋል፡፡ በሌላ በኩል በተለያዩ የአገሪቱ ገጠራማ ቦታዎች የአንበጣ መንጋ መከሰት፣ ድርቅና የሰላም ዕጦት እንዲሁም የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝን ለዋጋው መጨመር ትልቁን ድርሻ እንደሚይዝ ነጋዴዎቹ ያስረዳሉ፡፡ በተለይ ከአሁን በኋላ የዋጋ ንረት ከፍ ሊል ይችላል ብለው የሠጉት በበግ አራጅነት የሚታወቁት አቶ ሙሉጌታ ቦጋለ የደላላ አስተዋጽኦ ከፍ ያለ መሆኑን ነግረውናል፡፡

አቶ ሙሉጌታ፣ በዘንድሮ የበግ ቆዳ ዋጋ የአንዱ ከ25 እስከ 40 ብር ሲሆን፣ አንድ በግ ለመግፈፍ ከ200 ብር በላይ መሆኑን ነግረውናል፡፡ የሐበሻ ሽንኩርት ዋጋው እንደሚመጣበት የክልል ቦታዎች የሚለይ ሲሆን፣ የቡልጋ አንድ ኪሎ ሽንኩርት 35 ብር፣ የአሌልቱ ደግሞ 30 ብር እየተሸጠ ይገኛል፡፡

ኮረሪማ ከ150 ብር እና ከዚያ በላይ፣ ጥቁር አዝሙድ ከ280 እና ከዚያ በላይና ነጭ ሽንኩት 100 ብር እየተሸጠ ይገኛል፡፡

የዶሮ ዋጋ እንደሚመጣባቸው አካባቢዎች የሚለያይ ሲሆን፣ የወላይታ ዋጋው ከፍ የሚል መሆኑን ነጋዴዎች ነግረውናል፡፡ በሌላ በኩል የሐበሻ ዶሮ 350፣ 450፣ 550 ብር እና ከዚያ በላይ በሾላ ገበያ እየተሸጠ ሲሆን፣ ድቅል ዶሮዎች ደግሞ ከ400 ብር ጀምሮና ከዚያ በላይ ይሸጣሉ፡፡

የዓውድ ዓመት ሽታ አድማቂ ከሆኑት ውስጥ ቅቤ ተጠቃሽ ነው፡፡ በዘንድሮ የትንሳዔ በዓል ዋጋቸው ከፍ ካሉት የበዓል ግብዓቶች ውስጥ ቅቤ አንዱ ነው፡፡ ቅቤ መካከለኛው 530 ብር፣ ለጋ 580 ብር በኪሎ እየተሸጠ ይገኛል፡፡

በዳዊት ታዬና በሔለን ተስፋዬ

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች