Tuesday, February 27, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

ጥያቄ ያስነሳው አዲሱ የባንክ ማቋቋሚያ ካፒታል

ተዛማጅ ፅሁፎች

ከዛሬ 28 ዓመታት በፊት በኢትዮጵያ የግል ባንክ ኩባንያ ማቋቋም እንደሚቻል ሲፈቀድ የማቋቋሚያ ካፒታሉ ምን ያህል ይሁን የሚለው በግልጽ የተቀመጠ ነገር አልነበረም፡፡ ባንክ ማቋቋም መፈቀዱን ተከትሎ የግል ባንክ ለማቋቋም እንቅስቃሴ የጀመሩ ግለሰቦች፣ የማቋቋሚያ ካፒታሉ እስኪታወቅ ድረስ አክሲዮን ሽያጭ ከማከናወን ተገደቡም፡፡ ኋላ ላይም የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ አንድ ባንክ ለማቋቋም የሚያስፈልገው የተከፈለ ካፒታል አሥር ሚሊዮን ብር ነው የሚል መመርያ አወጣ፡፡ የመጀመርያዎቹ የግል ባንኮችም በዚሁ ሁኔታ ተመሥርተው ወደ ሥራ ሊገቡ ችለዋል፡፡

ከዚህ በኋላ የባንክ ማቋቋሚያ የካፒታል መጠን ወደ 20 ሚሊዮን ብር እንዲያድግ ተደርጓል፡፡ በሒደት ወደ 100 ሚሊዮን ብር አደገ፡፡ የዛሬ አሥር ዓመት ደግሞ የባንኮች የማቋቋሚያ ካፒታል 500 ሚሊዮን ብር ሆኗል፡፡ በአሁኑ ወቅት በሥራ ላይ ከሚገኙ 16 የግል ባንኮች ውስጥ አብዛኞቹ የተቋቋሙት በ100 ሚሊዮን ብርና ከዚያ በታች ካፒታል ያስፈልጋል በሚለው መመርያ ነው፡፡

የባንክ ማቋቋሚያ ካፒታል መጠኑ 500 ሚሊዮን ብር እንዲሆን ከተወሰነ በኋላ፣ እስካሁን ድረስ አንድም አዲስ ባንክ ወደ ሥራ ያልገባ ሲሆን፣ በዚህን ያህል ካፒታል ባንክ ለማቋቋም መንቀሳቀስ የተጀመረው በቅርቡ ነው፡፡፡ 100 ሚሊዮን ብር በሚጠየቅበት ወቅት ባንክ ለማቋቋም ላይ የነበሩ ባንኮች፣ የመመሥረቻ ካፒታል መጠኑ 500 ሚሊዮን ብር ሲሆንባቸው፣ 500 ሚሊዮን ብር መሙላት አንችልም ብለው የአክሲዮን ሽያጫቸውን አቋርጠው እንደነበር ይታወሳል፡፡

በ500 ሚሊዮን ብር ካፒታል ባንክ ለመመሥረት እንደ አዲስ እንቅስቃሴ የተጀመረው ከሦስት ዓመት ወዲህ ነው ማለት ይቻላል፡፡ ይህም ከአሥር ዓመት በፊት 500 ሚሊዮን ብር ካፒታል አክሲዮን ሸጦ ማሟላት አንችልም ብለው ያቆሙና ሌሎችን ጨምሮ 500 ሚሊን ብር ማሟላት ይቻላል ያሉ ወደ ሃያ ባንኮች አክሲዮን ሸጠው ኢንዱስትሪውን ለመቀላቀል እየተንቀሳቀሱ ቢሆንም፣ አዲሱ የብሔራዊ ባንክ የባንክ ማቋቋሚያ ካፒታል ካሰቡት በላይ እንዲዘጋጁ ግድ ብሏቸዋል፡፡

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ የባንክ ማቋቋሚያ ካፒታል መጠኑን ከ500 ሚሊዮን ብር ወደ 5 ቢሊዮን ብር ማሳደጉም ከገንዘብ ግሽበትና አቅም ጋር እንዲሁም ከኢኮኖሚያዊ ዕድገት ጋር የተገናዘበ ካፒታል ባንኮች ሊኖራቸው ይገባል ከሚል ነው፡፡

የባንክ ማቋቋሚያ ካፒታል መጠኑ 5 ቢሊዮን ብር እንዲሆንና ይህንንም ካፒታል ነባር ባንኮች በአምስት ዓመት፣ በምሥረታ ላይ ያሉ ባንኮች ደግሞ በሰባት ዓመት ያሟሉ ከሚለው ሰሞናዊ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ መመርያ ጋር ተያይዞ በኢንዱስትሪው ውስጥ ያሉ ተዋንያንን በተለያየ ምልከታም እያነጋገረ ነው፡፡

በአብዛኛው መመርያው አግባብና የሚጠበቅም ነው የሚል አስተያየት የተሰጠበት ቢሆንም፣ የአገሪቱን የፋይናንስ ኢንዱስትሪ ለማሳደግና የበለጠ እንዲራመድ ከተፈለ ግን የማቋቋሚያ ካፒታሉ መጠን አሁን እጅግ ዝቅተኛ ከመሆኑም ባሻገር ነገን ታሳቢ አድርጎ የተወሰነ አለመሆኑን የሚሞግቱም አሉ፡፡ ከእነዚህ ውስጥ ጎምቱው የፋይናንስ ባለሙያና የኅብረት ባንክ ቦርድ ሊቀመንበር አቶ ኢየሱስ ወርቅ ዛፉ አንዱ ናቸው፡፡

ብሔራዊ ባንክ የባንክ ማቋቋሚያ ካፒታል መጠን ወደ 5 ቢሊዮን ብር ከፍ ለማድረግ የሄደበት አቅጣጫ ጥሩ መሆኑን በመጠቆም አስተያየታቸውን የጀመሩት አቶ ኢየሱስ ወርቅ፣ ነገር ግን 5 ቢሊዮን ብር ካፒታል እጅግ ዝቅተኛ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ ‹‹በአምስት ዓመትና በሰባት ዓመት አምስት ቢሊዮን ብር ካፒታል ይኑራቸው ማለት በእኔ ዕይታ የፋይናንስ ዘርፉ ከድሮ ጠባብ ዕይታ ያልተቀላቀለ ስለመሆኑ ያሳየኝ ነው፤›› ብለውታል፡፡

በአሁኑ ጊዜ ካፒታላቸውን 5 ቢሊዮን ብር ያደረሱ ባንኮች አሉ፡፡ ከዚህም ያለፈ ካፒታል ያላቸው ስላሉ 5 ቢሊዮን ብር ካፒታል የባንክ ማቋቋሚያ ይሁን መባሉ ከምን ዕሳቤ የተወሰነ ስለመሆኑ ግራ የሚያጋባ ነውም ይላሉ፡፡

ምክንያቱን ሲገልጹ ደግሞ በተለይ አሁን ካለው የብር የመግዛትና ብር ከዶላር አንፃር ካለው የምንዛሪ አቅም አንፃር ሲታይ የዛሬ አምስት ዓመት አምስት ቢሊዮን ብር የሚኖረውን የመግዛት አቅም ያላገናዘበ ውሳኔ መሆኑን የሚያሳይና የተጠቀሰው ካፒታል መጠን እጀግ አነስተኛ ነው ሲሉም ይሞግታሉ፡፡

‹‹የባንኮችን ካፒታል የማሳደግ አቅጣጫ ትክክል ነው፡፡ ነገር ግን ለተሰጠው ጊዜ የተቀመጠው ገንዘብ በጣም ትንሽ ነው፡፡ በቅርብ ጊዜ ውስጥ ይህ ትክክል እንዳልሆነ እነሱ ራሳቸው ይረዳሉ ብዬ አስባለሁ፤›› ብለዋል፡፡

እንዲህ ዓይነት ውሳኔ የኢትዮጵያ የባንክ ዘርፍ ገና ነው ከሚል የመነጨ ይመስለኛል የሚሉት አቶ ኢየሱስ ወርቅ፣ በቅርብ ጊዜ ውስጥ ስቶክ ኤክስቼንጅ ስለሚቋቋምና የገንዘብ ማሰባሰብ ዕድልም በጣም የተሻለ ስለሚሆን ከዚያ አንፃር ካፒታልን ማሳደግ ይቻል እንደነበር አስረድተዋል፡፡  

በአሁኑ ወቅት ካሉት 16 ባንኮች በተጨማሪ በርካታ ባንኮች ወደ ኢንዱስትሪው ይገባሉ፣ እነዚህ ባንኮች ወደ ሥራ ሲገቡም የአገሪቱ ባንኮች ቁጥር ወደ 30 እና ከዚያም በላይ እንደሚያድግ በማስታወስ፣ ለአገሪቱ ግን 30 እና 40 ባንክ አያስፈልጋትም ብለዋል፡፡

አሁን ባለው የኢትዮጵያ ሁኔታ 10 እና 15 ባንኮች በቂ መሆናቸውን በመጥቀስም ጠንካራ ባንኮች ከተፈለጉ ጠንካራ ካፒታል የሚያሻ በመሆኑ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ መመርያም ይህንን ታሳቢ ማድረግ ነበረበት ሲሉ አክለዋል፡፡

ከዚህ መመርያ መውጣት ጋር ተያይዞ ሌላው እንደ ተግዳሮት እየተጠቀሰ ያለው ባንኮቹ አክሲዮኖቹን ሸጠው አምስት ቢሊዮን ብር ለመሙላት ይከብዳቸዋል የሚል ነው፡፡ በተለይ አዳዲሶቹ ለምሥረታ ያስፈልጋል የተባለውን 500 ሚሊዮን ብር ካፒታል ለመሙላት ሁለት ዓመት ድረስ ሲወስድባቸው ይታያልና ሊፈትናቸው ይችላል፡፡

አቶ የኢሱስ ወርቅ ግን ይህንን ሥጋት በፍፁም አይጋሩም፡፡ ለዚህም እርሳቸው በቦርድ ሊቀመንበርነት የሚመሩትን ኅብረት ባንክ በምሳሌ ያቀርባሉ፡፡ ኅብረት ባንክ ካፒታሉን ከሁለት ቢሊዮን ወደ አምስት ቢሊዮን ብር ለማሳደግ ሦስት ቢሊዮን ብር ተጨማሪ ካፒታል ይደረግ የሚል ሐሳብ በቀረበበት ጊዜ የነበረው እውነታ ጥሩ ማሳያ ነው ይላሉ፡፡

ባንካቸው፣ ካፒታል በሦስት ቢሊዮን ብር ይጨመር በተባለበት ጊዜ በአንድ ጊዜ ይህንን ያህል ካፒታል አሳድገን ማን ሊገዛን ነው የሚል ጥያቄ ቀርቦ እንደነበር ያስታውሳሉ፡፡ ወቅቱ ዳያስፖራ በኢትዮጵያ የፋይናንስ ዘርፍ እንዲገባ ሕግ እየተረቀቀ ባለበት ወቅት ስለሆነ፣ መመርያው ሲወጣ አክሲዮኑን ለዳያስፖራ በመሸጥ እንሞላለን በሚል ለማሳመን እንደሞከሩና እንደተሳካላቸው ይገልጻሉ፡፡

የአክሲዮን ሽያጩ ሲጀመር ሦስቱ ቢሊዮን ብር ዋጋ ካላቸው አክሲዮኖች ውስጥ 2.6 ቢሊዮን ብር ዋጋ ያላቸውን በሁለት ወር ተኩል ጊዜ ውስጥ ማጠናቀቅ መቻሉን በመግለጽ፣ ባንኮች ካፒታላቸውን አሳድጉ ቢባሉ አክሲዮን ለመሸጥ ይፈተናሉ የሚለውን ሐሳብ እንደማይቀበሉት አመልክተዋል፡፡

ባንኩ አቅርቦ ከነበረው ሦስት ቢሊዮን ብር አክሲዮን ውስጥ ቀሪውን 400 ሚሊዮን ብር በተመለከተ የሰጡት ማብራሪያም፣ ነባር ባንኮች አክሲዮን ለመሸጥ የማይቸገሩ መሆኑን ነው፡፡  የ400 ሚሊዮን ብር አክሲዮን ለዳያስፖራው ለመሸጥ ጊዜውን እናዘግይ ተብሎ ሐሳብ የቀረበ ቢሆንም፣ ዳያስፖራውን በፋይናንስ ዘርፉ ውስጥ እንዲሳተፉ የሚፈቅደው ሕግ ሲወጣ ግን የተመቸ አልነበረም፡፡

ምክንያቱም ለዳያስፖራው አክሲዮን መሸጥ የተፈለገው በውጭ ምንዛሪ ሆኖም ብሔራዊ ባንክ አክሲዮን ሸጣችሁ ከምታገኙት የውጭ ምንዛሪ 70 በመቶውን ለእኛ አስገቡ በማለቱ ለዳያስፖራ ይሸጣል የተባለውን ዕቅድ አፈረሰባቸው፡፡ ለዳያስፖራ የታሰበው አክሲዮንም እዚሁ እንዲሸጥ ተደረገ፡፡ እንዴት እንደሚሸጥ ሲወሰን ደግሞ መጀመርያ የመጣ መጀመርያ ይስተናገድ በሚል ማስታወቂያ ወጥቶ ይሸጥ ተባለ፡፡ ማስታወቂያው መሸጥ በጀመረ ቀን ከሁለት ሰዓት ጀምሮ አምስት ሰዓት ጀምሮ ሰዎች ሌሊት መጥተው ተሠለፉ፡፡ አምስት ሰዓት ሳይሞላ የ400 ሚሊዮን ብር አክሲዮን ተሸጠ፡፡ 400 ሚሊዮን አክሲዮን ሦስት ሰዓት ባልሆላ ጊዜ መሸጥ ተቻለ፡፡ አክሲዮን መሸጥ የሚቸገሩት ገና አዲስ ሲሆኑና በባንክ ዘርፍ የሚተማመኑበት አመራር ከሌለ ነው የሚሉት አቶ ኢየሱስ ወርቅ፣ ጥሩ የሚሠሩ ነባር ባንኮች አክሲዮን ለመሸጥ በምንም ሁኔታ አይቸገሩም የሚል እምነት አላቸው፡፡ ‹‹ምናልባት አንዳንዶች ከራሳቸው ባለአክሲዮኖች ውጪ አንሸጥም ካላሉ አክሲዮን ካወጡ ይሻጣሉ፡፡ ችግር የሚሆነው በስሜትና በጭፍን ሲኬድ ነው፤›› የሚል እምነት አላቸው፡፡

ባንኮች ካፒታላቸውን ያሳድጉ በሚለው አዲሱ መመርያ ላይ ሌላው የሚነሳው ጉዳይ የባንክ ማቋቋሚያ ካፒታል 5 ቢሊዮን ብር ይሁን ሲባል ባንኮች ወደ ውህደት ሊሄዱ ችላሉ የሚል ግምት ማሳደሩ ነው፡፡ እንደ አቶ ኢየሱስ ወርቅ፣ ለአገራችን 10 እና 15 ባንክ በቂ ነው፡፡ ባንኮችም ጠንካራ ካፒታል እንዲኖራቸው ይዋሃዱ ሲባል፣ አሁን እየተቋቋሙ ያሉትም ሆነ ቀደም ብሎ ከተቋቋሙት ባንኮች ውስጥ ጥቂት የማይባሉ ብሔር ተኮር ስያሜ ያላቸው መሆኑ ለውህደት እንቅፋት ይሆናል የሚል አስተያየት እየተሰጠበት ነው፡፡ ከዚህ አንፃር አቶ ኢየሱስ ወርቅ ትክክል ነው ይላሉ፡፡ አሁን ብሔራዊ ባንክ የወሰደው ዕርምጃ በአምስት ዓመት 15 ቢሊዮን ብር በሦስት ዓመት 10 ቢሊዮን ብር ይሁን ብሎ ቢሆን ኖሮ ባንኮች በግድ ጥምረት ይፈጥሩ እንደነበር ያምናሉ፡፡

ምክንያቱም ጥምረት አድርገው አዲስ ስም በመያዝ ሊሠሩ ችላሉ፡፡ በአንድ ብሔር ስም የተቋቋመ ባንክ ከሌላ ብሔር ጋር እንዲቆራኝ ቢደረግ ይዋሃዳሉ፡፡ ግን ይህ ተግባራዊ ይሆን የነበረው ጠንከር ያለ የካፒታል መጠን ቢጠየቅ ነበር፡፡ በአምስትና በሰባት ዓመት 5 ቢሊዮን ብር አድርሱ የሚል መመርያ አውጥቶ ለማዋሃድ የሚመች አይሆንም፡፡

በባንኮቹ ጉዳት ላይ መንግሥት በፍፁም ተዋሃዱ ማለት የሌለበት መሆኑን በመጥቀስም፣ ባንኮቹ ራሳቸው የሚፈለግባቸውን ለማሟላት አዲስ ካፒታል ያሰባስባሉ ወይም ይዋሃዳሉ ብለዋል፡፡ ነገር ግን አሁን የተጠየቀው ካፒታል በጣም ዝቅተኛ ስለሆነ አሁንም የተበታተነ የባንክ ዘርፍ ለተወሰነ ጊዜ ሊቀጥል ይችላል የሚል ግምት አላቸው፡፡

እስካሁን ድረስ ሲካሄድ የነበረው ትርክት ሲያበረታታ የነበረው የዘር ፖለቲካ መሆኑ፣ በባንክ ዘርፉ ብቻ ሳይሆን፣ በአገር ደረጃ እንዲሰርፅ ሲሠራ በመቆየቱ እሱን ማላላት አለብን ይላሉ፡፡ ምንያቱም ተወዳዳሪነትና ፉክክሩ መሆን ያለበት የኢትዮጵያ ባንኮች ከሌሎች የኬንያ፣ የቱኒዝያ፣ የዑጋንዳ፣ የናይጄሪያና የሌሎች አገሮች ባንኮች እንጂ ደቡብ፣ አማራ ኦሮሞ እየተባለ አይደለም በማለት ባንኮች ሰብሰብ ብለው ተወዳዳሪ ባንክ መፍጠር እንዳለባቸው መክረዋል፡፡

ኬንያ ካሉ ባንኮች እንወዳደር ቢባል ምን ያህል እንጓዛለን፣ የእኛ በጣም ትንንሾች ናቸው የሚሉት አቶ ኢየሱስ ወርቅ፣ ለውጪው ውድድር መዘጋጀት አለብን ብለዋል፡፡ ይህ ብቻ አይደለም አገራችን ውስጥ ሁልጊዜ በውጭ ኢንቨስትመንት ተደግፈን መኖር እንደማይቻል በመረዳት፣ የራሳችን ጠንካራ ኢንቨስተሮች፣ ትልልቅ ገንዘብ የሚያበድሩ ተቋማት መፍጠር አለብን ብለዋል፡፡ በኢትዮጵያ አንድ የእርሻ ባንክ ያስፈልጋታል የሚሉት አቶ ኢየሱስ ወርቅ፣  አንድ ኢንቨስትመንት ባንክም ሊኖራት ይገባልና እንዲህ ያሉ የባንክ ዓይነቶች ላይም ትኩረት ይሰጥ ብለዋል፡፡ ይህ ሁሉ የሚሆነው ግን ባንኮች ጠንካራ ካፒታል ሲኖራቸው ነው፡፡

አቶ ኢየሱስ ወርቅ፣ አሁን የሚወጡ መመርያዎችም ነገን ተሻግረው መመልከት ሲችሉ ነውና ብሔራዊ ባንክ የባንክ ማቋቋሚያ ካፒታል መጠን ማሻሻል አለበት፡፡ ይህንን ለማድረግ ራሱ ነባራዊ ሁኔታው ይገፋዋል፡፡ የገንዘብ የመግዛት አቅም እየቀነሰ ሲሄድ፣ ባንክም መመርያውን ሊያሻሽል ይችላል፡፡ አሁን ባለው ሁኔታ ግን ባንክ ለማቋቋም አምስት ቢሊዮን ብር ያውም አምስትና ሰባት ዓመት ሰጥቶ አይሆንም፡፡ አምስት ቢሊዮን ብር ኢምንት ነው፣ መጨመር አለበት፡፡ ይህም ለባንኮችና ለአገር ጠቃሚ ነው፡፡ በተለይ እንደ አገር ጠንካራ ተወዳዳሪ ለመሆን የባንኮች ካፒታል መጠን ማደግ መሠረታዊ ነው፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች