Saturday, June 10, 2023

በአማራ ተወላጆች ላይ የሚፈጸሙ ጥቃቶችና መንግሥታዊ ክፍተቶች

- Advertisement -spot_img

በብዛት የተነበቡ

የኢትዮጵያ ፖለቲካ ትኩሳት በተለያዩ ጊዜያት ከፍና ዝቅ ሲል የቆየ ቢሆንም፣ ከመጋቢት 2010 ዓ.ም. በፊት የነበረው ከፍተኛ ውጥረት የረገበው ግን በወቅቱ ከኦሮሞ ሕዝቦች ዴሞክራሲያዊ ድርጅት (ኦሕዴድ) ወደ የኦሮሞ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (ኦዴፓ) የስም ለውጥ ያደረገው ድርጅት ሊቀመንበር የነበሩትና የአሁኑ ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር)፣ የኢትዮጵያ ሕዝቦች አብዮታዊ ዴሞክራሲያዊ ግንባር (ኢሕአዴግ) ሊቀመንበር ሆነው መመረጣቸውን ተከትሎ ነበር፡፡ በጊዜው የአማራ ክልልን በሚወክለው የአማራ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (አዴፓ) እና በኦዴፓ መካከል የነበረውና የኦሮማራ ጥምረት በሚል የሚታወቀው ትብብር፣ አገሪቱን ለሦስት ዓመታት ገደማ ሲንጣት ከከረመው ሕዝባዊ አመፅና ተቃውሞ በኋላ የለውጡ ፊታውራሪ በመባል ስማቸው ተደጋግሞ ሲጠራ በነበሩ ፖለቲከኞች አማካይነት ነበር ዓብይን (ዶ/ር) ያስመረጡት፡፡

ከዚህ በኋላ እሳቸው ጠቅላይ ሚኒስትር ከሆኑ የመጀመሪያው፣ የኢሕአዴግ ደግሞ የመጨረሻው 11ኛ ድርጅታዊ ጉባዔ በሐምሌ ወር 2011 ዓ.ም. በሐዋሳ ከተማ ሲካሄድ በጉባዔው ሪፖርት ላይ እንደተጠቀሰው፣ የድርጅቱን አባላትና አጋር ፓርቲዎችን አካትቶ አንድ ወጥ ፓርቲ ለመመሥረት የውህደት ጥናት በግንባሩ ምክር ቤት እንዲከናወንና አዲስ ርዕዮተ ዓለም እንዲፈጠር በተወሰነው መሠረት፣ በተለይም በኦዴፓና በአዴፓ መሪነት ኢሕአዴግ ሊዋሃድና ብልፅግና ፓርቲ ሊመሠረት ችሏል፡፡ ምንም እንኳን የኢሕአዴግ መዋሀድ ሙሉ ለሙሉ በተዋሀዱት ፓርቲዎች አባላት ዘንድ እኩል ተቀባይነት ያልነበረው ቢሆንም፣ እንደ ድርጅት በውህድ ፓርቲው ውስጥ ላለመሳተፍ ወስኖ ራሱን ያገለለው ሕዝባዊ ወያነ ሓርነት ትግራይ (ሕወሓት) ብቻ ነበር፡፡

ይሁንና የአዴፓና የኦዴፓ ትብብር የኦሮማራ ጥምረት ፕሮግራም ወጥቶለት ጣና ሐይቅ ላይ የተንሰራፋውን እምቦጭ ለመንቀል ከኦሮሚያ ክልል ወደ ባህር ዳር በርካታ ወጣቶች እንዲሄዱ በማድረግ ይፋ መውጣቱን፣ ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ (ዶ/ር) በቅርቡ ባሳተሙት የመደመር መንገድ መጽሐፋቸው ላይ በግልጽ አስፍረውታል፡፡

ሆኖም ኢሕአዴግ ከተዋሀደና ሕወሓት ከእነአብዮታዊ ዴሞክራሲ አስተሳሰቡ ከስብስቡ ተገንጥሎ ትግራይ ከከተተ በኋላ ብልፅግና ፓርቲ በውስጡ የሚያጣብቀው ሙጫ ማጣቱን በሚያሳብቅበት ሁኔታ፣ በድርጅቱ ምሥረታ ላይ ጉልህ ሚና የነበራቸውና የለውጡ ፊታውራሪና የቡድን መሪዎች የነበሩ አባላቱ ልዩነታቸውን አደባባይ ማውጣት ቀጠሉ፡፡

በዚህ ላይ በግልጽ ሊጠቀሱ የሚችሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ የኢሕአዴግ ሊቀመንበር ሆነው ሊመረጡ ያስቻላቸውን መንገድ የጠረጉላቸውና የኦሕዴድ/ኦዴፓ ሊቀመንበርነታቸውን የለቀቁላቸው አቶ ለማ መገርሳ፣ ስለፓርቲው መዋሀድና ስለመደመር ርዕዮተ ዓለም (ጠቅላይ ሚኒስትሩ ርዕዮተ ዓለም ነው ይሉታል በመጽሐፋቸው) ልዩነት ያላቸው መሆኑን በይፋ መናገራቸው ነበር፡፡ በተጨማሪም አንዳንድ የኦዴፓ አባላት ባላቸው ልዩነት ሳቢያ ፓርቲውን ለቅቀው ሊወጡ ችለዋል፡፡ በተጨማሪም ብልፅግና ፓርቲ ውስጥ በአማራ ክልልና በኦሮሚያ ክልል ወኪሎች መካከል ያለው ልዩነት መስፋቱንና ቅራኔዎች መኖራቸውም መሰማት ከጀመሩ ሰነባብተዋል፡፡

ይህ የፓርቲዎቹ ልዩነት ገንኖ አገራዊ በሆኑ የፀጥታና የሰላም ጉዳዮች ላይ የጋራ አቋም ይዘው መፍትሔ ማበጀት ላይ የሚታዩ ውስንነቶች ንፁኃንን ዋጋ እያስከፈሉም ይገኛሉ፡፡ ይባስ ብሎም በችግር ልየታና መፍትሔ ላይ መተባበር ይቅርና ጠላትና ወዳጅን መለየትና ጎራን ለይቶ መታገል ላይ አቋም መያዝ እንደተሳናቸው በተደጋጋሚ ማየት ተችሏል፡፡ ለዚህ ደግሞ ከምንጊዜውም በላይ ተደጋጋሚ ጥቃት በአማራው ላይ እየደረሰ ነው በሚል ምክንያት፣ በአማራ ክልል ሁሉም አካባቢዎች የተደረጉ ሰላማዊ ሠልፎች ሁነኛ ማሳያ ናቸው፡፡

በአጣዬ አካባቢ ከአሁን ቀደም በመጋቢት ወር 2013 ዓ.ም. በከባድ መሣሪያዎችና በተሽከርካሪዎች በመታጀብ የደረሱ ጥቃቶች እንደገና አንሰራርተው የበርካቶችን ሕይወት ቀጥፈው፣ አካል አጉድለውና ቤት ንብረት አውድመው አልፈዋል፡፡ ምንም እንኳን እንደማይደገሙ ማስተማመኛ ባይኖርም፡፡ ነገር ግን በፌዴራል መንግሥትና በአማራ ክልል፣ እንዲሁም በኦሮሚያ ክልል ባለሥልጣናት መካከል የችግሩ መነሻ ምክንያቶችን በመተንተን ረገድ ልዩነቶች መኖራቸው ዕሙን ነው፡፡

ከአጣዬ ጥቃት በኋላ ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ በፓርላማ ተገኝተው ከአባላት ለቀረቡላቸው ጥያቄዎች በሰጡት ምላሽ፣ ጉዳዩን የታጠቁ አካላት ተደራጅተው የሚፈጽሙት እንደሆነ ሳይሆን የአካባቢው ማኅበረሰብ፣ በተለይም ወሰንተኛው አማራና ኦሮሞ እየተጋጨ እንዳለ አስመስለው ማቅረባቸው ትችት አስነስቷል፡፡

ለአብነትም የጠቅላይ ሚኒስትሩን አቀራረብ በመተቸት አስተያየታቸውን ለሪፖርተር የጻፉት የአማራ ክልል ፕሬዚዳንት የሕግ አማካሪ አቶ መርሐ ፅድቅ መኰንን ዓባይነህ፣ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ‹‹ረብ የለሽ ካድሬዎቻቸውን አምርረው ከመገሰጽና ከመካከላቸው ዕልቂቱን ሳያነሳሱ እንዳልቀሩ በሚገባ የተጠረጠሩትን የኦሮሞ ጽንፈኞች በኃላፊነት ከመጠየቅ ታቅበው፣ አማራና ኦሮሞ በማኅበረሰብ ደረጃ የተጋጨና ቀድሞውኑም ተፃራሪ ጥቅሞች ያሉት ይመስል፣ እንደ እሳቸው አነጋገር ደጋጎቹ የሰሜን ሸዋ አማሮች አብረዋቸው በፍቅርና በወንድማማችነት ከኖሩት ከወሎ ኦሮሞዎች ጋር ጎራ ለይተው መገዳደላቸውን እንዲያቆሙ ሊመክሩ ሲዳዳቸው በአንክሮ አስተውለናል፤›› ሲሉ የችግር መነሻ ልየታውን ተችተዋል፡፡

ሆኖም ከዚህ ንግግርና አገር አቀፍ ትኩረት በኋላ በአጣዬ፣ ማጀቴ፣ አንጾኪያና ሸዋሮቢት አካባቢዎች ዳግም ጥቃት ተሰንዝሮ ንፁኃንን ለሞት፣ ያከማቹትን የታጨደ እህልና ቤት ንብረት ለእሳት፣ ሴቶችና ሕፃናትን ለስደት የዳረገው፡፡

ነገር ግን በተደጋጋሚ በአገሪቱ በንፁኃን ላይ የሚሰነዘሩ ጥቃቶችን ለማስቆም ፍላጎት የለውም ሲሉ የሚያስተጋቡና በተለይም በተለያዩ አካባቢዎች በአማራ ብሔር ላይ ለይቶ የሚፈጸመውን ጥቃት ሆን ተብሎ በመንግሥታዊ ሥምሪት የሚፈጸም እንደሆነ እንደሚያምኑ የሚገልጹም አልጠፉም፡፡ ለአብነትም የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን) ሚያዚያ 11 ቀን 2013 ዓ.ም. ባወጣው መግለጫ የፌዴራሉም ሆነ የአማራ ክልል ምክር ቤት የሚደርሱ ጥቃቶችን ለማስቆም ምንም ዓይነት ፍላጎት እያሳዩ እንዳልሆነ፣ ‹‹በእርግጥም ችግሩ መንግሥታዊ ዘመቻና ሥምሪት የሚሰጥበት መሆኑ በተጨባጭ የታወቀ ሀቅ›› ነው በማለት ይከስሳል፡፡ ስለዚህም፣ ‹‹በአጠቃላይ በአማራ ሕዝብ ላይ ባልተቋረጠ መልኩ የሚፈጸሙት መንግሥት መራሽ የዘር ፍጅቶች ‹በገለልተኛ ኮሚሽን› በጥልቀት ተጣርተው በቀጥታ በጥቃት ውስጥ የተሳተፉ፣ ኃላፊነታቸውን ያልተወጡ፣ መንግሥታዊ መዋቅርን ለጥቃት ማስፈጸሚያነት ያዋሉ፣ ያስተባበሩና የተመሳጠሩት አካላት ማንነት ለሕዝብ በይፋ እንዲገለጽና ተጠያቂ እንዲሆኑ፤›› ሲል ጥሪ አቅርቧል፡፡

አብን ከዚህ አንድ ቀን አስቀድሞ ባወጣው መግለጫ፣ በአማራ ላይ ‹‹መንግሥታዊ ሽብር›› በተደራጀ መንገድ እየተፈጸመ ነው ሲል ከሷል፡፡

ነገር ግን በአጣዬና በተለያዩ አካባቢዎች እየተፈጸሙ ያሉት ጥቃቶች ኦነግ ሸኔ ነው ሲሉ የመጋቢት 6 ቀን 2013 ዓ.ም. ጥቃቶችን ተከትሎ ለሪፖርተር የተናገሩት የአማራ ክልል የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ ግዛቸው ሙሉነህ፣ የመጀመርያው ጥቃት ሲከሽፍባቸው በእልህ በተመለሱ የኦነግ ሸኔ ታጣቂዎች ከፍተኛ ጉዳት መድረሱን አክለዋል፡፡ ይሁንና ኦነግ ሸኔ የሚባል ሕጋዊም ሆነ የተለምዶ መጠሪያው ያደረገ ቡድን ባለመኖሩ ይኼ ማሳበቢያ ለበርካቶች የሚዋጥ አልሆነም፡፡

እነዚህን ጥቃቶች አስመልክቶ ግን የአማራና የኦሮሚያ ክልል ባለሥልጣናት የሕዝባቸውን ደኅንነት ለመጠበቅ ሲባል በትብብር ለመሥራት ያስችለናል ያሉትን ስብሰባ፣ በአማራ ክልል ፕሬዚዳንት አቶ አገኘሁ ተሻገርና በኦሮሚያ ክልል ፕሬዚዳንት አቶ ሽመልስ አብዲሳ ተሳታፊነት ያከናወኑ ቢሆንም፣ የተደረሰበት ውሳኔ ይኑር አይኑር አልታወቀም፡፡

እነዚህን ጥቃቶች መነሻ በማድረግም በአማራ ክልል የተለያዩ አካባቢዎች ሰፊ የተቃውሞ ሠልፎች የተደረጉ ሲሆን፣ በተለያዩ አካባቢዎችም የብልፅግና ፓርቲ የምርጫ ባነሮችና የተለያዩ ምልክቶች ጥቃት ደርሶባቸው መቀዳደዳቸውን በማኅበራዊ የትስስር ገፆች ሲዘዋወሩ የነበሩ ምሥሎች አሳይተዋል፡፡ በእነዚህ ሠልፎችም፣ ‹የአማራ ክልል አመራሮች አማራን አይወክሉም፣ በአማራዎች ላይ የሚፈጸም ግድያ ይቁም፣ አትንኩን ስትነኩን እንበዛለን፣ ተላላኪዎች ልብ ግዙ፣ ሕፃናትን መግደልና ከተማ ማፍረስ ጀግንነት አይደለም፤›› የሚሉ መፈክሮች ተደምጠዋል፡፡

እነዚህን ሠልፎች ተከትሎ ቅዳሜ ሚያዝያ 16 ቀን 2013 ዓ.ም. የብሔራዊ ደኅንነት ምክር ቤት ባወጣው መግለጫ እንዳስታወቀው፣ ‹‹በየአቅጣጫው የምናየው የወገኖቻችን አሰቃቂ ግድያ፣ ማፈናቀል፣ ቤትና ንብረት ማውደም፣ ነውጥና ሸፍጥ ሁሉ በአገር ውስጥ ብቻ የተመረተ አይደለም፡፡ አብዛኛው ጥፋት በውጭ ተመርቶ በአገር ውስጥ የሚገጣጠም ጥፋት ነው፡፡ ግጭቱንና ጥፋቱን ከውጭ አስመጥተው በአገር ውስጥ የሚገጣጥሙት  የእፉኝት ልጆች ናቸው፡፡ በዚህ ዓመት መጀመርያ የእፍኝቶችን ዋና መፈልፈያ አፍርሰነዋል፡፡ ከዚህ በፊት ፈልፍሎ እዚህና እዚያ የጣላቸው ግልገሎቹ ግን አሁንም ይቀራሉ፡፡ የትኛውንም ዓይነት የብሔርና የእምነት ስም ቢይዙ፣ ከየትኛውም የውጭ ኃይል የሚረዱትን ገንዘብና መሣሪያ ቢጨብጡ ኢትዮጵያን ይፈትኗት ይሆናል እንጂ አያሸንፏትም፤›› ሲል ማንነታቸው ያልተገለጸና ስም አልባ ጭራቆች አድርጎ የፈረጃቸውን ኃይሎች አውግዟል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ (ዶ/ር) ከዚህ መግለጫ በነጋታው ባወጡት መግለጫ፣ ‹‹ምርጫው የተሳካ ሆኖ ከተከናወነ ሕዝቦች ወደ ጎዳና መውጣት ሳያስፈልጋቸው በተወካዮቻቸው አማካይነት ድምፃቸው ስለሚሰማላቸው፣ ዜጎቻቸው ሰፊ ጊዜያቸውን በሌሎች ኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ ጉዳዮች ላይ አውለው፣ ራሳቸውንና አገራቸውን ለማሳደግ ይጠቀሙበታል፤›› ብለዋል፡፡

ሆኖም ችግሩ ይህ ነውና ለመፍታት ቆርጠናል ከማለትና ዕቅዳቸውን በግልጽ ከማሳወቅ፣ እንዲሁም ለተጎጂዎች ሐዘናቸውን ገልጸው ድጋፍ ከማድረግ ይልቅ ለምን ጎዳና ተወጣ የሚል ግሳፄ ማቅረብ ቀንቷቸዋል የሚሉ ተቺዎች አሉ፡፡ የጠቅላይ ሚኒስትሩ መግለጫ እንደሚያትተውም፣ ‹‹መቀመጫቸውን አሜሪካና አውሮፓ ያደረጉ፣ በሳይበርና በሜንስትሪም ሚሪያዎች ታግዘው ሲከናወኑ የነበሩ የአክቲቪዝም እንቅስቃሴዎች በአገር ውስጥ ካሉ የተቃውሞ ኃይሎች ጋር በመጣመር ዜጎች ድምፃቸውን በየጎዳናው እንዲያሰሙ በመገፋፋታቸው፣ ለብዙዎች ሕይወት መቀጠፍ ምክንያት ሆኗል፤›› ብለዋል ጠቅላይ ሚኒስትሩ፡፡

ይህም እንደሚያሳየው ጠቅላይ ሚኒስትሩ የችግሩን ምንጭ ከመጋፈጥ ይልቅ፣ በሩቅ ያለውን የማይጨበጥ ጠላት ተጠያቂ ማድረግን መምረጣቸው እንደሆነ የሚተቹ ድምፆች ተደምጠዋል፡፡

በተጨማሪም እሳቸው በፓርላማ ለሚቀርቡላቸው ጥያቄዎች አግባብ ያለውን ምላሽ መስጠት ሳይገዳቸውና ፓርላማውንም ‹‹ይኼንን ልትጠይቁኝ አትችሉም›› እስከ ማለት የደረሰ ማሸማቀቅ እያደረሱበት፣ ይኼ እሳቸው የሚሉት ጥያቄዎችን ‹‹ከጎዳና ወደ ፓርላማ›› ማምጣት የሚለው ተነሳሽነት ለምን ይታመናል ሲሉ የሚያጠይቁ አልታጡም፡፡ ሕዝብ የመረጠው ወኪል ጥያቄዎቹን ሙሉ ለሙሉ በፓርላማ አንስቶለት ፀጥ ረጭ ብሎ ወደ ሥራ ብቻ እንዲገባ ያስችለዋል ወይ የሚል ጥያቄም ማስነሳቱ አልቀረም፡፡ ምክንያቱም የተሻለ የዴሞክራሲ ሥርዓት አላቸው በሚባሉ የምዕራቡ አገሮች ሳይቀር፣ ተወካዮቻቸው ጥያቄዎቻቸውን በአግባቡ ማስተጋባት ስላልቻሉ አደባባይ መውጣት አዲስ ክስተት አይደለም በማለት የሚሞግቱ አሉ፡፡

ይኼ የችግሮችና የደኅንነት ሥጋቶች ትንታኔ ጉድለት ለአገራዊ ሰላምና መረጋጋት ከፍተኛ እንቅፋት ሊሆን የሚችል እንደሆነም በርካቶች ይስማማሉ፡፡ በዚህ መካከል የጠቅላይ ሚኒስትሩንና የአስተዳደራቸው ሹማምንቶች ትኩረት የሚያደርጉባቸው ብልጭልጭ ነገሮች ዕውን እነዚህ ሰዎች አገሪቱ ያለችበት ችግር ስለመረዳታቸው ጥያቄ የሚያስነሳ መሆኑ እንዳለ ሆኖ፣ ችግሩን እያወቁና የችግሩን መጠን እየተረዱ ሆን ብለው ትኩረታቸውን ማድረግ በመረጡበት ጉዳይ ላይ እያደረጉ ከሆነ ደግሞ ለአገሪቱ ይገዳቸዋል ወይ የሚል ጥያቄ ያጭራሉ ሲሉም የሚናገሩ አሉ፡፡

spot_img
- Advertisement -

ትኩስ ጽሑፎች

ተዛማጅ ጽሑፎች

- Advertisement -
- Advertisement -