- ምናለበት ብትዘጉት ይህን ቴሌቪዥን?
- ምነው?
- አትሰማም እንዴ መንግሥታችሁ የሚለውን? ዘወትር ቁርጠኛ ነኝ፣ ቁርጠኛ ነኝ ይላል፣ የኑሮ ውድነቱ ግን ሰማይ እየነካ ነው።
- በዚህ ጉዳይ ላይ እንኳን ቁርጠኝነቱ አለ… እየተረባረብንበት ነው።
- ቴሌቪዥኑ ላይ ነው?
- ምኑ?
- የምትረባረቡት?
- እየቀለድኩ አይደለም፣ የኑሮ ውድነቱን ለማረጋጋት ከፍተኛ ርብርብ እያደረግን ነው። ለመጪው በዓልም ስንዴና ዘይት ከውጭ እየገባ ነው።
- የሚገርመኝ እኮ ይኼ ጉዳይ ነው፡፡
- የቱ?
- ለበዓል የምትረባረቡት ነገር፣ ቆይ ግን ከበዓሉ በኋላስ እንደተለመደው የተበላሸ ስንዴ ልታስገቡ ነው?
- የምን የተበላሸ ስንዴ?
- አልሰማህም እንዴ ዜናው በሬዲዮ ተላለፈ እኮ?
- የትኛው ሬድዮ ነው ይህንን ያስተለለፈው? እንዳይገለጽ ተብሎ ነበር እኮ?
- እንዳይገለጽ ነው እንዲደበቅ?
- ለምን እንደብቃለን? መፍትሔ እስኪሰጠው ድረስ ሕዝብ እንዳይደናገር በማሰብ ነው።
- ከነቀዘ ነቀዟል ማለት እንጂ ሌላ ምን መፍትሔ አለው?
- አለው እንጂ፣ እሱ ላይ እየተወያየን ነበር።
- ምንድነው የምትወያዩት?
- የነቀዘው ስንዴ መግባት ስለሌለበት አንድ አማራጭ ላይ እየተወያየን ነበር።
- ምን ዓይነት አማራጭ?
- ስንዴው ተፈጭቶ ይግባ የሚል ጥሩ ሐሳብ ቀርቦ ነበር ግን…
- ግን ምን?
- አቅም ያለው ወፍጮ ቤት ማግኘት አልተቻለም፣ ባይሆን መፍትሔ የሚፈልግ ኮሚቴ ተቋቁሞ በቁርጠኝነት እየሠራ በመሆኑ በቅርቡ ውሳኔ ያገኛል።
- ሆሆ… ኮሚቴው የሰጠው መፍትሔ ይሻላል።
- ወሰነ እንዴ?
- ኮሚቴውማ ወሰነ፡፡
- ምን ወሰነ?
- ወደ ባህር እንዲጣል ወሰነ።
- ምን? ከየት ሰማሽ አንቺ?
- ሬዲዮ አወራው፣ እኛም ቁርጠኝታችሁን አየን።
- ለበዓሉ የሚደርስ ሌላ ስንዴ እየተጓጓዘ ነው፣ ለእያንዳንዱ ነዋሪ የሚበቃ ዘይትም ወደ አገር ውስጥ ገብቷል፣ አልሰማሽም?
- እሱ እንኳን አይነቅዝም።
- ምን አልሽ?
- እሱንም ባለሀብቱ ተቀራምቶ እንዳይጨርሰው ብቻ፡፡
- በጭራሽ አይሆንም፣ ለዚህ ጥሩ መፍትሔ ተበጅቶለታል።
- የተቸገርነው መቼ በችግሩ ብቻ ሆነና?
- ሌላ በምንድነው?
- በመፍትሔውም፡፡
- ጀመረሽ ደግሞ መቧለት… ዘይቱ ያለ ችግር ይከፋፈላል ስልሽ እመኚኝ፣ መፍትሔ ተቀምጦለታል።
- ምን ዓይነት መፍትሔ ብታስቀምጡ ነው እንዲህ እርግጠኛ የሆንከው?
- ነዋሪው የቀበሌ መታወቂያውን እያሳየ ብቻ ነው ዘይት ማግኘት የሚችለው። አንድ ነዋሪ በድጋሚ እንዳይሸምት ደግሞ መለያ ዘዴ አስቀምጠናል።
- ምን ዓይነት መለያ?
- አንድ ግለሰብ ዘይቱን ሲገዛ መታወቂያው በወረቀት መብሻ እየተበሳ ስለሚሰጠው ደግሞ ቢመጣ በዚያ ይለያል።
- ሃሃሃሃ….
- የምን ማሽካካት ነው? አሁን ያስቃል ይኼ?
- ከስንት ዓመት በፊት እንዲሁ መታወቂያ እየተበሳ ዘይት ሲከፋፈል አንድ እናት ተናገሩ የተባለው ፌዝ ትዝ ብሎኝ ነው።
- እሳቸው ምን ብለው ነበር?
- ለዘይት መታወቂያ ከበሳችሁ፣ ቅቤ ብታመጡማ ጆሯችንን ነው የምትበሱት፡፡
- አፊዙ እንጂ እናንተ ምን አለባችሁ?
- ወዳጄ ሲባል አልሰማህም እንዴ?
- ምን ሲባል?
- ፌዝን በፌዝ!
- አንቺ ገና ብዙ ታወሪያለሽ፣ በይ መተኛቴ ነው!
[ክቡር ሚኒስትሩ በጠዋት ወደ ቢሮ ለመግባት ቢያቅዱም የጠዋቱ ቅዝቃዜና ዝናብ ተጭኗቸው ከመኝታቸው አልተነሱም፣ ባለቤታቸው በሚኒስትሩ ማርፈድ ግራ ተጋብተው ወደ መኝታ ክፍሉ ገቡ]
- ምን ሆነሀል ሰዓቱ እኮ ረፍዷል… ልጆቹም እንድታደርሳቸው እየጠበቁህ ነው፡፡
- የሚጥለው ዝናብ እኮ ተጫጭኖኝ ነው፡፡
- ማን ነካኩ አላችሁ?
- ምኑን?
- ደመናውን?
- እባክሽ አትቀልጂ፣ ይልቅ ዩኒፎርሙን አሰናጂ፡፡
- ለብሰው ተሰናድተው እየጠበቁህ ነው አልኩህ እኮ፣ አልሰማኸኝም?
- ሰምቻለሁ፣ ዩኒፎርሙን አሰናጂ ነው ያልኩሽ።
- ለብሰው፣ ቁርሳቸውን በልተው እየጠበቁህ ነው እያልኩህ?
- የእኔን ዩኒፎርም ነው ያልኩሽ?
- [ፈገግ ብለው]…ውይ… በሞትኩት . . .
- በጠዋቱ ማፌዝ ልትጀምሪ ነው አይደል?
- ይህ ነገር በቃ ተጀመረ ማለት ነው?
- አለብስም ብዬ ነበር ግን አልሆነም።
- ለምን አልሆነም?
- ከላይ የወረደ አስገዳጅ ትዕዛዝ ነው።
- ሁላችሁም እንድትለብሱ ተባለ?
- ሁላችንም አልቀረልንም።
- ዩኒፎርም ብቻ ነው ወይስ ያዙ ትባሉ ይሆን?
- ምን?
- የምሳ ዕቃ?
- አዎ እንይዛለን… ደስ ይበልሽ!