Thursday, May 23, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

ማኅበራዊየወባ በሽታ ሥርጭትን የመከላከልና የማጥፋት በጎ ጅምሮች

የወባ በሽታ ሥርጭትን የመከላከልና የማጥፋት በጎ ጅምሮች

ቀን:

አንዳንድ የኅብረተሰብ ክፍሎች ‹‹ወባ አለ ወይ? በራሱስ ችግር ነው ወይ?››  ሲሉ ይደመጣሉ፡፡ እኩሉ ደግሞ ወባ መኖሩን ጭራሹኑ ይክዳል፡፡ የበሽታውን አቅም ያላገናዘቡ ማኅበረሰቦችም ወባን መከላከልና መቆጣጠር እንዲሁም በዚሁ በሽታ የተጠቃውን ሰው ማዳን ይቻላል ወይ? በሚል ብዥታ ውስጥ ገብው ለጭንቀት ሲዳረጉ ማየትም እየተለመደ መጥቷል፡፡

እነዚህን የመሰሉ ጉራማይሌ ጥያቄዎች ሊንፀባረቁ የቻሉት በሁለት ምክንያቶች መሆኑን ጥናቶች ይጠቁማሉ፡፡ አንደኛው ምክንያት በወባ ላይ ትኩረት ያደረገ ማስረጃ ዕጦት ወይም ለኅብረተሰቡ ተደራሽ አለማድረግ ሲሆን፣ በዚህም በርካታ ወገኖችች ለህልፈተ ሕይወት ተዳርገዋል፡፡

ሌላው ምክንያት ደግሞ ኅብረተሰቡ በቀላሉ ሊረዳውና ሊገነዘበው በሚችል መልኩ የተዘጋጀ የቅስቀሳና ግንዛቤ የማስጨበጫ ሥራ ባለመከናወኑ ነው፡፡

- Advertisement -

የጤና ልማትና ፀረ ወባ ማኅበር ከፍ ብሎ ለተንፀባረቁት ጥያቄዎች ምላሽ የሚሆኑ፣ ተግዳሮቶቹንም የመፍታት አቅም አላቸው ተብሎ እምነት የተጣለባቸው ሁለት ፕሮጀክቶችን ቀርፆ ወደ ሥራ ከገባ ውሎ አድሯል፡፡ ከፕሮጀክቶቹም መካከል የመጀመርያው የወባ መከላከልና መቆጣጠርን አስመልክቶ በዜማ፣ በግጥምና በውዝዋዜ የታጀበ ቪዲዮ ክሊፕ ማዘጋጀት ሲሆን፣ ሁለተኛው ደግሞ ወባ ከመከሰቱ አስቀድሞ ለመተንበይ የሚረዳ የዕውቀት ሽግግር ማካሄድ ነው፡፡

የማኅበሩ ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ አክሊሉ ጌትነት የኋላ፣ በወባ ላይ ብቻ ያተኮረውና ሚያዝያ 20 ቀን 2013 ዓ.ም. ለአጋር አካላት በማስተዋወቅ በይፋ የተበሰረው ይህ የቪዲዮ ክሊፕ፣ በአማራ ክልል ለወባ በይበልጥ በተጋለጡ የስድስት ወረዳዎች 141 ቀበሌዎች ውስጥ የሚኖረውንና ከአንድ ሚሊዮን በላይ የሆነውን የኅብረተሰብ ክፍል በወባ መከላከልና መቆጣጠር ላይ ያለውን ግንዛቤ ከፍ ለማድረግ እንዲያስችል ታስቦ የተዘጋጀ ነው፡፡

ይህ ዓይነቱም ግንዛቤ የማሳደግ ሥራ የሚያከናውነው ለየትምህርት ቤቱ ተማሪዎች፣ በየእምነት ተቋማቱ ለሚገኙ ምዕመናን፣ በገበያ ሥፍራዎችና በየሥፍራው ለሚሰባሰቡትና በአጠቃላይ ሕዝብ በብዛት በሚያዘወትርባቸው አካባቢዎች ቪዲዮ ካሴቱን በማሳየት ነው፡፡

ይህም እንቅስቃሴ በተጠቀሰው አካባቢ ለተወሰነ ጊዜ ብቻ እንደሚቆይ ፕሮጀክቱ የተሰጠውን የመቆያ ጊዜ ጨርሶ ሲወጣ ችግሩ ተመልሶ እንዳይመጣ ወይም ወባ ዳግም እንዳያገረሽ የአካባቢው ማኅበረሰብና መዋቅሮች አቅማቸውን በማጎልበት የቅስቀሳውንና ግንዛቤውን የማሳደግ ሥራ አጠናክረው እንዲቀጥሉ የማድረግ ሥራ ተጠናክሮ እንደሚቀጥልም ተገልጿል፡፡

ከምክትል ዋና ዳይሬክተሩ ማብራሪያ ለመረዳት እንደተቻለው፣ ከእንቅስቃሴው ባሻገር ወባ ከመከሰቱ ከስምንት ሳምንታት በፊት ለመተንበይ የሚያስችል የዕውቀት ሽግግር ሥራ፣ ከጤና ሚኒስቴርና ከሌሎችም የጤና ተቋማት ጋር በሚከናወን ላይ ነው፡፡ የዕውቀት ሽግግሩ እየተከናወነ ያለው በአሜሪካ ከሚገኘው ከሳውዝ ዳኮታ ስቴት ዩኒቨርሲቲ ጋር በመተጋገዝ ነው፡፡

በቅድመ ትንበያ ላይ ያተኮረው ይህ የዕውቀት ሽግግር ሥራ ለጊዜው አማራ ክልል እጅግ ወባማ የሆኑ 46 ወረዳዎችን ያቀፈ ሲሆን፣ ይህንንም ከአማራ ክልል ጤና ቢሮና ከባህር ዳር ዩኒቨርሲቲ ጋር በመተባበር በተሳካ ሁኔታ ማከናወኑን የገለጹት ዳይሬክተሩ፣ ወደፊትም በብሔራዊ ደረጃ ወባን ለማጥፋት ለተያዘው ስትራቴጂክ ዕቅድ እንደ ግብዓት እንደሚያገለግል ጠቁመዋል፡፡

እንደ አቶ አክሊሉ አባባል፣ ባለፉት ሃያ ዓመታት በዓለም ደረጃ ወባን ለማጥፋት በተካሄደው እንቅስቃሴ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎችን ከህልፈተ ሕይወት ለመታደግ ቢቻልም ዓለም በየዓመቱ በአማካይ የ655 ሺሕ ሰዎችን ሕይወት አጥታለች፡፡ ከአምስት ዓመት በታች የሆኑ ሕፃናትም በዚሁ በሽታ እየተጠቁ፣ ከዚህም ሌላ ከአምስት ዓመት በታች የሆኑ ጨቅላ ሕፃናትንም በየ60 ሰከንድ እየተቀጠፉ ነው፡፡

ወባ በጤናና በሕይወት ላይ ብቻ ሳይሆን በማኅበራዊ ሕይወትና በኢኮኖሚ ላይም ተፅዕኖ እንደሚያሳድር፣ በዚህም የተነሳ ከሰሃራ በታች የሚገኙ አገሮችን ኢኮኖሚ በየዓመቱ 1.3 በመቶ ወደ ኋላ እንደሚጎትትም አመልክተዋል፡፡ በአጠቃላይ በአፍሪካ ደረጃ በየዓመቱ 12 ቢሊዮን ዶላር እንደሚያወጣ ከአጠቃላይ ዓመታዊ የምርት መጠናቸውም (ጂዲፒ) እስከ ስድስት በመቶ የሚደርስ ጉዳት እንደሚያስከትልም ተናግረዋል፡፡

በቤተሰብ ደረጃ የሚያስከትለው ጉዳት ሲገመገም ደግሞ በቤት ውስጥ ታሞና ተኝቶ መዋልን ከትምህርትና ከምርት ማስተጓጎልን፣ የወባ ታማሚን ለመንከባከብ ሲባል ከ25 በመቶ በላይ የሆነውን የቤተሰብ ገቢ መውሰዱንና ሌሎች ተያያዥ የሆኑ መሰል ችግሮችን ማስከተሉ የማይቀር መሆኑንም አብራርተዋል፡፡

ኢትዮጵያ ውስጥ 75 ከመቶ የሚሆነው አካባቢ ለወባ ተጋላጭ ሲሆን፣ ከአጠቃላዩ ሕዝብ መካከል 80 በመቶ የሚሆነውንና በገጠሩ አካባቢ የሚኖረውን ሕዝብ ለማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ተፅዕኖ የዳረገው መሆኑን አቶ አክሊሉ ገልጸው፣ ጤና ሚኒስቴር በ2017 ዓ.ም. በወጣ ምክንያት የሚከሰተውን ሕመምና ሞት በግማሽ ለመቀነስ እንዲረዳው፣ በ2022 ዓ.ም. ወደ ዜሮ ለማውረድም የዓለም ጤና ድርጅት ማዕቀፍን ተከትሎ የተቀረፀውን ይህን ስትራቴጂ ለማሳካት ከሚንቀሳቀሱት የጤና ተቋማት መካከል አንደኛው የጤና ልማትና ፀረ ወባ ማኅበር መሆኑን ከምክትል ዋና ዳይሬክተሩ ማብራሪያ ለመረዳት ተችሏል፡፡

እንደ ዓለም ጤና ድርጅት ሪፖርት ወባ በደቂቃዎች ውስጥ አንድ ሕፃን ለሕልፈተ ሕይወት ይዳርጋል፡፡ ባለፉት ሁለት አሠርታት 11 አገሮች ከወባ ነፃ መሆናቸው ተረጋግጧል፡፡

የጤና ልማትና ፀረ ወባ ማኅበር የወባ ወረርሽኝ በወገን ላይ እያስከተለ ያለውን ጉዳት ለመከላከል ‹‹የአቅማችንን እናድርግ›› በሚሉ በጎ ፈቃደኛ ኢትዮጵያውያን ቀስቃሽነት ነሐሴ 17 ቀን 1990 ዓ.ም. መቋቋሙ ይታወቃል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የማዳበሪያ አቅርቦትና ውጣ ውረዱ

በቅፅል ስሙ “The Father of Chemical Warfare” እየተባለ የሚጠራው...

የኢትዮጵያ ልማት ባንክ የትርፍ ምጣኔውን ከ70 በመቶ በላይ አሳደገ

ከሁለቱ መንግሥታዊ ባንኮች መካከል አንዱ የሆነው የኢትዮጵያ ልማት ባንክ...