የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የጸሎተ ሐሙስና የረመዳን ኢፍጥር መርሐ ግብርን ሚያዝያ 21 ቀን 2013 ዓ.ም. ምሽት ምክትል ከንቲባ አዳነች አበቤና ታዳሚዎች በተገኙበት በስካይላይት ሆቴል ተካሂዷል፡፡ በመርሐ ግብሩ ላይ የተገኙት ብፁዕ አቡነ ፊሊጶስ የቅድስት ሥላሴ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንትና የደቡብ ኦሞ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ባደረጉት ንግግር፣ የጸሎተ ሐሙስ ዕለት የትህትና ዕለት ነው፣ የፍቅርና የአንድነት ዕለት፣ እንዲሁም ከፍ ያሉ ዝቅ ያሉበት፣ ባለሥልጣን የሆኑ በሥራቸው ያሉትን የባረኩበትና የቀደሱበት ያከበሩበት ዕለት ነው ብለዋል፡፡ ‹‹አስገራሚና አስደናቂ ለሆነው ለዚህ ዕለት እንኳን አደረሰን›› ደግሞ ያሉት የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት ፕሬዚዳንት ተቀዳሚ ሙፍቲ ሐጂ ዑመር እድሪስ በበኩላቸው፣ ‹‹ልንጣላ አይገባንም፣ ልንቃረን አይገባንም፣ አንዱ አንዱን ሊያወግዝ አይገባም፣ ልናፈናቅል አይገባም፣ ንፁህ የሆኑ ሰዎችን ደም ልናፈስ አይገባም፤ በሰላም ልንኖር ይገባናል፤›› ሲሉ መክረዋል፡፡
ፎቶ ናሆም ተስፋዬ