በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች እያጋጠሙ ያሉ ግጭቶች እንዲቆሙ፣ ገዥው ፓርቲና ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች በኃላፊነትና በሰከነ መንገድ በመወያየት በጋራ መሥራት አለባቸው ሲል፣ የኢትዮጵያ ሠራተኞች ማኅበራት ኮንፌዴሬሽን (ኢሠማኮ) አስታወቀ፡፡
ኢሠማኮ የዓለም ሠራተኞች ቀን (ሜይ ዴይ) አስመልክቶ ባወጣው መግለጫ፣ ግጭቶች እንዲቆሙ ሁሉም ባለድርሻ አካላት በጋራ ይሥሩ የሚል ጥሪ አስተላልፏል፡፡
‹‹ተባብሮና ተከባብሮ አንድ ላይ ከመቆም ይልቅ ወንድም ወንድሙን ሲገድል መስማትና ማየት፣ ውርደት እንጂ ዕድገትና ሥልጣኔ አይደለም፤›› ያለው ኢሠማኮ፣ ጤናማ የሆነ ሰው ማለት አንዱ ለሌላው በመከራ ጊዜ ከጎኑ ሲቆምና ከችግር ሲያወጣው ነው ብሏል፡፡
‹‹ማንም ሰው ከማንም በታች ወይም ከማንም በላይ አይደለም፡፡ እግዚአብሔር ሁሉንም የፈጠረው እኩል ነው፡፡ ማንም ሕዝብ ከማንም ሕዝብ የበላይ ወይም የበታች አይደለም፡፡ ሁሉም ሕዝቦች እኩል ናቸው፡፡ ይህንን ከልብ አምነንና ተቀብለን የጋራ መፍትሔ መፈለግ አለብን፤›› በማለት ወቅታዊውን የአገሪቱ ሁኔታ መፍትሔ ይሆናል ያለውን ሐሳብ ሰንዝሯል፡፡
‹‹እኛ ሠራተኞች ወጥተን የምንገባውና ሠርተን መኖር የምንችለው ሰላም ሲኖር ብቻ መሆኑን በመገንዘብ፣ ከላይ እስከ ታች በተደራጀ መንገድ የአገር ሰላም እንዲጠበቅ መላው ሠራተኛ የበኩሉን አስተዋጽኦ ያድርግ፡፡ የሰላም ጉዳይ የመንግሥትና የአሠሪው ወይም የሌላ አካል ጉዳይ ብቻ ሳይሆን እንደ ኢሠማኮ የበኩላችንን እናደርጋለን፤›› ብሏል፡፡
የሠራተኞችን መብትና ጥቅም በተመለከተ በመግለጫው እንደጠቀሰው፣ የሠራተኛው መብትና ጥቅሞች በአገሪቱ ሕግ መሠረት በአብዛኞቹ የግል ድርጅቶች በተለይም በኢንዱስትሪ ፓርኮች እየተከበረ አይደለም፡፡ በተመሳሳይ በጥቂት የመንግሥት የልማት ድርጅቶችም ሳይቀር የመደራጀትና የመደራደር መብት ያልተከበረ ስለሆነ፣ የመንግሥት አስፈጻሚ አካላት ኢትዮጵያ የፈረመቻቸውን ስምምነቶች ሕገ መንግሥቱንና የአሠሪና ሠራተኛ ጉዳይ አዋጁን ያስከብሩ ሲል ጠይቋል፡፡
የኑሮ ውድነትን በተመለከተ መግለጫው መሆን ይገባዋል ያለውን አቋሙን ያንፀባረቀው ኢሠማኮ፣ ‹‹በመላው ዓለም ሆነ በአገራችን በተከሰተው የኮቪድ-19 ወረርሽኝ ምክንያት ኢኮኖሚው የተቀዛቀዘ በመሆኑ፣ የዋጋ ንረት ተፈጥሯል፡፡ በመሆኑም በአንዳንድ ስግብግብ ነጋዴዎች ምክንያት ሠራተኛው በሚያገኘው እጅግ በጣም ዝቅተኛ ደመወዝ የዕለት ጉርሱን መሸፈን ስላልቻለ፣ መንግሥት የጀመረው ቁጥጥር ጠበቅ እንዲልና ተከታታይ ይሁን፤›› በማለት ጠይቋል፡፡
በሰሜኑ የአገሪቱ ክፍል በትግራይ ክልል በተፈጠረው ችግር አንዳንድ የግል ድርጅቶች ከፍተኛ ጉዳት የደረሰባቸው ስለመሆኑም ሲሠማኮ መግለጫው አስታውሷል፡፡ ከእነዚህ የግል ድርጅቶች አንዳንዶቹም የማምረቻ መሣሪያቸው በከፊል የተጎዱት ማስተካከያ ተደርጎላቸው በቀላሉ ሥራ መጀመር አለመቻላቸውን በመግለጫው ያስታወሰው ኢሠማኮ፣ በድርጅቶቹ ተቀጥረው ይሠሩ የነበሩ ሠራተኞች በከፍተኛ ችግር ላይ ይገኛሉ ብሏል፡፡ ስለሆነም መንግሥት አስፈላጊውን ድጋፍ በማድረግ መልሶ እንዲያቋቁማቸው ጥሪ አቅርቧል፡፡