Friday, June 2, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ማኅበራዊየአፍሪካ ልማት ፈንድ የሕፃናት መቀንጨርን ለመከላከል 31 ሚሊዮን ዶላር ድጋፍ አደረገ

የአፍሪካ ልማት ፈንድ የሕፃናት መቀንጨርን ለመከላከል 31 ሚሊዮን ዶላር ድጋፍ አደረገ

ቀን:

የአፍሪካ ልማት ፈንድ በኢትዮጵያ ከአምስት ዓመት በታች የሆኑ ሕፃናት የሚያጋጥማቸውን የተመጣጠነ ምግብ እጥረት ተከትሎ የሚደርሰውን የመቀንጨር ጉዳት ለመከላከል የሚያስችል የ31.2 ሚሊዮን ዶላር ድጋፍ አደረገ፡፡

የተደረገው ድጋፍ በኢትዮጵያ የጤና አገልግሎት ተደራሽነትን፣ የተመጣጠነ ምግብን ለሕፃናት በማቅረብ፣ የተሻሻለ የሥነ ምግብ ግንዛቤን፣ እንዲሁም ከአካባቢና ንፅህና አጠባበቅ ጋር የተገናኙ ሥራዎችን ለማቅረብ አስተዋጽኦ እንዳለው ተገልጿል፡፡

ፕሮጀክቱ ተግባራዊ የሚሆነው ከበርካታ ተቋማት በተውጣጡ የሕፃናት መቀንጨር ላይ እንዲሠራ ተግባራዊ በተደረገው ፕሮጀክት በኩል፣ በአማራና ትግራይ ክልሎች በተመረጡ 40 ወረዳዎች ላይ እንደሆነ ተገልጿል፡፡

ይህ ፕሮጀክት በጠቅላላው በ48 ሚሊዮን ዶላር ተግባራዊ የሚደረግ ሲሆን፣ በዋናነትም ሦስት የፕሮግራም ማዕቀፎችን ይዟል፡፡ ፈጣን የአገልግሎት ተደራሽነት ለማቅረብ የሚያስችል የመሠረተ ልማት ግንባታ፣ የምጣኔ ሀብት ድጋፍና የተመጣጠነ ምግብ አዘገጃጀት ግንዛቤ ማስጨበጫና የአቅም ግንባታ ሥልጠናዎችን የሚመለከት እንደሆነ ተመልክቷል፡፡

የአፍሪካ ልማት ባንክ የምሥራቅ አፍሪካ ዋና ዳይሬክተር ንነዋ ኑፎ እንዳስታወቁት፣ ፕሮጀክቱ በታለመባቸው አካባቢዎች የሕፃናት መቀንጨር ላይ የሚሠሩ ተቋማት እንቅስቃሴን ተከትሎ የሚደርሰውን ጉዳት ለመከላከል የሚያግዝ ሲሆን፣ ይህም አካባቢዎቹ ላይ ተጨባጭ ሥራዎችን ለመሥራት የሚያስችል መሆኑን ገልጸዋል፡፡

ፕሮጀክቱ ባንኩ በአፍሪካ የወጣቶች የሥራ ዕድል ከመፍጠርና ይህንንም ተግባራዊ ከማድረግ አንፃር በ2019 ዓ.ም. የተጀመረውን የአፍሪካ ኑትሪሽን አካውንተቢሊቲ ስኮር ቦርድ እየሄደበት ያለውን ጥረት የሚያሳይ እንደሆነ አስረድተዋል፡፡

የአፍሪካ ኑትሪሽን አካውንተብሊቲ ስኮር ካርድ በመረጃ የተደገፈ አመጋገብ ላይና መቀንጨር ላይ  ትኩረቱን ያደረገ በአፍሪካ መሪዎች የተመሠረተ ሲሆን፣ በአፍሪካ ልማት ባንክ፣ ግሎባል ፓናል ለግብርና የአመጋገብ ሥርዓት በተባለ ድርጅት፣ በቢልና ሚሊንዳ ጌትስ ፋውንዴሽንና የአፍሪካ ኅብረት ተነሳሽነት  የተመሠረተ ነው፡፡

በኢትዮጵያ ሕፃናት የተመጣጠነ ምግብ እጥረት አሁንም ከፍተኛ የልማት ችግር  እንደሆነ ይነገራል፡፡ ይህ ፕሮጀክት ዓላማ አድርጎ በሚንቀሳቀስባቸው አካባቢዎች  ዕድሜያቸው ከአምስት ዓመት በታች የሆኑ ሕፃናት ወደ 50 በመቶ የሚሆኑት በመቀንጨር የተጎዱ ናቸው፡፡    

የንፁህ የመጠጥ ውኃ አቅርቦትና የምግብ ስብጥር ማነስ በእነዚህ አካባቢዎች ለሚጠቀሱት የምግብ እጥረት መስፋፋት አስተዋጽኦ ያደርጋሉ፡፡

ፕሮጀክቱ እ.ኤ.አ. በ2030 በጤና ሚኒስቴር መሪነት ከሁለት ዓመት በታች የሆኑ ሕፃናትን መቀንጨር ለማስቆም በ2015 የተፈረመውን የሰቆጣ ቃል ኪዳን ስምምነት ጋር አብሮ የሚሄድ ሲሆን፣ ስምምነቱ ከግብርና፣ ውኃ፣ መስኖና ኢነርጂ፣ ትምህርት፣ ሴቶችና ሕፃናትና ወጣቶች፣ የሠራተኛና ማኅበራዊ ጉዳዮች፣ ትራንስፖርትና የገንዘብ ሚኒስቴርን ያካተተ ነው፡

የቀረበው  የፕሮጀክቱ ድጋፍ ኢትዮጵያ እ.ኤ.አ. በ2030 ለማሳካት የያዘቻቸውን የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ቀጣይ የልማት ዕቅድ የሆኑትን ረሃብን ማጥፋት፣ የምግብ ዋስትናን ማረጋገጥና ሥነ ምግብን ማስተካካል የሚባሉትንና የአፍሪካ ልማት ባንክ 2013 እስከ 2022 ዓ.ም. ዕቅድ ሁለቱ ግቦች ማለትም ለአፍሪካ ሕዝብ የኑሮ ሁኔታ ማሻሻልና አፍሪካን መመገብ የሚሉት ይይዛል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የአዛርባጃንን ብሄራዊ ቀን በአዲስ አበባ በድምቀት ተከበረ

የአዛርባጃን ኤምባሲ  የአዛርባጃንን ብሄራዊ ቀን በትላንትናው ዕለት አከበረ። ሰኞ...

የመንግሥትና የሃይማኖት ልዩነት መርህ በኢትዮጵያ

እንደ ኢትዮጵያ ባሉ አገሮች የሃይማኖት ተቋማት አዎንታዊ ሚና የጎላ...

ሐበሻ ቢራ ባለፈው በጀት ዓመት 310 ሚሊዮን ብር የተጣራ ትርፍ ማግኘቱን አስታወቀ

የአንድ አክሲዮን ሽያጭ ዋጋ 2,900 ብር እንዲሆን ተወስኗል የሐበሻ ቢራ...