Sunday, April 21, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ስፖርትበቅድመ ውድድር ዝግጅት ውዝግብ የማያጣው የኢትዮጵያ አትሌቲክስ

በቅድመ ውድድር ዝግጅት ውዝግብ የማያጣው የኢትዮጵያ አትሌቲክስ

ቀን:

‹‹የአገር ውስጥ የማጣሪያ ውድድር ላይ አልሳተፍም›› ቀነኒሳ በቀለ

የኢትዮጵያ አትሌቶች በዓለም መድረክ ላይ በኦሊምፒክ፣ በዓለም ሻምፒዮን፣ በአገር አቋራጭ እንዲሁም በግላቸው ባደረጓቸው ውድድሮች ሁሉ የራሳቸውን አሻራ ማኖራቸው ዕሙን ነው፡፡ በእነዚህ ውድድሮች ለመሳተፍ በቂ ዝግጅት አድርጎ ከመዘጋጀት ባልተናነሰ ሁኔታ ምርጫ ላይ ከፍተኛ ውዝግብ ሳያስተናግድ ያለፈበት ጊዜ የለም ማለት ያስችላል፡፡ ውድድሮች በተቃረቡ ቁጥር ከአኅጉር አቀፍ ሻምፒዮናዎች እስከ ኦሊምፒክ ጨዋታዎች የአትሌቶች ምርጫን ተከትሎ ውዝግብ ያልተስተናገደበት የለም ቢባል ብዙኃኑን የሚያስማማ ጉዳይ መሆኑ አያጠራጥርም፡፡ ለእነዚህ ሁሉ ውዝግቦች መነሻ የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን አትሌቶችን የሚያስተናግድበት መዋቅራዊ አሠራር ክፍተት እንደነበር ሲገለጽ ቢቆይም፣ ሊሻሻል ባለመቻሉ ዘንድሮም የአትሌቶች ምርጫን ተከትሎ ቅሬታ ማሰማት ጀምረዋል፡፡

የወራት ዕድሜ የቀረው የዘንድሮ የቶኪዮ ኦሊምፒክ በመላ ዓለም የሚገኙ ተካፋይ አገሮች ዝግጅታቸውን ማድረግ ከጀመሩ ሰነባብተዋል፡፡ ብሔራዊ አትሌቲክስ ፌዴሬሽንም ኢትዮጵያን የሚወክሉ አትሌቶችን መርጦ ዝግጅት ከጀመሩ ወራት ተቆጥረዋል፡፡ በአጭር፣ በረዥም እንዲሁም በመካከለኛ ርቀት ላይ የሚሳተፉ አትሌቶች ለቅድመ ማጣሪያ ዝግጅት ይረዳቸው ዘንድ በቅርቡ በተከናወነው የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ሻምፒዮን ላይ መሳተፍ የቻሉ ሲሆን፣ በዚህም ያሉበትን ወቅታዊ አቋም በጥቂቱም ቢሆን መገምግም አስችሏችዋል፡፡ በአንፃሩ በኦሊምፒክ ጨዋታው በማራቶን ብሔራዊ ቡድኑን ወክለው ወደ ቶኪዮ እንደሚጓዙ ግምት የተሰጣቸው አትሌቶች የትሪያል ውድድር በስዊዘርላንድ ያደርጋሉ ቢባልም፣ ውድደሩ ተሰርዞ በሰበታ በሚደረገው  የ35 ኪሎ ሜትር ውድድር መቀየሩ ተገልጿል፡፡

- Advertisement -

Video from Enat Bank Youtube Channel.

የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ረቡዕ ሚያዝያ 20 ቀን 2013 ዓ.ም. በሰጠው መግለጫ መሠረት፣ 12 ወንድ እና 8 ሴት ማራቶን አትሌቶች በቅድመ ማሟያ ውድድር ላይ እንዲሳተፉ ጥሪ ማቅረቡ ይታወሳል፡፡

ጥሪውን ተከትሎ የተወሰኑ አትሌቶች ቅሬታቸውን በይፋ አሰምተዋል፡፡ ቀነኒሳ በቀለን ጨምሮ በርካታ የማራቶን አትሌቶች ስማቸው የተዘረዘረ ሲሆን፣ በአንፃሩ ቀነኒሳ ውድድር እንደማያደርግ በይፋ መቃወሙን ተከትሎ የተለመደው ውዝግብ ተከስቷል፡፡

የፌዴሬሽኑ የሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ሚያዝያ 19 ቀን ባካሄደው ሰባተኛ መደበኛ ስብሰባ በቶኪዮ ኦሊምፒክ ላይ የሚሳተፉ የማራቶን አትሌቶችን በትራያል መምረጥ አስፈላጊ በመሆኑና በፌዴሬሽኑ ቴክኒክ ኮሚቴ፣ በአሠልጣኞችና በአትሌቶች በተደረገ የጋራ ውይይት የአገር ውስጥ ውድድር ለማሰናዳት መስማማቱን አስታውቋል፡፡

ውሳኔውን ተከትሎም በኢትዮጵያ በረዥም ርቀት ውድድሮች በርካታ ድሎችን የተቀዳጀው ቀነኒሳ በቀለ ተቃውሞውን የሚገልጽ ደብዳቤ ለብሔራዊ ፌዴሬሽኑና ለጋዜጠኞች ልኳል፡፡

በደብዳቤውም አትሌቱ ከዚህ ቀደም በመም፣ በአገር አቋራጭ እንዲሁም በሌሎች ርቀቶች አገሩን ወክሎ የአገሩን ሰንደቅ ዓላማ እንዲውለበለብ የበኩሉን መወጣቱና ሕዝቡ እንዲሁም መንግሥት ህያው ምስክሩ እንደነበሩ ጠቅሶ ቅሬታውን ያትታል፡፡

ከዚህ ጋር ተያይዞም እ.ኤ.አ. በ2016 በሪዮ ኦሊምፒክ ቡድን ውስጥ እንዳይካተት መደረጉን የገለጸው ቀነኒሳ ዓምና ሊከናወን በነበረው የቶኪዮ ኦሊምፒክ ላይ ጥሩ ሰዓት ስለነበረው ጨዋታ ከመራዘሙ በፊት መመረጡንና ዝግጅት ሲያደርግ መሰንበቱን አስረድቷል፡፡

‹‹ባለፈው ዓመት ሊካሄድ በነበረው የቶኪዮ ኦሊምፒክ ውድድር በማራቶን የውድድር ዘርፍ በፌዴሬሽኑ ሕግ መሠረት ጥሩ ሰዓት ስለነበረኝ በምርጫ ውስጥ በመካተቴ ዝግጅት ላይ ነበርኩ፤›› በማለት ቀነኒሳ ስለነበረው ዝግጅት ያብራራል፡፡

በአንፃሩ የኮሮና ወረርሽኝ መስፋፋቱንና ጨዋታው መራዘሙን ተከትሎ፣ ቀድሞ የነበረውን ሕግ በመሻር አዲስ በወጣው ሕግ በአገር ውስጥ ውድድር መሳተፍ አለባችሁ የሚለው በሕግ ተቀባይነት የሌለው ነው ሲል ቅሬታውን አስቀምጧል፡፡

‹‹የማጣሪያ ውድድሩ ወቅቱን ያልተጠበቀና የውድድሩ ጊዜውም በጣም የቀረበና በአትሌት ላይ ጉዳት ስለሚያስከትል ያላመንኩበት በመሆኑ፣ እንዲሁም ሌሎች የዓለም አገሮች አትሌቶች ሰዓት ጋር ሲታይ የተሻለ ሰዓት ስላለኝ፣ የአገር ውስጥ የማጣሪያ ውድድር ላይ አልሳተፍም፤›› በሚል ቅሬታውን አንፀባርቋል፡፡ 

ምንም እንኳን ብሔራዊ ፌዴሬሽኑ በአገር ውስጥ በሚደረገው የማጣሪያ ውድድር ከአንደኛ እስከ ሦስተኛ ደረጃን በመያዝ ያጠናቀቁ አትሌቶችን በቀጥታ የሚመርጥ ቢሆንም፣ ቀድሞ የነበረውንና አትሌቶች በዓለም አቀፍ ውድድሮች ባስመዘገቡት ውጤት መሠረት በቀጥታ የሚመረጡበትን መንገድ መሻሩ በብዙኃን ዘንድ ትችትን እንዲያስተናግድ አድርጎታል፡፡

ከዚህ ጋር ተያይዞም ቀነኒሳ አፋጣኝ ምላሻ እንደሚሻ በደብዳቤው የጠቆመ ሲሆን፣ ፌዴሬሽኑም አፋጣኝ ምላሽ ካልሰጠው በራሱ መንገድ ውድድሩ ላይ የሚሳተፍበትን ሒደት ሊከተል እንደሚችል ጠቅስዋል፡፡

‹‹በአገር ውስጥ የተዘጋጀውን የማጣሪያ ውድድር የማልሳተፍ መሆኑ ታውቆ፣ በቀጥታ አገሬን  በመወከል ለውድድር እንድመረጥ እየጠየቅኩኝ፣ በምርጫው የማልሳተፍ ከሆነ ፌዴሬሽኑ አገርን በመወከል በሚደረጉ ውድድሮች ላይ የማያሳትፈኝ መሆኑን የሚገልጽ ደብዳቤ እንዲሰጠኝና እኔም ሌላ አማራጭ እንድፈልግ እጠይቃለሁ፤›› ሲል  ቅሬታውን አክሏል፡፡

ከዚህ ጋር ተያይዞ የቀረበውን ቅሬታ ተከትሎ ብሔራዊ ፌዴሬሽኑን በጉዳዩ ምላሽ የሰጠ ሲሆን፣ ‹‹ጥሪ የቀረበላቸው ታላላቅና እንቁ አትሌቶቻችን እንደሚሳተፉ እምነት አለን፤›› የሚል ምላሽ ሰጥቷል፡፡ 

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ሰው መሆን ምንድን ነው? ቅርስና ማኅበራዊ ፍትሕ

በሱራፌል ወንድሙ (ዶ/ር) ዳራ ከጎራዎች፣ ከመፈራረጅ፣ ነገሮችን ከማቅለልና ከጊዜያዊ ማለባበስ ወጥተን...

ኢኮኖሚው ኢትዮጵያን እንዳያፈርሳት ያሠጋል

በጌታቸው አስፋው ኢትዮጵያን እንዳያፈርሱ የሚያሠጉኝ አንድ ሁለት ብዬ ልቆጥራቸው የምችላቸው...

የኢትዮጵያ የፖለቲካ ትግል በሕግ አምላክ ይላል

በገነት ዓለሙ የአገራችንን ሰላም፣ የመላውን ዓለም ሰላም ጭምር የሚፈታተነውና አደጋ...

በሽግግር ፍትሕ እንዲታዩ የታሰቡ የወንጀል ጉዳዮች በልዩ ፍርድ ቤት ሳይሆን በልዩ ችሎት እንዲታዩ ተወሰነ

የኤርትራ ወታደሮች በሌሉበትም ቢሆን ይዳኛሉ ተብሏል በፅዮን ታደሰ የሽግግር ፍትሕ የባለሙያዎች...