Friday, December 8, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ስፖርት‹‹የውዝግቡ መንስዔ ለስፖርቱ ዕድገት ሳይሆን የግል ፍላጎትን ከመሻት ይጀምራል›› አንተነህ ጎበዜ፣ የዋና...

‹‹የውዝግቡ መንስዔ ለስፖርቱ ዕድገት ሳይሆን የግል ፍላጎትን ከመሻት ይጀምራል›› አንተነህ ጎበዜ፣ የዋና ቡድን አሠልጣኝ

ቀን:

 

የቶኪዮ ኦሊምፒክ በኮቪድ-19 ምክንያት ለአንድ ዓመት ተራዝሞ ስያሜውን እንደያዘ  በመጪው ክረምት ሊጀመር የሦስት ወራት ዕድሜ ብቻ ቀርቶታል፡፡  ከሰሜን ኮሪያ በስተቀር በመድረኩ የሚሳተፉ የዓለም አገሮች ተወካዮቻቸውን በማዘጋጀት ይገኛሉ፡፡ እንደ አለመታደል ሆኖ ኦሊምፒክና ሌላም ተመሳሳይ ዓለም አቀፍ ዝግጅቶች ሲኖሩ ትርምስና ውዝግብ የማያጣው የኢትዮጵያ ስፖርት፣ ሰዓቱንና ጊዜውን ጠብቆ ዘንድሮም መወዛገቡን ቀጥሏል፡፡ ኢትዮጵያ በቶኪዮ 2020 ኦሊምፒክ ላይ በአትሌቲክስ፣ በዎርልድ ቴኳንዶ፣ በብስክሌት እንዲሁም የዓለም አቀፉ ኦሊምፒክ ኮሚቴ ለታዳጊ አገሮች በሚሰጠው ዕድል (ዩቨርሳሊቲ ፕሮግራም) በዋና እንደምትወከል ይጠበቃል፡፡ በዩኒቨርሳሊቲ ፕሮግራም ውክልናውን ያገኘው የኢትዮጵያ ውኃ ስፖርት ፌዴሬሽን ከጉዞና ተያያዥ ጉዳዮች ጋር ተያይዞ በተቋሙ ውስጥ የሚስተዋለው አለመግባባት የወቅቱ መነጋሪያ ሆኗል፡፡ በ2016 የሪዮ ኦሊምፒክ ወቅት በዚሁ ተቋም ውስጥ በተለይም ከአትሌት ምርጫ ጋር ተያይዞ ተከስቶ በነበረው ችግር በታላቁ የኦሊምፒክ መድረክ የአገሪቱን መልካም ስምና ዝና ያጠለሸ ክስተት ፈጥሮ ማለፉ አይዘነጋም፡፡ ወቅቱ አትሌቶችን ጨምሮ የኦሊምፒክ ልዑካን ዝርዝር ተሞልቶ ለኢትዮጵያ ኦሊምፒክ ኮሚቴ የሚተላለፍበት ቢሆንም፣ የኢትዮጵያ ውኃ ስፖርት ፌዴሬሽን ግን ተወዳዳሪ አትሌቶችና አሠልጣኙ ያልተካተቱበት የአሥር ሰዎችን ዝርዝር ለኢትዮጵያ ኦሊምፒክ ኮሚቴ መላኩን አሠልጣኙ አንተነህ ጎበዜ ይናገራል፡፡ ብሔራዊ ኦሊምፒክ ኮሚቴው ሆቴል አስገብቷቸው በዝግጅት ላይ የሚገኙት አሠልጣኙን ጨምሮ አትሌቶቹ ከሆቴል ለቀው እስካልወጡ ድረስ ተቋሙ እንደ ብሔራዊ አትሌት ዕውቅና የማይሰጣቸው መሆኑ፣ ከዚህም አልፎ የተለያዩ ማስፈራሪያዎች ለቤተሰቦቻቸው ሳይቀር እየተላከ መሆኑን አሠልጣኝ አንተነህ ይናገራል፡፡ በኢትዮጵያ ውኃ ፌዴሬሽንና ለቶኪዮ ኦሊምፒክ በዝግጅት ላይ የሚገኙ አትሌቶች ስለሚገኙበት ወቅታዊ ሁኔታ እንዲሁም የዝግጅቱ ቀጣይ ዕጣ ፈንታን አስመልክቶ ደረጀ ጠገናው ከአሠልጣኙ አንተነህ ጎበዜ ጋር ቆይታ አድርጓል፡፡

ሪፖርተር፡- የኢትዮጵያ ውኃ ስፖርት ፌዴሬሽን ምርጫ አላደረግኩም ይላል፡፡ በእርስዎ ዋና አሠልጣኝነት ደግሞ አንድ ወንድና አንድ ሴት ተወዳዳሪዎች በግዮን ሆቴል ዝግጅት ከጀመራችሁ ሰነባብቷል፡፡ ያለው ነገር ግልጽ አይደለም፡፡ በዚህ ሁኔታ ዝግጅት ማድረግ ይመከራል?

አሠልጣኝ አንተነህ፡- የምንሰማው ነገር እጅጉን የሚያሳዝን ነው፡፡ ሁሉም ሰው እንደሚያወቀው ኢትዮጵያ በዋና የመሳተፍ ዕድሉን ያገኘችው በዩኒቨርሳሊቲ ፕሮግራም ነው፡፡ የተገኘውን ዕድል ሕግና ሥርዓት ባለው መንገድ መጠቀም ሲቻል ‹‹ዕድሉ እኔን የማያካትት ከሆነ›› በሚል የግል ፍላጎት ኦሊምፒክ በመጣ ቁጥር ስፖርቱን የውዝግብና የትርምስ ቀጣና ማድረግ እንደ አንድ የስፖርቱ ሰው ያሳፍረኛል፡፡ እንደተባለው ዝግጅቱ ለእኔም ሆነ ለአትሌቶቹ እንቅልፍ የሚነሳ ነው፡፡ ስፖርት በባህሪው ሰላም ይፈልጋል፡፡ ውጤታማ መሆን የሚቻለውም ሰላሙ በተረጋገጠ ሁኔታ ውስጥ መሥራት ሲቻል ነው፡፡ ተከፋይ ባልሆነበት ስፖርት ፍላጎቱና ፍቅሩ ስላለን ብቻ ዋጋ የሚያስከፍል ሁኔታ ውስጥ ነን፡፡ በግልጽ እንነጋገር ከተባለ የኢትዮጵያ ውኃ ስፖርት ፌዴሬሽኑ እንደሌሎቹ ስፖርቶች አንድ እንኳ ክለብ የለውም፡፡ በኦሊምፒክ እንድንሳተፍ ዕድሉ የተገኘው በዩኒቨርሳሊቲ ፕሮግራም መሆኑ እየታወቀ፣ በዚያ ላይ ክለብ በሌለበት እኔን ጨምሮ ብዙዎቹ በግላችን ላደረግነው ጥረት ዋጋ እየተሰጠው አይደለም፡፡ በተለይ የፌዴሬሽኑ አመራር የኦሊምፒክ ልዑክ ለመሆን ካልሆነ ለስፖርቱ ዕድገት ቅንጣት ታህል ጉዳዩ አይደለም፡፡ እያየን ያለውም ይህንኑ እውነታ ነው፡፡

ሪፖርተር፡- እርስዎም ሆኑ ሁለቱ አትሌቶች ሆቴል ከመግባታችሁ በፊት የመጣችሁበት ሁኔታ በማጣሪያ ነው ወይስ እንዴት ነው?

አሠልጣኝ አንተነህ፡- በደቡብ ኮሪያ አስተናጋጅነት ከሦስት ዓመት በፊት በተደረገው የዓለም ዋና ሻምፒዮና በሁለት ወንድና በሁለት ሴቶች ተሳትፎ ማድረጋችን ይታወቃል፡፡ ተወዳዳሪዎቹ አብዱልመሊቅ ቶፊቅና አቻላ አያኮቫና  ሲሆኑ፣ በሴቶች ሊና ዓለማየሁና ራሔል ፍሥሐ ነበሩ፡፡ በሻምፒዮናው የተሻለ ሰዓት ያመጡት አብዱልመሊቅ ቶፊቅና ሊና ዓለማየሁ ናቸው፡፡ ከኮሪያው ሻምፒዮና በኋላ ደግሞ ፌዴሬሽኑ ከወራት በፊት ኮምቦልቻ ላይ ባዘጋጀው ሻምፒዮና ላይም እነዚሁ ልጆች ናቸው ውጤት ያስመዘገቡት፡፡ ሲቀጥል ብሔራዊ ፌዴሬሽኑ እንደ አሁኑ የተካረረ ነገር ውስጥ ከመግባቱ በፊት በቢሾፍቱ የማጣሪያ ውድድር አዘጋጅቶ አቻላና ራሔል ቢካፈሉም አሁንም ከሁለቱ አትሌቶች የተሻለ ሰዓት ማስመዝገብ አልቻሉም፡፡ እንዲያውም አቻላ የተባለው ዋናተኛ ተጨማሪ ዕድል ተሰጥቶ በሁሉም ከአብዱዱመሊቅ ቶፊቅ የተሻለ ሰዓት ማስመዝገብ አልቻለም፡፡ ውድድር ያቋረጠበት አጋጣሚም አለ፡፡ ማጣሪያው በዚህ ሁሉ ያለፈ እንደመሆኑ ምንም ዓይነት ቅሬታ ሊቀርብበት አይገባም፡፡ ቅሬታ ያለው ካለ የማጣሪያው የቪዲዮ ማስረጃ ስላለ በመመልከት መፍረድ ይቻላል፡፡

ሪፖርተር፡- ታዲያ ችግሩ ምን ሊሆን ይችላል?

አሠልጣኝ አንተነህ፡- አጋጣሚውን ተጠቅሞ የኦሊምፒክ ቡድኑ አካል ሆኖ ወደ ቶኪዮ ለመጓዝ ካልሆነ ለስፖርቱ ዕድገት እንዳልሆነ መረዳት ያስፈልጋል፡፡ ለዚህ አባባል ማሳያ የሚሆነን ኦሊምፒክ ሲቃረብ ካልሆነ፣ በሌላ ጊዜ እንዲህ የመሰለ ለያዥ ለገራዥ የሚያስችግር አለመግባባት ተፈጥሮ በግሌ ተመልክቼ አላውቅም፡፡

ሪፖርተር፡- እንደሚታየው ዝግጅት ላይ ናችሁ፣ ብሔራዊ ፌዴሬሽኑ ክትትል ያደርግላችኋል?

አሠልጣኝ አንተነህ፡- ክትትሉ ቀርቶ ማስፈራራቱ በቀረልን፡፡

ሪፖርተር፡- የሚያስፈራሩት ማንነት ይታወቃል?

አሠልጣኝ አንተነህ፡- አንዳንዶቹ የኢትዮጵያ ውኃ ስፖርት ፌዴሬሽን አመራር ከመሆናቸው ጎን ለጎን፣ የሚዲያ ባለሙያ ሆነው የምናውቃቸው ናቸው፡፡ የሚገርመው በአሁኑ ሰዓት በግዮን ሆቴል ዝግጅት ላይ የምትገኘው ሊና ዓለማየሁ፣ በአንድ ወቅት ለውኃ ስፖርት የነበራትን ተነሳሽነት ከግምት በማስገባት ይመስላል፣ ‹‹የማይከፈላት የውኃ ዋና ስፖርት ንግሥት›› በሚል ግለሰቡ ዶክሜንተሪ ሠርተውላታል፡፡ ይህን የሚዲያ ተቋሙን ጠይቆ ማረጋገጥ ይቻላል፡፡ አብዱልመሊቅ ቶፊቅም ቢሆን በሪዮ ኦሊምፒክ መሳተፍ ሲገባው የተሠራበት ሸፍጥ የአደባባይ ሚስጥር ነው፡፡ ልጁ የማንኛውንም ሰው የሞራል ድጋፍ ካልሆነ ወደ ፈለገበት ደረጃ መድረስ የሚፈልገው በብቃቱ ነው፡፡ አሁንም ቢሆን ከሁለቱ አትሌቶች የተሻለ ሰዓት ያላቸው ተወዳዳሪዎች ካሉ ዕድሉን ለመስጠት በግሌ ዝግጁ ነኝ፡፡ ከዚህ ውጪ ከሆነ ግን ለስፖርቱም ሆነ ለህሊና ከባድ ነው፡፡ ይሁንና እውነታውና የውዝግቡ መንስዔ ለስፖርቱ ዕድገት ሳይሆን የግል ፍላጎትን ከመሻት የሚጀምር መሆኑ ነው፡፡

ሪፖርተር፡- የአመራሩ ፍላጎት ተሳትፎው በዩኒቨርሳሊቲ ፕሮግራም ከሆነ ማጣሪያ ማድረግ የግድ አያስፈልግም ከሚል ከሆነስ?

አሠልጣኝ አንተነህ፡- እንዲያ ከሆነ በትክክለኛ አሠራርና አካሄድ የተመረጠን አካል ማስፈራራት ለምን አስፈለገ ታዲያ? ማጣሪያ እንዲኖር በጀት በጅቶ የወሰነው ራሱ ፌዴሬሽኑ ነው፡፡ በግሌ ዕድሉ ምንም እንኳ በዩኒቨርሳሊቲ ፕሮግራም የተገኘ ቢሆንም ዞሮ ዞሮ ስፖርቱ በሕግ እስከተቋቋመ ድረስ የተሻለ ብቃት ያላቸው ተወዳዳሪዎችን ማሳተፍ የተለመደና የኖረ አሠራር ነው፡፡ ከዚህ በፊት የኢትዮጵያ ውኃ ስፖርት በመላው አፍሪካ ጨዋታዎች ላይ ተሳትፎ ሲያደርጉ ከነበሩ ስፖርቶች አንደኛው ነው፡፡ ይህ ማለት ፌዴሬሽኑ ስፖርቱ አሁን ካለበት ደረጃ ከፍ እንዲል ፍላጎት አለው ማለት ነው፡፡ ይህ ከታሰበ ደግሞ በወቅታዊ ብቃታቸው አብዱልመሊቅና ሊና ዓለማየሁ ቀዳሚዎቹ እንደሚሆኑ መውሰድ ያስፈልጋል፡፡

ሪፖርተር፡- አሁን ባለው ሁኔታ ጫናው የሚቀጥል ከሆነ ምን ለማድረግ ነው ያሰባችሁት?

አሠልጣኝ አንተነህ፡- በችግሩ ምክንያት በተረጋጋ ነገር ውስጥ ለመዘጋጀት ዕድሉ ባይኖረንም፣ የዝግጅቱ ባለቤት የኢትዮጵያ ኦሊምፒክ ኮሚቴ ነው፡፡ ክትትልም እያደረገልን ነው፡፡ በዚያ መሠረት ቀጣይ ዕጣ ፈንታችን የሚወሰን እንደሚሆን እጠብቃለን፡፡

ሪፖርተር፡- የኢትዮጵያ ውኃ ስፖርት ፌዴሬሽን አሁን ባለው ሁኔታ የሚቀጥል ከሆነ የስፖርቱና የስፖርተኛው ዕጣ ምን ሊሆን ነው?

አሠልጣኝ አንተነህ፡- ኦሊምፒክ ሲቃረብ ካልሆነ ቀድሞም ስፖርቱን የምናዘወትረው በግላችን ነው፡፡ አሁን ላይ ማለት የምፈልገው ይብዛም ይነስም የአንድ ስፖርተኛ የመጨረሻ ግብ በኦሊምፒክ መሳተፍ ነው፡፡ ዕድሉ የተገኘው በዩኒቨርሳሊቲ ፕሮግራም ቢሆንም፣ በትክክለኛው መንገድ የመጡት ሁለቱ አትሌቶች የዚህ ዕድል ተጠቃሚ እንዲሆኑ መሥራት ያስፈልጋል የሚል እምነት አለኝ፡፡ ከዚህ ውጪ አመራሩ የራሱን ሥራ ይሥራ፣ የሙያተኛውን ሥራ ደግሞ ለሙያተኛው ይተውለት፡፡ እንዲያውም ችግሮች ሲፈጠሩ ስፖርተኛው ከመስማቱ በፊት መፍታት የአንድ አመራር ዋነኛ ኃላፊነት ይመስለኛል፡፡ አሁን ያለው ነገር እኔ የምልህን ካልሰማህ የቱንም ያህል አቅምና ችሎታው ቢኖርህ ምንም አታመጣም ዓይነት ነው፡፡ ያለው ነገር ከባድ ብቻ ሳይሆን ተስፋ አስቆራጭ ነው፡፡ የበለጠ እንዳዝን የሚያደርገኝ ስንት ነገር ባሳለፍኩበት ስፖርት ሦስት ወር ያልሞላው አመራር ተብዬ እኔን ካልሰማህ አግድሃለሁ፣ አባርርሃለሁ ማለቱ ነው፡፡ አንድ አሠልጣኝ ወይም ስፖርተኛ ባለው የሕግ ማዕቀፍ ውስጥ ሆኖ ሥራ መሥራት የማይችል ከሆነ ተቋሙ ሕጋዊ ተቋም ነው ብሎ ማለትስ እንዴት ይቻላል? የተቋሙ ችግር ኦሊምፒክ ከሆነ ከራሱ ከኦሊምፒክ ጋር ቁጭ ብሎ መነጋገር ሲገባ፣ በኦሊምፒክ ሙሉ ወጪ ዝግጅት የጀመረን ተወዳዳሪ ሆቴል ለቀህ ውጣ ምን ማለት ነው? የምንኖረው ኢትዮጵያ ውስጥ እስከሆነ ድረስ በእኔ ፍላጎት ልክ መሄድ ካልቻልክ መወዳደር አትችልም ማለትስ ምን ማለት ነው? በግልጽ እኔንና አትሌቶቹን እየገጠመን ያለው ችግር ይህ ነው፡፡ ስፖርቱስ በዚህ ሁኔታ የት ይደርሳል? ስለሆነም የሚመለከተው የመንግሥት አካል አንድ ሊለው ይገባል፡፡ ክለብ ለማቋቋም ፍላጎት የሌለው አመራር በዩኒቨርሳሊቲ ፕሮግራም በተገኘ ዕድል አቧራ ማስነሳት ምን የሚሉት በሽታ ነው፡፡

ሪፖርተር፡- ለረዥም ዓመታት በኦሮሚያ ፖሊስ ክለብ መሥራትህ ይታወቃል፡፡ ምናልባት ይህ የፌዴሬሽኑ አካሄድ ክለብ ለማቋቋም ፍላጎት ለሚኖራቸው አንዳንድ ተቋማት የሚያስተላልፈው መልዕክት አይኖርም?

አሠልጣኝ አንተነህ፡- ይህ እኮ ግልጽ ነው፡፡ የውኃ ስፖርት ቢሠራበት ውጤታማ እንደሚሆን በግሌ አምናለሁ፡፡ እንዴት የሚለው ግን ያሳስበኛል፡፡ ምክንያቱም አመራሩ እንደሚሠራ ለማሳየት የሚሞክረው ኦሊምፒክ ሲቃረብ የልዑካን ቡድን አባል ሆኖ ለመጓዝ ነው፡፡ አሁን ላይ እየደረሰብን ያለው ጫና መነሻው ከጉዞ ጋር ይያያዛል፡፡ የተወዳዳሪ አትሌቶች ዝርዘር ሳይላክ የልዑካን ቡድን አባላት ዝርዝር ሲላክ የችግሩ መንስዔ ግልጽ ይሆንልሃል፡፡ ለመሆኑ ስፖርተኛውን ያላካተተ ጉዞ ምን ለማምጣት ነው? የሚገርመው የአገሪቱ የስፖርት ሚዲያ ስፖርቱ ላይ ይህን ያህል ደባና ሸፍጥ ሲፈጸም ምን እየሆነ ነው ብሎ ወደ ስፖርተኛው ቀርቦ አለመጠየቁ ነው፡፡ ማኅተም ያለበት ውዝግብ ሲሆን ሚዲያው ይረባረባል፡፡ ማኅተም የሌለው ስፖርቱና ስፖርተኛው ምን እየደረሰበት ነው ብሎ እስካሁን የጠየቀኝ ሚዲያ የለም፡፡ ሚዲያው ካልሆነ በአትሌቱ ላይ የሚደርሰውን ችግርና ተግዳሮት ለኅብረተሰቡ ሊያደርስ የሚችለው ማን ነው? የኢትዮጵያ ስፖርት፣ ኦሊምፒክና የዓለም ሻምፒዮና በመጡ ቁጥር እየታመሰ የሚኖረውስ እስከ መቼ ነው? የኢትዮጵያ የውኃ ስፖርት ፌዴሬሽን የኋላ ታሪክ ይታወቃል፡፡ አሁንስ ያለው ነገር ምን ይመስላል? የአትሌቶች ዝግጅትስ ብሎ ሚዲያው የመጠየቅ ኃላፊነት እንዳለበት መታወቅ ይኖርበታል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ታዋቂው የኤሌክትሮኒክስ ብራንድ አይቴል የስትራቴጂ ለውጥ አካል የሆነውን አዲስ አርማ እና መለዮ ይፋ አደረገ።

በአለማችን ታዋቂ ከሆኑት የኤሌክትሮኒክስ ብራንዶች መካከል አንዱ የሆነው እና...

የጠቅላላ ጉባኤ ስብሰባ ጥሪ ለሸገር አነስተኛ የፋይናንስ ተቋም አ.ማ ባለአክሲዮኖች በሙሉ

ለሸገር አነስተኛ የፋይናንስ ተቋም አ.ማ ባለአክሲዮኖች በሙሉ የሸገር አነስተኛ የፋይናንስ...

[የክቡር ሚኒስትሩ ጸሐፊ፣ የሌላ ሚኒስትር ጸሐፊ ከሆነችው የቅርብ ወዳጇ ጋር በስልክ እየተጨዋወቱ ነው]

አንቺ ግን ምን ሆነሽ ነው? ጠፋሁ አይደል? ጠፋሁ ብቻ?! ምን ላድርግ ብለሽ...

በሱዳን ላይ ያጠላው የመከፋፈል ዕጣና ቀጣናዊ ተፅዕኖው

የሱዳን ጦርነት ስምንተኛ ወሩን እያገባደደ ይገኛል፡፡ ጄኔራል አብዱልፈታህ አልቡርሃን...