የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ሥር ነቀል ለውጥ ያሻዋል ተብሎ የተለያዩ ሥራዎች እየተሠሩ መሆኑ በተደጋጋሚ ሲነገር ቆይቷል፡፡ በተለይ ካለፈው አንድ ዓመት ተኩል ወዲህ በአዳዲስ የቦርድ አመራርና ማኔጅመንት እንዲመራም ተደርጓል፡፡ ባንኩ በመንግሥት ውሳኔ ጭምር አጠቃላይ አሠራሩን ይቀየር የሚል ውሳኔ ሲወሰን፣ የነበረበትን እጅግ አደገኛ ሁኔታ ከግንዛቤ ውስጥ በማስገባት ነው፡፡
ባንኩ የነበረበት አጠቃላይ ሁኔታ የአገር ኢኮኖሚን የሚያናጋ ለሌሎች ፋይናንስ ተቋማትም ጠር በመሆን የፋይናንስ ቀውስ ሊያስከትል በሚችል ደረጃ ላይ ደርሶ እንደነበር በግልጽ ሲነገር እንደነበር የሚታወስ ነው፡፡
የባንኩን አካሄድ መለወጥ እንዳለበት ሲታመንም ከአንድ ዓመት ተኩል በፊት የቀድሞ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ገዥ አቶ ተክለወልድ አጥናፉ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የቦርድ ሰብሳቢ ሆነው መሰየማቸው ከዚሁ ጋር ይያያዛል፡፡ የቦርድ አባላቱም በአብዛኛው በአዲስ እንዲተኩ ተደርጎ ባንኩን ሪፎርም ወደማድረጉ ሥራ ሊገባ ችሏል፡፡
አሁን በአመራር ላይ ያለው ቦርድ ገጥሞት የነበረው ፈተና ግን እንዲህ የዋዛ ባለመሆኑም ባንኩ ያለበትን ችግር ቀርፎ ወደ መስመር እንዲገባ ምን ይደረግ የሚያስብል ነበር፡፡
ረቡዕ ሚያዝያ 20 ቀን 2013 ዓ.ም. የባንኩ የዘጠኝ ወራት ሥራ አፈጻጸም በተገለጸበትና የባንኩ የቦርድና ከፍተኛ ማኔጅመንት አባላት በታደሙበት መድረክ ላይም ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ቦርድ ሰብሳቢ አቶ ተክለወልድ አጥናፉ የተደመጠው፣ ባንኩ አሥጊ ሁኔታ ላይ እንደነበር፣ አሁን ደግሞ በተደረጉ የተለያዩ የሪፎርም ሥራዎች እንዲሁም መንግሥት ባንኩ ተሸክሞ የነበረውን የመንግሥት ልማት ድርጅቶች ዕዳ ወደ ራሱ እንዲዛወር በመወሰኑ ከከፋ አደጋው ታድጎታል፡፡
አቶ ተክለወልድ ቦርዱ በአንድ ዓመት ተኩል ጊዜ ውስጥ ሲሠራ የነበረው ሥራ አሁንም ሊሠራ ያቀዳቸውን ሥራዎች ባብራሩበት ወቅት፣ ባንኩን ወደ ተሻለ ደረጃ ማራመድ ለአገር የሚኖረው የማይተካ ሚና ታሳቢ ተደርጎ ጭምር እንደሆነ ተናግረዋል፡፡
አዲሱ አመራር በመጀመርያ ደረጃ ያየው ባንኩ ምን ሕግጋቶች አሉት፣ የራሱንና የብሔራዊ ባንክን ሕጎች ምን ያህል ተግባራዊ አድርጓል በሚል እንደነበር ያስታወሱት አቶ ተክለወልድ፣ ለዚህም የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በተለያየ ጊዜ ያወጣቸውን ሪፖርቶች ፈትሿል፡፡ ዕርምት የሚያስፈልጋቸውን እያረመ አዳዲስ አሠራሮችንም እያካተተ ሪፎርሙን ሲያካሂድ ነበር፡፡
በሪፎርም ሥራ ውስጥ ሲገባ የልማት ድርጅቶች የቀድሞ ብድር፣ አዲስ ሥራዎች ላይ ብድር መስጠት የሚሉት ጉዳዮች ችግር የገጠማቸው ነበሩ፡፡ አቶ ተክለወልድ እንዳሉት፣ ይህንን የከፋ ችግር ከኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ፣ ከገንዘብ ሚኒቴርና ከማክሮ ኢኮኖሚ ኮሚቴ ጋር ውይይት በማድረግ እንዲቀረፍ ባይደረግ ኖሮ የባንኩ ዕጣ ፈንታ አሳዛኝ ይሆን ነበር፡፡ በተለይ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክን ሲያስጨንቁ የነበሩት የመንግሥት የልማት ድርጅቶች የብድር ዕዳ፣ የውጭ ምንዛሪ እጥረትና የመሳሰሉ ችግሮች በመንግሥት ውሳኔ መፍትሔ ባያገኙ ባንኩ ሊወጣቸው የማይችሉ ነበሩ፡፡
በሌላ በኩልም አዋጭ ያልሆኑ የልማት ድርጀቶች ብድር በገንዘብ ሚኒስቴርና በማክሮ ኢኮኖሚ ኮሚቴ በተወሰነው መሠረት እንዲተገበር መደረጉም ባንኩ የነበረበትን ውጥረት አቅልሏል ብለዋል፡፡
ከሁሉም በላይ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የመኖርና ያለመኖር አጣብቂኝ ውስጥ አስገብቶ የነበረው የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ለልማት ድርጅቶች የሚሰጠው ብድር ነበር፡፡ ይህ ለማልት ድርጅቶች የተሰጠው ብድር ከባንኩ አጠቃላይ ብድር 85 በመቶ የያዘ ሲሆን፣ ብድሩ በማንኛውም ሁኔታ ሊከፈል ያልቻለ፣ በቀጣይም ቢሆን ብድሩ የመመለሱ ሁኔታ አደጋች የነበረ ነው፡፡
ብድር ያልመለሱ የመንግሥት የልማት ድርጅቶች ደግሞ ባንኩን በከፍተኛ ሁኔታ የገንዘብ እጥረት ውስጥ የከተቱ ስለነበር ችግሩን ለመፍታት ብዙ ጥረቶች ተደርገው በመጨረሻ ለጠቅላይ ሚኒስትርና ለማክሮ ኢኮኖሚ ኮሚቴ ውሳኔ እንዲሰጥበት እስከ ማድረግ ተደርሷል፡፡
የልማት ድርጅቶቹ ብድርና ያስከተለው ችግር ለጠቅላይ ሚኒስትሩና ለማክሮ ኢኮኖሚ ኮሚቴው ቀርቦ ከፍተኛ ውይይትና ክርክር ተደርጎበት ዕዳው ከልማት ድርጅቶቹ ወጥቶ የመንግሥት ብድር ሆኖ እንዲዞር ሊወሰን ችሏል፡፡ ይህ ውሳኔ መንግሥት ባንኩን ያዳነበት ትልቅ ውሳኔ ተደርጎ ሊወሰድ እንደሚችል የጠቀሱት አቶ ተክለወልድ፣ ከዚህ ውሳኔ በኋላ ድርጅቶቹን የሚያስተዳድር ኮርፖሬሽንም በሚኒስትሮች ምክር ቤት ፀድቆ አሁን በሒደት ላይ ይገኛል ብለዋል፡፡ ይህ የመንግሥት ውሳኔ ንግድ ባንክን ብቻ ሳይሆን አጠቃላይ የፋይናንስ ተቋማት እንዳይጠፉ ያደረገ፣ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክንም ከውድቀት የታደገ ነው በማለት ንግድ ባንክ የነበረበትንና አሁን ቀና ለማድረግ የተሠራውን ሥራ አመልክተዋል፡፡
እንደ አቶ ተክለወልድ ገለጻ፣ ውሳኔው እንዲህ በቀላል የሚታይ ያለመሆኑን፣ የባንኩ የመቀጠልና ያለመቀጠልና የህልውና ጉዳይም ነበር፡፡ እንዲህ ያለውን ውሳኔ ከመወሰን ጀምሮ የባንኩ ዋና ዋና ማነቆ ናቸው የተባሉ ችግሮችን ለመፍታት ብዙ መሠራቱን ያመለከቱት የቦርድ ሰብሳቢው ባለፉት አሥርና 15 ዓመታት ባንኩ ሲሠራባቸው የነበሩ፣ እሳቸው ‹‹የሻገተ›› ያሉትን የባንኩ ፖሊሲ፣ አካሄድ መመርያና የመሳሰሉትን ወደ መቀየር ተገብቶ ተግባራዊ ሆኗል፡፡ ‹‹የ15 ዓመት ፖሊሲው ወረቀቱ ራሱ ሻግቷል፣ ግን በዚህ ነበር የሚመራው፡፡ ፖሊሲው ከአሁናዊ ሁኔታና ዓለም አቀፍ ልምድ አንፃር ተፈትሾ እንዲስተካከል ተደርጓል፡፡ ከባድ ሥራ ነበር፤›› በማለት አሠራሩን ለመለወጥ እንዲህ ያሉ ሥራዎች ጭምር መሠራቱን አመላክተዋል፡፡
ባንኩ ሥር ነቀል ለውጥ ያስፈልገዋል ከተባለ የሰው ኃይሉንም መፈተሽ አስፈላጊ በመሆኑ፣ የሰው ኃይል ፖሊሲውም እየታየ ነው፡፡ ቦርዱ ከዚህ ቀደም አንድ ሺሕ ተተኪ አፍርተናል የሚል ሪፖርት ተመልክቶ የነበረ ሲሆን፣ ወደ ውስጥ ሲገባ ግን የተተኪ ድርቀት ያለበት መሥሪያ ቤት መሆኑ ታይቷል፡፡ 67 ሺሕ ሠራተኛ ያለው የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ፣ ከዚህ ውስጥ 50 በመቶ የሚሆኑት ባለዲግሪ፣ በሺዎች የሚቆጠሩ ማስተርስ ያላቸውን ቢሆኑም የተተኪ ድርቀት አለበት፡፡
ባንኩ አለበት ያሉትን የተተኪ ድርቀት ያሳይልኛል ብለው የጠቀሱት አንድ ባንኩን በፕሬዚዳንትነት የሚመራ መጥፋቱ ነው፡፡ አንድ ፕሬዚንት ማፍራት ባለመቻሉም ፕሬዚዳንት ከሌላ ባንክ ተለምነው መጥተዋል፡፡ ስለዚህ ቀጣይ የቦርዱ የፕሬዚዳንቱ የከፍተኛ ማኔጅመንቱ ዳይሬክተር እስከ ሦስት ዓመት ድረስ ተተኪ የማፍራት ሥራ ዋነኛ ጉዳይ ይሆናል፡፡
ባንኩ ነበረበት ያሉት ሌላው ችግር ባለው ሁኔታ ሠራተኞች እናሸጋሽግ ተብሎ ወደ ሥራ ሲገባ፣ በዳይሬክተር ደረጃ የፆታ ስብጥር ለማድረግ ታስቦ በዚህ ደረጃ የተዘጋጀ ወይም የሚተካ ያለመኖሩ ነው፡፡ የባንኩን ዳይሬክተሮችም ኢትዮጵያን በሚገልጽ ሁኔታ እናሰባጥር ሲባልም፣ ሰው የለም የሚል ምላሽ በመገኘቱ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ሰው ኃይል አጠቃቀምና ስብጥር ብዙ ሥራ እንደሚቀረው ታውቋል፡፡
የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ እንደስሙ ኢትዮጵያን መምሰል እንደሚገባው አስረግጠው ተናግረዋል፡፡ ባንኩ የአንድ ክልል ምክር ቤት ወይም ካቢኔ ሊሆን ስለማይችል ከሁሉም የተውጣጣ ሠራተኛ መኖር መሆን አለበት ብለዋል፡፡
በመሆኑም የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ መለወጥና ዕድገት ሲታስብ ብዙ ሥራዎች የሚጠበቁ እንደሆነ በማመልከትም፣ የኢትዮጵያ የፋይናንስ አካታችነት በተግባር ዕውን እንዲሆንና የፋይናንስ ተደራሽነትና ተጠቃሚነትን ለማጎልበት ሚናው ከፍተኛ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የአሁን ላይ ብድር ከ770 ቢሊዮን ብር በላይ መድረሱ ጥሩ ቢሆንም፣ በቂ አይደለም የሚል የጠነከረ እምነታቸውን አንፀባርቀዋል፡፡ ለዚህ ማሳያ ይሁነኝ ብለው የገለጹት፣ ኢትዮጵያ ውስጥ ካሉ 580 ወረዳዎች 37 በመቶው የአንድም ባንክ ቅርንጫፍ የሌላቸው መሆኑን ነው፡፡
ይህ ማለት ካሉት 18 ባንኮች በ580 ወረዳዎች ውስጥ አንድም ቅርንጫፍ የሌላቸው መሆኑን ነው፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ 14,500 ቀበሌዎች ሲኖሩ፣ በእነዚህ ቀበሌዎች ውስጥ ማክሮ ፋይናንሶችና ኤጀንቶች ተደምረው መድረስ የቻሉት ሁለት ሺሕ ቀበሌዎች አይሞላም፡፡ ስለዚህ 13 ሺሕ ቀበሌዎች የፋይናንስ አገልግሎት ምን እንደሆነ አያውቁም ማለት ነው፡፡
የተጀመሩ ሥራዎች የሚያበረታቱ ቢሆንም፣ ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ እነዚያን 37 በመቶ የሚሆኑ ወረዳዎችን በሚቀጥሉ ዓመታት መድረስ እንዳለበት አመልክተው ለዚህም እየተሠራ ስለመሆኑ ገልጸዋል፡፡
የፋይናንስ ተቋማት ገና ብዙ ሥራ ይጠብቃቸዋል የሚለውን ለማጉላት በአሁኑ ወቅት በአገር ደረጃ እየተሰጠ ያለውን ብድር ጠቅሰዋል፡፡ ለምሳሌ የኢትዮጵ ንግድ ባንክ የተቀማጭ ገንዘብ ወደ 668 ቢሊዮን ብር ተሰባስቧል፡፡ ከዚህ ተቀማጭ ገንዘብ ውስጥ ከ65 በመቶ በላይ የሚሆነው ከአዲስ አበባ የተሰበሰበ ነው፡፡ ሌሎች የአገሪቱ ክፍሎች ተደምረው የተሰበሰበው ተቀማጭ ገንዘብ 35 በመቶ ብቻ ድርሻ ያለው ነው፡፡ ይህም የሚያሳየው የፋይናንስ ተደራሽነት ሥራው ገና ብዙ የሚቀረው መሆኑን ነው፡፡
ከብድር ጋር በተያያዘም አሁን ያለው አጠቃላይ ይዘት ምን እንደሚመስል ባመለከቱበት ገለጻቸው፣ የተሰጠው ብድር ትልቅ ዕድገት ማሳየቱን ነው፡፡ የብድር ምጣኔ ዕድገቱ በ13 በመቶ ጨምሮ 777 ቢሊዮን ብር ደርሷል፡፡ የፋይናንስ አገልግሎት አሁንም ከተማ አካባቢ በመሆኑ፣ ከተሰጠው ብድር ውስጥ ወደ 68 በመቶው ለአዲስ አበባ የተሰጠ ነው፡፡ ስለዚህ ይህንን ማሰባጠር ያስፈልጋል፡፡ ነገር ግን እየተሰጠ ያለው የብድር መጠን እያደገ መጥቷል፡፡ እስከ በጀት ዓመቱ ዘጠነኛ ወር መጨረሻ ድረስ ለግል ዘርፉ የተሰጠው ብድር 273 ቢሊዮን ብር ደርሷል፡፡ ይህ ከዛሬ ዓመት በፊት 81 ቢሊዮን ብር ነበር፡፡ የብድር አሰጣጡ ወደ ግል ዘርፉ ያደላ መሆኑን፣ የባንኩ አጠቃላይ ሀብት በ19 በመቶ አድጎ 934 ቢሊዮን ብር መድረሱን ተናግረዋል፡፡ በሪፎርሙ የተገኘው ውጤት የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ውጤት ብቻ ያለመሆኑን፣ የብዙ ባለድርሻ አካላት ድጋፍና ዕገዛ ታክሎበት እንደሆነም አስምረውበታል፡፡ አሁን በዘጠኝ ወር ያስመዘገበው ውጤት ጥሩ ነው ቢባልም፣ ብዙ የሚቀረው ስለመሆኑ የሚገልጹት አቶ ተክለወልድ፣ ባንኩን ለመለወጥና ዓለም አቀፍ ተወዳዳሪ ለማድረግ ማኢንዚ የተባለ ዓለም አቀፍ የፋይናንስ አማካሪ ተቋም በጨረታ አወዳድሮ በመቅጠር ወደ ሥራ መግባቱ ባንኩን የበለጠ እንደሚለውጠው ተናግረዋል፡፡