የበዓል ሰሞን ገበያ ይደራል፡፡ ሁሉም በአቅሙ ለበዓል የሚሆነውን ለመሸመት ተፍ ተፍ ማለቱ አይቀርም፡፡ ዋጋ ለመጨመር ሰበብ የሚሻው የአገራችን የግብይት ሥርዓት፣ የበዓል ሰሞን ገበያዎችን ‹‹እንደ መልካም አጋጣሚ›› ይጠቀማል፡፡ በልክ ማትረፍ የማይሆንላቸው ዋጋ ይቆልላሉ፡፡ አንዳንዴ በዓልን አስታከው የሚደረጉ የዋጋ ጭማሪዎች አደገኛ የሚያደርጋቸው ዓውደ ዓመቱን አስታኮ የተደረገው ዋጋ ጭማሪ በዚያው የሚቀጥልበት አጋጣሚዎች መኖራቸው ነው፡፡ እንዲህ ያለውን ጭፍን ድርጊት የግብይት ሥርዓታችን ውስጥ በመጥፎ ምሳሌነት ከምንጠቅሳቸው አንዱ ሊሆን ይችላል፡፡ የሰሞኑን የበዓል ዋዜማ ገበያ በወፍ በረር ስቃኝ አንድ ጉዳይ ላይ ከሌሎች በተለየ ትኩረት እንዳደርግበት አድርጎኛል፡፡
ይህም በሰሞኑ ገበያ ከሌሎች በበዓሉ ከሚፈለጉ ምርቶች ውስጥ በአዲስ አበባ የምግብ ቅቤ እየተሸጠበት ያለው ዋጋ ብዥታ የሚፈጥር ሆኖ ማግኘቴ ነው፡፡ ወደ ገበያ ከመውጣቴ በፊት የአንድ ኪሎ የቅቤ ዋጋ 600 ብር ገባ የሚለው ወሬ እዚህም እዚያም ሲናፈስ ሰምቼ ነበርና፣ ቅቤ በሁለት ወራት ልዩነት ዋጋው ከእጥፍ በላይ እንዴት ሊጨምር ይችላል ብዬ በእጅጉ ከንክኖች ስለነበር በተወሰነ ደረጃ ገበያውን ለመቃኘት ሞክሬያለሁ፡፡
አንድ ኪሎ ቅቤ ዋጋ በእርግጥም ዋጋው ከቀደመው ጊዜ የበለጠ እየተጠየቀበት መሆኑን ተረድቻለሁ፡፡ እንደ ቅቤው ዓይነት ዋጋው ቢለያይም፣ በቅቤ መደቦች (ገበያ) አንዱ ኪሎ ቅቤ ዝቅተኛ ዋጋው 400 ብር መሆኑን የተገነዘብኩ ቢሆንም፣ በዚህን ያህል ዋጋ ቅቤ የሚሸጥባቸው መደብሮች ጥቂት ነበሩ ማለት ይቻላል፡፡ አብዛኞቹ መደብሮች በተለይ ለጋ ቅቤ ከ400 ብር በላይ ዋጋ አውጥተውለት እየሸጡ ነው፡፡ በሌላ ገበያ ደግሞ 450 ብር፣ 470 ብር ሁሉ እየተሸጠ የነበረ ሲሆን፣ አንዱ ኪሎ ቅቤ 600 ብር እየተሸጠ ነው መባሉንም ሰምቻለሁ፡፡ ነገር ግን ተባልኩ እንጂ ገዛሁ ያለኝ ሰው አልነበረም፡፡ ስለዚህ አንድ ኪሎ ቅቤ 600 ብር ገባ በሚለው መከራከሩን ትተን በሁለት ሦስት ወራት ልዩነት የአንድ ኪሎ ቅቤ በአንዴ ከ400 እስከ 500 ብር እየተሸጠ መሆኑ በራሱ ብዙ የሚያነጋግር ነው፡፡ የቅቤ ዋጋ ላይ አሁን በገበያ ሲሸጥ ከነበረበት ዋጋ አንፃር ከፍተኛ የሚባል የዋጋ ጭማሪ ተደርጓል፡፡ ምክንያቱም ከሁለትና ከሦራት ወራት በፊት በአማካይ ከ300 ብር ባነሰ ዋጋ ይሸጥ ስለነበር፣ በአንዴ መቶና ሁለት መቶ ብር ጨመረ ሲባል ማስደንገጡ አይቀርም፡፡
በዓል ስለሆነ የተደረገ ጭማሪ ነው ቢባል እንኳን እንዲህ ባለ ደረጃ በቅቤ ላይ ጭማሪ የተደረገበት ወቅት አለ ማለት አይቻልም፡፡ ስለዚህ የሰሞኑ የቅቤ ዋጋ ምክንያታዊ ካለመሆኑም በላይ በበዓል ስም የተደረገው የተጋነነ የዋጋ ጭማሪ የተጋነነ ነው ተብሎ የሚታለፍ አይደለም፡፡ ምክንያቱም ከመደበኛ የቅቤ መገበያያ ሥፍራዎች ውጪ አንድ ኪሎ ቅቤ እስከ 350 ብር ሲሸጥ ስለነበር ነው፡፡
በአንዳንድ የገበያ ቦታዎችም 350 ብር ሲሸጥ እንደነበር መታዘብ ይቻላል፡፡ ተመሳሳይ የጥራት ደረጃ ያለው ቅቤ አንደኛው 570 ብር፣ ሌላኛው ደግሞ 350 ብር የገዙ ሸማቾች አሉ፡፡ ስለዚህ የቅቤው ዓይነት የቱንም ያህል ቢለያይ፣ በዚህን ያህል ደረጃ የዋጋ ልዩነት ሊኖረው ለምን እንደቻለ መመርመር ያስፈልጋል፡፡ በገበያ ውስጥም ከገበያ ውጪም የሚሸጠው ቅቤ በአብዛኛው ከተለመዱ አካባቢዎች የመጣ ይዘቱም አንድ መሆኑን የሚጠቅሱ ሸማቾች እንዴት የዚህን ያህል ልዩነት አመጣ ብለው ስለሚጠይቁም ነው፡፡ ይህ የሚያሳየን ሆን ተብሎ ዋጋን በማጦዝ የተሠራ ሥራ መኖሩን ነው፡፡ በግብይት ሥርዓቱ ውስጥ ሆን ተብሎ ዋጋ መስቀልና ውዥንብር መፍጠርም የተለመደ ሆኗል፡፡
የሰሞኑ ገበያ ዋጋ መናር ሰው ሠራሽ ስለመሆኑ ማረጋገጥ የሚቻልበት አንድ ማሳያ የሚሆነው ከገበያ ውጪ የአንድ ኪሎ ቅቤ ዋጋ በ350 ብር እንደ ልብ መሸጡን መታዘቤ ነው፡፡ ይህ የሚያሳየን በእርግጥም ቅቤን የሚያስወድድ ነገር ተፈጥሮ ሳይሆን የተለመደውና በስንጥቅ ትርፍ የመክበር ክፉ ልማዳችን የፈጠረው ነው፡፡
ዛሬ ኅብረተሰብ ኑሮ ተወደደ፣ ሸምተን ለመብላት እየተቸገርን ነው፣ እያለ በሚጮህበት ጊዜ፣ ሆን ተብሎ ያላግባብ የሚደረጉ የዋጋ ጭማሪዎችም የኑሮ ውድነቱን እንዲያበዙ አድርጓል፡፡
ከሰሞኑ የቅቤ ገበያ መታዘብ የምንችለውም ይህንኑ ነው፡፡ ቅቤ ተወደደ ለማስባል ቀደም ብሎ ቅቤ ዋጋው 600 ብር፣ 500 ብር ገባ በማለት የተነዛው ወሬ፣ ቅቤ ጠፍቶና ሊያስወድደው የሚችል ነገር ተፈጥሮ ሳይሆን፣ ገበያን ለመበረዝ የተሠራው ሥራ ሊሆን እንደሚችል መገንዘብ ይቻላል፡፡ ስለዚህ የግብይት ሥርዓታችን አካሄድ እንዲህ ባለ ብልሹ ድርጊቶች የታጀለ ሆኖ መቀጠል ኅብረተሰቡንም ለበለጠ ምሬት እየዳረገው ነው፡፡
በበዓል ሰሞን የተጨመረ ዋጋ በዓሉ ካለፈ በኋላ በዚያው የሚቀጥል መሆኑም ሌላው ችግር ነው፡፡ ይህ በቅቤ ላይ ብቻ ሳይሆን በሌሎች ምርቶች ላይም የሚታይ ነው፡፡ ከልምድ እንደምናየው ለዓውደ ዓመት ተብለው የተደረጉ ጭማሪዎች በዚያው ይቀጥላሉ፡፡ ለዚህ ሥጋ ጥሩ ማሳያ ነው፡፡ ሥጋ ቤቶች ሁለት ወራት የዘጉትን በር ሲከፍቱ ዋጋ አክለው የሚመጡ ስለመሆናቸው ልብ ሊባል ይገባል፡፡
ይህ ምክንያታዊ ያልሆነ ጭማሪ ከበዓል በኋላም እየቀጠለ ይሄዳል፡፡ እንዲህ ያለውን ብልሹ አሠራር ማን ሃይ ይበለን? የሚለው ጥያቄያችን ዛሬም የሚነሳ ሲሆን፣ ያላግባብ የሚደረጉ ጭማሪዎች ጉዳይ ልክ እያጡ፣ ተቆጣጣሪም የሌላቸው ሆነዋልና የመፍትሔ ያለ እንላለን፡፡ መልካም በዓል!