አምና ይካሄዳል ተብሎ ሲጠበቅ የነበረው ስድስተኛው ጠቅላላ ምርጫ፣ ዓለም አቀፍ ወረርሽኝ ሆኖ በተከሰተው የኮቪድ-19 ወረርሽኝ ሳቢያ ወደ ዘንድሮ ተሸጋግሮ የፊታችን ግንቦት 28 ቀን 2013 ዓ.ም. በአገር አቀፍ ደረጃ፣ ሰኔ 5 ቀን 2013 ዓ.ም. ደግሞ በአዲስ አበባና በድሬዳዋ ከተማ አስተዳደሮች እንዲካሄድ ቀን ተቆርጦለት የተለያዩ እንቅስቃሴዎች በመከናወን ላይ ናቸው፡፡
የዘንድሮ ጠቅላላ ምርጫ የፌዴራልና የክልል ምክር ቤት አባላትን ከመምረጥ ባለፈ፣ አዲስ ለተመሠረተው የብልፅግና ፓርቲ በአገሪቱ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ከመገንባት አንፃር ዓይነተኛ ፈተና እንደሆነ የሚገልጹ በርካቶች ናቸው፡፡
ከዚህ አኳያ በተቃውሞ ጎራው የሚገኙ የተወሰኑ ፖለቲከኞች ግንቦት 28 ቀን 2013 ዓ.ም. የሚካሄደውን ጠቅላላ ምርጫ እንደ ስድስተኛ ሳይሆን እንደ መጀመርያ ምርጫ የሚቆጠር ነው በማለት የሚጠቅሱት ቢሆንም፣ በሒደቱ ግን አጋጠመን የሚሉትን በርካታ ውጣ ውረድ በዝርዝር በማቅረብ መታረም ያለባቸው በርካታ ጉዳዮች እንዳሉ በመጥቀስና አፋጣኝ መፍትሔ በመሻት ላይ ይገኛሉ፡፡
ስድስተኛውን ጠቅላላ ምርጫ በስኬት ለማከናውን እየተንቀሳቀሰ የሚገኘው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የተለያዩ መርሐ ግብሮችን ያከናወነ ሲሆን፣ አሁን የመጨረሻ ምዕራፍ ሊሰኝ የሚችለውን የመራጮች ምዝገባ እያከናወነ ነው፡፡
ምንም እንኳን ቦርዱ የምርጫ ጊዜ ሰሌዳውንና መርሐ ግብሮቹን ይፋ ቢያደርግም፣ ከክልሎች አስተዳደር አካላት ያለመተባበር፣ በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች በሚያጋጥሙ የፀጥታ ሥጋቶች ሳቢያ በመጀመርያ የወጣውን የጊዜ ሰሌዳ ሲከልስና ቀድመው የወጡ መርሐ ግብሮችን ለማራዘም ሲገደድ ተስተውሏል፡፡
ከመጀመርያው የዕጩዎች ምዝገባ በታቀደለት ዕለት አለመጀመሩን ተከትሎ የፖለቲካ ፓርቲዎች ባቀረቡት አቤቱታ ሳቢያ መራዘሙ የሚታወስ ሲሆን፣ አሁን በመከናወን ላይ የሚገኘው የመራጮች ምዝገባም ቢሆን ይጠናቀቃል ከተባለበት ሚያዝያ 15 ቀን 2013 ዓ.ም. ከሁለት እስከ ሦስት ሳምንታት ጊዜ መራዘሙን ከግምት በማስገባት፣ ቦርዱ ነገሮች አልጋ በአልጋ እንዳልሆነለት ማሳያ እንደሆነ የሚገልጹ በርካቶች ናቸው፡፡
ቦርዱ ከፀጥታና ከቁሳቁስ አቅርቦት አንፃር ከሚገጥሙት ፈተናዎች ባሻገር፣ በዚህ ምርጫ ላይ ጥላውን ያጠላበት ሌላው ጉዳይ ደግሞ በኦሮሚያ ክልል የሚወዳደሩ ተቃዋሚ ፓርቲዎች በተለይ የኦሮሞ ነፃነት ግንባር (ኦነግ) እና የኦሮሞ ፌዴራሊስት ኮንግረስ (ኦፌኮ) ከምርጫው ራሳቸውን ማግለላቸው ተጠቃሽ ነው፡፡
ምንም እንኳን ስድስተኛው ጠቅላላ ምርጫ በቦርዱ በኩልም ሆነ በተወሰኑ ተቃዋሚዎች ዘንድ ፈታኝ የሆኑ ተግዳሮቶች እንዳጋጠሙት የሚገለጽ ቢሆንም፣ በምርጫው የሚሳተፉ ፓርቲዎች ደግሞ የምርጫ ማኒፌስቶአቸውን ይፋ በማድረግ፣ ቢመረጡ ለመጪዎቹ አምስት ዓመታት ለመሥራት የተለሙትን ዕቅድ በማቅረብ ቃል በመግባት ላይ ይገኛሉ፡፡
በምርጫው የሚሳተፉት ገዥው ብልፅግና ፓርቲ፣ እንዲሁም ተቃዋሚ ፖለቲካ ፓርቲዎች ማኒፌስቶአቸውን ለሕዝብ ያቀረቡ ሲሆን፣ በአጠቃላይም ቢመረጡ ለማከናወን ያቀዷቸውን ትልሞች ከማቅረብ ባሻገር፣ በተመሳሳይ ዜጎች በመብታቸው ተጠቅመው የሚፈልጉትን ዓይነት መንግሥትና አስተዳደር እንዲመሠርቱ ጥሪ በማቅረብ ላይ ናቸው፡፡
ከዚህ አንፃር ገዥው ፓርቲ ብልፅግናም ሆነ ተቃዋሚ ፓርቲዎች ያላቸውን ራዕይ፣ ተልዕኮ፣ እንዲሁም ዝርዝር አቋሞችን በተመሳሳይ ያቀረቡ ሲሆን፣ አብዛኞቹ ሪፖርተር የተመለከታቸው ማኒፌስቶዎች ለብሔራዊ መግባባትና ስምምነት ቅድሚያ ሰጥተው እንደሚሠሩ ያትታሉ፡፡ ከዚህ በተጨማሪም ፓርቲዎች ቢመረጡ በመጪዎቹ አምስት ዓመታት ለመተግበር ያቀዷቸውን ፖለቲካዊ፣ ማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ፣ እንዲሁም ከውጭ ግንኙነት አንፃር ያላቸውን አማራጭ ሐሳብ ያካተቱበትን ማኒፌስቶ አቅርበዋል፡፡ በማኒፌስቶዎቹ ውስጥ ተመሳሳይነት ያላቸው ጉዳዮች ያሉትን ያህል፣ እያንዳንዳቸው ፖለቲካ ፓርቲዎች ቢመረጡ በልዩነት ለመከወን ያለሙዋቸውን ጉዳዮች እንደሚከተለው ይቃኛሉ፡፡
የባህር በር ባለቤትነት ድርድር የሚጠይቀው ኢሶዴፓ
በመሠረታዊ የአገሪቱ ጉዳዮች ላይ ብሔራዊ መግባባት መፍጠር ለአገሪቱ እጅግ አስፈላጊ መሆኑን በመጥቀስ፣ ለዚህ ዓላማ ተግባራዊነት ከፍተኛ ትኩረት ሰጥቶ እንደሚሠራ በማኒፌስቶው ያስታወቀው በአንጋፋው ፖለቲከኛ በየነ ጴጥሮስ (ፕሮፌሰር) የሚመራው የኢትዮጵያ ሶሻል ዴሞክራቲክ ፓርቲ (ኢሶዴፓ) ነው፡፡ በዚህም መሠረት፣ ‹‹በመሠረታዊ የአገራችን ጉዳዮች ላይ ሁሉም የፖለቲካ ኃይሎች የሚወያዩበትና በጋራ መግባባት ላይ የሚደርሱበትን የውይይት መድረክ እንዲዘጋጅና ብሔራዊ መግባባት ላይ እንዲደረስ ሁኔታዎችን ያመቻቻል፤›› በማለት፣ ፓርቲው ተመርጦ ሥልጣን ሲይዝ አስቀድሞ የሚያከውነው ብሔራዊ መግባባትን ለማምጣት የሚያስችል መድረክ መፍጠር መሆኑን አስታውቋል፡፡
በአገሪቱ የፖለቲካ ልሂቃን ዘንድ በተደጋጋሚ ከሚነሱ አወዛጋቢ ጉዳዮች አንዱ የባህር በር ባለቤትነት የተመለከተው ነው፡፡ ከዚህ አንፃር የኢትዮጵያ ጥቅሞችና መብቶች ለሌላ ወገን አሳልፈው የሰጡትንና የሚሰጡትን ስምምነቶች እንደማይቀበል በመግለጽ፣ ‹‹የባህር በር ባለቤትነትን ጉዳይ እንደገና ድርድር እንዲካሄድበትና በአግባቡ መብታችንንና ጥቅማችንን በሚያስከብር መልኩ ለሰላማዊ መፍትሔ ያለመታከት ይሠራል፤›› በማለት ኢሶዴፓ በጉዳዩ ላይ ያለውን አቋም በማኒፌስቶው አማካይነት ይፋ አድርጓል፡፡
ከዚህ በተጨማሪም፣ ‹‹ኢሶዴፓ ተመርጦ ሥልጣን ቢይዝ ሌሎች የአገሪቱ ቋንቋዎች የሥራ ቋንቋ እንዲሆኑ እንደሚሠራም፣ ከአማርኛ በተጨማሪም ሰፊና ብዛት ያላቸው ሕዝቦች የሚናገሯቸውን ቋንቋዎች ተጨማሪ የፌዴራል መንግሥቱ የሥራ ቋንቋዎች ይሆናሉ፤›› በማለት ቃል ገብቷል፡፡
ፓርቲው ከሚከተለው የሶሻል ዴሞክራሲ ርዕዮተ ዓለም ጋር በሚጣጣም ሁኔታ፣ በርካታ መሠረታዊ አገልግሎቶችን ለዜጎች ከክፍያ ነፃ አሊያም ደግሞ በዝቅተኛ ከፍያ ለመስጠት የተለመው ኢሶዴፓ ሴተኛ አዳሪዎችን፣ ጎዳና ተዳዳሪዎችንና በልመና ሕይወታቸውን የሚመሩ ዜጎችን ማኅበራዊ ዋስትና ለማረጋገጥ እንደሚሠራም ቃል ገብቷል፡፡
ከዚህ በተጨማሪም አካል ጉዳተኞች ችግሮቻቸውን ያገናዘቡ የትምህርትና የሙያ ሥልጠናዎች እንዲያገኙ እንደሚያደርግ፣ እንዲሁም ጧሪ ቀባሪ ያጡ አረጋውያንና ወላጅ አልባ ሕፃናት በመንግሥትና በተለያዩ በመንግሥታዊና መንግሥታዊ ባልሆኑ ድርጅቶች አማካይነት እንክብካቤ እንደሚደረግላቸው ፓርቲው ቃል ይገባል፡፡
በአሁን ወቅት በአገሪቱ የተለያዩ ክልሎች የተዋቀረው ‹‹ልዩ ኃይል›› ከፍተኛ የደኅንነት ሥጋት እንደሆነ የሚገልጸው ኢሶዴፓ፣ ቢመረጥና የመንግሥት ሥልጣን ቢይዝ ይህን ኃይል በማፍረስ በፖሊስ ደረጃ እንዲደራጅ እንደሚያደርግም ቃል ገብቷል፡፡
የነእፓ የአካታች ብሔረ መንግሥት ግንባታ ጥሪ
በቅርቡ የአገሪቱን የፖለቲካ ምኅዳር ከተቀላቀሉት ፓርቲዎች ለዘብተኛ ሊበራሊዝም እንደሚከተል የሚገልጸው ነፃነትና እኩልነት ፓርቲ (ነእፓ) አንዱ ሲሆን፣ ፓርቲው በስድስተኛው ጠቅላላ ምርጫ ዋነኛ ተፎካካሪ ለመሆን እየሠራ መሆኑን ከመጥቀስ ባለፈ፣ ዝርዝር አገራዊ ጉዳዮችን ያካተተ የምርጫ ማኒፌስቶውን ይፋ አድርጓል፡፡
ነእፓ በዋነኛነት የአገሪቱ የታሪክ ትርክት ላይ መዛነፍ እንዳለ በመግለጽ፣ ይህንንም ለማረም እንደሚሠራ በመግለጽ ይኼም፣ ‹‹አካታች የሆነ ብሔረ መንግሥት መገንባት›› የሚለው ዋነኛ አጀንዳው እንደሚሆን በማኒፌስቶው አስታውቋል፡፡
‹‹በኢትዮጵያ ለነገ ተስፋና አብሮነት መሠረት የሚጥል ሚዛናዊ የሆነ የአገረ መንግሥት የታሪክ አረዳድ ያስፈልጋል፤›› ብሎ የሚያምነው ነእፓ፣ የአገሪቱ የቀደመ ታሪክ የድልና የከፍታ አሊያም የሽንፈትና የጭቆና ብቻ እንደነበር በመጥቀስ፣ ሁለቱንም የታሪክ ምዕራፎች በቅጡ መረዳት፣ መተንተንና ማስተጋባት ተገቢ እንደሆነ በማኒፌስቶው ያትታል፡፡
በመሆኑም፣ ‹‹የኢትዮጵያን ነባራዊ ሀቅ ታሳቢ ያደረገና ነገን የተሻለ ለማድረግ የሚያግዝ ሚዛናዊ የአገር ግንባታ ታሪክና አረዳድ መፍጠር፣ ለዛሬ መግባባትም ሆነ ለነገ አብሮነት ቁልፍ ሚና ይኖረዋል፤›› በማለት ነእፓ፣ ይህንን አጀንዳ ለማሳካት እንደሚሠራ አስታውቋል፡፡
ከዚህ ቀደም የአገሪቱ የፌዴራሊዝም ሥርዓት አተገባበር በርካታ ችግሮች እንዳለበት የሚገልጸው ነእፓ፣ በተለይም የሚከተሉትን መሠረታዊ ችግሮች በአገሪቱ ሲተገበር የቆየው ፌዴራሊዝም መገለጫ እንደሆነ ይገልጻል፡፡ እነዚህም ፌዴራሊዝሙ ‹‹እውነተኛ አልነበረም፣ ዴሞክራሲ አልባ ነበር፣ የግለሰቦችንና የህዳጣንን መብት ማክበር አልቻለም፣ ግጭትና መፈናቀል አስከትሏል፣ የሕግ የበላይነት አለመከበር፣ እንዲሁም አገራዊ አለመግባባት›› የሚሉ ሲሆን፣ እነዚህን ችግሮች ለመፍታትና ‹‹እውነተኛ›› ፌዴራሊዝም ለመተግበር ፓርቲው አሸንፎ ሥልጣን ቢይዝ የሚገነባው የፌዴራል ሥርዓት፣ ‹‹የክልሎች የድንበር አወሳሰን የሕዝብ ፍላጎትን፣ ቋንቋን፣ ባህልን፣ የአስተዳደር ምቹነትን፣ እንዲሁም መልክዓ ምድርን ታሳቢ ያደረገ›› እንዲሆን እንደሚሠራ አስታውቋል፡፡
ለትምህርት ከፍተኛ ትኩረት የሚሰጠው ነእፓ፣ በማኒፌስቶው ላይም የፓርቲው ዕቅዶች ማጠንጠኛ ‹‹ትምህርት ተኮር የልማት ስትራቴጂ›› እንደሆነ ገልጿል፡፡
‹‹አገራችን ያሉባትን ውስብስብ ችግሮች ለመፍታት ዋናውና አስተማማኝ መሣሪያ ትምህርት ነው፤›› የሚለው ነእፓ፣ ‹‹ትምህርት ሰዎች በግል ሕይወታቸው እንዲያውቁ፣ እንዲሠሩና የሕይወት ግባቸውን ማሳካት እንዲችሉ የሚያግዛቸው ሲሆን፣ በማኅራበራዊ ሕይወታቸው ሰላምንና ጠንካራ ማኅበራዊ መስተጋብርን እንዲፈጥሩ ያስችላቸዋል፡፡ ትምህርት የለውጥ፣ የነፃነት፣ የእኩልነትና የዕድገት ቁልፍ ነው፤›› የሚል እምነት እንዳለው በመጥቀስ፣ ጥራቱን የጠበቀ ትምህርት በማስፈን የአገሪቱን ችግር ለመፍታት በምርጫው ጎራ መሠለፉን ነእፓ በማኒፌስቶው ይገልጻል፡፡
ለዜጎች እኩል የሕይወት ዕድል የሚለው ኢዜማ
በመጪው ምርጫ ከሚሳፉ ፓርቲዎች አንዱ የሆነው የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትሕ (ኢዜማ) በበርካታ ጉዳዮች ላይ የሚያተኩር ማኒፌስቶውን ይፋ ካደረገ ሰነባብቷል፡፡ ይህ ፓርቲ ከሚከተለው የማኅበራዊ ፍትሕ ፖለቲካዊ ፍልስፍና አንፃር የተቃኘ በርካታ አዳዲስ ጉዳዮችን ያካተተ ማኒፌስቶ ለሕዝብ የቀረበ ሲሆን፣ አሁን በአገሪቱ ካለው ብሔር ተኮር ፖለቲካ በተቃራኒ የዜግነት ፖለቲካን መለያው አድርጎ እየሠራ እንደሆነ በማኒፌስቶው ያብረራል፡፡ በዚህም መሠረት ከማኅበራዊ ፍትሕ የፖለቲካ ፍልስፍናው የተቀዳ፣ ‹‹ዜጎች እኩል የሕይወት ዕድል ሊኖራቸው ይገባል፤›› የሚል አቋምን በመከተል ለሁሉም እኩል የሚያገለግል ሥርዓት ለመፍጠር በማኒፌስቶው ቃል ይገባል፡፡
ከዚህ ባሻገርም አሁን በአገሪቱ እየተተገበረ የሚገኘው የፌዴራል ሥርዓት ችግር ያለበት በመሆኑ፣ ሰፋ ወዳለና ሁሉንም አካታች በሆነ መንገድ ሊገነባ እንደሚገባ፣ ኢዜማም ይህን ለማድረግ የተለያዩ አቅጣጫዎችንና አማራጭ ሐሳቦችን ማዘጋጀቱን ይገልጻል፡፡
‹‹የዘውግ ማንነትን መሠረት ያደረገውን አግላይ መንግሥታዊ የፖለቲካ ሥርዓትና አደረጃጀት›› ሁሉም ዜጎች በእኩልነት ወደሚስተናገዱበት መንግሥታዊ የፖለቲካ ሥርዓት ለመቀየር ቁርጠኛ እንደሆነ የሚገልጸው ኢዜማ፣ ለተቋማት ግንባታ ከፍተኛ አትኩሮት በመስጠት በከፍተኛ ደረጃ በሠለጠኑ ባለሙያዎች የሚመሩ የደኅንነት ማኅበረሰብ፣ የመከላከያ ኃይልና የዴሞክራሲያዊ ተቋማትን ከፖለቲካ ወገንተኝነት በፀዳ መንገድ እንደሚገነባ ቃል ይገባል፡፡
ከ1960ዎቹ ጀምሮ በአገሪቱ የፖለቲካ ልሂቃን ዘንድ አጨቃጫቂ ከሆኑ ፖለቲካዊ ጉዳዮች አንዱና ዋነኛው የመሬት ባለቤትነት ጥያቄ በመሆኑ፣ ይህን ጥያቄ ‹‹በማያዳግም ሁኔታ›› ለመመለስ እንደሚሠራ የሚገልጸው ኢዜማ፣ በዚህም መሠረት መሬትን ‹‹በግል፣ በማኅበረሰብና በመንግሥት ይዞታነት›› እንዲያዝ እንደሚያደርግ በማኒፌስቶው ይፋ አድርጓል፡፡
አገሪቱ ውስጥ መሠረታዊ የሆነ ፖለቲካዊ፣ ማኅበራዊ፣ እንዲሁም ኢኮኖሚዊ ለውጥ ለማምጣት የሕገ መንግሥት መሻሻል አስፈላጊ ነው ብሎ የሚያምነው ኢዜማ፣ ‹‹በ2013 ምርጫ አሸናፊ ከሆነ ቅድሚያ ሰጥቶ ከሚሠራቸው ሥራዎች ውስጥ አንዱና ዋነኛው አሁን በሥራ ላይ ያለው ሕገ መንግሥት መሻሻል አለበት? ወይስ የለበትም? የሚል ሕዝበ ውሳኔ እንዲካሄድ ማድረግ ነው፤›› በማለት፣ ሕገ መንግሥታዊ ማሻሻያውን በፓርቲው ውሳኔ ከማድረግ ይልቅ ወደ ሕዝቡ እንደሚያቀርበው ይገልጻል፡፡
ለብሔራዊ መግባባትና አገራዊ ዕርቅ ቅድሚያ የሰጠው ኅብር ኢትዮጵያ
ብሔራዊ መግባባትና አገራዊ ዕርቅ ሳይደረግ ወደ ምርጫ መግባት የለብንም በማለት ሲሟገት የሰነበተው ኅብር ኢትዮጵያ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (ኅብር ኢትዮጵያ)፣ አሁንም ወደ ምርጫው የገባው ‹‹አማራጭ አጥቶና አገርን ለማዳን›› እንደሆነ በማኒፌስቶው የገለጸ ሲሆን፣ በምርጫው አሸንፎ መንግሥት ቢመሠርት በአገሪቱ ዘላቂ የሆነ ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊ፣ ማኅበራዊና ሥነ ልቦናዊ ለውጥና መረጋጋትን ለመፍጠር የሚያስችል የብሔራዊ መግባባትና ዕርቀ ሰላም መድረክ ዕውን እንደሚያደርግ ከማስታወቅ ባሻገር፣ ይህ አጀንዳም ከማናቸውም ጉዳዮች የቀደመ ተግባሬ ይሆናል ብሏል፡፡
ከዚህም ባሻገር፣ ‹‹በአገሪቱ በብሔራዊ መግባባት መርህ መሠረት ወደ ዴሞክራሲዊ የሽግግር ሒደት የምታደርገው ዕርምጃ እስኪጠናቀቅ ድረስ የመከላከያ፣ የክልልም ሆነ የፌዴራል ፖሊስ ኃይሎች፣ እንዲሁም የደኅንነት መዋቅሩ ተጠሪነቱ ለብሔራዊ መግባባትና የሽግገግር ሸንጎ ብቻ እንዲሆን ይደረጋል፤›› በማለት፣ ፓርቲው ምርጫ አሸንፎ እንደሚያቋቁመው የገለጸው የሽግግር ሸንጎ ወደ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት የሚደረገውን ሽግግር በበላይነት እንደሚመራ አስታውቋል፡፡
ኅብር ኢትዮጵያ ምንም እንኳን በቀጥታ ስም ባይጠቅስም፣ ‹‹ለብሔራዊ ደኅንነት ሥጋት የሆኑ የጎረቤት አገሮች ወታደሮችና የደኅንነት ሠራተኞች በአስቸኳይ ከአገራችን ለቀው እንዲወጡ ያደርጋል›› በማለት፣ በምርጫውን ቢያሸንፍ የሚወስደውን ሌላ ዕርምጃ ይፋ አድርጓል፡፡
የአገር መከላከያ ሠራዊት የሚለውን ስያሜ ወደ ‹‹የኢትዮጵያ ብሔራዊ ሠራዊት›› እንደሚቀይር የሚገልጸው ኅብር ኢትዮጵያ፣ ሠራዊቱን ለማዘመንም የተለያዩ የተሃድሶ ሥራዎች እንደሚሠራም ቃል ይገባል፡፡
መደመርን ማዕከል ያደረገው ብልፅግና
አዳዲስ የ‹‹እፈጽማለሁ›› ቃል ከመግባት ይልቅ እስካሁን የተመዘገቡትን ድልና ስኬቶች በመደመር ፍልስፍና አጠናክሮ ለመቀጠል ቃል የሚገባው የገዥው ብልፅግና ፓርቲ ማኒፌስቶ በበኩሉ፣ ከተመረጠ የእስካሁን ውጤቶችን አጠናክሮ እንደሚቀጥል ይገልጻል፡፡
ሆኖም አብዛኞቹ ፓርቲዎች እንደሚሉት ብልፅግናም፣ ‹‹ለአገረ መንግሥታችን ቀጣይነት መሠረታዊ በሆኑ ብሔራዊ ጉዳዮች ላይ ብሔራዊ መግባባት ላይ ለመድረስ፣ ሁሉንም የአገራችን ሕዝቦች አካታች በሆነ መልኩ የውይይት ዓውድ እንዲፈጠር ይሠራል፤›› በማለት ሐሳቡን ያጋራል፡፡
ከዚህ አንፃር፣ ‹‹የአገሪቱ ልሂቃን ለብሔራዊ መግባባት የሚኖራቸው ሚና ከፍተኛ እንደሆነ እንደሚገነዘብ የሚገልጸው ብልፅግና፣ ‹‹የፖለቲካ ልሂቃን ለብሔራዊ መግባባት የሚጠበቅባቸውን ሚና እንዲጫወቱ፣ በጥናት ላይ የተመሠረተ ውይይትን የሚያስቀድሙ ድርድሮችን ከሁሉም የአገራችን የፖለቲካ ልሂቃንና ፓርቲዎች ጋር በማድረግ የብሔራዊ መግባባት ለማዳበር አበክሮ ይሠራል፤›› በማለት በማኒፌስቶው ያትታል፡፡
የመንግሥት ተቋማት ወደ ግል ይዞታ ለማዛወር መሥራቱን እንደሚቀጥል የሚገልጸው ብልፅግና ‹‹ፓርቲያችን መንግሥት በባለቤትነት በሚያስተዳድራቸው የንግድ ተቋማት የሚታየውን ደካማ ምርታማነት ለመቅረፍ በጥናት ላይ ተመሥርቶ፣ ተቋማቱ በከፊል ወይም ሙሉ በሙሉ ወደ ግል እንዲዛወሩ የማድረግ ሥራ ይሠራል፤›› በማለት፣ የመንግሥትን የንግድ ተቋማት ወደ ግል የማዛወሩ እንቅስቃሴ እንደሚቀጥል አስታውቋል፡፡
የአገሪቱን ዜጎች ከዕለት ወደ ዕለት እየፈተነ የሚገኘውን የዋጋ ግሽበትን ለመከላከል የአቅርቦት እጥረት ያለባቸው ሸቀጣ ሸቀጦች ላይ ለሚሰማሩ አምራቾች ልዩ ማበረታቻ እንደሚጥ የሚገልጸው ብልፅግና፣ ‹‹እጥረት ያለባቸው ምርቶች ከፍ ባለ መጠን እንዲመረቱ በማድረግ ኅብረተሰቡ በአነስተኛ ዋጋ የተለያዩ ሸቀጣ ሸቀጦችን እንዲያገኝ ይደረጋል፤›› በማለት፣ የዋጋ ግሽበትን ሊያስቀር ይችላል ያለውን የመፍትሔ አቅጣጫ በማኒስቶው አመላክቷል፡፡
የአገልግሎት ተደራሽነትን ከማስፋፋት አንፃር ደግሞ፣ ‹‹ኦፍ ግሪድና ግሪድ አማራጮችን በመጠቀም በአምስት ዓመቱ መቶ በመቶ የመብራት አቅርቦትን ለማዳረስ ይሠራል፤›› በማለት ቃል ይገባል፡፡
እነዚህ ከላይ የተዘረዘሩት ሐሳቦች ፓርቲዎቹ ቢመረጡ በመጪዎቹ አምስት ዓመታት ለመፈጸም ቃል የገቧቸው ትልሞች ናቸው፡፡ ምን ያህሉ እንደሚፈጸሙ፣ ምን ያህሉ ደግሞ ቃል ብቻ ሆነው እንደሚቀሩ ለማየት ከምርጫው በኋላ ያሉት አምስት ዓመታት ይጠበቃሉ፡፡