በቅርቡ በአሜሪካው ፕሬዚዳንት ጆ ባይደን የአፍሪካ ቀንድ ጉዳዮች ልዩ መልዕክተኛ ሆነው የተሾሙት አንጋፋው ዲፕሎማት ጄፍሪ ፊልትማን በአፍሪካ ቀንድ ያለውን ቀውስ ለመፍታት በሚደረገው ጥረት ኢትዮጵያን ጨምሮ በሱዳን፣ በግብፅና በኤርትራ ጉብኝታቸውን ማክሰኞ ሚያዚያ 26 ቀን 2013 ዓ.ም. ጀመሩ፡፡
ልዩ ልዑኩ ወደ ምሥራቅ አፍሪካ አገሮች የሚያደርጉት ጉብኝት በኢትዮጵያ ያለውን ቀውስ፣ የህዳሴ ግድብን፣ የኢትዮጵያንና የሱዳን የድንበር ውዝግብ፣ እንዲሁም ሌሎች ቀጣናዊ ጉዳዮች ላይ መፍትሔ ማፈላለግ ያለመ እንደሆነ ለማወቅ ተችሏል፡፡
ከአንድ ሳምንት በላይ በሚዘልቀው የልዩ መልዕክተኛው የአራቱ አገሮች ጉብኝት ወቅት ከየአገሮቹ መሪዎች፣ ከተባበሩት መንግሥታት ድርጅትና ከአፍሪካ ኅብረት ኃላፊዎች፣ እንዲሁም ከሌሎች የፖለቲካና የሰብዓዊ ዕርዳታ ባለድርሻ አካላት ጋር እንደሚወያዩና እንደሚመክሩ፣ የአሜሪካ ኤምባሲ ለሪፖርተር ከላከው መግለጫ መረዳት ተችሏል፡፡
የልዩ ልዩ መልዕክተኛው ጉብኝት በአፍሪካ ቀንድ አካባቢ በፀጥታ፣ በፖለቲካ፣ እንዲሁም ሰብዓዊ ቀውስን አስመልክቶ ያሉ ችግሮች በዘላቂ ዲፕሎማሲያዊ መንገድ እንዲፈቱ የአሜሪካ መንግሥት ያለውን ቁርጠኝነት ለማሳየት እንደሆነም በመግለጫው ተመላክቷል፡፡
አንጋፋው ዲፕሎማት ጄፍሪ ፊልትማን ለበርካታ ዓመታት አሜሪካን በዲፕሎማሲው መስክ ያገለገሉ ሲሆን፣ ከዚህ ቀደም በሊባኖስ የአሜሪካ አምባሳደር ሆነው ሠርተዋል፡፡ ከዚህ በተጨማሪም የመካከለኛው ምሥራቅ ረዳት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር (Assistant Secretary of State) በመሆን ሠርተዋል፡፡
ከእነዚህ አገልግሎቶች በኋላ ደግሞ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የፖለቲካና የፀጥታ ኃላፊ ሆነው አገልግለዋል፡፡
እ.ኤ.አ. በ1986 የዲፕሎማሲውን ዘርፍ የተቀላቀሉት ፊልትማን የመጀመርያ ሥራቸው በሃይቲ ኮንሱላር በመሆን የሚጀምር ሲሆን፣ አብዛኛውን የሥራ ዘመናቸውን በምሥራቅ አውሮፓና በመካከለኛው ምሥራቅ እንዳሳለፉ የሥራ ልምዳቸው ያሳያል፡፡ በመካከለኛው ምሥራቅ በነበሩበት ወቅትም በጆርዳን ዩኒቨርሲቲ ዓረብኛ ቋንቋን መማራቸውም እንዲሁ ተጠቅሷል፡፡