Sunday, November 27, 2022
ሌሎች ዓምዶች
  - Advertisment -
  - Advertisment -

  ዘለዓለማዊ ክብር ለጀግኖች አርበኞቻችን!

  ከ125 ዓመታት በፊት በዝነኛው የዓድዋ ድል ድባቅ የተመታው የኢጣሊያ ወራሪ፣ 40 ዓመታት በኋላ ከመቼውም ጊዜ በላይ ተደራጅቶ ወረራ ሲፈጽም የተመከተውና የተባረረው በዱር በገደሉ በተሰማሩት በጀግኖች አርበኞቻችን ተጋድሎ ነው፡፡ በቤኒቶ ሙሶሎኒ የፋሽስት ፓርቲ የሚመራው የኢጣሊያ ወራሪ ሠራዊት ዳግም ኢትዮጵያን ቅኝ ለመያዝ በተለያዩ አቅጣጫዎች በከፈተው ጥቃት የተመከተው፣ ወደር የሌለው መስዋዕትነትከፈሉ ጀግኖች አርበኞች መሆኑን ታሪክ ለዘለዓለም ይዘክራል፡፡ ለዓለም ጥቁሮች መመኪያ የሆነውን ታላቁን የዓድዋ ድል በተጎናፀፉት ጀግኖች አባቶችና እናቶች እግር የተተኩት ወጣቶቹ አርበኞች፣ በተከታታይ ትውልዶች በምሳሌነት የሚወሳውን ፀረ ፋሽስት ትግል በድል ከተወጡ እነሆ 80 ዓመታት ተቆጥረዋል፡፡ የዓድዋን ሽንፈት ለመበቀል ለዳግም ወረራ የዘመተው የኢጣሊያ ፋሽስት ሠራዊት በዘመኑ በጣም የሠለጠነ፣ እጅግ ዘመናዊ የሚባሉ የነፍስ ወከፍ መሣሪያዎች፣ መትረየሶች፣ መድፎች፣ ታንኮችና የጦር አውሮፕላኖች የታጠቀ ነበር፡፡ በተጨማሪም በዓለም የተከለከለውን የመርዝ ጋዝ ጭምር በመጠቀም ነበር ኢትዮጵያን የተቆጣጠረው፡፡ በወቅቱ እጅግ በጣም አነስተኛ የሆነ ድርጅትና ከግል መሣሪያው (አሮጌ ጠመንጃ፣ ጋሻና ጦር) በስተቀር ያልነበረው የኢትዮጵያ ሕዝብና ጦር የነበረው ጥልቅ የሆነ የአገር ፍቅርና ወኔ ብቻ ነበር፡፡ ፋሽስቶቹ በታጠቁዋቸው ዘመናዊ መሣሪያዎችና የመርዝ ጋዝ አማካይነት ከባድ ጉዳት አድርሰው ኢትዮጵያ ሲቆጣጠሩ፣ ጀግኖቹ ኢትዮጵያውያን ደግሞ ነፃነት ወይሞ ሞት ብለው የነፃነት ትግል ጀመሩ፡፡ እነዚህ ዘለዓለማዊ ክብር የሚገባቸው ጀግኖች ታሪክ መቼም የማይዘነጋውን ጀግንነት አሳዩ፡፡

  ጀግኖቹ ኢትዮጵያዊያን አርበኞች ወራሪውን የፋሽስት ጣሊያን ሠራዊት ለአምስት ዓመታት ተዋግተው ድል የነሱበት 80 ዓመት መታሰቢያ፣ ረቡዕ ሚያዝያ 27 ቀን 2013 .. ይዘከራል፡፡ ኢትዮጵያ ለዓለም የሽምቅ ውጊያን ያስተማረችበት የጀግኖቹ አርበኞች ታሪካዊ ገድል ሲዘከር፣ አሁን ያለው ትውልድ ዙሪያውን የከበቡትን ችግሮች እንዴት በድል መወጣት እንደሚችል ትምህርት መቅሰም ይኖርበታል፡፡ ከሃምሳ ሚሊዮን በላይ ሕዝብ ያለቀበት የሁለተኛው የዓለም ጦርነት ከመጀመሩ በፊት፣ በፋሽስት ጣሊያን ወረራ ዘመናዊ የጦር መሣሪያዎችና ጥቅም ላይ እንዳይውሉ በተከለከሉ የመርዝ ጋዞች ከማንም በፊት ዕልቂት የተፈጸመበት ጀግናው ሕዝባችን፣ ታሪክ በማይረሳው ታላቅ ተጋድሎ አገሩን ተከላክሏል፡፡ ጀግኖቹ አርበኞች ስንቅና ትጥቅ ሳይቀርብላቸው ልጆቻቸውንና የትዳር አጋሮቻቸውን ጭምር በማሠለፍና በዘመኑ የነበረው ውስጣዊ ሽኩቻ ሳይበግራቸው፣ እግራቸውን ለጠጠር ደረታቸውን ለጦር ሰጥተው እናት አገራቸውን በከፍተኛ ፍቅርና ጀብዱ ከፋሽስቶች ባርነት ታድገዋል፡፡ ኢትዮጵያን ብቸኛዋ ለቅኝ ገዥዎች ያልተንበረከከች አፍሪካዊት አገር በማድረግ ስሟን በደማቅ ቀለም አሥፍረዋል፡፡ ይህ ታላቅ ተጋድሎ ሲዘከር ይህ ሁሉ ውለታ መታወስ አለበት፡፡

  የጀግኖች አርበኞችን ገድል ስናወሳ በወቅቱ በፍፁም ሊመክቱት ከማይችሉት ኃይል ጋር የተፋለሙበትን ንፅፅር ማየት ጠቃሚ ነው፡፡ በታሪክ ድርሳናት ላይ እንደ ሠፈረው፣ የኢትዮጵያ ተዋጊዎች የታጠቁት መሣሪያ እጅግ በጣም ኋላቀር ነበር፡፡ ለምሳሌ ዘመን ያለፈባቸው 234 መድፎች፣ ከአንድ ሺሕ የሚያንሱ አሮጌ መትረየሶች፣ በጥቂት ሺዎች የሚቆጠሩ አሮጌ ጠመንጃዎች፣ በአንደኛው የዓለም ጦርነት ሥራ ላይ የዋሉ ጥቂት አሮጌ ተሽከርካሪዎች ነበሩዋቸው፡፡ አራት መቶ ሺሕ ያህል ተዋጊዎች እንደነበሩ ቢገለጽም፣ መደበኛ የውትድርና ሥልጠና የነበራቸው በጣም ትንሽ ነበሩ፡፡ ከዚህ በተቃራኒ የፋሽስት ኢጣሊያ የሠለጠነ ወራሪ ሠራዊት ቁጥሩ 685 ሺሕ ሲሆን፣ የወረራውን ድል የሚዘግቡ 200 ጋዜጠኞችን አስከትሎ ነበር፡፡ በዘመኑ እጅግ ዘመናዊ የተባሉ ስድስት ሺሕ መትረየሶች፣ ሁለት ሺሕ ዘመናዊ መድፎች፣ 599 ዘመናዊ ታንኮች፣ የዘመኑ ሥሪት የሆኑ 390 የጦር አውሮፕላኖች ከማሠለፉም በላይ፣ በዓለም የተከለከለውን የመርዝ ጋዝ ጭምር ታጥቆ ነበር፡፡ ጀግኖች አርበኞቻችን የተፋለሙት ከእንዲህ ዓይነቱ ግዙፍ ወራሪ ጋር ስለነበር ዘለዓለማዊ ክብር ይገባቸዋል፡፡

  የጀግኖቹ ኢትዮጵያዊያን ተጋድሎ ሲወሳ ለአምስት ዓመታት የተደረገ እልህ አስጨራሽ ትግል መሆኑን መዘንጋት አይገባም፡፡ ይህ መራር ትግል ፅናትን የሚፈታተን፣ መፈጠርን የሚያስጠላ፣ የገዛ አባት ወይም እናት፣ ወንድም ወይም እህት፣ እንዲሁም ወገኖች ሳይቀሩ በፋሽስቶች ጭካኔ የተጨፈጨፉበት፣ ሞት በየዕለቱ በርካቶችን ያጋዘበት፣ በፋሽስቶች አውሮፕላኖችና መድፎች መንደሮች ሲወድሙ የሕፃናትና የእናቶች እሪታ ከዕልቂት ጋር በየዕለቱ የተሰማበት፣ ለፋሽስቶች ባደሩ ባንዳዎች ስመጥር አዋጊዎች ሳይቀሩ በሽምቅ የተገደሉበትና የፋሽስቶች ፕሮፓጋንዳ እየተነዛ መወላወል የተስተዋለባቸው ፈታኝ ሥቃዮች እንደታለፉ በታሪክ ድርሳናት ብዙ የተባለበት ነው፡፡ ፊት ለፊት ከገጠመ ግዙፍ አውሮፓዊ ጠላት ጋር ከሚደረገው ትንቅንቅ ባልተናነሰ፣ በግለሰብ አመራሮች መካከል በሚፈጠር አለመግባባት ከፍተኛ ጉዳት እየደረሰ ተስፋ አስቆራጭ አጋጣሚዎች እንደነበሩም ይታወሳል፡፡ የሆነ ሆኖ ብዙኃኑ ጀግኖች ኢትዮጵያዊያን ለተጋድሎ የተሠለፉበትን መሠረታዊ ዓላማ በሚገባ ያውቁ ስለነበር፣ ከምንም ነገር በፊት አገራቸውን በማስቀደም በውድ ሕይወታቸው የማያልፍ ታሪክ አኑረው መስዋዕት ሆነዋል፡፡ የፋሽስቶች ግፍ ከመጠን በላይ ሆኖ ንፁኃን ሳይቀሩ በመርዝ ጋዝ ተጨፍጭፈዋል፡፡ በአዲስ አበባ ከተማ በሩዶልፎ ግራዚያኒ ላይ በተወረወረ ቦምብ ምክንያት ከ30 ሺሕ በላይ ኢትዮጵያዊያን ለመጨፍጨፋቸው፣ ስድስት ኪሎ የሚገኘው የሰማዕታት አደባባይ ምስክር ነው፡፡ ፋሽስቶች በታሪክ ዘግናኝ የሚባለውን ጭፍጨፋ የፈጸሙት ዘር፣ ፆታ፣ ቋንቋ፣ እምነትና የመሳሰሉትን ሳይለዩ መሆኑን ልብ ማለት ይገባል፡፡ ኢትዮጵያዊያንም የአርበኝነት ተጋድሎ ያደረጉት ልዩነቶች ሳይገድቧቸው በአንድነት ተሠልፈው መሆኑን፣ ይህ ትውልድ እውነተኛውን ታሪክ በመመርመር መረዳት ይኖርበታል፡፡

  ወደ አሁኑ ትውልድ መለስ ሲባል ግን በርካታ ውጥንቅጦች አሉ፡፡ አገራቸውን እንደ ቀደመው ትውልድ ከሚያፈቅሩና ማናቸውንም ዓይነት መስዋዕትነት ለመክፈል ከማያንገራግሩ ቆራጦች ጀምሮ፣ ‹ከራስ በላይ ንፋስ› ብለው ግላዊ ጥቅማቸውን ብቻ እስከሚያሳድዱ ከንቱዎች ድረስ በየዓይነቱ ይስተዋላሉ፡፡ ከአገር ይልቅ በማንነት ስም ጠባብ መንደር ላይ የሚያተኩሩ፣ ለባዕዳን በማጎብደድ ለምን ቅኝ አልተገዛንም እያሉ የሚቆጩ ድረስ ይተራመሳሉ፡፡ የፖለቲካ ሥልጣንና ጥቅም እስከተገኘ ድረስ፣ ለብሔራዊ የጋራ ጉዳዮች ደንታ የሌላቸውም ቁጥራቸው አይናቅም፡፡ ለሰብዓዊና ለዴሞክራሲያዊ መብቶች በመታገል ሽፋን አምባገነንነትን ለማንገሥ የሚክለፈለፉም እንዲሁ፡፡ በመሠረቱ ልዩነቶች መኖራቸው ተፈጥሮአዊ መሆኑን መገንዘብ የግድ ይላል፡፡ ልዩነቶች ግን አገርን ለድርድር የሚያቀርቡ መሆን የለባቸውም፡፡ የፌዴራል ሥርዓት ከ26 ዓመታት በላይ በተዋወቀባት አገር ውስጥ በነፃነት፣ በእኩልነትና በፍትሐዊነት እንዴት አብሮ መኖር እንደሚቻል ከበቂ በላይ ልምዶችን መቅሰም እየተቻለ፣ ስለመገንጠልና ስለመበታታን ማሟረትና ማላዘን ካላሳፈረ ለትውልዱ ጭምር ስድብ ነው፡፡ ኢትዮጵያዊያን ደጉንና ክፉውን ጊዜ አብረው እያሳለፉ ተባብረው የዘለቁት፣ ለዓለም ጥቁር ሕዝቦች አንፀባራቂ የሆኑ ገድሎችን በማከናወንና ተምሳሌት በመሆን እንደሆነ ታሪክን ደጋግሞ ማስታወስ የግድ ነው፡፡ ከዚህ ውጪ ያለው ትርክት የሚያመራው ወደ ውድቀት ጎዳና ነው፡፡ ከውድቀት ደግሞ ውርደት እንጂ ክብር አይገኝም፡፡

  ከትውልድ ወደ ትውልድ እየተሸጋገረ 80ኛ ዓመት ክብረ በዓል ላይ የደረሰው የጀግኖች አባቶችና እናቶች ገድል ሲዘከር፣ ከምንም ነገር በላይ ጉልህ ሆኖ መወሳት ያለበት ለእናት አገር ፍቅር የሚከፈለው መስዕዋትነት የዋዛ አለመሆኑ ነው፡፡ ከሕይወት መስዋዕትነትና በአካል ላይ ከሚደርስ ጉዳት በተጨማሪ፣ የአገር ፍቅር ስሜት ከትውልድ ወደ ትውልድ የሚሸጋገር የነፃነት ተጋድሎ መገለጫ ጭምር ነው፡፡ ከፀረ ፋሽስት ትግሉ በፊት ኢትዮጵያን ለመቀራመት ያሰፈሰፉ በርካታ ወራሪዎችን አሳፍሮ የመለሰው ጀግናው የኢትዮጵያ ሕዝብ፣ የእናት አገር ፍቅር ስሜት ምን ማለት እንደሆነ በተለያዩ ትውልዶች አማካይነት አሳይቷል፡፡ በፀረ ፋሽስት ትግሉ ወቅት ግንባራቸውን ለጥይት ደረታቸውን ለጦር ያለ ስስት አሳልፈው የሰጡ ጀግኖችን ከመዘከር በላይ የሚያረካ ነገር የለም፡፡ እነሱን ከማወደስ በተጨማሪ በሕይወት ያሉትን መጦርና መንከባከብ የትውልዱ ድርሻ ነው፡፡ የእነሱንም የአገር ፍቅር ስሜት በመውረስ ኢትዮጵያችንን ከተደቀኑባት አደጋ መታደግም የትውልዱ ግዴታ መሆን አለበት፡፡ አሁንም ዘለዓለማዊ ክብር ለጀግኖች አርበኞቻችን ይሁን!

  በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

  ከውጭ ይገቡ የነበሩ 38 ዓይነት ምርቶች እንዳይገቡ ዕግድ ተጣለ

  የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ 38 ከውጪ የሚገቡ ምርቶች ላይ ዕገዳ...

  አዋሽ ባንክ ካፒታሉን 55 ቢሊዮን ብር ለማድረስ ወሰነ

  የአዋሽ ባንክ ዳይሬክተሮች ቦርድ ዛሬ ህዳር 17 ቀን 2015...

  የቴሌቪዥን ፈቃድ ክፍያ የማይከፍሉ በወንጀል እንዲቀጡ የሚያደርግ ረቂቅ ሕግ ውድቅ ተደረገ

  የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ሐሙስ ኅዳር 15 ቀን 2015...

  ክፍያ የፈጸሙ ተገልጋዮች ሁሉ አስቸኳይ ፓስፖርት እንዲያገኙ ሊደረግ ነው

  በኢሚግሬሸንና ዜግነት አገልግሎት አስቸኳይ ፓስፖርት ለማግኘት የተቀመጡ ቅድመ ሁኔታዎችን...
  - Advertisment -

  ትኩስ ፅሁፎች

  በችግር የተተበተበው የሲሚንቶ አቅርቦት

  ሲሚንቶን እንደ ግብዓት ተጠቅሞ ቤት ማደስ፣ መገንባት፣ የመቃብር ሐውልት...

  ‹‹የናይል ዓባይ መንፈስ›› በሜልቦርን

  አውስትራሊያ ስሟ ሲነሳ ቀድሞ የሚመጣው በተለይ በቀደመው ዘመን የባህር...

  ‹‹ልብሴን ለእህቴ››

  ለሰው ልጅ መኖር መሠረታዊ ፍላጎት ተብለው ከተዘረዘሩት ውስጥ ልብስ...

  የአዲስ አበባ ትምህርት ቤቶች የምርመራ ውጤት እስከምን?

  በፍቅር አበበ የትምህርት ጥራትን፣ ውጤታማነትንና ሥነ ምግባርን ማረጋገጥ ዓላማ አድርጎ...

  ከመሬት ለአራሹ ወደ ደላላ የዞረው የመሬት ፖለቲካ

  ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) በአንድ ወቅት ለመጀመርያ ጊዜ...
  spot_img

  ተዛማጅ ፅሁፎች

  መንግሥት ለአገር የሚጠቅሙ ምክረ ሐሳቦችን ያዳምጥ!

  በሕዝብ ድምፅ የተመረጠ መንግሥት ለሕዝብ የሚጠቅሙ ሐሳቦችን የማዳመጥ ኃላፊነት አለበት፡፡ ሥራውን ሲያከናውንም በግልጽነት፣ በተጠያቂነትና በኃላፊነት መርህ መመራት ይኖርበታል፡፡ እያንዳንዱ ዕርምጃው በሕግ ከተሰጠው ኃላፊነት አኳያ...

  የሰላም ስምምነቱ ተግባራዊ ይደረግ!

  የሰላም ስምምነቱ ‹‹ታጥቦ ጭቃ›› ሊሆን የሚችልባቸው ምልክቶች እየተስተዋሉ ነው፡፡ ሚሊዮኖችን ለዕልቂት፣ ለመፈናቀል፣ ለከፍተኛ ሰብዓዊ መብት ጥሰትና መሰል ሰቆቃዎች የዳረገው አውዳሚ ጦርነት በፕሪቶሪያው ስምምነት መሠረት...

  ዘረፋ የሚቆመው በተቋማዊ አሠራር እንጂ በዘመቻ አይደለም!

  ኢትዮጵያ ውስጥ ሌብነት ከመንግሥት አቅም በላይ ሆኖ ለያዥ ለገናዥ ሲያስቸግር ከማየት በላይ አሰቃቂ ነገር የለም፡፡ በፌዴራል፣ በክልሎችና በከተማ አስተዳደሮች መረን የተለቀቀው ሌብነት አስነዋሪ መሆኑ...