የሚኒስትሮች ምክር ቤት ቅዳሜ ሚያዝያ 23 ቀን 2013 ዓ.ም. ሕወሓትና ኦነግ ሸኔ የተባሉ ድርጅቶች በአሸባሪነት እንደፈረጁ ባሳለፈው የውሳኔ ሐሳብ ላይ፣ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ሐሙስ ሚያዝያ 28 ቀን 2013 ዓ.ም. ውሳኔ ለመስጠት እንደሚሰበሰብ ተገለጸ፡፡
ምክር ቤቱ በላከው መግለጫ የሚኒስትሮች ምክር ቤት ተወያይቶ ባሳለፈው ውሳኔ ሐሳብ ላይ የተወያይቶ ውሳኔ ለማሳለፍ ለሚያዝያ 28 ቀን 2013 ዓ.ም. ቀጠሮ የያዘ ሲሆን፣ ባለፈው ዓመት በወጣው የፀረ ሽብር አዋጅ መሠረትም በአሸባሪነት እንዲፈረጅ የውሳኔ ሐሳብ የቀረበበት ድርጅት ወይም ግለሰብ ራሱን የመከላከል መብት እንዲሰጠው የሚደነግገውን አንቀጽን በመጥቀስ፣ የውሳኔ ሐሳብ የቀረበባቸው ድርጅቶች የቀረበውን ውሳኔ ሐሳብ ለማስቀረት ያስችላል ያሏቸውን መከላከያዎች በአካል ቀርበው እንዲያስረዱ የ48 ሰዓት ጊዜ ገደብ መስጠቱን አስታውቆ ነበር፡፡
ሚያዝያ 28 ቀን 2013 ዓ.ም. በሚደረገው ውይይት ምክር ቤቱ የውሳቤ ሐሳቡን ተቀብሎ የሚያፀድቀው ከሆነ፣ መንግሥት በእነዘህ ድርጅቶች ውስጥ በአመራርነትና በአባልነት የሚያገለግሉ ግለሰቦች በአሸባሪነት ለመጠየቅ የሚያስችለው ይሆናል፡፡
ከዚህ በተጨማሪም የተጠቀሱት ድርጅቶና የድርጅቶቹ አመራሮች ሀብትን ለመውረስ እንዲችል የፀረ ሽብር አዋጅ ይደነግጋል፡፡ የፌዴራል ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ ከሳምንታት በፊት መግለጫ ከሕወሓት አመራሮችና ግንኙነት አላቸው ተብለው የተጠረጠሩ ግለሰቦች የባንክ ሒሳብ ውስጥ የሚገኝ 6.7 ቢሊዮን ብር እንዲታገድ ማድረጉን ማስታወቁ ይታወሳል፡፡
ከዚህ በተጨማሪም በሕወሓት ባለቤትነት ሥር የነበረውን ኤፈርት የተባለ ኢንዶውመንት ሀብቶች፣ በፌዴራል መንግሥት ሥር በተቋቋመ ባለአደራ አስተዳደር ሥር እንዲተዳደር መወሰኑ አይዘነጋም፡፡
ይሁን እንጂ የፀረ ሽብር ፍረጃውን መሠረት አድርጎ ከላይ የተገለጹትን ሀብቶች መንግሥት መውረስ ይችላል የሚለው ጥያቄ የሕግ ክርክር ከወዲሁ ፈጥሯል፡፡