Friday, December 8, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ስፖርትየቀነኒሳ በቀለ ቅሬታና የቶኪዮ ኦሊምፒክ ማጣሪያ

የቀነኒሳ በቀለ ቅሬታና የቶኪዮ ኦሊምፒክ ማጣሪያ

ቀን:

ዓለም አቀፍ ወረርሽኝ ባስከተለው የጤና ሥጋት ሳቢያ በርካታ ዓለም አቀፍ ክንውኖች እንዳይካሄዱ ተስተጓጉለዋል፣ አሊያም ተሰርዘዋል፡፡ ዓምና መካሄድ የነበረበት የቶኪዮ ኦሊምፒክ ወደ ዘንድሮ ተሸጋግሮ አገሮች ተሳታፊ አትሌቶቻቸውን በማዘጋጀት ላይ ይገኛሉ፡፡

በቶኪዮ ኦሊምፒክ የተሳታፊነት ቦታን ለማግኘት አገሮች የተለያዩ ማጣሪያዎችን በማከናወን ላይ የሚገኙ የመኖራቸውን ያህል፣ ኮቪድ-19 ከመከሰቱ በፊት ለቶኪዮ ኦሊምፒክ ተሳትፎ የሚያበቃቸውን ሰዓት (ሚኒማ) ያሟሉ አትሌቶችን ይዘው ዝግጅት የሚያደርጉ አሜሪካና ጀርመን የመሳሰሉ አገሮችም ዝግጅቶቻቸውን እያከናወኑ መሆኑ ይታወቃል፡፡

በዚህ ዓለም አቀፍ የስፖርት ትዕይንት ላይ አገራቸውን የሚወክሉ አትሌቶችን በመምረጥ ላይ ከሚገኙት ኢትዮጵያ አንዷ ናት፡፡ የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን በታላቁ መድረክ አገሪቱን በማራቶን የሚወክሉ አትሌቶችን ለመለየት ባለፈው ቅዳሜ ሚያዝያ 23 ቀን 2013 ዓ.ም. በሰበታ ከተማ 35 ኪሎ ሜትር የማጣሪያ ውድድር አከናውኖ ከአንደኛ እስከ አምስተኛ የወጡ አትሌቶችን በሁለቱም ፆታ መዝግቦ ይዟል፡፡

ምንም እንኳ የተመረጡት አትሌቶች በውድድሩ አሸናፊነታቸው ተረጋግጦ ለቶኪዮ ኦሊምፒክ በማራቶን ኢትዮጵያን ይወክላሉ ቢባልም፣ የዓለማችን ሁለተኛው ፈጣን የማራቶን ሰዓት ባለቤት፣ እንዲሁም በረዥም ርቀት የኦሊምፒክና የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና የድርብ የወርቅ ሜዳሊያ አሸናፊ የሆነው ቀነኒሳ በቀለ በሰበታው ማጣሪያ ላይ እንደማይሳተፍ መግለጹን ተከትሎ በብሔራዊ ፌዴሬሽኑ ውሳኔ በዘርፉ ያሉ በርካታ ሙያተኞች አስተያየቶቻቸውን እየሰጡ ይገኛሉ፡፡

ቀነኒሳ በቀለ ለአገሩ ከዚህ ቀደም ከዋለው ውለታ አንፃር በተለይ ደግሞ በኦሊምፒክ፣ በዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮናና በዓለም አገር አቋራጭ ውድድሮች ላይ በአንድ የውድድር ወቅት ሲያስመዘግባቸው የነበረውን ሁለት የወርቅ ሜዳሊያዎችን በማስታወስ፣ እንዲሁም በ2019 በርሊን ማራቶን ላይ ያስመዘገበውን 2፡ 01፡ 41 ሰዓት (የዓለም ክብረ ወሰን 2፡ 01፡ 39 ነው) ከግምት በማስገባት በማራቶን መሳተፍ እንደሚገባው የሚሞግቱ በርካቶች ናቸው፡፡

ከዚህ ባለፈም ቀነኒሳን የሚያህል በዓለም አቀፍ ደረጃ የገነነ አትሌት እንዲህ ባሉ አሠራሮች ከኦሊምፒክ እንዲቀር ከተወሰነ፣ በተደጋጋሚ በተለያዩ ዘርፎች የሚጠቀሰው ‹‹ባለውለታዎችን አለማክበር መገለጫ ነው›› በማለት የሚጠቅሱም አልጠፉም፡፡

ብሔራዊ ፌዴሬሽኑ ባለፈው ቅዳሜ በሰበታ ከተማ ባዘጋጀው 35 ኪሎ ሜትር ማጣሪያ ውድድር ላይ እንዲሳተፉ ጥሪ ያደረገላቸው 12 ወንዶችና ስምንት ሴቶች አትሌቶች ናቸው፡፡ ከወንዶቹ መካከል ቀነኒሳ በቀለና ሙስነት ገረመውን ጨምሮ ስድስት አትሌቶች እንዳልተሳተፉ የሚናገሩ አሉ፡፡ ከተሳተፉት ውስጥ ሹራ ቂጣታ፣ ሌሊሳ ዲሳሳ፣ ሲሳይ ለማ፣ ጫሉ ደሶና ክንዴ አያናው ከአንደኛ እስከ አምስተኛ ያለውን ደረጃ በማግኘታቸው ተመርጠዋል፡፡ በሴቶች ከቀረቡት ትዕግሥት ግርማ፣ ብርሃኔ ዲባባ፣ ሮዛ ደረጀ፣ ዘይነባ ይመርና ሩቲ አጋ የተመረጡ መሆናቸውን ፌዴሬሽኑ በማኅበራዊ ትስስር ገጹ ይፋ አድርጓል፡፡

የኢትዮጵያ ኦሊምፒክ ኮሚቴ በበኩሉ፣ ከትናንት በስቲያ ሰኞ ሚያዝያ 24 ቀን በጽሕፈት ቤቱ በሰጠው መግለጫ፣ የኢትዮጵያ ኦሊምፒክ ኮሚቴ ዋነኛ ፍላጎት አገራዊ ባንዲራን ከፍ የሚያደርግ ውጤት እንዲመዘገብ ማድረግ ነው፡፡ በመሆኑም ‹‹ተገቢ ባልሆኑ አሠራሮች እንደ ቀነኒሳ በቀለ የመሰሉ ወቅታዊ ብቃታቸው በጥሩ ደረጃ ላይ የሚገኙ አትሌቶች ከውድድሩ እንዲቀሩ አንፈቅድም፤›› ብሏል፡፡ የብሔራዊ ኦሊምፒክ ኮሚቴው ፕሬዚዳንት አሸብር ወልደ ጊዮርጊስ (ዶ/ር) ይህንኑ በመግለጫው ወቅት አስረግጠው ተናግረዋል፡፡

 ‹‹ለአገሬ ከሠራሁት ሥራ አኳያ ካለፈው የሪዮ አሊምፒክ ጀምሮ እስከ ቶኪዮ ኦሊምፒክ በተለይ በእኔ ላይ እየተፈጸመ ባለው ነገር ልቤ ተሰብሯል፤›› በማለት የሚናገረው ቀነኒሳ በቀለ፣ ኦሊምፒክን ጨምሮ እያንዳንዱ ዝግጅትም ሆነ ምርጫ የራሱ የሆነ የአሠራር ሒደት አለው፡፡ ላለፉት በርካታ ዓመታትም ሲሠራበት የኖረው በዚሁ አካሄድና አሠራር መሠረት መሆኑ ልብ ሊባል እንደሚገባው ጭምር ይናገራል፡፡

የቶኪዮ 2020 ኦሊምፒክ በኮቪድ-19 ወረርሽኝ ምክንያት እንዲራዘም በመደረጉና የዓለም አቀፍ ኦሊምፒክ ኮሚቴም ችግሩን ታሳቢ በማድረግ ተወዳዳሪዎች በወቅቱ ያስመዘገቡት ሰዓት ዋጋ እንደሚኖረው ገልጾ የነበረ መሆኑን የሚናገረው ቀነኒሳ፣ ማጣሪያ ማድረግ አስፈላጊ ነው ቢባል እንኳ  መነገር የነበረበት በሳምንት ጊዜ ውስጥ ሳይሆን ከስድስት ወራት በፊት መሆን እንደነበረበት ይናገራል፡፡

ሌላው ቀነኒሳ እንደ ክፍተት የሚያነሳው ማጣሪያ የተደረገበት ሰበታና አካባቢው ከፍታው (አልቲትዩድ) ከፍተኛ ከመሆኑ ባሻገር የውድድሩ አሸናፊ የተለየው 35 ኪሎ ሜትር ላይ ነው፡፡ ይህ ደግሞ በማራቶን ውድድሩ ተጀመረ የሚባልበት ጊዜ እንጂ ተጠናቀቀ የሚባልበት እንዳልሆነ ጭምር ያስረዳል፡፡

የማጣሪያው አስፈላጊነት አትሌቶች የሚገኙበትን ወቅታዊ በቃት ለመገምገም ይቻል ዘንድ ያለመ ነው ቢባልም፣ በዚህ የማይስማማው ቀነኒሳ ወቅታዊ ብቃት ለመገምገም ከሆነ የልምምድ ጊዜን መጠቀም ለምን አልተቻለም ሲል ይጠይቃል፡፡ ችግሩ አመራሮቹም ሆነ አሠልጣኞች የየራሳቸው ፍላጎት ያላቸው መሆኑ ብቻ ሳይሆን አብሮ የመሥራት ፍላጎትም ባህልም የሌላቸው በመሆኑ ነው ይላል፡፡

ከኮማንደር ደራርቱ ቱሉና ገዛኸኝ አበራ ጋር በጉዳዩ መነጋገሩን የሚናገረው ቀነኒሳ፣ ‹‹የእኛ ፍላጎት ሆቴል እንድትገነባ አይደለም፣ አንተ በቡድናችን መካተትህ በራሱ ለእኛ ክብር ነው፤›› ብለውት መለያየታቸውን ያስረዳል፡፡ በወቅቱ ማጣሪያ እንኳ ቢኖር ውድድሩ የሚደረገው በሐዋሳ አሊያም በስዊዘርላንድ ሊሆን እንደሚችል በወሬ ደረጃ መስማቱን ካልሆነ፣ በሰበታ እንደሚደረግ ያወቀው በሳምንት ጊዜ ውስጥ ስለመሆኑ ጭምር ይናገራል፡፡

ቀጣይ ውሳኔውን በተመለከተ ቀነኒሳ፣ ‹‹ሰዎች እንዲረዱኝ የምፈልገው በግሌ ኦሊምፒክን ጨምሮ ለበርካታ ዓመታት ታላላቅ ክብሮችን አሳክቻለሁ፣ ይሁንና ይህንን ሁሉ ክብርና ዝና ባገኘሁባት አገሬ እኔን ለመጉዳት ሲባል ብቻ ከተለመደ አሠራር መውጣት፣ በተለይ ለተተኪ አትሌቶች ጉዳት እንዳለው ለመግለጽ ስለምወድ ነው፡፡ በተረፈ ሁለተኛ አገር የለኝም፣ ሰዎች እንጂ አገሬ አልጎዳችኝም፣ እኔም ለአገሬ ያለኝን ሁሉ አድርጌያለሁ ብዬ አምናለሁ፣ የማልደብቀው ቢኖር ግን በተደረገብኝ ነገር ስሜቴ ተጎድቷል፤›› በማለት ቅሬታውን ይገልጻል፡፡ አትሌቱ ለሚያነሳቸው ቅሬታዎች የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ምን ይላል የሚለውን ለማወቅ ያደረግነው ጥረት አልተሳካም፡፡               

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ታዋቂው የኤሌክትሮኒክስ ብራንድ አይቴል የስትራቴጂ ለውጥ አካል የሆነውን አዲስ አርማ እና መለዮ ይፋ አደረገ።

በአለማችን ታዋቂ ከሆኑት የኤሌክትሮኒክስ ብራንዶች መካከል አንዱ የሆነው እና...

የጠቅላላ ጉባኤ ስብሰባ ጥሪ ለሸገር አነስተኛ የፋይናንስ ተቋም አ.ማ ባለአክሲዮኖች በሙሉ

ለሸገር አነስተኛ የፋይናንስ ተቋም አ.ማ ባለአክሲዮኖች በሙሉ የሸገር አነስተኛ የፋይናንስ...

[የክቡር ሚኒስትሩ ጸሐፊ፣ የሌላ ሚኒስትር ጸሐፊ ከሆነችው የቅርብ ወዳጇ ጋር በስልክ እየተጨዋወቱ ነው]

አንቺ ግን ምን ሆነሽ ነው? ጠፋሁ አይደል? ጠፋሁ ብቻ?! ምን ላድርግ ብለሽ...

በሱዳን ላይ ያጠላው የመከፋፈል ዕጣና ቀጣናዊ ተፅዕኖው

የሱዳን ጦርነት ስምንተኛ ወሩን እያገባደደ ይገኛል፡፡ ጄኔራል አብዱልፈታህ አልቡርሃን...