Wednesday, December 7, 2022
ሌሎች ዓምዶች

  በህንድ የኮቪድ ታማሚዎች ቁጥር 20 ሚሊዮን ተሻገረ

  - Advertisement -spot_img

  በብዛት የተነበቡ

  ወደ ሩብ ሚሊዮን የሚጠጋ ሰው ሕይወቱን አጥቷል

  ከ1.3 ቢሊዮን ሕዝብ በላይ ያላት ህንድ በኮቪድ መፈተን የጀመረችው እንደተቀረው ዓለም ዓምና ቢሆንም፣ ዘንድሮ ግን የተለየ ፈተና ገጥሟታል፡፡ ከወራት በፊት በሽታውን በመቆጣጠርና የተሻለ አገልግሎት በመስጠት ሆስፒታሎቿ የተመሰገኑትን ያህል አሁን ላይ ወረርሽኙ ከአቅማቸው በላይ ሆኗል፡፡

  ሁለተኛ ዙር ነው በተባለው የኮቪድ-19 ወረርሽኝ ዜጓቿ እየረገፉ ነው፡፡ በህንድ በተለይ ሰሞኑን የጤና ሥርዓቱን ያቃወሰው ኮቪድ-19፣ ሰዎች በየመንገዱ፣ በየመኪናቸውና በያገኙት ሥፍራ ሆነው ‹‹የጤና ባለሙያ ያለህ›› ማለት እንዲጀምሩ አድርጓል፡፡ የመታከም ዕድል የገጠማቸው ሲያገግሙ ያጡት ግን እያሸለቡ ነው፡፡ በርካቶችም ‹‹ወገኖቻችን ሕክምና ለማግኘት ቢዋትቱም ባለማግኘታቸው ሕይወታቸው አልፏል›› ሲሉ የየቤታቸውን ገጠመኝ ለዓለም አቀፍ መገናኛ ብዙኃን አጋርተዋል፡፡

  በሕዝብ ቁጥር ማየል ሳቢያ በተለያዩ የህንድ ከተሞች ያለው የአኗኗር ዘይቤ የተቀራረበ በመሆኑ ኮቪድ-19  እንዲነግሥ አመቺ ሁኔታ ቢፈጥርለትም፣ እዚህ ሳይደርስ የኮቪድ መከላከያ ፕሮቶኮሎች አለመተግበራቸው ወይም መላላታቸው ህንድን ለአሁኑ ጉልህ ችግር እንዳጋለጣት እየተነገረ ነው፡፡

  ኮቪድ-19 መጀመርያ የገባ ሰሞን ዜጓቿን በማሰርና ጥንቃቄ ያላደረጉትን በማስቀጣት ቫይረሱን ተቋቁማ የነበረችው ህንድ፣ መሀል ላይ በነበረ የቁጥጥር መላላትና የሕዝቦቿም ቸልተኝነት ዛሬ ላይ ዋጋ እየከፈለች ነው፡፡

  በህንድ የኮቪድ ታማሚዎች ቁጥር 20 ሚሊዮን ተሻገረ

   

  አሜሪካ ካስመዘገበችው ከ33 ሚሊዮን በላይ የኮቪድ ታማሚ በመቀጠል ከ20 ሚሊዮን በላይ ያስመዘገበችው ህንድ፣ የሟቾች ቁጥሯም ከአሜሪካና ከብራዚል ቀጥሎ ከ220 ሺሕ በላይ ሆኖ መመዝገቡን ወርልድሜትሪስ ከሁለት ቀን በፊት ያሰፈረው መረጃ ያሳያል፡፡

  ከሚያዝያ መጀመርያ አንስቶ በህንድ ተከስቷል የተባለው ሁለተኛው ዙር የኮቪድ ወረርሽኝ በብዛት የተጠቁት የህንድ ዋና ከተማ ኒውዴልሂ፣ ፑን፣ ቤንጋሉሩ፣ ሙምባይን ጨምሮ የተለያዩ ከተማ ነዋሪዎች ቢሆኑም፣ ሥርጭቱ ወደገጠር እየተስፋፋ መምጣቱ ለጤና ሥርዓቱ ተጨማሪ ፈተናና የሕዝቡ ሥጋት ሆኗል፡፡

  የኮቪድ-19 ቅድመ መከላከያ ፕሮቶኮሎች መላላት፣ ሕዝባዊ ፌስቲቫሎችና የምርጫ ዘመቻ አባብሶታል በተባለው ወረርሽኝ በየቀኑ ከ300 ሺሕ በላይ ታማሚዎች እየተመዘገቡ ሲሆን፣ የቁጥሩ መጨመርም ከሆስፒታሎች የመቀበል አቅም በላይም ሆኗል፡፡

  የመመርመር ሆነ የማከም ሁኔታውም ተስተጓጉሏል፡፡ የሚመጡ ታማሚዎችን ለማከም አልተቻለም፡፡ የወሳኝ መድኃኒቶችና የኦክስጅን እጥረትም ተከስቷል፡፡ የሕክምና ባለሙያዎች ደክመዋል፡፡ ይህም የሞቱን ቁጥር አሻቅቦታል፡፡ በየከተሞቹም የቀብር ሥነ ሥርዓት ተበራክቷል፡፡

  የህንድ መንግሥት 222 ሺሕ ሰዎች በላይ በቫይረሱ ምክንያት ሞተዋል ቢልም፣ በርካቶች የሞት ቁጥሩ ከሚነገረው በላይ ሊሆን እንደሚችል እየተናገሩ ነው፡፡ ሙታንን ለማቃጠል የሚውሉ ሥፍራዎች በቀባሪዎች መጨናነቅና ወረፋ መጠበቅ፣ አስከሬን በጅምላ ለማቃጠል የሚያስችሉ የእንጨት ርብራቦች በብዛት መሠራትና ወረርሽኙ በተንሰራፋባቸው ከተሞች አስከሬን ለማቃጠልም ሆነ ለመቅበር ሥፍራ እየጠፋ እንደሆነም ቢቢሲ ዘግቧል፡፡

  በህንድ በሺሕ ቶን የሚለካ ኦክስጅን በየቀኑ ቢመረትም፣ በኒውደልሂ ብቻ በየሕክምና ሥፍራው የሚጎርፈውን ታማሚ መድረስ አልቻለም፡፡ ህንድ በቀን 3689 ከፍተኛውን የሞት ቁጥር ያስመዘገበችውም በዚሁ የኦክስጅን እጥረት ነው ተብሏል፡፡

  በርካታ የህንድ ግዛቶች ገደብ የጣሉ ሲሆን፣ አንዳንድ ከተሞች ሙሉ ለሙሉ ከቤት አለመውጣትን ተግብረዋል፡፡ በየቀኑ ወደ 13 ሺሕ የሚጠጉ ታማሚዎችን መመዝገብ የጀመረችው ቢሃር ከተማ ሙሉ ለሙሉ ከቤት አለመውጣትን ከተገበሩ ከተሞች አንዷ ናት፡፡ በዚህች ከተማ ከወሳኝ የመንግሥት አገልግሎት ሰጪ ተቋማት፣ ከግሮሰሪዎችና ከሆስፒታሎች በስተቀር ማንም አገልግሎት መስጠት አይችልም፡፡

  ህንድ የገጠማትን ጉልህ የኮቪድ-19 ወረርሽኝ ተፅዕኖ ለመከላከልና የሕክምና ሥርዓቷን ለመደገፍ ዓለም አቀፍ ተቋማት እየሠሩ ነው፡፡ በ40 አገሮች የሚገኙ የዕርዳታ ድርጅቶች ሰው ሠራሽ የመተንፈሻ አካልን ጨምሮ የተለያዩ የሕክምና ቁሳቁሶችን እያቀረቡ ነው፡፡

  ከዚሁ ጎን ለጎን ደግሞ አሜሪካን ጨምሮ በርካታ አገሮች ከህንድ የአየር በረራ ሆነ ጉዞ ላይ ገደብ ጥለዋል፡፡

  የህንድ መንግሥት ኮ-ዊን ፖርታል እንደሚያሳየው፣ በህንድ ከሚገኙ 1.35 ቢሊዮን ሕዝቦች 9.5 በመቶ ሁለቱንም ዙር የኮቪድ-19 ክትባት ወስደዋል፡፡

  spot_img
  - Advertisement -

  ትኩስ ጽሑፎች

  ተዛማጅ ጽሑፎች

  - Advertisement -
  - Advertisement -