Sunday, March 26, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -

‹‹በጣፋጭ ምርቶች ላይ የተጣለው ከፍተኛ ኤክሳይዝ ታክስ እንደሚስተካከል ተስፋ እናደርጋለን›› አቶ ኤልያስ ተሾመ፣ የንብ ከረሜላ ፋብሪካ ዋና ሥራ አስኪያጅ

ከጣፋጭ ምግቦች መካከል ኢትዮጵያ ውስጥ በግንባር ቀደምትነት ተመርቶ ገበያ ላይ የዋለው ደስታ ከረሜላ ሲሆን፣ አምራቹም ወንጂ ስኳር ፋብሪካ ነው፡፡ በቀጣይ ተመርቶ ገበያውን የተቀላቀለው ደግሞ ጠጠርማና ኮሮሾ ቅርፅ ያለው ከረሜላ ነው፡፡ አምራቹም ንብረትነቱ የቤተሰብ የሆነው ንብ ከረሜላ ፋብሪካ ነው፡፡ የፋብሪካው ዋና ሥራ አስኪያጅና የኢትዮጵያ ስኳርና ጣፋጭ ምግቦች ማኅበር ምክትል ፕሬዚዳንት አቶ ኤልያስ ተሾመ ናቸው፡፡ የፋብሪካውን አመሠራረት፣ ዕድገትና ያጋጠሙ ተግዳሮቶችን በተመለከተ ታደሰ ገብረማርያም አነጋግሯቸዋል፡፡

ሪፖርተር፡- ፋብሪካው እንዴትና መቼ ተቋቋመ?

አቶ ኤልያስ፡- ፋብሪካው በቤተሰብ ባለንብረትነት ይዞታ ሥር ያለ ሲሆን፣ የተቋቋመውም መርካቶ አካባቢ በሚገኘው 20 ሜትር ካሬ በሆነ ቤት ውስጥ ነበር፡፡ የመሠረቱት አባታችን አቶ ተሾመ ጀቢራ ናቸው፡፡ ፋብሪካው የተቋቋመው ከዛሬ 47 ዓመት በፊት ሲሆን፣ ለመጀመርያ ጊዜ አምርቶ ለተጠቃሚ ያቀረባቸው የከረሜላ ዓይነቶች ጠጠርና ኮሮሾ ይባሉ ነበር፡፡ በግሉ ዘርፍ ለመጀመርያ ጊዜ የተቋቋመው ይህ ፋብሪካ፣ በደርግ ሥርዓት ትንሽ ተዳክሞ ነበር፡፡ ይህም ሊሆን የቻለው ሲሰጠው የነበረው የስኳር መጠን በመከልከሉና በዘመኑ በግሉ ዘርፍ የተቋቋሙት ኢንዱስትሪዎች ተፈላጊነታቸው ይኼን ያህል ባለመሆኑ ነበር፡፡ ሆኖም በመጠኑም ቢሆን የማምረት ተግባሩን ማከናወን አላቋረጠም፡፡ ከጠጠር ከረሜላ በተጨማሪም ቀይና ነጭ ቀለም ያለው የዱላና የእጅ ሰዓት ቅርፅ ያለው ከረሜላ ያመርት ነበር፡፡

ሪፖርተር፡- ሥርዓቱ በሚያራምደው የኢኮኖሚ መርህ መሠረት የቀዘቀዘው ፋብሪካ በምን መልኩ እንደገና ሊንሠራራ ቻለ?

አቶ ኤልያስ፡- ፋብሪካው ከተቋቋመበት ሥፍራ በ2004 ዓ.ም. ዊንጌት አካባቢ በሚገኘው 1000 ሜትር ካሬ ስፋት ባለው ቦታ ላይ ተስፋፍቶ ወደ ፒኤልሲ ተዛወረ፡፡ ትንሽ ቆይቶም ቡራዩ ከተማ ታጠቅ የኢንዱስትሪ ዞን በሚገኘው 15,000 ሜትር ካሬ ቦታ ላይ ደረጃውን በጠበቀ መልኩ እንደገና የማስፋፋት ሥራ ተከናውኗል፡፡ በፋብሪካው ውስጥ የተሻሻሉና ደረጃቸውን የጠበቁ የተለያዩ ከረሜላዎች ማምረትን በስፋት ተያያዝነው፡፡ በዚህም ሎሊፖፕን ለማምረት ቻልን፡፡ ፓኬጆቹም ደረጃቸውን የጠበቁ እንዲሆኑ ተደረገ፡፡ የአመራረቱ ሒደት ሳይንሱን የተከተለ ሆኖ፣ ፓኬጆቹም ላይ ገላጭ ጽሑፍ ያላቸው እንዲሆኑ ተደረገ፡፡ በከረሜላ ምርት ላይ ይህ ዓይነቱን የማሻሻል ሥራ ካካሄድን በኋላ ቸኮሌት ማምረት ጀመርን፡፡ በኢትዮጵያ በግሉ ዘርፍ ቸኮሌትን ለመጀመርያ ጊዜ ያመረተው የንብ ከረሜላ ፋብሪካ ነው፡፡

ሪፖርተር፡- ቸኮሌት ማምረት የጀመራችሁት በስንት ዓመተ ምሕረት ነው? ስንት ዓይነት ቸኮሌት ነው የምታመርቱት?

አቶ ኤልያስ፡- ቸኮሌት ማምረት ከጀመርን ወደ ስምንት ዓመት ሆኖናል፡፡ ቸኮሌት ምርቶቻችን በአብዛኛው በሱፐርማርኬትና በአንዳንድ ባለ አምስትና አራት ኮከብ ሆቴሎች ውስጥም ይገኛሉ፡፡ አንዳንዱ ተጠቃሚ ቸኮሌት ኢትዮጵያ ውስጥ መመረቱን ቶሎ አይረዳውም፡፡ ፓኬጅ ላይ ሜድ ኢን ኢትዮጵያ የሚል ጽሑፍ አለበት፡፡ ጽሑፉን ሳያነብ ከፓኬጁ እያወጣ ቸኮሌቱን ሲጠቀም ይስተዋላል፡፡ እኩሉ ደግሞ ፓኬጁን በማንበብ ወይም ከተነገረው በኋላ ልብ ይለዋል፡፡ በተረፈ ወደ 18 ዓይነት ቸኮሌቶችን እናመርታለን፡፡ ለአብነት ያህል ኬክና ኩኪስ ይገኙበታል፡፡ አሁን እንደውም የኢትዮጵያ አየር መንገድ ኬተሪንግ ከውጭ የሚያስመጣውን ቸኮሌት ትቶ ፋብሪካችን የሚያመርተውን እየተጠቀሙ ነው፡፡ ከፋብሪካችን እየተመረተ የሚወጣውን ቸኮሌት እየገዙ ለውጭ አገር ኤክስፖርት ሲያደርጉም የሚስተዋሉ አሉ፡፡ ከዚህ አኳያ ፋብሪካችን በቀጥታ  ወደ ውጭ ባይልክና ምንም እንኳን ተጠቃሚ ባንሆንም በተዘዋዋሪ መንገድ በሌሎች ሰዎች አማካይነት ኤክስፖርት እየተደረገ ነው፡፡

ሪፖርተር፡- የቸኮሌት ቡኮ እያመረታችሁ ነው? ግለሰቦች የአቅማቸውን ያህል እየገዙ መውሰድ ይችላሉ? ተጠቃሚዎቻችሁ የትኞቹ የማኅበረሰብ ክፍሎች ናቸው?

አቶ ኤልያስ፡- የቸኮሌት ቡኮ ለግለሰቦች እንደየአቅማቸው በኪሎ እንሸጣለን፡፡ ግለሰቦችም ቤታቸው ወስደው በልዩ ልዩ መልክ ይጠቀሙታል፡፡ ኬክ አምራቾች፣ ካፌና ሬስቶራንቶችም ደንበኞቻችን ናቸው፡፡

ሪፖርተር፡- የፋብሪካው የማምረት አቅሙ ምን ያህል ነው?

አቶ ኤልያስ፡- ፋብሪካው የሚንቀሳቀሰው በ24 ሰዓት በሚቀያየሩና በሁለት ፈረቃ በተመደቡ ሠራተኞች አማካይነት ነው፡፡ የፋብሪካው ቸኮሌትና ከረሜላ የማምረት አቅሙም በቀን እስከ 150 ኩንታል ይደርሳል፡፡ ሆኖም በተለያዩ ምክንያቶች የአቅሙን ያህል እያመረተ አይደለም፡፡ አንደኛው ምክንያት ከፍተኛ የሆነ የኤሌክትሪክ ኃይል እጥረት ሲሆን፣ ሁለተኛው ምክንያት ደግሞ የፋብሪካውን አቅም ያላገናዘበ ከፍተኛ የኤክሳይዝ ታክስ ማለትም 30 በመቶ የኤክሳይዝ ታክስ መንግሥት በመጣሉ ነው፡፡ በዚህና ካለው የኑሮ ውድነት ጋር ተያይዞ የተጠቃሚውን የመግዛት አቅም ገድቦታል፡፡

ሪፖርተር፡- ይህ ዓይነቱ ኤክሳይዝ ታክስ እንዲሻሻል ጉዳዩ በይበልጥ ለሚመለከተው መሥሪያ ቤት ለማሳወቅ የተደረገ ጥረት የለም?

አቶ ኤልያስ፡- እንዲሻሻል በጣም ጥረቶች አድርገናል፡፡ ካደረግናቸው ጥረቶች መካከል በኢትዮጵያ ስኳርና ጣፋጭ ምግቦች ማኅበር አማካይነት ለገንዘብና ኢኮኖሚ ሚኒስቴር በተደጋጋሚ ችግሩን  አሳውቀናል፡፡ ለሌሎችም ባለድርሻ አካላት አሳውቀናል፡፡ ተስፋ እየሰጡን ነው፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ ቸኮሌትን የሚያመርተው ንብ ከረሜላ ፋብሪካ ቢሆንም፣ ማስቲካና ከረሜላ የሚያመርቱ ወደ 100 የሚጠጉ ፋብሪካዎች አሉ፡፡ ከእነዚህም መካከል በኤክሳይዝ ታክስ ሳቢያ ወደ 40 የሚጠጉ ፋብሪካዎች ተዘግተዋል፡፡ ኤክሳይዝ ታክሱ የተጣለውም ሳንወያይ ነው፡፡

ሪፖርተር፡- ቸኮሌት ለማምረት ምን ዓይነት ጥሬ ዕቃዎችን ትጠቀማላችሁ?

አቶ ኤልያስ፡- ቸኮሌትን ለማምረት የምንጠቀማቸው የተያዩ ግብዓቶች አሉ፡፡ ስኳር፣ ወተትና በዋናነት ካካዋ እንጠቀማለን፡፡ ካካዋ የምናስመጣው የዓለምን ፍላጎት እስከ 70 በመቶውን ከሸፈነው ከምዕራብ አፍሪካ ነው፡፡ በአገር ውስጥ የተወሰኑ ግብዓቶች ላይ ምርምር አድርገን በሙከራ ደረጃ የምንጠቀምባቸው አሉ፡፡ እነርሱም ቡና እና ጤፍ ናቸው፡፡ ወደፊት ተስፋ የሚሰጡ ነገሮች ታይቶባቸዋል፡፡ የፆም ቸኮሌት የለም የሚሉ ወገኖች አሉ፡፡ ይኼ ትክክል አይደለም፡፡ ከካካዋ ብቻ ትንሽ ስኳር ተደርጎበት የፆም ቸኮሌት እናመርታለን፡፡ ካካዋ ደግሞ ተክል ነው፡፡

ሪፖርተር፡- ፋብሪካው የቸኮሌት ምርቱን በራሱ ኤክስፖርት ለማድረግ ለምንድነው የተሳነው?

አቶ ኤልያስ፡- መጀመርያ የአገር ወስጥ ገበያውን በደንብ መያዝና ፍላጎቱን መሸፈን ያስፈልጋል፡፡ ዓለም አቀፍ ይዘት ያለው አይሶ 2015 ስታንዳርድ ሠርተፊኬት ለማሟላት ዳር ላይ ደርሰናል፡፡ ይኼንን ካሟላን በኋላ ወደ ውጭ ገበያው እንገባለን ብለናል፡፡ በተረፈ በአገር ውስጥ ያለውን የደረጃ መዳቢ ምልክቶች አለን፡፡ ነገር ግን ኢትዮጵያ ውስጥ ከከረሜላ በስተቀር የቸኮሌት ደረጃ የለም፡፡ የኢትዮጵያ ተስማሚነትና ምዘናና የኢትዮጵያ ምግብና መድኃኒት ባለሥልጣን የዕውቅና ሠርተፊኬቶች አሉን፡፡

ሪፖርተር፡- ፋብሪካው ምን ያህል ሠራተኞች አሉት?

አቶ ኤልያስ፡- በጠቅላላው 300 ሠራተኞች አሉን፡፡ ቀደም ሲል ግን የሠራተኞቹ ቁጥር ወደ 400 ይጠጋ ነበር፡፡ የሰው ኃይል የማይጠይቁና ዘመናዊ ቴክኖሎጂዎች የታከሉባቸው አዳዲስ ማሽኖችን አስመጥተን በማስተከላችን የተነሳ የሠራተኞቹ ቁጥር ቀንሷል፡፡

ሪፖርተር፡- የፋብሪካው ቁልፍ ችግር ምንድነው?

አቶ ኤልያስ፡- ትልቁ ችግራችን ከፍተኛ የኤክሳይዝ ታክስ መጣሉ ነው፡፡ ከውጭ በሚመጡ በአንዳንድ የመለዋወጫ ዕቃዎች ላይ እስከ 40 በመቶ ኤክሳይዝ ታክስ ተጥሎባቸዋል፡፡ ይህም ከፍተኛ ችግር በመሆኑ የተነሳ ዋጋው እንዲንር አድርጎታል፡፡ በዚህም የተነሳ ቸኮሌት ከውጭ እያስመጡ አገር ውስጥ መሸጡ ያዋጣ ይሆን? ወደሚል ጥያቄ ውስጥ እያስገባን ነው፡፡ ለማንኛውም ገንዘብና ኢኮኖሚ ሚኒስቴር ጥያቄያችንን ተቀብሎታል፡፡ ጥሩ ምላሽ እናገኛለን ብለን በተስፋ እየተጠባበቅን ነው፡፡ ይህ ከሆነ ግን ከአንድ ዓመት በላይ ሆኖታል፡፡

ሪፖርተር፡- የቸኮሌትና ከረሜላ መጠቅለያ ከየት ነው የምታስመጡት? ከውጭ የሚገቡት ቸኮሌቶች በፋብሪካው ምርት ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ አላሳደሩም?

አቶ ኤልያስ፡- መጠቅለያውን ከውጭ አሳትመን እናስመጣለን፡፡ አገር ውስጥ የሚያመርቱ ድርጅቶች ስላሉም ከእነሱም እንገዛለን፡፡ ከውጭ ወደ አገር ውስጥ የሚገቡ አንዳንድ ቸኮሌቶች ፋብሪካችን እያመረተ ከሚያወጣቸው ቸኮሌቶች ዋጋ ባነሰ ሲሸጡ ይስተዋላል፡፡ እንደእነዚህ ዓይነት የውጭ ቸኮሌቶች ወደ አገር ውስጥ የገቡት ሕጋዊውን መንገድ ተከትለው ነው ወይስ በኮንትሮባንድ? የሚለውን አናውቅም፡፡ በተለይ በምሥራቅ ኢትዮጵያ በኩል በብዛት ይገባሉ፡፡ ሽያጫቸውም በጣም ርካሽ ነው፡፡ ያመረትነው ቸኮሌት እንዳይሸጥና በፋብሪካችንም ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ እያሳደሩብን ነው፡፡

ሪፖርተር፡- በቸኮሌት ምርት ላይ በቅርቡ የተደረገ የማሻሻያ ሥራ እንዳለ ይነገራል፡፡ ይህን ጉዳይ በዝርዝር ሊያስረዱን ይችላል?

አቶ ኤልያስ፡- በቸኮሌት አመራረት ላይ ‹‹ቢን ቱ ባር›› የሚባል አካሄድ አለ፡፡ ‹‹ቢን›› የካካዋ ተክል ላይ የሚገኝ ፍሬ ነው፡፡ በኢንዱስትሪ የበለፀጉ አገሮች ከምዕራብ አፍሪካ ቢኑን ይገዙና ፕሮሰስ አድርገው የቸኮሌት ዱቄቱን ለገበያ ያቀርባሉ፡፡ ከዚህ አኳያ ብዙዎቹ ታዳጊ አገሮች የሚገዙት ፕሮሰስድ የሆነውን ቸኮሌት ነው፡፡ ፋብሪካችንም ለብዙ ዓመታት ሲጠቀም የቆየው በዚሁ መልክ ፕሮሰስ የሆኑትን የቸኮሌት ዱቄቶችን በማስመጣት ነበር፡፡ ከቀርብ ጊዜ ወዲህ ግን ከዚህ ዓይነቱ ግዥ ተላቀን ራሱን ቢኑን እየገዛንና በፋብሪካችን ፕሮሰስ እያደረግን ለተጠቃሚውና ለገበያ እያቀረብን ነው፡፡ ይህ የአመራረት ዘዴም በኢትዮጵያ ብቸኛ ያደርገናል፡፡

ተዛማጅ ፅሁፎች

- Advertisment -

ትኩስ ፅሁፎች ለማግኘት

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

በወለድ ነፃ የባንክ አገልግሎት የተሰበሰበው ከፍተኛ ሀብት ጥቅም ላይ እየዋለ አይደለም ተባለ

በኢትዮጵያ ከወለድ ነፃ የባንክ አገልግሎት የተሰበሰበው የተቀማጭ ገንዘብ መጠን...

ጥቁር የመልበስ ውዝግብና የእምነት ነፃነት በኢትዮጵያ

ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) ኅዳር ወር ላይ በፓርላማ...

መንበሩ ካለመወረሱ በስተቀር መፈንቅለ ሲኖዶስ መደረጉን ቤተ ክህነት አስታወቀ

ቅዱስ ሲኖዶስ ከነገ ጀምሮ ውይይት እንደሚጀምር ተነገረ ‹‹እኛ ወታደርም ሆነ...

ወ/ሮ መሰንበት ሸንቁጤ የአዲስ አበባን ንግድና ዘርፍ ምክር ቤትን በፕሬዚደንትነት ለመምራት በተደረገው ምርጫ አሸነፉ

የአዲስ አበባ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤትን በፕሬዚደንትነት ለመምራት፣...