ከሁሉም ክልሎች የተመረጡ የ50 ከተሞች ከንቲባዎች ከግሉ ዘርፍ ጋር የሚመክሩበት ኮንፍረንስ ሊካሄድ ነው፡፡
ሚያዝያ 28 እና 29 ቀን 2013 ዓ.ም. የሚካሄደውን ኮንፍረንስ የኢትዮጵያ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤትና ሌሎች ባለድርሻ አካላት በጥምረት ያዘጋጁት ሲሆን፣ በተመረጡ ርዕሰ ጉዳዮች ላይ ጥናታዊ ጽሑፎች ቀርበው ውይይት የሚደረግባቸው ይሆናል፡፡
‹‹ከተሞች የኢንቨስትመንት መነሻና ማስፋፊያ ሞተሮች›› የሚል ስያሜ የተሰጠው ይህ የከንቲባዎችና የግሉ ዘርፍ ኮንፍረንስ፣ ከንቲባዎች የራሳቸውን ምኅዳር የሥራ ፈጠራ ሥርዓት፣ የምጣኔ ሀብት እንቅስቃሴዎችን የሚያሻሽሉ አዳዲስ ፖሊሲዎችን የማዘጋጀትና በሚያስተዳድሯቸው ከተሞች ውስጥ ተግባራዊ ለማድረግ በሚችሉበት መንገድ ዙሪያ ግንዛቤ የሚያስጨብጥ ይሆናል ተብሎ እንደሚታመን ከኢትዮጵያ ንግድ ምክር ቤት የተገኘው መረጃ ያመለክታል፡፡
ይህንን መድረክ በቴክኒክና በፋይናንስ ድጋፍ በማድረግ ከኢትዮጵያ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ጋር እንዲዘጋጅ ያደረገው የፓን አፍሪካን የንግድና ኢንዱስትሪ ምክር ቤት የፕሮጀክት ኃላፊ አቶ ጌታቸው መላኩ እንደገለጹት፣ እንዲህ ዓይነቱ መድረክ እንዲካሄድ ብዙ ዝግጅቶች ሲደረጉ ቆይተዋል ብለዋል፡፡
ለአገራዊ ኢኮኖሚ ዕድገት የከተሞች ሁለንተናዊ ዕድገት ወሳኝ በመሆኑ የተመቸ የቢዝነስ ምኅዳር መፍጠር የሚቻለውም ከታች ካሉ ከተሞች በመነሳት ስለሆነ ለከተሞች ልዩ ትኩረት በመስጠት የተሰናዳ ስለመሆኑም ከተደረገው ገለጻ ለመገንዘብ ተችሏል፡፡
የቢዝነስ እንቅስቃሴን ለማሳለጥና ምቹ የቢዝነስ ሥነ ምኅዳር ለመፍጠር ከዚህ ቀደም በግሉ ዘርፍና በመንግሥት መካከል ከሚደረገው የምክክር መድረክ በተለየ እንደሚሰናዳና በንግድ ምክር ቤቱ በኩል በቋሚነት የሚቀጥል መድረክ ስለመሆኑም ታውቋል፡፡
‹‹ከዚህ ቀደም የነበረው የመንግሥትና የግሉ ዘርፍ ምክክር መድረክ ታች ያሉትን ሰዎች የማያሳትፍና ከከፍተኛ ባለሥልጣናት ጋር የሚካሄድ እንደነበር ያስታወሱት አቶ ጌታቸው፣ ቢዝነስ ካላደገ ከተሞች ማደግ እንደማይችሉ ከተሞች በፖሊሲ ላይ የተመሠረተ አሠራር እንዲኖራቸው መድረኩ ዕገዛ እንደሚያደርግላቸው ገልጸዋል፡፡
ከአቶ ጌታቸው ገለጻ መረዳት እንደተቻለው፣ በሁለቱ ቀናት የውይይት መድረክ ጥናታዊ ጽሑፎች የሚቀርቡ ሲሆን፣ ከእነዚህም ውስጥ አንዱ የሥራ ፈጠራን የሚመለከት ነው፡፡ በዚህ ጉዳይ በከተማ ውስጥ በተከፈቱ ቢዝነሶችም ሆኑ ኢንዱስትሪዎች ውስጥ የሚሠሩ ሰዎች ላይ ያለው ክፍተት የሚዳሰስበት ይሆናል፡፡ ከሥራ ብቃት ጋር በተያያዘ ያሉ ክፍተቶች ላይም ይመክራል፡፡
ሌላው መወያያ አጀንዳ በመንግሥት አስተዳደር በተለይ የአገልግሎት አሰጣጡ ለቢዝነስ ልማቱ አስተዋጽኦው አነስተኛ መሆኑ ጋር የተያያዘ ነው፡፡ የአገልግሎት አሰጣጥን በማዘመን በኩል የከተሞች መዘጋጃ ቤቶች ድክመት አለባቸው፡፡ በዚህ የተነሳ ጊዜና ገንዘብ ይጠፋል፡፡ የመልካም አስተዳደርና የአገልግሎት አሰጣጥ መታጎል ወደ ሙስና ጭምር የሚወስድበት ዕድል ስላለ እንዲህ ያለውን ችግር ለመፍታት መድረኩ ጠቀሜታው የጎላ ይሆናል፡፡
የከተሞች ዘላቂ ልማት ላይ ምን መደረግ አለበት? የሚለውን ጭብጥ በመያዝ ከተሞች በዘላቂነት እንዲያድጉ ከተፈለገ በዋናነት ሊጠቀስ የሚችለው የቢዝነስ ልማት ስለሆነ በዚህ ላይ የከንቲባዎች ሚና ምን መሆን እንደሚገባው የሚያመለክት ይሆናል ተብሏል፡፡
ለቢዝነሶች እንቅፋት የሆኑት አሠራሮች ላይ መምከር ሌላው መወያያ አጀንዳ ነው፡፡ ‹‹ከተሞች ማደግ ካለባቸው በከተሞቹ ቢዝነስ ማደግ አለበት፤›› ያሉት አቶ ጌታቸው፣ ቢዝነሱ እንዳያድግ እንቅፋት የሚሆኑ ነገሮች ምንድናቸው? በተለይ ኢትዮጵያ ካለው ያልተመጣጠነ ዕድገት አንፃር ምን መደረግ አለበት የሚለው በመድረኩ የሚቀርብ ይሆናል፡፡
መድረኩ የከተማ ከንቲባዎች በወቅታዊና ዓለም አቀፍና አገራዊ የንግድና የኢንቨስትመንት ስምምነቶች ላይ ያላቸውን ግንዛቤ ከፍ ለማድረግ ያስችላል የተባለም ነው፡፡ እንደማሳያ በቅርቡ ኢትዮጵያ የፈረመችው የአፍሪካ ነፃ የንግድ ቀጣናና ሌሎች ዓለም አቀፍና አኅጉር አቀፍ ስምምነቶች የከተማ ከንቲባዎችን ትልቅ ትኩረት የሚጠይቁ በመሆናቸው ከዚህ አንፃር ሊሠራ የሚገባው ላይ ውይይት ይደረጋል ተብሏል፡፡
ኮንፍረንሱን ከኢትዮጵያ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤትና ከፓን አፍሪካ ንግድና ኢንዱስትሪ ምክር ቤት በተጨማሪ የከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን ሚኒስቴር፣ የሥራ ፈጠራ ኮሚሽን፣ የንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር በተባባሪነት ያዘጋጁት ነው፡፡
በዚህ ኮንፈረንስ ላይ ከተሰጠ ተጨማሪ መረጃ መረዳት እንደሚቻለው እስካሁን ጥሪው ከተላለፈላቸው ከ60 በላይ ከንቲባዎች ውስጥ 50ዎቹ ተሳታፊ ለመሆን ማረጋገጫ ሰጥተዋል፡፡