Saturday, July 13, 2024
- Advertisment -
- Advertisment -

አምስቱ የወረራ ዘመን

በባህሩ ዘውዴ (ፕሮፌሰር)

ሚያዝያ 27 ቀን የኢትዮጵያ የድል ቀን ሆኖ በየዓመቱ ይከበራል፡፡ ይህም የፋሺስት ጣሊያን ጦር ከ1928 ዓ.ም. እስከ 1933 ዓ.ም. በወረራ የቆየበትን ጊዜ ማክተሙ ያበሰረበት የወቅቱ ንጉሠ ነገሥት ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ በድል አድራጊነት መናገሻ ከተማቸው የገቡበት ልዩ ቀን ነው፡፡ ስለአምስቱ ዘመን ታሪካዊ ገጽታ ፕሮፌሰር ባሕሩ ዘውዴ ከጻፉት  የኢትዮጵያ ታሪክ ከ1847 እስከ 1983 ያገኘነውን ሐተታ ታሪክ አቅርበናል፡፡

የጣልያን አገዛዝ ከተመሠረተ ከመጀመሪያው ቀን ጀምሮ አገር አቀፍ የሆነ ተቃውሞ ነው ያጋጠመው፡፡ ምንም እንኳ ጣልያኖች በከፋፍለህ ግዛ ፖሊሲ ተቃውሞውን ለማዳከም ቢሞክሩም፣ ሰጥ ለጥ ብሎ የተገዛላቸው አንድም ክልል ወይም ብሔረሰብ አልነበረም፡፡ ፀረ ጣልያን ተቃውሞውን በሁለት ዐቢይ ምዕራፎች ከፍሎ ማየት ይቻላል፡፡ የመጀመሪያው ምዕራፍ ከግራዚያኒ እልቂት በፊት የነበረው ሲሆን እሱም በመሠረቱ የጦርነቱ ተከታይ የሆነ፣ ከመደበኛ ጦርነት እምብዛም ያልተለየና ባብዛኛውም በመሳፍንቱ የሚመራ የነበረ ነው፡፡ ከአይነተኛ ባሕርዮቹ አንዱም ማወላወልና ለመደራደርም ዝግጁነት ማሳየቱ ነው፡፡ ሁለተኛው በዝቅተኛ መኳንንት የሚመራ የደፈጣ ውጊያ ነው፡፡ ዝቅ ብለን እንደምናየው አንዳንድ መሠረታዊ ድክመቶች ብኖሩትም ይህ ምዕራፍ የጣልያን አገዛዝ አምርሮና ያለማመንታት የሚቃወም ነበር፡፡

በመጀመሪያው ምዕራፍ ተቃውሞ የመሪነቱን ሥፍራ በመያዝ ጎላ ብለው የሚታዩት ራስ እምሩ፣ ራስ ደስታና ወንድማማቾቹ አበራና አስፋወሰን ካሣ (የራስ ካሣ ልጆች) ናቸው፡፡ ቀደም ብለን እንዳየነው በነበረው ተጨባጭ ሁኔታ ራስ እምሩ በሽሬ ግንባር ያሳየው የአመራር ችሎት የሚደነቅ ነበር፡፡ ይሁን እንጂ የኢትዮጵያ ጦር ከተፈታና በተለይም የጣልያኖችን የማይበገር የመሣሪያ ኃይል በቅርብ ከተመለከተ በኋላ ውጊያውን የመቀጠል ሐሞቱ ፈሰሰ፡፡ ንጉሠ ነገሥቱ ሲሰደድ እምሩን እንደራሴ አድርጎ ቢሰይመውም የፀረ ጣልያን ተቃውሞ አስተባባሪነትን ተግባር ለመሸከም ዝግጁ አልነበረም፡፡ እንዲያውም ተስፋ በመቁረጥ እሱም በበኩሉ ወደ ሱዳን ወይ ወደ ኬንያ ለመሰደድ ሐሳብ ነበረው፡፡ ነገር ግን እያፈገፈገ ጐሬ ስደርስ፤ ባላሰበው መንገድ ራሱን ተበታትኖ የነበረው የኢትዮጵያ ኃይል ሁሉ አሰባሳቢና አለኝታ ሆኖ አገኘው፡፡ በዚያን ጊዜ ጐሬ ንጉሠ ነገሥቱ ከተሰደደ በኋላ እሱን ወክሎ የሚሠራ መንግሥት የተቋቋመባት መዲና ነበረች፡፡ ይህ “የጐሬ መንግሥት” በእርግጥ ሙሉ በሙሉ የመንግሥትነት ባሕርይ ነበረው ለማለት ቢያዳግትም፤ የኢጣልያን አገዛዝ ሕጋዊ ዕውቅና ለመንሣት ለሚደረገው ዲፕሎማሲያዊ ትግል መጠነኛ ጠቀሜታ ነበው፡፡ የራስ እምሩን ወደ ጐሬ መምጣት በታላቅ ደስታ ከተመለከቱት ቡድኖች ዋነኛው ጥቁር አንበሳ በሚል ስም የሚታወቀው ምሁራንና የሆለታ ወጣት መኰንኖች ያቋቋሙት ድርጅት ነው፡፡

በተለይም ትግሉ ይቀጥል የሚል መልዕክት በስደት ላይ ከሚገኘው ንጉሠ ነገሥት ይዤ መጥቻለሁ የሚለው የብላቴን ጌታ ኅሩይ ወልደ ሥላሴ ልጅ ፈቃደ ሥላሴ ኅሩይ ራስ እምሩን ሳይወድ ገፋፍቶ የአርበኞች መሪ እንዲሆን በማድረጉ ረገድ ከፍተኛ ሚና እንደተጫወተ ይነገርለታል፡፡ እምሩ ከሰሜን ይዞ የመጣውን ጦር፣ የጥቁር አንበሳን ወጣት አርበኞችና በወለጋና ኢሉባቦር ሰፍረው የነበሩትን ነፍጠኞች አስተባብሮ በድፍረት ዘመቻውን ወደ አዲስ አበባ አቀና፡፡ ግን አዲስ አበባ እንዲህ ቅርብ አልነበረችም፡፡ ቀደም ብለው በነበረው አገዛዝ ያኰረፉት የኦሮሞ ነዋሪዎችም ጦሩ አገራቸውን አቋርጦ እንዲያልፍ ፈቃደኛ አልነበሩም፡፡ በተስፋና በቅልጥፍና የተነሳው የእምሩ ጦርም ያገሬው ሰው ያባረራቸው መጤዎች እየተጠጉት ጓዘ ብዙ ሆኖ እንዲሁ በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሲንከራተት ከቆየ በኋላ በመጨረሻ ጐጀብ ወንዝ አጠገብ ለጠላት እጁን ለመስጠት ተገደደ፡፡

በደቡብ ኢትዮጵያ የራስ ደስታ ጦር በዶሎ ላይ የሰነዘረው ደፋር የማጥቃት ዕርምጃ ከሽፎበት ተሸማቀ ከተመለሰ በኋላ ጣልያኖችን ዕረፍት መንሣቱን አላቋረጠም፡፡ በዚህም፣ በተለይ መጀመሪያው ላይ በደጃች በየነ መርዕድ ጦርና በደጃች ገብረ ማርያም ጋሪ ጦር ይታገዝ ነበር፡፡ ጣልያኖች ባደረጉት ራስ ደስታን የማደን ዘመቻዎች ግራዚያኒ ራሱም ተሳትፎ ነበር፡፡ በራስ ደስታ በኩል የታየው አንድ ድክመት ተቃውሞውን በመቀጠልና እጅ በመስጠት መካከል ማወላወሉ ነው፡፡ እንደሚባለውም በትግሉ እንዲገፋበት ያስገደደው ወደሱ ጦር የገቡት ኤርትራውያን አስካሪዎች የነበራዠው የማያወላውል አቋም ነው፡፡ በእነሱ ግምት እጅ መስጠት ማለት እርግጠኛ ሞት ስለነበር ጦርነቱን ከመቀጠል ሌላ አማራጭ አይታያቸውም ነበር፡፡ ይሁን እንጂ የደስታ ማወላወል ዞሮ ዞሮ የሌሎች ተከታዮቹን ሞራል ማዳከሙ አልቀረም፡፡ ስለዚህም መጀመሪያ የነበረው የሰው ኃይል እየመነመነ ሄዶ እሱም ከቦታ ቦታ ሲባረር በመጨረሻ በየካቲት 1929 በጉራጌ አገር ጎጌቲ በተባለ ስፍራ ተሸንፎ ተያዘ፡፡ ጣልያኖችም እንደ አደገኛ ጠላት የሚያዩትን ምርጦኛቸውን ሳይውል ሳያድር ረሸኑት፡፡ እንዳጋጣሚ ይህ ሁሉ የሆነው አዲስ አበባ የግራዚያኒ እልቂት በሚካሄድበት ወቅት ነው፡፡

የመጀመሪያውን ምዕራፍ ተቃውሞ ቁልጭ አድርጎ የሚያሳየው በ1928 ማለቂያ ላይ የተደረገው በቅጡም ያልተናጀው አዲስ አበባን የማጥቃት ዕርምጃ ነው፡፡ በዕቅዱ መሠረት ከገጠር የአርበኞቹ ኃይል በተለያየ አቅጣጫ ሲያጠቃ፣ ከተማው ውስጥ ደግሞ ሕዝባዊ አመፅ ተቀስቅሶ የጣልያን አገዛዝ ባጭሩ ለመቅጨት ነበር፡፡ ከገጠር የሚያጠቁት በሰሜን በኩል አበራና አስፋወሰን ካሣ፣ በደቡብ ደጃች ባልቻ ሳፎ፣ በሰሜን ምዕራብ ባላምባራስ (ኋላ ራስ) አበበ አረጋይ፣ በምሥራቅ ደግሞ ደጃች ፍርቀ ማርያም ይናዱ ነበሩ፡፡ የአርበኞቹን መንፈስ በማነቃቃት ከፍተኛ ሚና የተጫወተው የጣልያን አገዛዝ በጽኑ የሚቃወመው የወሎው ጳጳስ አቡነ ጴጥሮስ ነበር፡፡ የሆነ ሆኖ ይህ ብዙ ኃይሎችን ያቀፈ ዕቅድ በኅብረት የጣልያንን ጦር ማጥቃቱ ቀርቶ የተበታኑ ጀብዱዎች የታዩበት ሆነና ተሰናክሎ ቀረ፡፡ አቡነ ጴጥሮስ ተይዞ ስቃይ ከበዛበት ምርመራ በኋላ በአደባባይ ተረሸነ፡፡ አበራና አስፋወሰን እስከ መሀል ከተማ ድረስ ካጠቁ በኋላ ወደ ስላሴ እንዲያፈገፍጉ ተገደዱ፡፡ ከዚያ በኋላ ራስ ኃይሉ ምንም አይደርስባችሁም ብሎ አግባብቷቸው እጃቸውን ከሰጡ በኋላ ጣልያኖች ያለምሕረት ረሸኗቸው፡፡ ደጃች ባልቻም ከጠላት ጦር ጋር ተናንቆ ሞተ፡፡

የጣልያን ፋሺዝም ፅልመታዊ ገጽታ ቁልጭ ብሎ የወጣው በየካቲት 12 ቀን 1929 ዓ.ም. ነው፡፡ አብርሃ ደቦጭና ሞገስ አስገዶም የተባሉ ሁለት ወጣቶች በግራዚያኒ ላይ ቦምብ ጥለው ካቆሰሉት በኋላ አዲስ አበባ ላይ መዓት ወረደባት፡፡ “ጥቁር ሸሚዝ” እየተባሉ የሚትወቁት የፋሽስት ደቀ መዛሙርት በፋሽስቱ አገዛዝ አይዞህ ባይነት አዲስ አበባን ቄራ አደረጓት፡፡ የሰው ልጅ ጭንቅላት እንደ ዶሮ እየተቀነጠሰ ወደቀ፡፡ ቤቶች ከነነዋሪዎቻቸው ጋዩ፡፡ እርጉዝ ሴቶች በሳንጃ ተወጉ፡፡ የጭፍጨፋው ተቀዳሚ ዒላማ የተማሩ ኢትዮጵያውያን ነበሩ፡፡ በተለይም የጥቁር አንበሳ አባላት ከራስ እምሩ ጋር እጃቸውን ከሰጡ በኋላ በከተማይቱ ይገኙ ስለነበር በወረንጦ እየተለቀሙ ተረሸኑ፡፡ ይህ የምሁራን ጭፍጨፋ አንድ ትውልድ እንዳለ የጠፋ በመሆኑም በአገሪቱ የፖለቲካና ምሁራዊ ታሪክ ላይ የማይሻር ቁስል ጥሎ አለፈ፡፡ ይህ የፋሽስት ጭፍጨፋ በሌላ መልኩ በወራሪና ተወራሪ መካከል ያለውን ቅራኔ መካረር በማመልከት የፀረ ኢጣልያ ተቃውሞውም ከመጀመሪያው ወደ ሁለተኛው ምዕራፍ፣ ከመደበኛ ወይም ከፊል መደበኛ ጣርነት ወደ ሽምቅ ውጊያ መሸጋገሩን አረጋገጠ፡፡

ይሀን ሁለተኛ የተቃውሞ ምዕራፍ በተመለከተ ማለት የሚቻለው አንድ ዐቢይ ነገር አገር አቀፍ መሆኑ ነው፡፡ ምንም እንኳ የአርበኞቹ እንቅስቃሴ ጎላ ብሎ የሚታየው በሸዋ፣ በጎጃምና በበጌምድር ቢሆንም ጣልያኖች ያለተቃውሞ የገዙት ክፍለ አገር አልነበረም”” አገሪቱ በታደለችው የተፈጥሮ ምሽጎች እየተጠቀሙ ደፈጣ ተዋጊዎቹ ጣልያኖችን ጤናና ፋታ ነሷቸው፡፡ እንደሁኔታው አመችነት ስልታቸውን ከማጥቃት ወደ መከላከል፣ ከመከላከል ወደ ማጥቃት እየለመጡ የመገናኛ መስመሮችን ይቆርጡ፣ በተነቃናቂ የጠላት ጦር ላይ አድፍጠው አደጋ ይጥሉ፣ ወይም ደግሞ ፊት ለፊት ጦርነት ይገጥሙ ነበር፡፡ እንደ ማንኛውም የደፈጣ ተዋጊዎች ሁሉ ትልቁ የትግል መሣሪያቸው በፍጥነት ከቦታ ቦታ መንቀሳቀሳቸውና እንደ አስፈላጊነቱ ለመበታተንና ለመሰባሰብ መቻላቸው ነበር፡፡ ምንም እንኳ አብዛኛዎቹ የአየር መቃወሚያ መሣሪያ ባይኖራቸውም በዚህ የትግል ስልታቸው አማካይነት ጣልያኖችን መጀመሪያ በሁሉም ጦር ግንባር የነበራቸውን የአየር ላይ የበላይነት ነሷቸው፡፡

የአርበኞቹ ዐቢይ ችግር የስንቅ እጥረት ነበር፡፡ ብዙውን ጊዜ ቀለባቸውን ማግኘት የሚችሉት መከረኛውን ባላገር በማስጨነቅ ሆነ፡፡ በዚህ ረገድ በየገበሬው ቤት ፋኖ እስከ መምራት ተደርሶ ነር፡፡ ይሁን እንጂ ከዚህ ሻል ያለ ሠራዊቱን የመቀለብ ዘዴ መሞከሩ አልቀረም፡፡ በአንዳንድ ቦታዎች ሠራዊቱ በሁለት ተከፍሎ “ደረቅ ጦር” የተባለው ሙሉ በሙሉ በውጊያው ላይ ሲያተኩር “መደዴ ጦር” የተባለው ግን ውጊያው ተግ ሲል በእርሻ ተግባር እንዲሠማራ ተደርጓል፡፡ በሌላ ጊዜ ደግሞ ከጠላት ጋር ያበሩ ሰዎችን እህል በመዝረፍ ሕሊናን ብዙ በማያውክ መንገድ የሠራዊቱን ቀለብ ማበራከት ተችሏል፡፡ ሲከፋ ሲከፋ ደግሞ የዱር አራዊት ማደንና ፍራፍሬ እየለቀሙ መብላትም የተለመደ ነበር፡፡ ሌላው የአርበኞቹ ችግር መድኃኒት ነበር፡፡ ጠላት መሀል ሆነው ከሚቦረቡሩት የውስጥ አርበኞች ጋር ግንኙነት ኖሯቸው መድኃኒት ካላገኙ በቀር፣ ያላቸው ምርጫ በባሕላዊ ወጌሻዎችና መድኃኒት የተወሰነ ነበር፡፡ የጦር መሣሪያን በተመለከተ ደግሞ አርበኞቹ ትጥቃቸውን የማያደረጁባቸው ሁለት ዋና መንገዶች በምርኮና ጠላትን ከድተው በሚቀላቀሏቸው ተዋጊዎች አማካይነት ነው፡፡ በሌላ ጊዜ ደግሞ የጠላትን አውሮፕላን አቅጣጫ በማሳት ስንቅና ትጥቅ አርበኞች በመሸጉበት አካባቢ እንዲጥል ያስደርጉ ነበረ፡፡

ፋኖዎቹ መረጃ የመሰብሰቢያ ዘዴም ነበራቸው፡፡ ወደ ጠላት ጦር ጠጋ ብለው የሚያደፍጡ ቃፊሮች የጠላትን ጣር እንቅስቃሴ ይዘግቡላቸው ነበር፡፡ከሁሉም በላይ መረጃ ለመሰብሰብ በኩል ቁልፍ ሚና የተጫወቱት ግን የውስጥ አርበኞች ነበሩ፡፡ ከጠላት ጋር አብረው እየዋሉ እያደሩ፣ የጠላትን ጦር ጥንካሬ፣ የታሙ ዘመቻዎችንም ሆነ ወታደራዊ እንቅስቅሴዎችን በተመለከተ አርበኞቹ አስቀድመው በማስጠንቀቅ የጠላትን ዕቅዶች ያጨናግፉ ነበር፡፡ ከዚያም አልፈው በአስተዳደሩ ውስጥ ባላቸው ኃላፊነት በመጠቀም ለአርበኞቹ የሐሰት የይለፍ ፈቃድና መታወቂያ ወረቀት የወጡ፣ ጠላት ለሚያሳድዳቸውም መሸሸጊያ ይሰጡ ነበር፡፡ ምግብ፣ ልብስና መድኃኒትም ያቀርቡላቸው ነበር፡፡ አንዳንዴም የሚያውቋቸውን የኢጣልያን ባለሥልጣኖች በመማጠን በተያዙ አርበኞች ላይ የሚተላለፈውን ፍርድ ያለዝቡ ነበር፡፡ ይህ ሕጋዊ ሽፋናቸውን እንደጠበቁ የሚያደርጉት ሲሆን፣ በሌላ ጊዜ ደግሞ ማንነታቸውን በመሸሸግ ተቋማትን በማፍረስና በሽብር ፈጠራ ተግባርም ይሰማሩ ነበር፡፡

ለዚህም ሁሉ ሥራ ሴቶች ከወንዶች ይልቅ ስለማይጠረጠሩ በተለይ ያመቹ ነበሩ፡፡ ከሴቶች የውስጥ አርበኞችም ከፍተኛ ዝና ያገኘችው አርበኞች አዲስ ዓለም የመሸገውን የጠላት ጦር እንዲደመስሱ ሁኔታዎችን ያመቻቸላቸው ሸዋረገድ ገድሌ ናት፡፡ የውስጥ አርበኞች ድርጅት ከፍተኛ ደረጃ ሊደርስ የቻለው በሁለቱ ከተሞች፣ በአዲስ አበባና በጐንደር፣ ነው፡፡ በተለይም በዋና ከተማው የምድር ባቡር ሠራተኞች በመዋቅሩ የተጫወቱት ቁልፍ ሚና እንቅስቃሴውን ላብ አደራ ባሕርይ ሰጥቶት ነበር፡፡ በአጠቃላይ ጣልያኖች ናላቸው የዞረው አርበኞቹ ከሚያደርሱባቸው ጥቃት ይልቅ የውስጥ አርበኞቹ በሚያደርጉባቸው ግዝገዛ ነበር ማለት ይቻላል፡፡ ምክንያቱም አርበኞቹ በርቀት የሚወጓቸው ሲሆኑ፣ የውስጥ አርበኞቹ ግን እነሱኑ መስለው፣ አንዳንዴም ቢጠራጠሩ እንኳ እንዳይያዙ የሽፋን ስም እየተጠቀሙ በመሆኑ ነው፡፡

እዚህ ላይ የአርበኞቹን የትግል ስልት በተመለከተ ሊጠቀስ የሚገባው አንድ ሌላ ነገር አንዳንዴ የሚጠቀሙበት የማዘናጋት ታክቲክ ነው፡፡ በተለይም በ1932 ራስ አበበ አረጋይ የኢጣልያን ሹማምንት እጁን ለመስጠት ዝግጁ ነኝ ብሎ ማቄሉ ለዚህ አንድ ጥሩ ማስረጃ ነው፡፡ እንዲህ ያለ የመታለል ፅዋ የደረሰበትም ምክትል እንደራሴና የሸዋ ገዥ የነበረው ጄኔራል ናዚ ነው፡፡ አበበ ለናዚ እጅ ለመስጠት ዝግጁ መሆኑን ይግለጽ እንጂ በጎን ለሌሎች የአርበኞች መሪዎች ይህ ሁሉ ፋታ ለማግኘት እንጂ ከምር እንዳልሆነ በስውር ልኮባቸው ነበር፡፡ የሆነ ሆኖ እውነቱን ሊጠረጥር ያልቻለው ናዚ በነገሩ ተታሎ የሰላም ድርድሩን ከልቡ ተያይዞት ነበር፡፡ በመጨረሻ ራስ አበበ ጦሩ ቀደም ብሎ ከደረሰበት ጥቃት ማገገሙን በቅጡ ካረጋገጠ በኋላ፣ ጣልያኖች በሌሎች አርበኞች ላይ ያደረሱትን አንድ ዕልቂት ሰበብ በማድረግ ድርድሩን አፍርሶ ትግሉን ቀጥሏል፡፡

በአጠቃላይ መልኩ ስናየው የአርበኞች የነፃነት ትግል በዘመናዊ የኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ አንድ አኩሪ ምዕራፍ ነው፡፡ ኢትዮጵየውያን ለአርነትና ለነፃነት ሲሉ ለመሞት ዝግጁ ለመሆናቸው አንድ ለላ ማረጋገጫ ነው፡፡ ትግሉን የበለጠ ግምት የሚያሰጠው የወራሪውን ኃይልና ጭካኔ በመገንዘብ አመቺ የሆኑ አዲስ ስልቶች ለመቀየስ መቻሉ ነው፡፡ አርበኞች በጠላት ላይ የገኟቸው ድሎች የወሳኝነት ባሕርይ ባይኖራቸውም የኢጣልያ ሠራዊት በአርበኞች ጥቃት ተደናብሮና ተጎሳቁሎ በመጨረሻ እንግሊዞች አገሪቱን ነፃ ለማውጣት ለከፈቱት ዘመቻ ክፉኛ ተጋለጠ፡፡

ይህን ካልን በኋላ ግን የአርበኞቹ ተጋድሎ ያሳያቸውን አንዳንድ ድክመቶች ሳንጠቁም ብናልፍ ከነፃነት በኋላ በአገሪቱ የሰፈነውን ሥርዓት በቅጡ ለመረዳት ያዳግተናል፡፡ መጀመሪያ ነገር የነፃነት ትግሉ በስፋት አገር አቀፍ ቢሆንም ቅሉ በጥልቀት ሁሉን አቀፍ አልነበረም፡፡ በታሪክ ተደጋግሞ እንደሚታየው ለአርነት ተጋድሎ ባለበት ሥፍራ ሁለ፣ ከጨቋኝ ጋር አብሮ መሥራትም (ባንዳነትም) አለ፡፡ በዚህ መሠረትም አየሌ ኢትዮጵያውያን በግል ጥቅም ተታለው ወይም “ራስክን አድን” በሚለው መርህ የኢጣልያን ባንዳ ሆነዋል፡፡ ውስጠ ዐዋቂበመሆናቸውም እነዚህ ባንዳዎች በአርነት ትግሉ ላይ የኢጣልያ ሠራዊት ካደረሰው የበለጠ ጉዳት አድርሰዋል፡፡ ይህም ሆኖ ግን ነፃነት ከተመለሰ ወዲህ በስደተኞችና በባንዳዎች መካከል የተፈጠረው ግንባር ተጠቃሚ በመሆን ከቅጣትና ውርደት ይልቅ የጠበቃቸው ሹመትና ሽልማት ነበር፡፡

ለነፃነት ለመታገል በቆረጡት መሀልም ቢሆን ብዙውን ጊዜ ከኅብረት ይልቅ ልዩነት ነበር የሚታየው፡፡ በአያሌ የሽምቅ ተዋጊ ቡድኖች መካከል የሰፈነው ስሜት የጎጠኝነትና የእርስ በርስ መፎካከር ነበር፡፡  የአንድ ጓድ አባላት አፈንግጠው ከሌላው መቀላቀል፣ ይህም የሚያስከትለው የአንዱ ማበጥና የሌላው መኰስመን ግንኙነቶችን ለማቃቃር ረድቶ ነበር፡፡ ስለሆነም አርበኞቹ ብዙ ጊዜ ጠላትን አብረው ከውጋት ይልቅ እርስ በርስ መፋጀቱን ነበር የተያያዙት፡፡ ለዚህም ሁኔታ በምሳሌነት መጥቀስ የሚቻለው በጎጃም በደጃች መንገሻ ጀምበሬና በደጃች ነጋሽ በዛብህ መካከል፣ እንዲሁም በልጅ ኃይሉ በለውና በልጅ በላይ ዘለቀ መካከል የነበረውን ችግር ነው፡፡ በአርበኞቹ መካከል ኅብረት ለመፍጠር ያዳገተው የሚጋሩት ርዕዮትና የፖለቲካ ድርጅት ቀርቶ ሁሉም መሪያችን ብሎ የሚመከተው አንድ ሰው ባለመኖሩ ነው፡፡

አርበኛው ያውራ ያለህ በማለቱ ይመስላል አሁንም ስሙ የልሞተው የኢያሱ ልጆች ፊት መኖራቸው እንኳ ያልታወቀውን ያህል በችግሩ ጊዜ የአርበኞች መሰባሰቢያ አድባር ለመሆን የበቁት፡፡ በዚህም መሠረት ዮሐንስ ኢያሱ የጐንደር አርበኞች ሲያስተባብር፣ መልአከ ፀሐይ ኢያሱ ደግሞ የሸዋ አርበኞች አውራ ሆኖ ማዕረግና ሹመት ሊሰጥ ችሏል፡፡ (ለምሳለ አበበ አረጋይን ራስ ማሰኘት)፡፡ ከዚህ ለየት ባለ መንገድ ደግሞ ሪፑብሊካዊ ዝንባሌ የነበረው ታከለ ወልደ ሐዋርያት ከክፍለ ሀገር ክፍለ ሀገር እንዲሁም ከኢትዮጵያ ሱዳን፣ ከሱዳን ኢትዮጵያ በመመላለስ አርበኞቹን በአንድ የፖለቲካ ድርጅት ጥላ ሥር ለማሰባሰብ ያልተሳካ ሙከራ አድርጓል፡፡ የአርበኞቹ ትግል የጐጠኝነት ባሕርዩን እንደያዘ በመዝለቁም ግልጽ የሆነ የፖለቲካ አቅጣጫ ማግኘት ተስኖታል፡፡ ፖለቲካዊ በወታደራዊ፣ እስትራቴጂው በታክቲክ ተውጦ ቀርቷል፡፡

ይህን ድክመት በጠኑ ሊያካክሱ የቻሉ ሁለት ክስተቶች ነበሩ፡፡ እነዚህም የጥቁር አንበሳ ድርጅትና በሱዳን በነበሩ ስደተኞች ዘንድ የተጀመረው ሪፑብሊካዊ ንቅናቄ ናቸው፡፡ እርግጥ ሁለቱም በነፃነት ትግሉ ላይ የነበራቸው ተፅዕኖ ውሱን ነበር፡፡ የመጀመሪያው ጣልያኖች በገቡ ዓመት ባልሞላ ጊዜ ውስጥ ባጭሩ ሲቀጭ፣ ሁለተኛው ደግሞ ካገሪቷ ክልል ውጭ የሚካሄድ በመሆኑ የነበረው ጠቀሜታ ከፖለቲካው ይልቅ አካዳሚያዊ ነበር ማለት ይቻላል፡፡ ይሁን እንጂ ሁለቱም የነፃነት ትግሉን ፖለቲካዊና ርዕዮታዊ ፈር ለማስያዝ የተደረጉ የሚደነቁ ጥረቶች ነበሩ፡፡

የጥቁር አንበሳ ድርጅት ከሆለታ ወጣት መኰንኖችና ከውጭ አገር ተምረው ከተመለሱ ምሁራን የተውጣጣ ሲሆን፣ ፕሬዚዳንቱ በእንግሊዝ አገር የከብት ሕክምና ያጠናው ዶ/ር አለመወርቅ በየነ ነበር፡፡ የድርጅቱን የፖለቲካ አመራር የሚሰጠው የሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴው ሲሆን፣ በተጨማሪም በኤርትራዊው መኰንን በሌ/ኰሎኔል በላይ ኃይለ አብ የሚመራ የሥልጠና ካውንስል ነበረው፡፡ ድርጅቱ የሚተዳደረው በባለ አሥር አንቀጽ የመተዳደሪያ ደንብ ሲሆን፣ ከእነዚህም በከፍተኛ ደረጃ ሊጠቀስ የሚችለው የፖለቲካው አመራር በወታደራዊ አመራሩ ላይ የለውን የበላይነት የሚያረጋግጠው አንቀጽ ነው፡፡ አሁን እንደሚታወቀው ይህ የሽምቅ ውጊያ አደረጃጀት መሠረታዊ ሕግ ሆኗል፡፡ ከዚህ በተጨማሪ መተዳደሪያ ደንቡ አባላቱ ገበሬውን እንዳያንገላቱ አጥብቆ ከመከልከሉም በላይ ለጦር ምርኮኞች ሰብአዊ ርኅራኄ እንዲያሳዩ፣ ስደትን እንዳይሹና በጠላት እጅ ከመውደቅ ይልቅ ሕይወታቸውን እንዲያጠፉ ይደነግግ ነበር፡፡ የመጨረሻውን የፖለቲካ ሥልጣን በተመለከተ ግን ድርጅቱ ለአፄ ኃይለ ሥላሴና ለንጉሣዊው ቤተሰብ ያለውን ታማኝነት አረጋግጦ ነበር፡፡

በዚህ በኋለኛው ረገድ ሪፐብሊካዊው እንቅስቃሴ ንጉሣዊ አገዛዝን በሪፐብሊክ ለመተካት በማለሙ አንድ ዕርምጃ ወደፊት የሄደ ነበር፡፡ ንቅናቄው ማቆጥቆጥ የጀመረው ከጣልያን ወረራ በፊት ድሬዳዋ በነበሩ የፈረንሳይ ትምህርትና ባህል በቀመሱ ምሁራን አካባቢ ነው፡፡ በስደት ላይ የነዚህን ፈለግ የተከተሉት ሪፐብሊካውያን ከሁሉም በላይ የአርበኞችን ኅብረት አበክረው ጠየቁ፡፡ ኋላ እንግሊዞች በኢትዮጵያ ላይ የጫኑትን ጥገኝነት አስቀድመው በመተንበይ ይመስላል የኢትዮጵያ ሕዝብ ራሱን በራሱ ነፃ ማውጣት እንዳለበት እንጂ በውጭ ዕርዳታ መተማመን እንደሌለበትም በጥብቅ አስገነዘቡ፡፡ ከነፃነት በኋላም ፍላጎታቸው ሕዝብ የመረጠው መንግሥት እንዲቋቋም እንጂ ዘውዳዊ አገዛዝ እንደገና ተመልሶ እንዲቋቋም አልነበረም፡፡ አሁን ካለንበት የታሪክ ወቅት አንፃር ይህ ንቅናቄ የበለጠ ጠቀሜታ የሚኖረው የኢትዮጵያን የተለያዩ ግዛቶች ባሕርያት ለማቻቻል እንዲያመች የፌዴራላዊ ቅርጸ መንግሥት ሐሳብ ማቅረቡ ነው፡፡ ይህን ተንተርሶም ነው “የሸዋ አበባ ያብባል ገና” የሚለውን የአጀብ ዘፈን “አዲስ አበባ ያብባል ገና” በሚል የተካው፡፡ የንቅናቄው አባላት አስተሳሰብ የመጀመርያው አንድ ግዛት የሚያሞካሽ በመሆኑ የዚያው ግዛት ተወላጅ ባልሆኑት ላይ ቅሬታ ሲፈጥር፤ ሁለተኛው ግን የጋራ የሆነችውን ዋና ከተማ በማወደሱ ሁሉን ለማሰባሰብ ይችላል የሚል ነው፡፡ ከነፃነት በኋላ ግን ሁኔታው ለንቅናቄው አመቺ አልነበረም፡፡ አባላቱ በንጉሠ ነገሥቱም በሪፐብሊካዊነታቸው፣ እንግሊዞች ደግሞ በአፍቃሪ ፈረንሳይነታቸው ጠምደዋቸው ደብዛቸው ሊጠፋ በቃ፡፡

የአርነት ትግሉ የመጨረሻውንና ወሳኙን ምዕራፍ የያዘው አርበኞቹ በጉጉት ይጠብቁ እንደነበሩት ጦርነቱ ዓለም አቀፋዊ ስፋት ሲያገኝ ነው፡፡ በሰኔ 1932 ሙሶሊኒ ምናልባትም በሕይወቱ ዐቢይ ሊባል የሚችለውን ስህተት ፈጸመ፡፡ ይኸውም የሂትለር አጋር በመሆን ሁለተኛ ዓለም ጦርነት ውስጥ መግባቱ ነው፡፡ በዚህ ዕርምጃም የኢትዮጵያ ወረራውን ያሳካለትን የእንግሊዝና የፈረንሳይን አይዞህ ባይነት ከመቅጽበት አጣ፡፡ በተለይም እንግዞች በፊት እንደዋዛ ያልተመለከቱትን ያህል አሁን በምሥራቅ አፍሪቃ ቅኝ ግዛቶቻቸው ላይ እንደሚያንዣብብ አደገኛ መቅሰፍት አዩት፡፡ በዚህም አኳኋን ከ19ኛው መቶ ዓመት መገባደጃ ጀምሮ የጣልያን ጽኑ ወዳጅ የነበረችው እንግሊዝ ወደ ቀንደኛ ጠላትነት ተለወጠች፡፡ ባንፃሩም የኃይለ ሥላሴ የፖለቲካ ጠቀሜታ ገዝፎ መታየት ጀመረ፡፡ ኢትዮጵያያውያንን በሙሉ ሊያስተባብርላቸው የሚችል ዓይነተኛ መሣሪያ ሆኖ ስላገኙት እንግሊዞች በስደት ከነበረበት የገጠር ከተማ አውጥተው ወደ ጦር ግንባሩ አሸጋገሩት፡፡

እንግሊዞች ከጣልያን ላይ ጦር የከፈቱት ከሱዳንና ከኬንያ ነበር፡፡ በማጀር ጀኔራል ሰር ዊልያም ፕላት የሚመራ ጦር በኤርትራ የሚገኘውን የኢጣልያ ጦር ሲያጠቃ፣ በኮሎኔል ዳንኤል ሳንፎርድና በሻለቃ ኦርድ ቻርልስ ዊንጌት የሚመራው “የጌዴዎን ጣር” የተባለው ንጉሡን አጅቦ ወደ ጎጃም አመራ፡፡ በደቡብ በኩል ደግሞ በሌተናል ጄኔራል ሰር አላን ከኒንግሃም የሚመራው ጣር ወደ ኢጣልያ ሶማሊላንድ፣ ብሎም ወደ ሐረር አቀና፡፡ ሆኖም የጣልያ ጦር በቀላሉ የሚበገር አልሆነም፡፡ በተለይ እንግሊዞች ከረንን መያዝ የቻሉት በሁለቱም ወገን ብዙ መስዋዕትነት ከተከፈለ በኋላ ነው፡፡ ከከተማይቱ ወጣ ብሎ የሚታየው የአያሌ እንግሊዞች መቃብር ለፍልሚያው መራራነት ቋሚ ማስረጃ ነው፡፡ ጣልያኖች በተጨማሪም ለአጭር ጊዜ የእንግሊዝ ሶማሌላንድን ለመያዝና በመተማ በኩል የተሰነዘረውንም ጥቃት ለመመከት ችለው ነበር፡፡ ይሁን እንጂ አምስቱ ዓመት የአርበኞች ትግል ያመነመነው ጣር በመጨረሻ የሽንፈት ጽዋ ከመቅመስ ሊድን አልቻለም፡፡ የእንግሊዝና የአርበኞች ጦር ማጥቃቱን ቀጥሎ፣ አዲስ አበባ በመጋቢት 28 ቀን 1933 ከጠላት ነፃ ለመሆን ቻለች፡፡ ከዚያም በሚያዝያ 27 ጣልያኖች በገቡበት ልክ በአምስት ዓመቱ ኃይለ ሥላሴ በድል አድራጊነት ወደ መናገሻ ከተማው በመግባት ለሠላሳ ሦስት ዓመት የሚቆየውን ሥልጣኑን እንደገና መሠረተ፡፡

ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እንገልጻለን፡፡

spot_imgspot_img
- Advertisment -

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

Related Articles