Monday, March 20, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -

የተመረጡ ፅሑፎች

ስንቱን እንልመደው?

ሰላም! ሰላም! ፍቅር፣ ጤና፣ በረከት ከእናንተ ዘንድ አይጥፋና እንዴት ከርማችኋል? ኧረ እንደ እኔ ዓይነቱን ሰላምተኛ ተው ጠበቅ እያደረጋችሁ ያዙ ተው! ምቀኛ፣ ቀማኛ፣ ሐሜተኛ፣ ሐኬተኛ ምኑ ቅጡ በበዛበት በዚህ ዘመን እንደ እኔ እንደ አንበርብር ምንተስኖት ዓይነት ሰው እንዴት ቸል ይባላል? ምንድነው እንዲህ ራስን ማዋደድ እንዳላችሁኝ ጠረጠርኩ። ጎበዝ በዚህች መከረኛ አገራችን የመጣ የሄደው በሕዝብ ስም ራሱን ሲያዋድድ አልኖረምና ነው የእኔ የሚገርማችሁ? ወደን ነው እንዴ ከዚህ ቀደም ብዙዎችን የተቀየምነው? ወሬ እንደ ሸረሪት ድር እያደሩ ከሚያወዛግቡን ዓይናቸውን እያፈጠጡብን እስከሚያስፈራሩብን ድረስ ስንቱን አሳለፍን፡፡ አቤት ስንቱ በራሱ ዓለም ትልቅ ነኝ ሲል ወደቀ መሰላችሁ? እኔማ ስንቱን እታዘበዋለሁ ይብላኝ እንጂ ማስተዋል ለተሳነው። ‹‹እኔምለው ማስተዋልና ማመዛዘን የሚባሉትን የጠቢብ ሰው መለያዎች ከፈረንጅ አገር ማስመጣት ይቻል ይሆን እንዴ?›› በማለት ምሁሩን የባሻዬ ልጅ ብጠይቀው፣ ‹‹አንተ ደግሞ አዕምሮአችንን ብናሠራው ኖሮ ከማን እናንስ ነበር? ፈረንጅ አምላኪ ሆነን እንጂ በጥንቶቹ የእኛ ሰዎች ስንት ታሪክ ተሠርቷል እኮ…›› አለኝ። እኔማ ፈረንጅ የማይፈበርከው የለም ከሚል የሞኝ አስተሳሰብ መላ ያገኘሁ መስሎኝ ነበር። ‹‹የቸገረው እርጉዝ ያገባል›› ነዋ ተረቱ። ኧረ ዘንድሮ ነገር ያረገዘው በዝቷል!    

እግረ መንገዳችንን ስለእርጉዝ እናቶች አንስተን ትንሽ ብናወራስ? ያው እንዳልኳችሁ ትንሽ በዛ ብለውብኛል። እናም አንድ ወዳጄን ‹‹ምንድነው እሱ?›› ብዬ ብጠይቀው፣ ‹‹ያለፈው ዙር ተጋቢዎች ናቸው። አንዳቸውም አልጠሩህም ነበር?›› ብሎ በሽሙጥ መለሰልኝ። ያለፈው ተጋቢዎች ማለቱ የተገለጠልኝ ቆይቶ ነው። አቤት የአንዳንዱ ሰው ሽሙጥ እኮ፡፡ እናማ ከእርግዝና ጋር ተያይዞ አንድ ማለዳ ከባሻዬ ልጅ ጋር ታክሲ እየጠበቅን ስለሕዝብ ቁጥር መጨመር የተጨዋወትነው ትዝ አለኝ። የባሻዬ ልጅ፣ ‹‹አካሄዳችን እንደዚህ አገም ጠቀምና ኑሮ ሰጥቶ እየነሳን እንዲህ የምንቀጥል ከሆነ ጉዳዩ ሊታሰብበት ይገባል…›› ሲል ሐሳቡን አካፍሎኛል። ወዲያው ከእሱ ጋር ተለያይተን ታክሲ ይዤ ወደ ሥራዬ ስሄድ አጠገቤ የደረሰች እርጉዝ መጥታ ተቀመጠች። ‹‹ስንት ወርሽ ነው?›› ብላት፣ ‹‹አይታወቅም አሁንም ሊመጣ ይችላል…›› ብላ ቀልቤን ገፈፈችው የታክሲው ሰው በሙሉ ሲያዋልድ ታሰበኝ፡፡ ኧረ ዘንድሮ ከመሬት ተነስቶሚያስፈራራን በዛ ጎበዝ፡፡ ‹‹ለመሆኑ መውለድንና የሕዝብ ቁጥር መጨመርን እንዴት ታያቸዋለሽ?›› አልኳት ቀስ ብዬ። ‹‹ልጅማ መወለድ አለበት። የሚወለደው ልጅ እኮ ምላስ ብቻ ሳይሆን እግርና እጅም አለው። እንዴት አድርገን ጠንካራ፣ ታታሪና ብርቱ ሠራተኛ እንደምናደርገው ነው ማሰብ ያለብን። ቻይናን አታይም? 1.5 ቢሊዮን ሆነው ዓለምን በዕድገት እየመሩ ነው…›› ብላኝ እርፍ። ወይ ጉድ አልኩላችኋ፡፡ ለነገሩ ልጆቻችንን እንዴት በሥርዓት ማሳደግ እንዳለብን አዋቂዎች የሚነግሩንን ሳስታውስ፣ ይህች ሴት ልበ ብርሃን ናት በማለት ደመደምኩ፡፡ ማወቅ እንዲህ ነዋ! 

እንዲያው ልፉ ቢለን ቅድም ተስቶን ስለማይሰማን አጓጉል ወሬ ነገር ተነጋግረናል ለካ? ለነገሩ አለመደማመጥ ፋሽን ስለሆነ ብዙ አንገረምም። እንደ እሳት የተዛመተው ወሬ በዘመኑ ነገሮችን እየቆራረጠ አለመደማመጡን ማብዛቱን ታስታወሳላችሁ አይደል? ‹‹አይ የለም ይኼ አያዋጣንም ያንን እንሞክረው…›› እውነት የሚል ጠፍቶ ይመስላችኋል ብዙ ነገራችን በአንድ ቦይ ብቻ የሚፈሰው? አይደለም፡፡ ክፉኛ አልደማመጥ ብለናል ወገኖቼ፡፡ አዛውንቱ ባሻዬ፣ ‹‹ይኼ ማኅበራዊ ሚዲያ የምትሉት ሰውን አላከባብረው አለ። ያም ከአንዱ ይኼም ከአንዱ የአገር መረጃ ሲጎለጉሉ ቆይተው አካኪ ዘራፍ ይሉብናል። ፌስቡክ የምትሉት ጉድ ለአገር ለምድሩ የጥላቻ ንግግር ማባዘቻ መሆኑ ይታወቃል፡፡ ሰው ግን ወፈፍ እያደረገው ነው እንዴ?›› ቢሉኝ ትዝብታቸው ገርሞኝ ተደመምኩ፡፡ ‹‹በበኩሌ ከቴክኖሎጂው ሠፈር አልያም ከቡቲኩ መንደር፣ ብቻ ከየትኛው ገዝተን እንዳጠለቅነው አልገባኝ ብሏል…›› ስላት፣ ‹‹ምኑን?›› አለችኝ ማንጠግቦሽ ድንግርግር እያለች። ‹‹እንዴ መደማመጥ አለመቻልን ነዋ፡፡ ስለምን እያወራን ነው ታዲያ?›› አልኩዋት ልቤን እየደከመው። አንዳንዶቻችን ግን ኑሮ ምን ቢወደድ የተሻሻሉ የቴክኖሎጂ ውጤቶችንና ፋሽን ልብሶችን መግዛት ያቃተን  አንመስልም]፡፡ ‹‹እንዴት ላዳምጥህ አንበርብር? ወትሮ ለወር ሲበቃን የነበረው የሸመታ ገንዘብ ዛሬ ሩቡን አልችልልኝ አለ። የበዓሉ ወጪ ሲታከልበት ደግሞ የማይቀመስ ሆነ፡፡ ያለን መስሎህ ነው? ሐሳብ ጨረሰን እኮ…›› ብትለኝ ወከክ አልኩላችሁ። አይ ጊዜ!

ጨዋታን ጨዋታ ያነሳዋል አይደል? እስኪ ስለፌስቡክ ደግሞ ትንሽ እንጨዋወት። በድለላ የማገለግላቸው አንዳንድ ደንበኞቼ፣ ‹‹በዚህ ኑሮ ቤት ለመሥራት የቁጠባአካውንትከመክፈት የፌስቡክአካውንትመክፈት ይቀላል…›› ይሉላችኋል። ‹‹እንዴት?›› ስላቸው፣ ‹‹አብዛኛው ሰው ውሎና አዳሩ እዚያ ሆኗል…›› ነው መልሳቸው። በበኩሌ ፌስቡክን ሳስብ ሐሳብን በነፃነት የመግለጽ መብት ጎልቶ ይታሰበኛል።የፕሬስ ነፃነት ተገድቧልየሚሉ ወገኖችንሄዳችሁ ፌስቡክ ላይ ፈልጉትተብሏል ብለው ስም ሲያጠፉ የሰማሁትም ጉድ አለላችሁ። ብቻ ጆሮ ስትሰጡ እኮ ብዙ ስለሚወራ ብዙ መስማታችሁ ግድ ነው። በነገራችን ላይ በእኛ አገር ብቻ ሳይሆን በመላው ዓለም ምሬት ተፈጥሯል፡፡ ታዋቂ ስፖርተኞች በእነ ፌስቡክ፣ ትዊተርና ኢንስታግራም የሚባሉ ገጾቻቸውን ዘግተው መቀመጣቸውን የነገረኝ ምሁሩ ወዳጄ ነው፡፡ ከዘረኛው እስከ ግድያ ጠንሳሹ የተከማቹበት ሠፈር በባለቤቶቹ ካልፀዳ በስተቀር እስከ ወዲያኛው ከዚህ ጉድ እንሰናበታለን ማለታቸውንም አክሎልኛል፡፡

እንግዲህ በክፋት ልባቸው የተለከፈውን ለጊዜው ያሉትን ትተን ወደ ራሳችን ወግ እንግባ፡፡ አንድ ማኅበራዊ ድረ ገጽ በአገርኛ ሥልት መዘርጋት ቢያቅተንም ማኅበራዊ ወሬኞች መሆን ግን አላቃተንም። ‹‹እኔስ የምፈራው መብላት መጠጣታችንንምኮምፒውተራይዝድአድርገነዋል እንዳይሉን ነው…›› አለኝ አብሮኝ ጨዋታውን ሲኮመኩም የቆየው ወዳጄ። እናቅለው ስንል የምናከብደውን ሳስብ የዓለም ነገር አንገሸገሸኝ። ‹‹አወይ ዴሞክራሲ፣ እንዲህ ሄደሽ ሄደሽ መጨረሻሽ ምን ይሆን?›› ይላል ምሁሩ የባሻዬ ልጅ እንዲህ አንዳንድ ነገሮች ሲሰማ። ምን ይበል ታዲያ!

አንድ ወጣት ሰፋ ያለ ቤት ተከራይቶ መሥራት ፈለገና ቤት እንድፈልግለት ነገረኝ። እኔም ተንከራትቼ ኮንዶሚኒየም ሕንፃ ምድር ላይ ያለ ቤት አገኘሁለት። ተስማማውና ተዋውሎ ሲያበቃ፣ ‹‹ለመሆኑ ምን ይሆን የምታዘጋጀው?›› ብዬ ጠየቅኩት። በረጅሙ ተንፍሶ፣ ‹‹ብዙ ነገር። ግን ዋናው ኮምፒውተርን ከእግር ጥፍሩ እስከ ራስ ቅሉ ድረስ በአማርኛ ቋንቋ እንድንጠቀምበት ለማድረግ ነው…›› አለኝ። ‹‹ይኼ ነው እውነተኛው ትራንስፎርሜሽን!›› አልኩ ጮክ ብዬ። ስሜታዊ ጭምር ሆኜ መናገሬን ለዘብ ብሎ አስተውሎ፣ ‹‹አየህ እንደኛ ያለ ሕዝብ ልጣለው ቢል እንኳ ብዙ የማይለቀው የማንነቱ መገለጫ አለ። ማስተዋል ቢሰጠን የሚያምርብንንና የማያምርብንን፣ የሚያኮራንንና የሚያዋርደንን ነገር በጊዜ ብንለይ ጥሩ ነበር። ከወዲሁ ሥራ የሚፈልጉ ነገሮች ቢኖሩም ከአገራዊ ማንነት በፊት የሚቀድሙ አይደሉም…›› ሲለኝ ከመጪው ትውልድ አዲስ ነገር የመጠበቅ ጉጉቴ ጨመረ። ቀጠለናም፣ ‹‹ስንቱን ዘለልነው መሰለህ? ትንሽ ተጉዘን ስናርፍ፣ ትንሽ ሠርተን ሲደክመን፣ ትንሽ ይዘን ስንጣላ ስንቱን ዕድሜና አቅም አባከንነው? ስንቱን ቀዳዳ ሳንደፍን ዘለልነው መሰለህ?›› ሲለኝ በአንዴ ዕድሜ ያስተማረው አዛውንት መስሎ ታየኝ። ኧረ የአንዳንዱስ ወጣት ልብ ከደረጀ ቆይቷል እናንተዬ!

ታዲያ አገራችን አሁን በተያያዘችው የዕድገት ጎዳና (ስለ ዕድገት አልገባን ያለው ሁሉ እንዳለ ሆኖ) ዋናው ግንበኛ ወጣቱ ትውልድ መሆኑ ነው፡፡ ሐሳብ የጠፋበትና ቁሳዊነት የገዘፈበት ዘመን ከቶ ከዚህ በፊት መቼ ይሆን? ምን ላጫውታችሁ መሰላችሁ? ምሁሩ የባሻዬ ልጅ፣ ‹‹አንበርብር!›› አለኝ የሆነ ቀን ከሥራ መልስ ስንገናኝ። ‹‹እህ ምን ተገኘ?›› ስለው፣ ‹‹አንበርብር አገራችን ከባድ ጊዜ ውስጥ ናት፡፡ ይህች አሜሪካ የሚሏት ሰይጣን ግብረ አበሮቿን አሰባስባ ዙሪያችንን እያንዣበበች ነው፡፡ እኛ ደግሞ እንደምታየን እርስ በርስ እየተቧጨቅን ለጠላት ከበባ እየተመቻቸን ነው…›› አለኝ፡፡ በጣም ነው የደነገጥኩት፡፡ ድንጋጤዬ ዙሪያችንን የመከበባችንን ብቻ ሳይሆን እኛ መከበባችንን ችላ ብለን በማይረቡ ነገሮች ላይ መጣዳችን ነው፡፡ ልበ ብርሃኖች አርቀው አስበው ምን ይሻላል ብለው ላይ ታች ሲሉ፣ አዕምሮአቸው የተቆለፈባቸው ደግሞ ተደናቁረው ያደናቁሩናል፡፡ የሆነስ ሆነና እንዲያው ሌላው ቢቀር እንደ አራዳ ልጆች አዕምሮአችንን ከፈት አድርገን ዙሪያችንን ማማተር ያቃተን ለምን ይሆን ብለን ራሳችንን መጠየቅ ያለብን አይመስላችሁም ብዬ ምክር ይቃጣኝና እተወዋለሁ፡፡ ለምን ብትሉ የዘመኑ ሰው ልቡ የተሰቀለው አቋራጭ መንገድ ላይ ስለሆነ ነው፡፡ ግን አቋራጭ ፈላጊው የዘንዶ ጉድጓድ አፍ ላይ ደርሶ ለመሸሽ ዞር ሲል ከኋላው የጅብ ወይም የነብር መንጋ ከች ሲልበት፣ ያኔ ነበር መተያየት ብዬ ለራሴ እየነገርኩ እቆዝማለሁ፡፡ ልፋ ያለው ነገር!

መቼም ቀን መንጎዱን፣ ዕድሜ መጨመሩን፣ ሕይወት መቀጠሏን የምናውቀው እንዲህ ስንገናኝና የሰማነውንና ያየነውን አዲስ ነገር ስንጨዋወት ነው።ከፀሐይ በታች አዲስ ነገር የለምየሚባል ቢሆንም፣ በምድር ስንኖር ግን አሮጌም እኮ አዲስ አለው። ቆይቶ ቆይቶ ተመልሶ ሲመጣ አዲስ መባሉ ይቀርና ነው ታዲያ እጅግ የሚያስደንቅ ነገር እንዲህ ሲገጥማችሁ ወይ ሲያገኛችሁ፣ ይህችንማ ማወራረጃ ይዘን ነው መኮምኮም ያለብን ትባባሉና ወደ ግሮሰሪ ታመራላችሁ። በትንሳዔ በዓል ሰሞን ስለሚጠጣውና ስለሚበላው ነገር ማስታወቂያ በበዛበት ጊዜ፣ እንደ እኔና እንደ ባሻዬ ልጅ አመል ያለበት የሚሮጠው ግሮሰሪ ነው። ሊስተናገድ እንጂ ሊያስተናግድ የቆመ የማይመስለውን አስተናጋጅ፣ በልምምጥና በመከራ የምንፈልገውን ነግረነው ጨዋታችንን ቀጠልን። ‹‹እኔምለው? ለመሆኑሪል ስቴት ቤትህ በመዘግየቱ ምን ልታደርግ አስብሃል?›› አልኩት ቤት የማግኘት ጉጉቱን ስለማውቅ። ‹‹አይ አንበርብር! የእኔ ቢጤዎችን አሰባስቤ በሕግም ቢሆን መጠየቄ አይቀርም። ከዚያ በፊት ግን ብርቱ ውይይት ያስፈልገናል…›› አለኝ እየተጎነጨ። ‹‹ምን ይሆን ውይይቱ?›› ስለው፣ ‹‹እንዲያው ስም ሆኖ ነው እንጂ ምንም የሚያጣላን በሌለበት ክፋትና ስስት ካልሆነ በስተቀር፣ ደንበኞችን ከገንቢዎች ጋር የሚያጋጨን ምክንያት አልነበረም…›› ብሎኝ የያዘውን ጅው አድርጎ ተጋተው። እኔም የነገረኛ ፖለቲከኞችን ነገር ሳስብ ውስጤ በገነ። መጠጥና ብሽቀት ባይጣጣሙም እኔም የመጣልኝን ማንቆርቆር ጀመርኩ፡፡ እንጠጣው እንጂ!

ግሮሰሪው ውስጥ የታደሙትን ማየት ጀመርኩ፡፡ ከጥግ እስከ ጥግ የአገሬ ልጆች ነገን የረሱ እስኪመስሉ የቀረበላቸውን በአንድ ትንፋሽ ይጨልጣሉ፡፡ የዛሬው አጠጣጥ ለየት ስላለብኝ ወደ ባሻዬ ልጅ ዞር ስል የቀረበለትን በአንድ ትንፋሽ ጨልጦ ድጋሚ መጠባበቅ ጀምሯል፡፡ ‹‹ምነው ዛሬ ፈጠን አልክ?›› አልኩት፡፡ ሳቅ እያለ እያየኝ፣ ‹‹ማጅራት መቺ በበዛበት ዘመን ቶሎ ላፍ ላፍ አድርጎ በጊዜ ወደ ቤት መግባት አይሻልም?›› አለኝ፡፡ ውስጠ ወይራ ዘይቤ በበዛበት በዚህ ዘመን አነጋገሩ የበለጠ ጠጠር አለብኝ፡፡ ‹‹የምን ማጅራት መቺ?›› በማለት ጥያቄ አቀረብኩለት፡፡ ‹‹አንበርብር ነገር ይግባህ እንጂ? በዚህ በሠለጠነ ዘመን እንደ ወረደ ወሬ ቀርቷል…›› ሲለኝ ባይባኝም እንደገባው ለመሆን ሞከርኩ፡፡ ስንቶቻችን እንሆን እያስመሰልን የምንኖረው? ‹‹ማስመሰልና አስመሳይነት በሚያዋጣበት በዚህ ዘመን አጉል ድርቅና ወይም ግትርነት ዋጋ የላቸውም…›› ያለኝ ራሱ የባሻዬ ልጅ ነው፡፡ እኔም ዛሬ ከድርቅና ወደ አስመሳይነት ሽግግር በማድረግ ያልገባኝን እንደገባኝ ተቀብዬ ወደ ቤቴ አዘገምኩ፡፡ በሴረኞች ዘመን ስንቱን እንልመደው? መልካም ሰንበት!

Latest Posts

- Advertisement -

ወቅታዊ ፅሑፎች

ትኩስ ዜናዎች ለማግኘት