መንግሥት ከኬንያ ጋር የሚያገናኘውን የላሙና ከሱዳን ጋር የሚያስተሳስሩትን የሱዳን ወደብ ኮሪደሮች፣ ከውጭ ኩባንያዎች ጋር በጋራ የማልማት ዕቅድ እንዳለው አስታወቀ፡፡
ይህ የተገለጸው መንግሥት የውጭ ኩባንያዎች በደረቅ ወደብ ልማት እንዲሳተፉ ያደረገውን የኢንቨስትመንት ማሻሻያ ተከትሎ፣ የተባበሩት ዓረብ ኤምሬትስ ዲፒ ወርልድ ኩባንያ የኢትዮጵያን ድርሻ የበርበራ ወደብ ኮሪደር ለማልማት የሚያስችል ስምምነት በተፈራረመበት ወቅት ነው፡፡
ስምምነቱ የትራንስፖርት ሚኒስትሯ ወ/ሮ ዳግማዊት ሞገስና የዲፒ ወርልድ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ሡልጣን አህመድ ቢን ሱላይም በተገኙበት፣ ሐሙስ ሚያዚያ 28 ቀን 2013 ዓ.ም. በሐያት ሬጀንሲ ሆቴል ተፈርሟል፡፡
ወ/ሮ ዳግማዊት በወቅቱ እንዳስረዱት መንግሥት ባዘጋጀው የትራንስፖርት ዘርፍ የአሥር ዓመት መሪ ዕቅድና ብሔራዊ የሎጂስቲክስ ዘርፍ ፖሊሲ ላይ፣ አማራጭ ወደቦችን የማስፋትና ሌሎች ኮሪደሮችን የመጠቀም ዕድል አስቀምጧል፡፡
መንግሥት የኢትዮጵያን ድርሻ የበርበራ ወደብ ኮሪደርን ለማልማት የሚያስችል ስምምነት ከዲፒ ወርልድ ጋር እንደተፈራረመው ሁሉ፣ በቀጣይ የላሙ ኮሪደርን ከኬንያ ጋር፣ እንዲሁም ከሱዳን ጋር የሚያገናኘውን ኮሪደር ከሱዳን ጋር ለማልማት የሚያስችል ዕቅድ እንደተያዘ ሚኒስትሯ አስታውቀዋል፡፡
‹‹የጂቡቲ ወደብ ኮሪደር ዋነኛ የምንጠቀመው ኮሪደር ሆኖ ይቀጥላል፤›› ያሉት ሚኒስትሯ፣ ነገር ግን ኢትዮጵያ ሰፊ አገር ከመሆኗ አንፃር ሁሉንም ነገር ከአንድ ቦታ በሚመጡ ገቢ ምርቶች ማዳረሷ በሎጂስቲከስ ዘርፍ ውጤታማ እንዳትሆን እያደረጋት ነው ብለዋል፡፡ ‹‹በመሆኑም አማራጩን በማስፋት በአጭር ጊዜ፣ በዝቅተኛ ወጪና ውስብስብነቱ በቀነሰ መንገድ ገቢና ወጪ ምርቶችን ከአገር ውስጥና ወደ አገር ውስጥ ማስገባት አለብን ብለን ስለምናምን፣ እንደ መጀመሪያ እንቅስቃሴ ከዲፒ ወርልድ ጋር ስምምነቱን ለመፈራረም በቅተናል፤›› ሲሉ አስረድተዋል፡፡
በቀጣይ ከሌሎች ኩባንያዎች ጋር መሰል ስምምነቶች እንደሚኖሩ በመጠቆም፣ የአገሪቱ በሎጂስቲክስ ዘርፍ ያላትን ደረጃ እንድታሻሽል ከሚያደርጓት ዕርምጃዎች አንዱ ይህ ዓይነቱ እንቅስቃሴ በመሆኑ ዕርምጃው ቀጣይነቱ እያደገ የሚሄድ እንደሆነ ወ/ሮ ዳግማዊት አስታውቀዋል፡፡
ከዚህ ቀደም የደረቅ ወደብ ማልማት ሥራ በመንግሥት ብቻ የሚከናወን እንደነበረ፣ ሆኖም ከዓመት በፊት መንግሥት በወሰነው መሠረት የውጭ ባላሀብቶች በደረቅ ወደብ ልማት ለመሳተፍ የሚያስችላቸው የሕግ ማዕቀፍ እንደተዘጋጀ ይታወቃል፡፡
ከዲፒ ወርልድ ጋር የተደረገው ስምምነት በዋናነት በኢትዮጵያ ግዛት ውስጥ የበርበራ ኮሪደርን ማልማት በመሆኑ ይህም ደረቅ ወደብን የመገንባት፣ እስከ ግማሽ መርከብ ዕቃን የሚችሉ ጎተራዎች (Sailos)፣ የኮንቴይነር ዴፖዎችና ቀዝቃዛ መጋዘኖችን፣ የመንገድና ሌሎች የመሠረተ ልማት ሥራዎችን መገንባት ያካትታል፡፡
ዲፒ ወርልድ የሚያከናውነው የበርበራ ኮሪደር ልማት በአጠቃላይ አንድ ቢሊዮን ዶላር የሚጠይቅ ሲሆን፣ ሙሉ ለሙሉ የኮሪደሩን ሥራ ለማጠናቀቅ እስከ አሥር ዓመት የሚደርስ ጊዜ ይጠይቃል፡፡ ሆኖም በልማቱ ላይ የሚደረጉት የተናጠል ሥራዎችን በመጠቀም እንቅስቃሴ ከተያዘው ዓመት መባቻ ጀምሮ አገልግሎት ላይ የሚውል እንደሆነ ተገልጿል፡፡
የዲፒ ወርልድ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ሡልጣን አህመድ ቢን ሱለይም ኩባንያቸው የሚያከናውነው የሎጂስቲክስ መሠረተ ልማት ግንባታ የኢትዮጵያን የዘርፉን ዕቅድ ዕውን ከማድረጉ ባሻገር፣ ኮሪደሩ ከተገነባ በኋላ የሚፈጠሩ አዳዲስ የሥራ ዕድሎችና የኢንቨስትመንት አማራጮችን በማገዝ ረገድ ትልቅ አስተዋፅኦ እንዳለው አስታውቀዋል፡፡