ከሰበታ እስከ ደወሌ የኢትዮጵያ ጠረፍ ድረስ በተዘረጋው የኢትዮ-ጂቡቲ የባቡር መስመር መሠረተ ልማት ላይ የሚፈጸመው ዝርፊያ መባባሱ ተገለጸ፡፡
በባቡር መስመሩ መሠረተ ልማቶች ላይ የሚፈጸመው ከፍተኛ ዝርፊያ አለመቆሙንና በዚህም ሳቢያ ከፍተኛ የአገር ሀብት የፈሰሰባቸው የባቡር ሐዲድ ብሎኖች እንደሚዘረፉ የገለጹት፣ የኢትዮ ጂቡቲ ስታንዳርድ ጌጅ የባቡር ትራንስፖርት አክሲዮን ኩባንያ ዋና ዳይሬክተር አቶ ጥላሁን ሳርካ (ኢንጂነር) ናቸው፡፡
ዝርፊያው በዚህ የሚቀጥል ከሆነ በኩባንያውም ሆነ በአገር ላይ ከፍተኛ ጉዳት ያስከትላል ብለዋል፡፡ በሌሎች አገሮች በመሠረተ ልማት ስርቆትና ውድመት የሚሳተፉ ግለሰቦች የሚወሰድባቸው ዕርምጃ ከፍተኛ ነው ያሉት ጥላሁን (ኢንጂነር)፣ በኢትዮጵያም ሕጉ በዚያው ልክ ሊጠናክር እንደሚገባና በአጥፊዎች ላይ የማያዳግም ሕጋዊ ዕርምጃ መወሰድ እንዳለበት አሳስበዋል፡፡
በአራት ቢሊዮን ዶላር የተገነባው የባቡር መሠረተ ልማት የአገሪቱ ሀብት መሆኑን እያንዳንዱ ማኅበረሰብ ሊረዳ ይገባል ያሉት ዋና ዳይሬክተሩ፣ በተለይም ከሰበታ እስከ ደወሌ ባለው የባቡር መስመር ግራና ቀኝ የሚኖሩ ማኅበረሰቦች ኃላፊነታቸውን እንዲወጡ አስገንዝበዋል፡፡
በየኢትዮጵያ የባቡር መሠረተ ልማቶችን በአግባቡ በመጠቀም ረገድ ትልቅ ክፍተት እንዳለ ገልጸው፣ የቀድሞው የባቡር መሠረተ ልማት ሀብት አገልግሎት እየሰጠም ሆነ አገልግሎቱን ካቆመ በኋላ ዝርፊያ ሲፈጸምበት እንደቆየ ጠቁመዋል፡፡
በባቡር እንቅስቃሴው ወቅት በሚያጋጥሙ አደጋዎች ከካሳ ከፍያ ጋር በተያያዘ ከፍተኛ ወጪ እንደሚወጣ ይታወቃል፡፡ ሆኖም ይህን የካሳ ክፍያ መሠረት በማድረግ አንዳንድ ግለሰቦች ሆነ ብለው በእንስሳቱ ላይ ጉዳት እንዲደርስ ያደርጋሉ ያሉት ጥላሁን (ኢንጂነር)፣ ማኅበረሰቡ ለእንስሳት ከሚሰጠው ቦታ አንፃር የሚደረገው የካሳ ክፍያ እምብዛም እንዳልሆነና እንስሳቱ መኖራቸው ለማኅበረሰቡ ትልቅ ጥቅም እንዳለው አስረድተዋል፡፡
በተያያዘም የኢትዮ-ጂቡቲ የባቡር መስመር ማቋረጫዎች ላይ ነዋሪዎች ከአንዱ ቀበሌ ወደ ሌላኛው በሚያደርጉት እንቅስቃሴ ከፍተኛ አደጋዎች እንደሚያጋጥሙ የተገለጸ ሲሆን፣ ምንም እንኳን የድርጅቱ ሠራተኞች ምልክቶችን ተጠቅመው ባቡር መምጣትን ቢያመላክቱም በዘላቂነት አደጋውን ለመቀነስ ማኅበረሰቡን ለማስተማር ይሠራል ተብሏል፡፡
በኅዳር ወር አክሲዮን ማኅበሩ በዘርፉ የትራንስፖርት አገልግሎትና መሠረተ ልማት ደኅንነት ላይ የሚያተኩር ውይይት በአዳማ እንዳካሄደ የሚታወስ ሲሆን፣ በወቅቱ እንደተገለጸው ባለፉት ሦስት ዓመታት በ875 እንስሳት ላይ ጉዳት፣ 961 ጊዜ ስርቆትና የንብረት ውድመት ማጋጠሙን፣ የ27 ሰዎች ሞትና የ11 ሰዎች የአካል ጉዳት መመዝገቡን፣ በስርቆትና በውድመት ብቻ ከሰባት ሚሊዮን ብር በላይ ኪሳራ መድረሱ መገለጹ ይታወሳል፡፡