የሕዝባዊ ወያኔ ሓርነት ትግራይ (ሕወሓት) እና ሸኔ የተባሉ ድርጅቶችን በአሸባሪነት መሰየም ዓለም አቀፍ ትብብርን በመጨመር፣ በኢትዮጵያ ላይ እየደረሰ ያለውን ሰብዓዊና ቁሳዊ ውድመት ለመቀነስ ከፍተኛ ሚና እንደሚኖረው የፌዴራል ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ አስታወቀ።
የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ሚያዝያ 23 ቀን 2013 ዓ.ም. እነዚህን ሁለት ድርጅቶች በአሸባሪነት ለመሰየም በሚኒስትሮች ምክር ቤት የፀደቀውን የውሳኔ ሐሳብ ተቀብሎ፣ ሚያዝያ 28 ቀን 2013 ዓ.ም. ባደረገው 13ኛ መደበኛ ጉባዔው ላይ ከተወያየ በኋላ በአንድ ድምፅ ተአቅቦ በሙሉ ድምፅ አፅድቆታል።
የፓርላማ አባላቱ ሁለቱን ድርጅቶች በሽብርተኝነት ለመሰየም የቀረበው ሐሳብ ዘግይቶ የመጣ ቢሆንም፣ በአገሪቱ ላይ እየደረሰ ያለውን ጉዳት ለማስቆም አስፈላጊነቱ ከፍተኛ እንደሆነ ጠቁመዋል።
ድርጅቶች ከጀርባቸው የፖለቲካ አስተሳሰብን መነሻ በማድረግ የፖለቲካ ዓላማን ወይም ግብን ለማሳካት በአገሪቱ እየተከሰቱ ላሉ የዜጎች ሕይወት መጥፋት፣ መፈናቀልና የሀብት ውድመት በዕቅድ፣ በሀብት፣ በገንዘብ፣ በሚዲያና በሰው ኃይል ዕገዛ በማድረግ ፈጻሚና አስፈጻሚ መሆናቸውን ለፓርላማው የቀረበው የውሳኔ ሐሳብ ያመላክቷል።
መሐንዲስ መላኩ የተባሉ የምክር ቤቱ አባል ሁለቱ ድርጅቶች ያደረሱት ጥፋት አልቃይዳ እ.ኤ.አ. በ2011 በአሜሪካ ላይ ካደረሰው ጥቃት፣ አይኤስ የተባለው አሸባሪ ድርጅት በሶሪያና በሌሎች አገሮች እያደረሰ ካለው ጥቃትና ቦኮ ሐራም የተባለው ቡድን በናይጄሪያ እያደረሰው ካለው ግፍ ጋር ቢመዘን በኢትዮጵያ ያለው ግፍ የከፋ ቢሆን እንጂ ያነሰ አይሆንም ብለዋል።
በመሆኑም እነዚህን ድርጅቶች በአሸባሪነት ከመሰየም በላይ ሌላም ተግባር መከናወን እንዳለበት በመጠቆም፣ ያደረሱትን ጉዳት ለዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ በግልጽ ማሳወቅ ለምን አልተቻለም ሲሉ ጠይቀዋል።
ዋና ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ ጌዲዮን ጢሞቲዎስ (ዶ/ር) ለቀረበው ጥያቄ በሰጡት ምላሽ፣ በምክር ቤቱ የፀደቀው የውሳኔ ሐሳብ ዓለም አቀፍ ትብብርና ዕገዛ ለማድረግ ይረዳል ብለዋል። በዚህም ከዓለም አቀፍ የሕግ ስምምነቶች አልፎ ጉዳዩ ሰፊ የሆነ የዲፕሎማሲ ሥራ የሚጠይቅ በመሆኑ፣ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር እንደሚሠራ አስረድተዋል።
‹‹በተለይ በሽብርተኝነት የተሰየሙት ሁለቱ ድርጅቶች ምን ዓይነት ጥፋት አጥፍተዋል? ምንስ እየሠሩ ነበር? አሁንም ምን እያደረጉ እንደሆነ ለሌሎች አገሮች በማስረዳትና በማስገንዘብ አገሮች ከኢትዮጵያ ሕዝብ ጎን እንዲቆሙ፣ እንዲህ ዓይነቱን የሽብር ድርጊት ለማስቆም እንዲያግዙ ጥረት እናደርጋለን፤›› ሲሉ አክለው ተናግረዋል።
‹‹ይሁን እንጂ አንዳንድ አገሮች ዘንድ ስንሄድ ‘አውቆ የተኛን ቢቀሰቅሱት አይሰማም’ እንደሚባለው ነውና የሚሆነው፣ የእነዚህን የሽብርተኛ ቡድኖችን እንቅስቃሴና እኩይ ተግባር እያወቁ ከድርጅቶቹ ጋር የሚተባበሩና ችላም ሊሉ የሚችሉ ስለሚሆን ያ በራሱ አግባብ ይታያል፤›› ብለዋል።
ፓርላማው ያሳለፈው የውሳኔ ሐሳብ በአገሪቱ ባለፉት ጥቂት ዓመታት ኢትዮጵያን የማመሰቃቀል፣ የማፍረስና የማዳከም ፍላጎት ያላቸው የውጭ ኃይሎች እነዚህን ቡድኖች በቅጥረኝነት እየተጠቀሙባቸው እንደሆነ አመላክቷል።
በአሸባሪነት ለተሰየመው ድርጅት በተለያየ መንገድ ድጋፍና ዕርዳታ ማድረግ፣ በመሰል ድርጅቶች በአባልነትም ሆነ በአመራርነት መሳተፍ በሕግ እንደሚያስጠይቅ፣ ሰላማዊና ዜጎች ከድርጅቶቹ ጋር እንዳይተባበሩ፣ እንዲሁም ለድርጅቶቹ ማንኛውም ዓይነት ድጋፍ ከመስጠት እንዲቆጠቡ ለማሳሰብ እንደሚጠቅም የውሳኔ ሐሳቡ ያስረዳል።
የሽብር ወንጀልን ለመቆጣጠርና ለመከላከል በ2012 ዓ.ም. የወጣው አዋጅ ቁጥር 1176 መሠረት፣ በአሸባሪነት የተሰየመ ድርጅት ንብረት በፍርድ ቤት ትዕዛዝ እንደሚወረስ ተደንግጓል።
በሌላ በኩል የሽብር ወንጀል ለመፈጸም የዛተ ሰውን እስከ አምስት ዓመት፣ ያቀደና የተሰናዳ ከሦስት እስከ ሰባት፣ የፈጸመ አካል ደግሞ ከአምስት እስከ 12 ዓመት ድረስ በፅኑ እስራት እንደሚቀጣ ይደነግጋል።
በሌላ በኩል ከሽብር ወንጀል ጋር የተገናኘ ንብረት መሆኑን እያወቀ ንብረቱን ይዞ የተገኘ ወይም የተገለገለበት ማንኛውም ሰው፣ የንብረቱ መወረስ እንደተጠበቀ ሆኖ ከሦስት እስከ አሥር ዓመት እንደሚቀጣ ተደንግጓል።
አዋጁ በተጨማሪ በአሸባሪነት ተሰይሞ ወይም በመሰየም ሒደት ላይ እያለ ድርጅቱ ስሙን፣ ምልክቱን፣ ዓርማውን፣ አካባቢውን ወይም መሰል ጉዳዮችን ቀይሮ ወይም ከዚህ ድርጅት ተገንጥሎ፣ ተከፍሎ በመውጣት እናት ድርጅቱን ሽብርተኛ ያሰኘው ወይም ለማሰኘት መሠረት ከሆነው ሁኔታ ወይም አካሄድ ጋር መሠረታዊ ልዩነት ሳይኖረው ሌላ ድርጅት ቢመሠርት፣ እንደ ሌላ ድርጅት እንደማያስቆጥረውም ይደነግጋል።