Friday, July 12, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
እኔ የምለዉየግብርና ዘርፉ ዕምቅ አቅሞችና በአሥር ዓመቱ መሪ የልማት ዕቅድ የተዳሰሱ የፖሊሲ ድጋፍ...

የግብርና ዘርፉ ዕምቅ አቅሞችና በአሥር ዓመቱ መሪ የልማት ዕቅድ የተዳሰሱ የፖሊሲ ድጋፍ ማዕቀፎች

ቀን:

በፕላንና ልማት ኮሚሽን

በግብርና ዘርፉ የተደረጉ በርካታ ጥናትና ምርምሮች በሚገባ እንደሚያመለክቱት ከሆነ አገራችን ከገጠሟት በርካታ አያዎች (Paradox) መካከል ለግብርና በእጅጉ የሚመች መልክዓ ምድርና ሀብቶችን በጉያ ይዞ መራብና የውኃ አገር (Water Tower) ሆኖ መጠማት ሲሆኑ፣ እስካሁን ድረስ ሀብትን ታቅፎ ከግራ ከቀኝ ድህነትና ወቅት እየጠበቀ የሚያጠቃ ረሃብ ቂሌ የሚያጫውተን ምናልባትም የመጨረሻዎቹ የዓለም ሕዝቦች ልንሆን እንችላለን፡፡ እንዲሁም በቀጣይ ጊዜያት ምናልባትም እየመጡ ያሉት የውኃ ሀብት ዕጥረትና የይገባኛል ሽኩቻዎች፣ የዓለም ሙቀት መጨመርና የተፈጥሮ ሥነ ምኅዳር መዛባት ሥጋቶች የሕዝብ ብዛት፣ የተፈጥሮ ሀብት መራቆት፣ ማዕበል ወዘተ ሌሎች በርካታ የዓለም አገሮች ተቋቁመውት ወይም ተሸንፈው አልፏቸው ቢሆንም፣ በሌላ የምጣኔ ሀብት ዘርፎች ላልጎለበቱት እንደ እኛ መሰል አገር ደግሞ ከድጡ ወደ ማጡ እንደሚሆን ሳይታለም የተፈታ ክሱት ሀቅ ነው፡፡ ባለፉት ተጠቃሽ የቅርብ ዓመታት ዘርፉ እንደ አቅሙ ልኬት እንዳይጎለብት ማነቆ ሆኖ የቆየበት ሌላው፣ ጉዳይ በምርምርና በጥናት አስደግፎ ዕድገቱን ከማምጣትና ዘላቂ ከማድረግ ይልቅ ገበሬውንና ግብርናን የፖለቲካ ርዕዮተ-ዓለም ትንታኔ መሠረትና የድጋፍ መደብ መጠጊያ ሆኖ ተደርጎ ዓመታትን እንደተሻገረ በርካታ ተጨባጭ ማሳያዎችን መጥቀስ ይቻላል፡፡ በዚህም ከእነ ችግሩ ሲጎተት ቆይቶ የተጠራቀመ ዕዳ የሚመስል ሸክም ለዚህ ትውልድ አድርሶታል፡፡

ይህ ማለት የግብርና ዘርፍ በሚገባው ልክ ትኩረት ከተሰጠው፣ የተቀናጀ የአሠራር ሥርዓት ከተነደፈለትና የሠለጠኑ ባለሙያዎች ዕገዛ ካገኘ፣ ለአገራችን ብሎም ለሌሎች የተፈጥሮ ሀብት አጠር አገሮች መድኅን ሊሆን እንደሚችል ሳይታለም የተፈታ ነው፡፡

በዚህ ረገድ በአገራችን በቀጣዮቹ አሥር ዓመታት ሊኖር እንደሚችል የሚገመተውን አዳጊና ከፍተኛሕዝብ ቁጥር የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ፣ ለመሠረታዊ ፍጆታዎች ፍላጎት ማሟያ ከውጭ ወደ አገር ውስጥ የሚገቡ ሸቀጦችና ለውጭ ዕዳ ክፍያ በመካከለኛ ጊዜ የሚያስፈልገውን የውጭ ምንዛሪ ግኝት ለማሳደግ፣ የዘርፉን መዋቅራዊ ሽግግርን ባጠረ ጊዜ ዕውን ለማድረግ፣ ለኢንዱስትሪውናሌሎች ወሳኝ ዘርፎች በቂግብዓትና የሰው ኃይል ለማቅረብ፣ ለሌሎች የአምራች ዘርፎች ምርቶች የተጠቃሚ ገበያ ወይም ፍላጎት የማጎልበትና በስፋት የሥራ ዕድል የመፍጠር አበርክቶት ከግብርናው ዘርፍ ይጠበቃል። ይሁን እንጂ ለረዥም ዘመን ሲንገራገጭ የቆየው የአገራችን የግብርና ዘርፍ ሙሉ በሙሉ በሚባል ደረጃ በኋላቀር የአስተራረስ ሥነ ዘዴና በዝናብ ላይ የተመሠረተ በመሆኑ፣ ለዝቅተኛ ምርታማነትና ለምርት ጥራት ማጣት የተጋለጠ ነው።ዚህም የተነሳ በአዝመራ ወቅት ምርቱ ከግርዱ ተለይቶ የሚሰበሰበው መጠን ከዝናብ መጠን መዋዠቅና በየጊዜው ከሚከሰቱ የድርቅ አደጋዎች ጋር ተያይዞ ከዓመት ዓመት ከፍተኛ ውጣ ውረዶች ይታዩበታል።

መንግሥት እነዚህንና ሌሎች የዘርፉን ፅኑ ደንቃራዎች ለመፍታትና በቀጣዮቹ አሥር ዓመት ሊደረስበት ለታሰበው የልማት ዕቅድ ግብ በርካታ ፈርጀ ብዙ ምላሽና ትስስር የሚጠይቁ ተግባራትን ለመከወን ታሳቢ አድርጓል፡፡

 

በዚህም ቀዳሚው ግብ እስካሁን በነበረው የግብርናና ገጠር ልማት ሥልቶች የተሄደበት መንገድ የሚጠበቀውን የግብርና ትራንስፎርሜሽን ለማምጣትና የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ አመር ስላልሆነ፣ በቀጣዮቹ አሥር ዓመታት ለመስኖ ልማት ትኩረት መስጠት እጅግ አስፈላጊ መሆኑ ታምኖበታል

ለዚህም በቀጣይ ለግብርና ሥራ የሚያገለግሉ አነስተኛ፣ መካከለኛና ትልልቅ የመስኖ ልማቶች በመንግሥት፣ በልማት አጋሮች፣ በግሉ ዘርፍ እንዲሁም በማኅበረሰቡ ትብብር የሚገነቡ ይሆናል። እነዚህን የመስኖ መሠረተ ልማቶች ተጠቅሞ በዓመት ውስጥ ያሉንን የምርት ወቅቶች አሁን ካሉበት ወደ ሦስት ወይም አራት ከፍ በማድረግ የምግብ ዋስትናን ከማረጋገጥም በላይ፣ ለግብርና ማቀነባበሪያ ኢንዱስትሪዎች ግብዓትና ለወጪ ንግድ በቂ ምርት ከማቅረብ አኳያ ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንዲኖረው ይደረጋል፡፡ ለአገራችን ልዩ ልዩ መልክዓ ምድሮችና አግሮ-ኢኮሎጂ ቀጣናዎች ተስማሚ የሆኑ የቴክኖሎጂ ውጤቶችን በመጠቀምና ተደራሽነታቸውን ለአርሶ/አርብቶ አደር በማረጋገጥ ላይ የተመሠረተ፣ የአርሶ/አርብቶ አደሩን አቅም ያገናዘበ አገር በቀል የግብርና ሜካናይዜሽን ቴክኖሎጂዎች ፈጠራና ሥርጭት ሥርዓትን በማጎልበት ምርትና ምርታማነትን በማሳደግ የአርሶ አደሩን ገቢ ትርጉም ባለው መልኩ ማሳደግ እንደ ግብ ተይዟል፡፡ ለዚህም ግብ ስኬት እንዲረዳ በሚቀጥሉት አሥር ዓመታት የግብርና ዘርፉ የሚጠቀማቸውን ማናቸውንም የቴክኖሎጂ ግብዓቶችና ማሽነሪዎችን ከግብር ነፃ በማድረግና የሊዝ ፋይናንሲንግ የብድር ሥርዓት በመገንባት ግብርናን ለማዘመን በትኩረት ይሠራል። ምንም እንኳ የግብርናው ሜካናይዜሽን አገልግሎት ዋና ምሰሶ የግሉ ዘርፍ መሆኑ ቢታመንም፣ መንግሥታዊ ዘርፉ ደግሞ ከአጋዥ አካላት ጋር በመሆን የቁጥጥርና ፍተሻ እንዲሁም ክትትል ሥራዎችን ይሠራል። በዚህ ዘርፍ ግንባር ቀደም ሚና ያለውን የግሉን ዘርፍ በሚገባው ልክ ለማሳተፍም የተለያዩ ዓይነታዊና አኃዛዊ የማበረታቻ ሥልቶች ተግባራዊ ይደረጋሉ።

ሌላው ዘርፉን ለማዘመንና ምርታማነቱን ለማሻሻል መንግሥት ለመከተል ታሳቢ ካደረጋቸው መንገዶች ውስጥ ተጠቃሹ፣ የመሬት ማሰባሰብና ኩታ ገጠም ግብርና ነው፡፡

ይኸውም በከፍተኛ ምርታማነታቸውና ከአንድ ወቅት በላይ አብቃይነታቸው ሚታወቁ የምግብ ሰብል አምራች አካባቢዎች ያሉ አርሶ አደሮች የመሬት ይዞታዎቻቸው እጅግ አነስተኛ፣ የተበጣጠሱበተለያዩ ቦታዎች በሁዳድ መልክ ተበታትነው የሚገኙ በመሆናቸው የእርሻ ሜካናይዜሽንንና ሌሎች የተሻሻሉ የግብርና ቴክኖሎጂዎችን ለመጠቀም አዋጪ ካለመሆኑም በላይ፣ የድኅረ ምርት ማሰባሰብና ጥራት ቁጥጥር ሥራዎችን ለመሥራትም አዳጋች አድርጎታል። ይህንን ችግር በዘላቂነት ለመፍታትና ዘርፉን ለማዘመን አርሶ አደሮች በመሬታቸው የመጠቀም መብትን እንዲሁም መሬት ነክ ሕገ መንግሥታዊ ድንጋጌዎችን በማይነካ ሁኔታና ይህን መሰሉ ትግበራ አዋጭ በሆነባቸው አካባቢዎች ብቻ ኩታ ገጠም መሬቶችን አንድ ላይ በማሰባሰብ (Land Consolidation)፣ የኩታ ገጠም ይዞታ አሠራር ሥርዓት መዘርጋት አስፈላጊነቱ የማያጠያይቅ ነው በመሆኑም በረቂቅ የመሬት አጠቃቀም አዋጁ ላይ የተጠቀሱትን የተለያዩ ዘዴዎችን በመጠቀምና ከባለድርሻ አካላት ጋር በመቀናጀት፣ የገጠር መሬት የኩታ ገጠም ይዞታ የግብርና አሠራርን የማሻሻልና የኮንትራት እርሻ አሠራርን የማጎልበት ሥራ በልማት ዕቅዱ ዘመን በስፋት ይሠራል።

ይህም አርሶ አደሮችን በተነፃፃሪ የተሻለ የመሬት ይዞታ እንዲኖራቸው በማገዝ፣ ምርትና ምርታማነታቸውን በማሻሻል፣ ገበያ ተኮር ሰብሎችን በማምረትና የተቀናጀ የገበያ መረጃ ሥርዓት በመፍጠር ቀስ በቀስ ወደ ኢንቨስተርነት እንዲያድጉ ያግዛቸዋል፡፡

ሌላው በዘርፉ የፖሊሲ ማዕቀፍና የአሥር ዓመቱ የልማት ዕቅድ ትኩረት የተሰጠበት ዓብይ የግብርና ሀብት የእንስሳት ሀብት ልማት ነው፡፡

በተጨባጭ እንደምንረዳው የእንስሳት ሀብት ልማትን መደገፍ የአረባብ ሥርዓትን ከማሻሻልና ገበያ መር ከማድረግ ይጀምራል። ለዚህም በእንስሳት ጤና አገልግሎት ውስጥ የግሉን ዘርፍ ሚና ማሳደግ፣ የመኖ ምርትን ስብጥር መጨመርና ማስፋፋት፣ እንዲሁም የግብይት ማዕከላትን ማጠናከር ዋና ዋና ትኩረት የሚደረግባቸው ጉዳዮች ናቸው። የኳራንቲን ማዕከላትን አጠናክሮ ወደ ሥራ ማስገባትና ሌሎች ከግብይት ጋር የተያያዙ መሠረተ ልማቶችን በመንግሥትና የግሉ ዘርፍ ሽርክና ማሟላት፣ ዘመናዊ የምርት ዱካ ሥርዓትን መተግበር፣ የግብርና ፋይናንስና ኢንሹራንስ ሥርዓቶችን ማሻሻል፣ የአርብቶ አደር አካባቢዎችን ከእንስሳት በሽታዎች የፀዱ ማድረግና ሕገወጥ ንግድን ትርጉም ባለው መንገድ መቆጣጠር በቀጣይ ትኩረት የሚደረግባቸው ይሆናል። በተያያዘም በኤክስፖርት ቄራዎችና በአርቢዎች መካከል ቀጥታ የምርት ግብዓት ግንኙነቶችን ማዳበር ትኩረት ይደረግበታል።

የአትክልትና ፍራፍሬና ዕፀ ጣዕም (ሆርቲካልቸር) ልማት ዋና የትኩረት አቅጣጫ የግብዓት አቅርቦት ሥርዓቱን ማዘመን ነው።

ይህም ማለት ገበያ ተኮር የሆነና የገበያውን ፍላጎት የሚያሟሉ ከፍተኛ ምርታማነት ያላቸው ዝርያዎችን በጥናትና ምርምር እንዲሁም በሥርፀት ማፍለቅና ማሰራጨት፣ እንዲሁም በዘርፉ የግሉን ዘርፍ ተሳትፎ ማሳደግን ያጠቃልላል። በተጨማሪም የዘመናዊ ችግኝ ማፍያ ልማት ስትራቲጂያዊ በሆኑ ቦታዎች ላይ ማጠናከር፣ የግብይት ማዕከላትን ለአርሶ አደሩ ቅርበት ባላቸው አካባቢዎች ማደራጀት፣ የማቀዝቀዣ ማሽኖችን መሠረተ ልማት ከግሉ ዘርፍ ጋር በመሆን ማመቻቸት፣ እንዲሁም ከገበያ ትስስር ጋር በተያያዘ በትልልቅ የሆርቲካልቸር ምርት ሰብሳቢዎችና በአርሶ አደሮች መካከል ቅርበት የሚፈጠርበትን ሥርዓት መዘርጋት ትኩረት የሚሰጣቸው ይሆናል።

ሌላው በግብርናው ልማትና ዝመና ረገድ የሚከናወነው ተግባር የፈርጀ ብዙ ምላሽ ሥራዎችን የሚያስተገብሩ ትልሞችን መንደፍ ነው፡፡

በአጠቃላይ የግብርና ልማትን በማፋጠን አገራዊ ልማትን ለማረጋገጥ የገጠርና ከተማ ትስስር ወሳኝ በመሆኑ የተሟላና ውጤታማ የግብርናና ገጠር ልማት ላይ በትኩረት ይሠራል። ለዚህም የተቀናጀ ቤተሰብ ተኮር አሠራሮችን በሙከራ ደረጃ በመፈተሽ በልማት ዕቅዱ ዘመን በስፋት ለመተግበር አቅጣጫ ተቀምጧል።

በተለይም በሙከራ ደረጃ ላይ የሚገኘውን የዘርፈ ብዙ ወረዳ ትራንስፎርሜሽን ውጥን ማስፋት ላይ በትኩረት ይሠራል። ይህም ቤተሰቦች የተሻለ ገቢ፣ የአኗኗር ዘይቤ፣ የዕውቀት ደረጃና ጤናማ ቤተሰብ እንዲኖሯቸው የሚያስችል እንደሚሆን ይታመናል። በተጨማሪም ለአካባቢያቸው ሁለንተናዊ ደኅንነት በባለቤትነትና አብሮነት መንፈስ እንዲተጉ የትብብር ዓውዶችን የሚያመቻችና ለኅብረተሰቡ የቀረበ የአሠራር ሥርዓት በመዘርጋት፣ ልምምድን የሚፈጥር መርሐ ግብር ይሆናል ተብሎ ይጠበቃል። ለዚህም የመንግሥት ተቋማትን፣ የኅብረተሰቡን፣ የግሉን ዘርፍና መንግሥታዊ ያልሆኑ አጋር አካላትን ተሳትፎ ለማጠናከር የሚያስችል አሠራርን በዘላቂነት ለመዘርጋት የሚያስችል ሲሆን፣ የመንግሥት ተቋማት ተናቦና ተቀራርቦ መሥራትን በሁሉም ደረጃና በተለይም ለኅብረተሰቡ ቅርበት ባላቸው አካላት ላይ ትኩረት አድርጎ መሥራትን ዕቅዱ በቅድሚያነት ይዟል። 

በዚህ የልማት ሥልት ተመጋጋቢ የገጠርና የከተማ መስተጋብርን ለመፍጠር የተሻሻለ የመሬት አስተዳደርና አጠቃቀም፣ አማራጭ የሥራ ዕድል ፈጠራ፣ የተሻሻለ መሠረታዊ የመሠረተ ልማት አቅርቦት፣ የተጠናከሩ አገልግሎት ሰጪ ተቋማትና ጠንካራ የማስፈጸም አቅም ግንባታ ቁልፍ ተግባራት ናቸው። ይህ የልማት ሥርዓት የገጠርና የከተማ መስተጋብር ምርታማነትን በማሻሻል፣ የገበያ አማራጮችን በማስፋት፣ አገልግሎትን በማሳለጥና አመጋገብን በማሻሻል ጤናማና ዘላቂነት ያለው ዕድገት እንዲመዘገብ የራሱን ከፍተኛ ሚና ይጫወታል። ይህ አሠራር በተጨማሪም የኅብረተሰቡን ዕምቅ የልማት ኃይልና የማደግ ፍላጎትን አዋህዶ የቤተሰብ ለውጥን በማሳለጥ፣ የቀበሌ፣ ወረዳ፣ ክልልና አገራዊ  ለውጥን በአጭር ጊዜ በማምጣት የዘላቂ ልማት ግቦችን አካታች በሆነ መልኩ ለማሳካት የሚያስችል ነው።

ከላይ በአለፍ ገደም ለማየት እንደሞከርነው በእርግጥም ግብርናችን ብዙ እጅ ጠምዣዥ ጉዳዮችን ተገዳድሮ አልፏል፡፡ በእርግጥም ግብርናው ለዘመናት የአየር ነውጥ እንደ ድርቅ፣ የፖለቲካ አለመረጋጋት ቀውስ፣ እንደ ጦርነት፣ የገበያ መዋዥቅ፣ የዕውቀት አጠር አተገባበር ዳፋ፣ የተፈጥሮ መክዳት፣ የቸነፈር መብዛት ተለዋዋጭ ፖሊሲዎች የተተረማመሱበት ሜዳ የመሆኑን ያህል ሁሉም የየአቅማቸውን እጅ መጠምዘዣ አድርገውበት ተንገዳግዶ አሁን ላይ ደርሷል፡፡ እንዲሁ ከላይ ለማሳየት እንደተቻለው ኢትዮጵያ ዘመን ተሻጋሪ የግብርና ተመራጭ ቦታ ሆና ትኖራለች፣ ኖራለችም፡፡ ለዚህም ወሳኙ አሳማኝ ማሳያ ብዙም ወጪ የማይጠይቀው ምቹና ዝግጁው የተፈጥሮ ልግስናችን ነው፡፡ በዝናብ ወይም በመስኖ ለመልማት ብዙ ዕምቅ ዕድሎች አሉን፡፡ እርግጥ ነው አሁን ባለንበት ባለ ብዙ ገበሬና ብጥስጣሽ መሬት ላይ በሚጣል የሰብል ግብርና ዘርፉን ብዙም ማፈናጠር ባይቻልም፣ ዘርፉን በተቀነሰና የሠለጠነ የሰው ኃይል ስምሪት፣ ከተደራጁ የግብርና መሣሪያዎች፣ ቴክኖሎጂዎችና የግብርና ማቀነባበሪያዎች ጋር በማያያዝ የአገራችን ግብርና የተፈጥሮን ሚዛንን በማስጠበቅ ከአሁን በተሻለ ውጤታማ ልናደርገው እንደምንችል ተጨባጭነት ያለው ምልከታ ነው፡፡

መንግሥት ባለፉት ሦስት የለውጥ መስፈንጠሪያ ዓመታት ከላይ በዓይነታዊ ድጋፍ ማዕቀፎች፣ ግልጽ መሥፈርቶችና መገለጫዎችን ለማመላከት ከተዘረዘሩ ነጥቦች አንፃር የለውጡን ትሩፋት ወደ አርብቶና አርሶ አደሩ ሌማትና ኪስ ለመክተት በርካታ ተግባራትን ማከናወኑን አስረጂ የሚሆኑ አኃዛዊ እውነታዎችን ለመጠቆም ያህል፣ የግብርና ዝመና ዕውን ለማድረግ ባለፉት ሦስት ዓመታት በርካታ ሪፎርሞች በዘርፉ የተካሄዱ ሲሆን፣ እስካሁን በተከናወኑ ተግባራትም በመስኖ ስንዴ ልማት ከ145 ሺሕ ሔክታር መሬት በላይ ምርት በማከናወን በቆላማ ሥፍራዎች ጭምር በመስኖ ስንዴን የማምረት ሥራ ተከናውኗል። ቆላማ ባልሆኑ አካባቢዎች ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ አሲዳማ አፈርን የማከምና የግብዓት አቅርቦትን የማሻሻል በርካታ ሥራዎች የተከናወኑ ሲሆን፣ የኩታ ገጠም አስተራረስ ዘዴ በሰፊው እየተለመደ እንዲሄድ እየተሠራ ይገኛል።

በግብርና ልማት የግሉን ዘርፍ፣ የማኅበራትን እንዲሁም ሌሎች ተዋንያኖችን ያላቸውን ሚና ለማጎልበት እንዲሁም ምርትና ምርታማነትን ለማጎልበት የሜካናይዜሽን ግብርና መሣሪያዎች ከቀረጥ ነፃ ወደ አገር ውስጥ እንዲገቡ የማድረግ አሠራሮች ተግባራዊ ሆነዋል። በዚህም መሠረት እስካሁን ድረስ የግብርና ሜካናይዜሽንን በማፋጠን ዘርፉን ለማዘመን የሚረዱ በርካታ ቴክኖሎጂዎች ወደ አገር ውስጥ እንዲገቡ ተደርጓል።

የግብርና ፋይናንስን ለማሻሻል በብድር ማስያዣ፣ በፋይናንስ አካታችነትና በመሳሰሉት ዙርያ የግብርና ኢንቨስትመንትንና ምርታማነትን የሚያሻሽሉ በርካታ ሥራዎች የተሠሩ ሲሆን፣ ከዚህም ውስጥ ተንቀሳቃሽ ጥሪቶች ተያዥ በማድረግ አርሶ አደሩና አርብቶ አደሩ የፋይናንስ አቅርቦት እንዲያገኙ ለማድረግ በብሔራዊ ባንክ በኩል አዳዲስ መመርያዎችና ደንቦች እንዲወጡ ተድርጓል። ለግብርና ሜካናይዜሽን የግብዓት ገቢ ንግድ እንዲነሳ በተደረገው ቀረጥና ታክስ ምክንያት የነፃ ቀረጥ ተጠቃሚዎች ቁጥርና ዓይነት እየጨመረ የመጣ ሲሆን፣ እስካሁን ድረስ ከ50 በላይ አዳዲስ የግሉ ዘርፍ ባለሀብቶች በግብዓት አቅርቦት ላይ ለመሳተፍ ከግብርና ሚኒስቴር ፈቃድ ወስደዋል። ከማይክሮ ፋይናንስ ተቋማትና የገጠር ብድርና ቁጠባ ማኅበራት ጋር በመተባበር የግብርና የምርት ግብዓት ብድር ሥርዓት (Inputs Voucher System) ትግበራ የተጀመረ ሲሆን፣ በግብዓት የምርት ግብዓት ብድር ሥርዓት የሚጠቀሙ አርሶ አደሮች ከ49 በመቶ በላይ ጨምሯል። በአጠቃላይ ከሰባት ሚሊዮን አርሶ አደሮች በላይ የዚህ ሥርዓት በመጠቀም ማዳበርያ፣ ምርጥ ዘርና የግብርና ኬሚካሎችን ገዝተዋል። በዚህም አርሶ አደሮች በቅድሚያ መክፈል የሚጠበቅባቸውን የምርት ግብዓት ወጪ እንዲቀንስላቸው ማድረግ ተችሏል። በአጠቃላይ በተወሰዱት ዕርምጃዎች ከ1.5 ሚሊዮን በላይ የሥራ ዕድሎችን በገጠሪቱ የአገራችን ክፍል ለመፍጠር ተችሏል። ከዚህም ውስጥ 67 በመቶ ቋሚ የሥራ ዕድሎች ሲሆኑ ከተፈጠሩት የሥራ ዕድሎች ደግሞ 30 በመቶ በሴቶች የተያዙ ናቸው። የሥራ ፈጠራን ለማስፋፋትም ከ55 ሺሕ በላይ ኢንተርፕራይዞች ተቋቁመዋል።

ሆኖም መንግሥት እኔ ያቀረብኩት ይኼ አማራጭ ብቻ ለዘርፉ መጎልበት እንደ መዳኛ ነው ብሎ ሳይወስድ ከተለያዩ ባለሙያዎች በሚቀርቡ የጥናትና ምርምር ሥራዎች በመታገዝና ከነባራዊ ሀቅ ጋር የማላመድ አቀራረቦችን (Pragmatic Approaches) በመከተል፣ ለባለሙያዎች የተለያየ የመከራከሪያ ሐሳብ እንዲመነጭ በማድረግ ከዚህ ሐሳብ በበለጠ ተተግባሪና የበሰሉ ትልሞችንና ሥልቶችን መቅረፅ እንደሚቻል መረዳት እንደሚገባው ያምናል፡፡

ከአዘጋጁ:- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እየገለጽን፣ በኢሜይል አድራሻቸው [email protected] ማግኘት ይቻላል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የሰብዓዊ መብት ጉዳይና የመንግሥት አቋም

ሰኔ ወር አጋማሽ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት (ተመድ) ከፍተኛ የሰብዓዊ...

ከሰሜኑ ጦርነት አገግሞ በሁለት እግሩ ለመቆምና ወደ ባንክነት ለመሸጋገር የተለመው ደደቢት ማክሮ ፋይናንስ

በኢትዮጵያ የፋይናንስ ኢንዱስትሪ ውስጥ በቀዳሚነት ስማቸው ከሚጠቀሱት ውስጥ ደደቢት...