Wednesday, June 12, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

እኔ የምለዉጉራማይሌው ሕገ መንግሥታችን

ጉራማይሌው ሕገ መንግሥታችን

ቀን:

በመርሐ ፅድቅ መኮንን ዓባይነህ

እኛ ኢትዮጵያውያን ቀደምት አባቶቻችንና እናቶቻችን እንደ የትኛውም ቅይጥ ኅብረተሰብ በብዝኃ ልሳን፣ በባህል፣ በሃይማኖት፣ በጎሳ፣ ወዘተ. ስብጥሮች ቢለያዩ እንኳ ከውጭ ጠላት በኩል በጋራ ህልውናቸው ላይ ይቃጣባቸው የነበረውን ማናቸውንም ዓይነት የቅርብ ወይም የሩቅ ጥቃት ሲመክቱ የኖሩት፣ እርስ በርስ እየተደጋገፉና ጭቃና ጨፈቃ እየሆኑ ነበር፡፡ ትንሽ የኋሊት ብንሳብ እንኳ በወርቅ ቀለም እንደተጻፈ ዘመናትን የተሻገረውና ገና የሚሻገረው አኩሪ የዓድዋ ድል ታሪካቸው፣ ቀረብ ብንል ደግሞ በደም የተከተበው አንፀባራቂ የካራማራ ገድላቸው አጉልቶ የሚያሳየን ይህንኑ የነጠረና የማያወላውል ሀቅ መሆን አለበት፡፡

የዛሬውን አያድርገውና ከ25 ዓመታት በፊት ወራሪው የሻዕቢያ ሠራዊት በባድመና በዛላ አንበሳ ግንባሮች በኩል ወሰን ገስግሶና የድንበር መቆጣጠሪያ ኬላዎችን በዕብሪት ጥሶ ከፍቶብን የነበረውን የግፍ ጦርነትስ ቢሆን በፅናት የመከትነው፣ በአሸናፊነት የተወጣነውና የግዛት ሉዓላዊነታችንን ያስከበርነው ጥቃቅን ልዩነቶቻችንን ለጊዜው ወደጎን በመተው መላ ኢትዮጵያውያን ከዳር እስከ ዳር ተጠራርተንና ለአንድ የተቀደሰ ዓላማ በአንድነት ተሠልፈን አልነበረም እንዴ? ታዲያ የዘመናዊ ዕሳቤ ተቋዳሽ የሆነው ይህ ተተኪ ትውልድ ምን አዲስና የተለየ ሁኔታ ቢያጋጥመው ነው፣ የጋራ ግንባር ፈጥሮ የጠላቶቻችንን ድብቅ ሴራ በአፋጣኝ ለማክሸፍና የአገሩን ሉዓላዊነት በተጠንቀቅ ለመጠበቅ የተሳነው እስኪመስል ድረስ መንታ መንገድ ላይ ቆሞና ፍፁም ግራ ተጋብቶ የምንመለከተው? ኢትዮጵያችን በረዥሙ የመንግሥትነት ታሪኳ የቅርብ ጎረቤቶቿን ይቅርና ሌሎች የሩቅ አገሮችንም ቢሆን የመተናኮል ልማድ የላትም፡፡ በተፃራሪው ይህችኑ ጭምት አገር እስከ ወዲያኛው ለማፍረስ ወይም ራሷን በራሷ እንድታፈርስ ለመጋበዝና ለማደፋፈር የገዛ ጡት ነካሽና የበሉበትን ወጭት ሰባሪ ልጆቿን ሳይቀር በስፋት እየተጠቀሙ፣ በትጋት የሠሩ የውጭ ጠላቶቻችን ቁጥር ግን የሚናቅ አልነበረም፣ አይደለምም፡፡

- Advertisement -

እንዳሰቡት አልሆንላቸው ብሎ እንጂ እንደ ታላቋ ብሪታንያና ፋሽስት ጣሊያን ያሉ አውሮፓውያን ቅኝ ገዥዎች በቀሪው የጥቁር አፍሪካ ክፍለ ዓለም ባደረጉት ልክ ማኅበረሰቦቻችንን በጎሳና በሃይማኖት እየከፋፈሉ አገራዊ አንድነታችንን ሊሸረሽሩ፣ ሉዓላዊነታችንን ሊዳፈሩና አልፎ አልፎ በለስ የቀናቸው እንደሆነም ግዛታችንን በኃይል ሊቆጣጠሩ በተለያዩ ጊዜያት ተነሳስተዋል፣ ተንደርድረዋልም፡፡

በእርግጥ እነዚህ ወራሪ ኃይሎች እንዳመጣጣቸው ነፃነት ወዳድ በነበሩት ጀግኖቻችን የተባበረ ክንድ ክፉኛ እየተደቆሱ አፍረው ቢመለሱም፣ እንደ አገር ዘላቂና ሁለንተናዊ ጉዳት አላደረሱብንም ማለት ከቶ አይቻልም፡፡ ከሁሉም በላይ ዘመን ተሻጋሪ በሆነ ራስን አብዝቶ የመከላከል ጦርነት ተጠምደን ይበልጥ በልማት ሥራው ላይ እንዳናተኩር፣ እስካሁንም ከምንገኝበት የድህነትና የኋላቀርነት አረንቋ ወጥተን የኑሮ ደረጃችን እንዳይሻሻል ዓይነተኛ መሰናክሎችን ጋርጠውብን አልፈዋል፡፡

ከታሪክ እንደምንረዳው ከሆነ መዋዕለ ዘመናችን ዕርባና በሌለው የእርስ በርስ ግጭት የተሞላ ነው፡፡ ይልቁንም በዚህ ያልተቋረጠ ሁከት ውስጥ ባዕዳን ኃይሎች ባሻቸው ጊዜ እንደ ልባቸው ሰርገው እየገቡ በግፈኝነት ሲያጠቁንና እንደ ሕዝብ ሲያደሙን የኖሩት፣ አብዛኛውን ጊዜ ይህንኑ ውስጣዊ አለመረጋጋታችንና በሆነ ባልሆነው እርስ በርሳችን የምንቆራቆስባቸውን ምቹ አጋጣሚዎች በመደላድልነት ተጠቅመው ነው፡፡

እንዲያ በመሆኑ ይመስላል አለመታደል ሆኖ የዕድሜያችንን ያህል አልጎለመስንም፣ በጉልበትም አልደረጀንም፡፡ ዕምቅ የተፈጥሮ ሀብታችንን በሚገባ አልምተን አልበለፀግንበትም፡፡ ከዚያ ይልቅ እንዳይፈርስ አድርጎ ድህነት ቤቱን ሠርቶብናል፡፡ ብሔራዊ ምጣኔ ሀብታችን ፍፁም ደካማ ነው፡፡ በቀን ሦስት ጊዜ የመመገብ አቅም ያላቸው የዜጎቻችን ቁጥር እዚህ ግባ የሚባል አይደለም፡፡ ዓመታዊ የመንግሥት ሥራዎች ማንቀሳቀሻ በጀታችን ሳይቀር፣ በከፊል የሚሸፈነው ከለጋሽ አገሮችና ከዓለም አቀፍ ድርጅቶች በኩል ጥብቅ ቅድመ ሁኔታዎችን ተንተርሶ በሚቸር እርጥባን ወይም ድጎማ መሆኑ ሊያስቆጨን ይገባል፡፡

‹‹በደንባራ በቅሎ ቃጭል ተጨምሮ›› ሆነና ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ደግሞ ጭራሹን ሰላምና ፍቅር ከእኛ ርቋል፡፡ እርስ በርስ ተነጋግሮ መግባባት እንኳን አቅቶናል፡፡ የውጭ ጠላቶቻችን በየመድረኩ መሳቂያና መሳለቂያ አድርገው እስኪያቀርቡን ድረስ የፖለቲካ ተግባቦታችን በእጅጉ ተወሳስቧል፡፡ በመካከላችን የሚፈጠር አንዳች ዓይነት የሐሳብ ልዩነት ብቻውን የተሳለ ሰይፍ ያማዝዘንና በጭካኔ ያስተራርደን ጀምሯል፡፡

ከትናንቶቹ ጋር ስንነፃፀር የዛሬዎቹ ኢትዮጵያውያን በእውነቱ ምን እንደነካን አይታወቅም፡፡ ሌላው ቀርቶ የሕይወታችንን ሦስት ጉልቻ ስንመሠርትና የዘላቂ ትዳር ጓደኞቻችንን ስናጭ እንኳ በታሪክ አንተ ማነህ አንቺ ማነሽ ተባብለን የማናውቀው ሁሉን አቃፊ ወገኖች፣ ከደደቢት በረሃ እስከ ደምቢዶሎ ጫካዎች ተጠራርተው በመሀላችን የተበተኑ ርኩሳን መናፍስት ባሠራጩልንና ዘግይቶ በተጣባን ኋላቀር የብሔርተኝነት ደዌ ከመለከፋችን የተነሳ፣ በመረረ የዚህ ወይም የእዚያ ዘውግ ጥላቻ ተመርዞ በጭካኔ በትር እስከ መመታታትና እስከ መገዳደል ደርሰናል፡፡

በትር የሚለው የወል ቃል እንደ ቀስትና ገጀራ ያሉትን ባህላዊ መሣሪያዎች እያካተተ የሰውን ልጅ በአደባባይ ለማረድ በጥቅም ላይ መዋሉን ስንመለከት ደግሞ አብዝቶ ያመናል፣ ይዘገንነናልም፡፡ ስለሆነም በቶሎ ካልነቃን ከየራሳችን ጉያ በበቀሉ አደገኛ አራሙቻዎች አቀነባባሪነት የተዘረጋልንን የጥፋት ወጥመድ ያለ ጊዜው ተስፈንጥሮ ጉዳት ከማድረሱ በፊት በብልኃት ካላከሸፍነው በስተቀር፣ እንዳንቀላፋን መቅረታችን ነው፡፡ ይህንን በቅጡ ልብ ልንል ይገባል፡፡

እውነት እውነት እላችኋለሁ፣ በስማችን ሲምሉና ሲገዘቱ ውለው የሚያነጉት ዘር አምላኪ ፖለቲከኞች፣ የየወጡባቸውን ብሔሮች አባላት ቀርቶ ራሳቸውን እንኳ በሦስተኛ ወገኖች ፊት የመወከል ብቃት እንደ ሌላቸው ከወዲሁ መታወቅ ይኖርበታል፡፡ እንዲያ ቢሆን ኖሮ የአንድን ብሔር አባላት መብቶችና ጥቅሞች በፖለቲካ ረገድ ለማስተጋባት፣ ከአንድ በላይ የፖለቲካ ድርጅቶች በዓይን አውጣነት እየተሠለፉ ብዙኃኑን ማደናገራቸው አስፈላጊ ባልሆነ ነበር፡፡

አሁንም ድረስ እንደ ሕወሓት የፖለቲካ ፕሮግራም የሚቆጠረውና በሥራ ላይ ያለው የኢፌዴሪ ሕገ መንግሥት ከዜጎች አላቆ ሰማይ የሚሰቅለውና የሚያነግሠው በራሱ መንገድብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦችእያለ በቁልምጫ የሚጠራቸውን ስብስቦች ነው፡፡ ለዜጎች ዕውቅና የሚሰጠው በስማ በለው ሲሆን ወልድ ለሥጋው አደላእንደሚባለው፣ መጀመርያውኑ የብሔር ብሔረሰቦች ማሽበልበያ ሰነድ ነውና ከግለሰብ መብቶች ይልቅ ለቡድን መብቶች ጥበቃ አብዝቶ ቢያደላና ስስታምነት ቢያድርበት ላይገርመን ይችል ይሆናል፡፡

ከዚህ የተነሳም የአገሪቱን መሬትና የተፈጥሮ ሀብት ለየመንደሩ ጠባብና ጽንፈኛ ብሔርተኞች እየሸነሸኑ በብቸኝነት ለማደላደልና ለማከፋፈል የሚያስችለውን ሥርዓት ይዘረጋል፡፡ የዚህ ወይም የዚያ ወገን አይደሉም የተባሉ ዜጎችን ደግሞ መጤዎች ናቸው እያሰኘ ከየመኖሪያ ቀዬአቸው በባይተዋርነት እንዲፈናቀሉ ያደርጋል፡፡

ይሁን እንጂ ይኸው መናጢ ሕገ መንግሥት ወረድ ብሎ በሦስተኛው ምዕራፍ ሥር ሁልቆ መሳፍርት የሌላቸውንና በግለሰብ ደረጃ ሊከበሩም ሆነ የተሟላ ጥበቃ ሊደረግላቸው የሚገቡትን ዝርዝር ሰብዓዊ መብቶችና ዴሞክራሲያዊ ነፃነቶች ጭምር በተቃራኒው አሥፍሮ እንመለከተዋለን፡፡ እንዲያውም ይህ አልበቃው ብሎ አገሪቱ ከተቀበለቻቸው ዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብት ስምምነቶች ጋር ራሱን ለማወዳጀት ጭምር በይፋ ቃል ገብቶ እናገኘዋለን፡፡ እንግዲህ በአንድ ራስ ሁለት ምላስይሏችኋል ይህ ነው፡፡

ለመሆኑ የየአካባቢውን ሀብትና ሥልጣን አስቀድሞ ለብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ያለ ይሉኝታ ሸንሽኖ ለማከፋፈል የወሰነ ልዕለ ሕግ ዜግነታቸውን ብቻ መነሻ በማድረግ፣ አንደኛው ከሌላው ጋር በከፍተኛ ደረጃ ተሰበጣጥረውና ተዋህደው የሚኖሩትን መላ ኢትዮጵያውያን መሠረታዊ መብቶችና ነፃነቶች እኩልና ያለ አድልኦ አከብራለሁ ሲል፣ በአስመሳይነት ቢመፃደቅ ማን አምኖ ሊቀበለው ይችላል? በመሠረቱ ጉራማይሌው ሕገ መንግሥታችን የጽንፈኛ ብሔርተኞችን ጠባብና ዕኩይ ፍላጎት ከማስተናገድ የዘለለ ፋይዳ የለውም፡፡ ይኸው የበላይ ሕግ በአንቀጽ 32 ሥር ያጎናፀፋቸውን ከለላ እየተማመኑ በዜግነታቸው ኮርተውና በመላ አገሪቱ ተሠራጭተው የሚኖሩት ወገኖቻችን እኮ፣ በተለየ ማንነታቸው ምክንያት ብቻ እየተከበቡ ውጡልን ተብለዋል፡፡ ፈቃደኞች ሆነው ያልተገኙት ከየመኖሪያ ቀዬአቸው በኃይል ሲፈናቀሉና በላባቸው ጥረውና ግረው ያፈሩት ሀብትና ንብረት ሳይቀር በወሮበሎች ሲዘረፍ ወይም በእሳት ተያይዞ እንዲጋይ ሲደረግ፣ ፈጥኖ የደረሰላቸውና ከጥፋት ተከላክሎ የታደጋቸው ክልላዊም ሆነ ፌዴራላዊ መድኅን አላገኙም፡፡

ከመካከላቸውም ለሕዝባዊ ምክክር እንድትሰበሰቡ ተብለው በአካባቢ አስተዳደር አካላት ጥሪ አደባባይ ከወጡና ሸንጎ ከተቀመጡ በኋላ እንደ ፍሪዳ በጭካኔ የታረዱ፣ ቦምብ የተወረወረባቸው፣ የጥይት ዕሩምታ እንደ በረዶ የወረደባቸውና አልፎ አልፎም በተገኙበት እሳት የተለቀቀባቸው ሰለባዎች ይገኙባቸዋል፡፡

እነሆ ከኦሮሚያና ከቤኒሻንጉል ጉምዝ ክልሎች ብቻ ከመታረድ ተርፈው በአፈሙዝ አስገዳጅነት ከቀዬአቸው እየተፈናቀሉ በተለያዩ ጊዜያት ወደ አማራ ክልል የገቡት አያሌ ዜጎቻችን፣ የዚህ ዘውግ ተኮር ጫና ዓይነተኛ ማሳያዎች ናቸው፡፡ መጭው ክረምት ሊገባ በተቃረበበት በአሁኑ ወቅት እንኳ የተጠቀሰው ክልል ከመተከልና ከወለጋ ዞኖች ተቀብሎ እንደ ቻግኒ (አዊ) እና ጃሬ (ደቡብ ወሎ) ባሉ አካባቢዎች በጊዜያዊነት ያስጠለላቸው ተፈናቃዮች አኃዝ ግማሽ ሚሊዮንን ተሻግሯል፡፡:

ይህ ቁጥር በራሱ በአማራ ክልል ውስጥ በቅርቡ ተከስቶ ከነበረው የታጠቁ ቡድኖች ወረራ ጋር በተገናኘ ከሰሜን ሸዋና ከኦሮሞ ብሔረሰብ አስተዳደሮች ሳይታሰብ ተፈናቅለው፣ በደብረ ብርሃንና በመሀል ሜዳ ከተሞች የተጠለሉትንና ከሦስት መቶ ሺሕ በላይ የሚሆኑትን ሌሎች ሰለባዎች አይጨምርም፡፡

እንግዲህ ይህ ሁሉ መከራ በንፁኃን ወገኖቻችን ላይ እየደረሰ ያለው ከግለሰብ መብቶች ይልቅ፣ ለቡድን መብቶች ጥብቅና ቆሜያለሁ በሚለው ፌዴራላዊ ሕገ መንግሥት አነሳሽነትና የእርሱ ጨፍጫፊ ልጆች ሆነው እየተቀረፁ ሥራ ላይ እንዲውሉ በተደረጉት የየክልሉ ቁንፅል ሕግጋተ መንግሥታት አስተግባሪነት መሆኑ ሊሰመርበት ይገባል፡፡

ለዚህ ወይም ለዚያኛው ብሔር የበለጠ እንቆረቆራለን የሚሉ የክልል መንግሥታትና የተዋረድ አስተዳደራዊ እርከኖቻቸው ታዲያ፣ ሰውነትን ይቅርና ዜግነትን በውል ተገንዝቦ ከጎሰኝነት የፀዳ ፍትሐዊ አገልግሎት የመስጠት አቅማቸው እስከ ወዲያኛው የተሰለበ ሆኖ ቢታይ እምብዛም ሊደንቀን አይገባም፡፡

በሌላ አነጋገር ለምሳሌ በኦሮሚያም ሆነ በቤኒሻንጉል ጉምዝ ክልሎች ውስጥ ሠርቶ ለመኖርም ሆነ መንግሥታችን አጥብቆ እንደሚመኘው ሀብት አፍርቶ ወደ ብልፅግናው ማማ ለመረማመድ፣ በዜግነት ኢትዮጵያዊ ሆኖ መገኘት ብቻ አይበቃም፡፡ ከዚያ ይልቅ ጉራማይሌው ሕገ መንግሥታችን እንደሚያበረታታው የኦሮሞ፣ የበርታ፣ የጉምዝ፣ ወዘተ. ብሔር ወይም ብሔረሰብ አባል ሆኖ መገኘት ያስፈልጋል፡፡ በአገልግሎቶች አቅርቦት ረገድም ቢሆን የቀደምትነት መብት ያሰጣል፡፡

ይህ መቼም ለመላው የሰው ዘር የማይበላለጥ ልዕልና ካለንና ምንጊዜም ቢሆን ሊኖረን ከሚገባው ትክክለኛ እሳቤ ጋር በእጅጉ ይፃረራል፡፡ ቀድሞውኑ የሰው ልጅ ከበሬታና ባለዋጋነት፣ ፈረንጆቹ (The Dignity and Worth of the Human Person) ይሉታል፡፡ የሚመነጨው ከሰብዕናው እንጂ ከመጣበት የትውልድ ሐረግ፣ ከሚታቀፍበት የጎሳ መስመር፣ ከሚከተለው ሃይማኖት፣ ከሚናገረው ልሳን እንዳልሆነ ይታወቃል፡፡ ከዜግነቱም እንኳ ሊሆን አይችልም፡፡

ሰውነት ከዜግነት ጋር ሲነፃፀር በብዙ እጥፍ የሚልቅ ዕሳቤን ያመሳጥራል፡፡ ዜግነት በአገሮች የሉዓላዊነትና የግዛት ወሰን ተገድቦ መንግሥታዊ ጥበቃ የሚደረግለት አቋም ነው፡፡ ሰውነት ግን በፀባዩ ኩሉ ዓለማዊ (Universal) ይዘት ያለውና መላውን የሰው ዘር የሚያቅፍ ሰፊ ጽንሰ ሐሳብ መሆኑን እዚህ ላይ በጥሞና ያስተውሏል፡፡

ከአዘጋጁጸሐፊው በሕግ ሙያ የመጀመርያ ዲግሪያቸውን 1981 .. ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የቀድሞው የሕግ ፋኩልቲ ያገኙ ሲሆን፣  በሐምሌ ወር 2001 .. ደግሞ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲና በተመድ የሰላም ዩኒቨርሲቲ ጣምራ ትብብር ይካሄድ ከነበረው የአፍሪካ ፕሮግራም በሰላምና በደኅንነት ጥናት የማስተርስ ዲግሪያቸውን ሠርተዋል፡፡ በአሁኑ ወቅት በአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት በቢሮ ኃላፊ ማዕረግ የርዕሰ መስተዳድሩ ዋና የሕግ አማካሪ ሆነው በማገልገል ላይ ናቸው፡፡ ጽሑፉ የእሳቸውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እየገለጽን፣ በኢሜይል አድራሻቸው [email protected] ማግኘት ይቻላል፡፡  

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

[ክቡር ሚኒስትሩ በመንግሥት የሚታወጁ ንቅናቄዎችን በተመለከተ ባለቤታቸው ለሚያነሱት ጥያቄ ምላሽ ለመስጠት እየሞከሩ ነው]

እኔ ምልህ? እ... ዛሬ ደግሞ ምን ልትይ ነው? ንቅናቄዎችን አላበዙባችሁም? የምን ንቅናቄ? በመንግሥት...

የመንግሥት የ2017 ዓ.ም በጀትና የሚነሱ ጥያቄዎች

የ2017 ዓመት የመንግሥት ረቂቅ በጀት ባለፈው ሳምንት መገባደጃ ለሚኒስትሮች...

ከፖለቲካ አባልነትና ከባንክ ድርሻ ነፃ የሆኑ ቦርድ ዳይሬክተሮችን ያካተተው ብሔራዊ ባንክ ያዘጋጃቸው ረቂቅ አዋጅና መመርያዎች

የኢትዮጵያ የብሔራዊ ባንክ የፋይናንስ ተቋማትን የተመለከቱት ድንጋጌዎችንና የባንክ ማቋቋሚያ...

የልምድ ልውውጥ!

እነሆ መንገድ ከቦሌ ሜክሲኮ። አንዱ እኮ ነው፣ ‹‹እንደ ሰሞኑ...