Friday, December 1, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ተሟገትእናት አገር ለህልውናና ለዴሞክራሲ ትጣራለች!

እናት አገር ለህልውናና ለዴሞክራሲ ትጣራለች!

ቀን:

በገነት ዓለሙ

ከሦስት ዓመት ወዲህ ጀምሮ ደስ እያለን፣ በኩራትና በተስፋ ጭምር ለውጥና ሽግግር ውስጥ መሆናችንን፣ ይህ ለውጥና ሽግግር ደግሞ የአገራችንን ዋናና መሠረታዊ፣ ለብዙ ዘመናትም መፍትሔ፣ መላና ዕይታ አጥቶ የኖረውን ችግራችን (ከ1960ዎቹ ጀምሮ ተገትሮ የቀረውን ዴሞክራሲን የማደላደል አደራችንን) የሚፈታ፣ ዴሞክራሲን የሚያደላድል፣ ዴሞክራሲ የሚፈልጋቸውን ከቡድን ገለልተኛ የሆኑ የመንግሥት አውታራትን የምንገነባበት ምዕራፍ መሆኑን ስንናገር፣ ስንነጋገር ቆይተናል፡፡ ለውጥና ሽግግር ላይ ነን ስንል፣ በዚህ አዲስ በተከፈተው የዴሞክራሲን የማደላደል ግዳጅ ውስጥ አገርንና የአገር ልጆችን በርቱ፣ ግፉ ገና ነው እያልን ስናበረታታ፣ ይህ ውሸት ነው፣ ለውጥ የለም፣ እንዲያውም ሕገ መንግሥቱ እየተጣሰ ነው የሚሉን የለውጥ ተጠናዋቾች እንደነበሩ አልረሳንም፡፡ ከእነዚህ እኩልና ከእነዚህ ጋር ለውጡ ተጠልፏል፣ ሽግግሩ ተቀብልሷል ብለው በለውጡና በሽግግሩ መንገድ ላይ የቆሙና የወደቁ እንደነበሩም አንዘነጋም፡፡

ለውጡና ሽግግሩ ‹‹ድንገት›› ከተፍ ያለው ሕዝብ ፍላጎቱንና ብሶቱን በይፋ በሚናገርበት፣ በደሉን ለመናገርና መብቱን ለማስከበር በማይፈራበት፣ የእኔና የአገሬ የሚለው የነፃነት አየር ተፈጥሮ ያንን አገርና ሕዝብ ኑሮውና ድባቡ ባደረገበት ሰማይ ሥር ይመስል፣ ፓርቲዎች በልክ በዝተው፣ ተባዝተው የድምፅ ብልጫ አግኝቶ ፍላጎትን ውሳኔ ማድረግ የሚያስችል የጨዋታ ሜዳ፣ ሕግና የጨዋታ ባህል ባለበት አገር እንኖር የነበር ይመስል፣ በ2012 ዓ.ም. ስድስተኛው ምርጫ መጣ፣ ‹‹መጣብን››/‹‹መጣልን›› ብለን ተደናበርን፡፡ በዚህ ድንባሬም ውስጥ ተጣላን፣ ተበጣበጥን፡፡ ዓለምን የፈተነውና የበጠበጠው የኮቪድ-19 ወረርሽኝ ምክንያት ሆኖ ምርጫው ቢራዘምም፣ ይህም ከመከፋፈልና ከክፍልፋይነት አላዳነንም፡፡

ምርጫ ውስጥ የምንገባው እስከ ዛሬ ድረስ ባለፉት 27 ዓመታት የውሸት ምርጫ ስናደርግ የነበረበትን ሥርዓታዊ ሕመማችንን ድነን፣ ለነፃና ለዴሞክራሲያዊ ሚና የሚፈልጉ ዝግጅቶችን አድርገን ነው ወይ ብለን በደንብ ሳንስማማ፣ በዚህም የመሰናዶ የጨዋታ ሕግ ላይ የጋራ ግቢ ውስጥ መኖርን ሳንለምድ ይህንኑ የለውጥና የሽግግሩ አካል የሆነውን ምርጫ ራሱን የሚያምስ፣ ለውጡንና ሽግግሩን ራሱን ዓላማ ያደረገ በመከላከያ የአገር አቅም ላይ ያነጣጠረና ከፍተኛ ጉዳት ያደረሰ ወረራና ጥቃት አጋጠመን፡፡ እውነትን ቀና ብሎ ማየት ያቃተው ዓለም አቀፋዊው ኅብረተሰብም ከዳን፣ ተረባረበብን፡፡

እዚህ ጥቃት፣ ክህደትና ከበባ የበረታበት የችግርና የጭንቅ ጊዜ ውስጥ እናት አገር፣ ከ80 ዓመት (በፋሺስት ወረራ) ወይም ከ44 ዓመት (የ1969 ዓ.ም. የዚያድ ባሬ ወረራ) ወዲህ ለመጀመርያ ጊዜ ‹‹ኑ ሙቱልን›› እያለች እንደገና እየተጣራች ነው፡፡ ለዚህ የእናት አገር ጥሪ፣ አገርን የማዳን የጣር ጩኸት የሚሰጠውን ምላሽ ግን ዥንጉርጉርነታችን፣ ልዩ ልዩነታችን፣ በሐሳብ መለያየታችን በጭራሽ ሊያሰናክለውና ሊያውከው አይገባም፡፡ የትም ቦታ በምንም ምክንያት ለውጡና ሽግግሩ ውስጥ ሆነን፣ ዴሞክራሲያችንን የማደላደል ዓብይ ተግባራችን ላይ አተኩረን ሽርደዳም፣ ማብጠልጠልም፣ ጥቃትም፣ ክዳትም የተቃጣበት ይህንን ምርጫም የለውጡና የሽግግሩ አካል አድርገን፣ አገር ያቀረበችልንን ‹‹የእናት አገር ጥሪ›› በጋራ መመለስ እንችላለን፡፡

አሁን ምርጫ ክርክርና ቅስቀሳ ውስጥ የምናየውና የምንሰማው፣ በዚህ እየከፋ በመጣው የአገር የህልውና አደጋ ውስጥ የምንታዘበው ልዩ ልዩነት ግን ዴሞክራሲያዊ ትግላችንን ብቻ ሳይሆን፣ አገራዊ ህልውናችንን ጭምር የሚፈታተን እንጂ የሚያግዝ አይደለም፡፡

ዛሬም እንደ ትናንትናው ሥልጣን ቢይዙ ሕገ መንግሥቱን ስለሚለውጡ፣ ፌዴራላዊነቱን ስለሚያሻሽሉ፣ አከላለልን ስለሚቀይሩ ፓርቲዎች እንሰማለን፡፡ ብልፅግና ማለት ኢሕአዴግ ነው የሚሉ ‹‹ፀብ ያለሽ በዳቦ!››ዎችን እናያለን፡፡ ከለውጡ ወዲህ የደረሰውን የሞት፣ የመፈናቀልና የጥቃት አደጋ ከዚያ በፊት በ27 ዓመታት ውስጥ ከደረሰው ፍጅት፣ መፈናቀል፣ ወዘተ ጋር ‹‹እያወዳደሩ›› የለውጡን መንግሥት የሚከሱ ማየት የሚያሳፍር አልሆነም፡፡

አገራችን ብዙ ችግሮች አሉባት፡፡ ከእነዚህም መካከል ክፍልፋይ ወገንተኛነትና አፈናቃይነት አንዱና ዋነኛው ነው፡፡ ይህንንም የአገር ችግር ሆነ ሌሎችን ሕመሞቻችንን ለማዳን ሕገ መንግሥት ማረም፣ መለወጥ አስፈላጊ ነው ከተባለ፣ ይህ መደረግ ያለበት በብዙ ወሳኝ ምክንያቶች በሕገ መንግሥቱ ውስጥ ሆኖ ነው፡፡ ለምን? ሰላማዊና ሕጋዊ (ዴሞክራሲያዊ) መሆን ያለበት ትግላችን ከመሬት መነሳት፣ ካለበት ማኮብኮብ፣ ከሚኖርበት ሁኔታ ውስጥ በሕግ መረማመድን መኗኗሪያው አድርጎ መረማመድ አለበት፡፡

ኢሕአዴግና ሕገ መንግሥቱ ባለፉት 27 ዓመታት በዚህች አገር ብዙ ነገሮች ለዋውጠዋል፡፡ እነዚህ ለውጦች ዝም ብለው የሚሰረዙና የሚለወጡ አይደሉም፡፡ ሕግና የሕዝብ ፈቃድ መሠረት አድርገው የሚለውጡት መለወጥ አለባቸው፡፡ አለበለዚያ ከ1983 ዓ.ም. ኢሕአዴግ፣ ከ1967 ዓ.ም. ደርግ በምን እንለያለን? ከለውጡ በፊት ባለው ሁኔታ ውስጥ ሆነን ጥቂት እናብራራው፡፡

ኢሕአዴግ በድኅረ ደርግ ኢትዮጵያ የማኅበራዊ አዕምሮ ሙሽት ላይ ርዕዮተ ዓለማዊ አሻራውን አሳርፏል፡፡ የአገሪቱን ፖለቲካዊና አስተዳደራዊ መልክዓ ምድር ቀይሯል፡፡ የብሔረሰብ መብትን አነሰም በዚያ የተመረኮዘ ነው፡፡

የአስተዳደር ይዞታ አሸናሽንን፣ የፓርቲ አደረጃጀትንና የሥልጣን አያያዝን ያመጣ ሕገ መንግሥት ተክሏል፡፡ ኢሕአዴግ በሥልጣን ዘመኑ ውስጥ ተቃውሞና ድጋፍ እንዳፈራ ሁሉ፣ ሕገ መግሥቱም ደጋፊና ተቃዋሚ አፍርቷል፡፡ እንዲያውም የሕገ መንግሥቱን መዝለቅ የህልውናቸው ዋስትና አድርገው የሚያዩትንና ‹‹ሕገ መንግሥቱ ሊያሠራ ይችላል፣ ተግባራዊ የሚያደርገው ታጣ እንጂ›› የሚሉትን የኢሕአዴግ ደጋፊዎችና ተቃዋሚዎች አንድ ላይ ወስደን፣ ‹‹ለሰላማችን ጠንቅ የሆነው ሕገ መንግሥቱ ነው›› ከሚሉት የተቃዋሚ ክንፎች ጋር ስናነፃፅር እነዚህኞቹ በቁጥር የሚያንሱ ናቸው፣ ወይም የሚያንሱ ይመስላሉ፡፡ ይህ ሁኔታ በራሱ ኢሕአዴግን (ሕወሓት አሻፈረኝ አለ እንጂ)፣ ሕገ መንግሥቱን በኢትዮጵያ ዴሞክራሲ ግንባታ ውስጥ ወደ ጎን የማይባሉ አስፈላጊ ሰበዞች ያደርጋቸዋል፡፡ በተጨማሪም የኢሕአዴግና የተቃዋሚዎቹ ዴሞክራሲን ተጋግዞ የመገንባት ዕድል ዕውን የመሆን ተስፋ የሚኖረው ‹‹የሽግግር መንግሥት ይቋቋም›› በሚል ጥያቄ በኩል ሳይሆን፣ ያለውን ሕገ መንግሥት የጋራ መገናኛ በማድረግ በኩል እንደሆነም የሚያሳይ ነው፡፡ እናም በሽግግር መንግሥት ጥያቄ አማካይነት ካለው ሕገ መንግሥት ለማምለጥ መሞከር ለተከፋፈለ የፖለቲካ ንጠት በር መክፈት ነው፡፡

 ኢሕዴግንና ሕገ መንግሥቱን አስፈላጊ የሚያደርጋቸው ሌላም ሰበዝ አለ፡፡  ኢሕአዴግ በሥልጣን አወጣጡና ‹‹በአዲስ›› አገዛዝ ግንባታው የራሱን ሠራዊትና የፀጥታ ኃይል ከእነ ርዕዮተ ዓለሙ በዋናነት የተጠቀመ መሆኑ አውታረ አገዛዙን ገለልተኛ እነፃ ገና የጎደለው መንታ ተፈጥሮ (ከውስጥ ባሻ/በጨነቀ  ጊዜ አድራጊ ፈጣሪ ለመሆን የሚያስችል ኢሕአዴጋዊ ቡጥ፣ ከውጭ ደግሞ ‹‹የዴሞክራሲ›› ቅርፊት) እንዲኖረው አድርጓል፡፡ የዴሞክራሲ መብቶችን ተግባራዊ ሕይወት ከሲታ እንዲሆን ያደረገው፣ የኢሕአዴግንም በሥልጣን ላይ መቆየት በሕዝብ ድምፅ ብቻ የማይወሰን እንዲሆን ያደረገው ይኼው የቡጥና የቅርፊት አለመጣጣም (የቡጡ ቅርፊቱን ለመጫን መቻሉ) ነው፡፡ የኢሕአዴግ ፓርቲ በምርጫ ድምፅ ቢሸነፍና ሽንፈቱን ተቀብሎ ከሥልጣን ለመውረድ የተስማማበት ሁኔታ ቢከሰት እንኳ፣ ከአገዛዙ የሥልጣን ኃይል ውስጥ ዘራፍ ብሎ ወታደራዊ ግልበጣ የማድረግ ምናልባት ሁሉ ሊያጋጥም ይችላል፡፡  በአገሪቱ የፖለቲካ ጉዞ ውስጥ የኢሕአዴግ ሰበዝ (ፋክተር) ለበጎም ለክፉም ውጤት መዋል ይችላል፣ እንዳያያዛችን፡፡

እንጂማ ለመከራችን፣ አሁን የምንገኝበት ችግር ውስጥ የዘፈቀን፣ እንክትካች ወገንተኛነት ውስጥ የቀረቀረን፣ ኢሕአዴግ ሲል እንደኖረው የአፈጻጸም ችግር እንዳልሆነ እናውቃለን፡፡ ኢትዮጵያን ብሔረሰብ ነክ መጋደሎች፣ መጤ እያሉ መደበልና መግፋት ሲያንቀረቅቧት ቆይተዋል፡፡ ዘግናኝ ግድያዎችም ታይተዋል፡፡ በሚሊዮን የሚደርስ ሕዝብን ያፈናቀለ ቀውስም ተዘርግፎባታል፡፡ እስካሁንም ይህ ቀውስ የሚያዛልቅ መፍትሔ ገና አላገኘም፡፡

በቤተኛነትና በመጤነት መጥመድና ማፈናቀል በተግባር የተጀመረው ግን ገና በጠዋቱ ከ1983 ዓ.ም. ማብቂያ ጀምሮ አንድን ብሔረሰብ በነፍጠኛነት ከማዋከብ ጋር ነው፡፡ በ1983 ዓ.ም. የነሐሴው ቻርተር መሠረት በተካሄደው ሽንሸናም ሆነ፣ በ1987 ዓ.ም. ሕገ መንግሥት በፀደቀው አከላለል ውስጥ ሚዛን ያጡ እንደ ሐረርና ጋምቤላ ያሉ ሚጢጢዎችንና ኦሮሚያና አማራ የሚባሉ ግዙፎችን የፈጠረው፣ ከአጠራር አንስቶ ድርሻህ፣ ቤትህ፣ የባለቤትነትህ ‹‹መሬት›› ይህ ነው የሚል መልዕክት የረጨውና የክልል ስያሜን ያመጣውም ይኼው ጎጆና ብሔርተኝነት ነው፡፡

ለብሔረሰብ ጥያቄ መልስ መስጠት የኢትዮጵያ፣ የኢትዮጵያውያን፣ የኢትዮጵያ ብሔር/ብሔረሰቦችና የፖለቲካቸው ግዴታ ነው፡፡ ይህ በጭራሽ በቀጠሮ የማያድር የኢትዮጵያ ዴሞክራሲ ጥያቄ ነው፡፡ የሕወሓት/ኢሕአዴግ ፖለቲካ ግን ለብሔር ጥያቄ መልስ እሰጣለሁ ብሎ እስከ ዛሬ የኖሩትን፣ አሁንም እንደ አዲስ የተዘረገፉትን ግትልትል ችግሮች አምጥቶብናል፡፡

ለብሔር ጥያቄ መልስ እሰጣለሁ ካለ የኢሕአዴግ የፖለቲካ ተግባር የተወለዱትን ችግሮች በአጭሩ ብናስቀምጣቸው በጎጆኛነት የእኔ የሆነና ያልሆነ ሕዝብ ብሎ መለየት፣ ከዚሁ ጋር የእኔ ብሔረሰብ የሚሉትን መሬት በመተሳሰብ ውስጥ መጠመድ፣ የእኔ የተባለ ሕዝብና መሬት ለይቶ ገዥነትንና በሊታነትን መቆጣጠር፣ በዚህም አማካይነት ጎጆኛ አዕምሮን ማስፋፋት (ከወጥንቅጥ ከተሜ አደግነትና ከአማራነት ጋር የተዛመደ ኢትዮጵያዊነት ላይ ያተኮረን ዕይታ በብሔር ማንነት በማፈርና ሌላውን በመዋጥ ትምህክታዊነት እየቀጠቀጡ ወደ ጎጆኛነት መበጣጠስ)፣ የአካባቢን ኅብረተሰብ በቤተኛነትና በባይተዋርነት ማንጓለል፣ ከዚህም ባስ ሲል ማፈናቀል፣ ብሔረሰብ/አካባቢ የለዩ የንግድ ተቋማትን ፈጥሮ አካባቢ አለፍ የሀብት ሽሚያ ውስጥ መግባት፣ ምድሬ በሚሉት ሥፍራ ውስጥ ግን በባይተዋርነት በዝባዥነት በፈረጁት ላይ አትነግድብን የሚል ቅዋሜና ውድመት ማድረስ ተብለው መጠቃለል ይችላሉ፡፡

እነዚህ ጣጣዎች ሥርዓቱ ያመጣቸው ሳይሆኑ ከአፈጻጸም/ከአያያዝ የፈለቁ ናቸው ባይነት እውነት መናገር? ወይስ በእውነታ ላይ ዓይን ጨፍኖ ምኞታዊነትን ሙጥኝ ማለትና ሕመምን መደበቅ? አዕምሯቸውን ያልዘጉት የራሳቸውን መደምደሚያ መቅረፅ እንዲችሉ ጥቂት ነገሮችን እናክል፡፡ የኢፌዴሪ ሕገ መንግሥትና ፌዴራላዊ አወቃቀሩ ጎጇዊ ብሔርተኛነትንና የኢትዮጵያን እውነታ የማስተናገድ ዲቃላ ውጤቶች እንደ መሆናቸው የችግር ምንጭነታቸው ድርሻ ከፊል ነው፡፡ እነሱ ራሳቸው የብሔርተኝነት ከፊል ውጤት እንደ መሆናቸው የችግር እናትነቱን ሥፍራ የሚወስደው ጎጇዊ ብሔርተኝነት ነው፡፡

ብሔርተኝነት ‹‹ሀ›› ብሎ የሚጀምረው ሕዝቤ፣ ብሔሬ ወይም ብሔረሰቤ ብሎ ነው፡፡ ይህንን ብሎ ሲነሳ ሌላውን የእኔ ያልሆነ፣ ሌላ ሕዝብ፣ የእነሱ ሕዝብ ብሎ መለየቱ ነው፣ ይለያልም፡፡ በብሔረሰብ ማንነት አለማፈርና መብትን አስከብሮ ከሌላው ጋር መኖር ከብሔርተኝነት ጋር በጣም የተለያየ ነገር ነው፡፡ ብሔርተኝት ብሔረሰባዊ መብትን አስከብሮ ከመኗኗር ያለፈ፣ ፕሮግራምን ነድፎ የያዘ ፖለቲካ ነው፡፡ በንቅናቄ መልክም ሆነ በፓርቲ መልክ ተደራጅቶ ወደ ሥልጣን ሲሄድም ሆነ በሥልጣን ላይ ሆኖ ፕሮግራሙን እያናፈሰ ይቀሰቅሳል፣ ይመለምላል፡፡ ሻዕቢያ፣ ኦነግም ሆነ ሕወሓት ሕዝቤ/መሬቴ ማለት የጀመሩት ገና በጎረቤት አገር ውስጥም ሆነ በበረሃ ውስጥ ሲላወሱ ነው፡፡ የይዞታ ካርታ የሠሩት ሁሉ ለሥልጣን ከመብቃታቸው በፊት ነበር፡፡ 1983 ዓ.ም. ሻዕቢያ ድል መታሁ ሲል ከያዘው ውጪ ቀረኝ የሚለውን መሬት በመቆጣጠር እንቅስቃሴ ውስጥ ነበር የተጠመደው፡፡ የኦነግ ዋና ሩጫም በአካልም በርዕዮተ ዓለምም የኦሮሞ ያለውን መሬት መቆጣጠር ነበር፡፡ ትግራይን ከመቆጣጠር አልፎ አዲስ አበባ የገባውና ኢሕአዴጋዊ የኢትዮጵያ ገዥነትን ያቀደው ሕወሓት ግን በየብሔረሰቡ ብሔርተኞች በመብራት እየፈለጉ የመሻረክ፣ የማደራጀትና የማራባት፣ አብሮም እነ ኦነግን ከመሳሰሉ ተቀናቃኞች ጋር የመሽቀዳዳም ሥራ ነበረበት፡፡ 

የሐምሌ 15 ቀን 1983 ዓ.ም. ቻርተር በአንቀጽ 2 (ለ) ላይ ‹‹እያንዳንዱ ብሔር፣ ብሔረሰብና ሕዝብ በራሱ የተወሰነ መልክዓ ምድራዊ ክልል ውስጥ›› (ሰረዝ የተጨመረ) ቁልጭ አድርጎ ድርሻን ይናገራል፡፡ የ1987 ዓ.ም. የኢፌዴሪ ሕገ መንግሥት በአንቀጽ 39 (1-3) ‹‹የብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች››ን መብት ሲያስቀምጥ የቀነሰው ነገር ቢኖር፣ ‹‹በራሱ›› የምትለዋን የባለቤትነት ገላጭ ነው፡፡ አንቀጽ (1) ላይ ባለው የክልሎች ዝርዝር በመጀመርያዎቹ አምስት ተራዎች ውስጥ ‹‹የትግራይ ክልል›› በማለት ዓይነት የአካባቢውን ስም ተከትሎ ‹‹ክልል›› የሚለው ቃል ይመጣል፡፡ ከስድስተኛው እስከ ስምንተኛው ተራ ውስጥ ላይ ዓይነተ ብዙነት ይጠቆማል፡፡ በተለይም  ስምንተኛው ተራ ላይ ‹‹የጋምቤላ ሕዝቦች›› ሲባል እስከ አምስተኛ ተራ ቁጥር ‹‹ሕዝቦች›› አለመታከሉ፣ ሌሎቹ ከግዙፉ ብሔረሰብ እኩል ባለ መብት እንዳልሆኑ ታስቦ ይሆን? የሚል ጥያቄ የሚጭር ነው፡፡ ዘጠነኛው ላይ ደግሞ በነጠላ ‹‹የሐረሪ ሕዝብ ክልል›› መባሉ ቁርጥ ባለ አነጋገር የሐረሪ ድርሻ ለማለት የተፈለገ ያህል ያስገርማል፡፡ ሕገ መንግሥቱ ውስጥ በዚህ መልክ ይቀመጥ እንጂ ክልሎቹን የሚገዙት ብሔርተኛ ፓርቲዎች ሰዎች፣ መንግሥቶቻቸውም፣ ባለሥልጣኖቻቸውም ሲናገሩም ሲጽፉም ‹‹ብሔራዊ ክልል›› ማለታቸው የተለመደ ነው፡፡ ይህ የትናንት የሕወሓት/ኢሕአዴግ ዘመን ‹‹አስደናቂ›› ታሪክ አይደለም፡፡ ዛሬም በለውጡና በሽግግሩ ውስጥ በራሱ በለውጡ አመራር ውስጥ ሳናውቀው፣ ሳይታወቀን የምናጠናክረው፣ እንደ ክፉ አመል አልለቀን ያለ ክፉ ልምድ ነው፡፡ አንድ ምሳሌ ልጥቀስ፡፡ ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) አሁን ሳምንታዊ ያደረጉትን ‹‹ከክልል ፕሬዚዳንቶችና ከምርጫ ቦርድ ጋር›› የሚያካሂዱትን የምርጫ ቅድመ ዝግጅት ግምገማ ገና እንደ ጀመሩ የካቲት 17 ቀን 2013 ዓ.ም. ባስተላለፉት የፌስቡክ ገጽ መልዕክት ላይ፣

‹‹ዛሬ ጠዋት ከፌዴራልና ከክልል አመራሮች ጋር ፊታችን ስለሚካሄደው ምርጫ ተወያይተናል፡፡ የመንግሥትና የፓርቲ ሥራዎችና ኃላፊነቶች አንድ ተደርገው እንዳይቆጠሩ ግልጽ መለያዎችን አስቀምጠናል፡፡ በዚህም ምርጫ የመንግሥት ኃላፊነት፣ ሰላማዊ፣ ነፃና ፍትሐዊ ምርጫ እንዲካሄድ ማድረግ ነው፡፡ በዚህ መሠረት፣ የክልል ብሔራዊ መንግሥታትም በምርጫው ሒደት ተወዳዳሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች ውጤታማ ተሳትፎ እንዲያደርጉ ለማገዝ ቁርጠኝነትን አሳይተዋል፡፡››

በማለት ልምዱ ምን ያህል ገና እንደተጫነን አሳይተውናል፡፡ የመለመዱ ብዛት፣   በሕገ መንግሥቱ ውስጥ ‹‹ብሔረ ክልል›› ተብሎ የተጻፈ እስኪመስለን ህሊናችንን ተጭኖናል፣ ሕገ መንግሥቱን እስከ ማመሳከር ድረስ፡፡

‹‹የትግራይ ብሔራዊ ክልል››፣ ‹‹የሶማሌ ብሔራዊ ክልል››፣ ‹‹የኦሮሚያ ብሔራዊ ክልል››፣ ወዘተ እየተባለ ሲነገር ቁልጭ ብሎ ስለይዞታ መወራቱ ነው፡፡ እነዚህን ይዞታዎች የሚገዙት ብሔርተኛ ቡድኖች አጠራርም ባለ ‹‹ይዞታው››ን ሕዝብ የሚያሳውቅ ነው፡፡ የሚገርመው ታዲያ ‹‹ብሔራዊ ክልል›› የተሰኘው አጠራር በደቡብ ሕዝቦች ክልልም ላይ የተለመደ መሆኑ ነው፡፡

ሌላም የሚደንቅ ነገር አለ፡፡ በኢሕዴን ውስጥ የነበሩ አማራ ፖለቲከኞች ወደ ብሔረ አማራ ንቅናቄነት ወርደው በዚያው መቅለጣቸው፣ ነባር የብሔር ጭቆና ቁስልና እህህታ የሌለባቸው መሆኑ ብርታት እንኳ ሆኗቸው የሚገዙት ክልል ኅብረ ብሔራዊ ግቢ የመሆኑን እውነታ ውስጣዊ የብሔረሰቦች አስተዳደሮች በመፍጠርና ከአማርኛ ውጪ በአገውኛ፣ በኦሮሚኛና በትግሪኛ ሥርጭት በማካሄድ እንደገለጹ ሁሉ፣ የክልሉንም የፓርቲያቸውንም መጠሪያ አርመው በአስተዳደር ግቢያቸው ውስጥ ያሉ ሕዝቦችን ኦሮሞ ነሽ ትግሬ ብሎ ያላስቀረ፣ ሁሉንም አካታች የፓርቲ ባህርይ በመያዝ ለቀሪዎቹ ብሔርተኛ ፓርቲዎች አርዓያ ሳይሆኑ መቅረታቸው ለምን የሚያሰኝ ይመስለኛል፡፡

የኢትዮጵያ መላ ሕዝቦች የዴሞክራሲ አገዛዝ ግንባታ ዕድል የተስተጓጎለው በብሔር የተደራጀው ሕወሓት/ኢሕአዴግ ሠራዊቱን የአገሪቱ የታጠቀ ኃይል ማደራጃ ሲያደርግ ነበር፡፡ ከዴሞክራሲ በመለስም፣ አገሪቱ ባላት የሙያና የዕውቀት አቅም ሙስናን እየታገሉ ዕድገትን የማራመድ አቅሞች ክፉኛ የመጎሳቆልና የመባከን ቀውስ ውስጥ የገቡትም፣ የከተማ ኢኮኖሚና ማኅበረሰብ ይቅርና የረባ ትምህርት ቀመስ እንኳ ያልፈጠሩ ብሔረሰቦች ራሳቸውን የቻሉ ክልል ሲደረጉ፣ በሌሎች ሻል ያለ አቅም ባለባቸው አካባቢዎችም ቢሆን፣ አድርጉ የተባሉትን ለማድረግ የሚመቹ እበላ ባዮችን እያግበሰበሱ በ‹‹አብዮታዊ ዴሞክራሲ›› ማጥመቅ ሲካሄድና ከበረሃ የመጡ ታጋዮችን ከአቋራጭና ከሩጫ ሥልጠና/ትምህርት ጋር ወታደራዊ ባልሆኑ አውታራትም ውስጥ መሰግሰግ ሲመጣ ነበር፡፡ ሐሰተኛ የትምህርት ማስረጃ ማቅረብ ከደርግ ጊዜ በበለጠ በሩ ወለል ያለለትም የአቋራጭና የጥድፊያ ትምህርት ሲጀመርና ለወራት ሳይማሩ ለፈተና መቅረብና የይስሙላ ማሟያ ፈተና ወስዶ ማለፍ፣ በመደበኛ ትምህርት ቤቶች ውስጥ ‹‹ፍትሐዊ መብት›› ሲደረግ ነበር፡፡

ብሔርተኛ ቡድኖች በቻርተራዊ/ሕገ መንግሥታዊ የክልል ይዞታዎች ገዥ ሲሆኑና ክልሎች ውስጥ ክፍልፋይ ብሔርተኝነት እየተስፋፋ ሲሄድ፣ በዚያው ልክ የዕውቀትና የሙያ ብቃት የለሽነት ጎሰኛ አድላዊነትን ተገን አድርጎ መሹለክለክ ቻለ፡፡ ‹‹ትምክህተኞች››ን ከጥቅምና ከእኩል መብት በመግፋትና የጭቁን ብሔረሰቦችን ያለፈ ተበዳይነትን በማካካስ ሽፋን ውስጥ ተጠያቂነት የሌለበት ዘረፋም እየተባዛ ሄደ፡፡ በአማራ የተጀመረው መጤ እየተባሉ እስከ መፈናቀል የሄደ መገፋትም በስተኋላ ለትግራዩ፣ ለኦሮሞው፣ ለጉራጌው፣ ለወላይታው፣ ለሶማሌው፣ ለኑዌሩ፣ ለአኙዋኩ፣ ወዘተ ሁሉ የሚደርሰውና ሁሉም አካባቢ የሚፈጽመው ለመሆን በቃ፡፡ በአጭሩ የጎጆ ብሔርተኛ ፖለቲካና ገዥነትን ስሙን ‹‹ዴሞክራሲያዊ ብሔርተኛነት›› አልነው፣ አላልነው በኢትዮጵያ የ27 ዓመታት ልምድ እንደታየው፣ ጎሰኛ አድሏዊነትን በአስተሳሰብም በተግባርም የሚያራባ፣ ለብሔረሰቦች መብትና እኩልነት ዋስትና የማይሆን፣ የሙያ ሥነ ምግባርንም ሆነ የሰውነትና የዜግነት መብቶችን ለፍርድ አቅርቦ የሚያንገላታ ርዕዮተ ዓለም ነው፡፡ በኢትዮጵያ እውነታ የብሔረሰቦች መብቶች መከበርና እኩልነት የሚገኘው፣ ከብሔርተኛ ገዥነትና ከብሔርተኝነት ሳይሆን ከዴሞክራሲና ከዴሞክራትነት መሆኑ ቁልጭ እያለ ወጥቷል፡፡

አማራጮች ሁሉ ተፍረጥርጠው እየወጡ፣ እየተጎለጎሉና እርስ በርስ እየተብላሉ  የተሻለውን ለመምረጥ፣ ስለዚህም የትኛውም የመፍትሔ ሐሳብ የሕዝብን የድምፅ ብልጫ አሸንፎ የአገር ውሳኔ እንዲሆን ለማድረግ፣ ከዚህ በኋላ የቱም ዓይነት የኢትዮጵያ የበላይ ሕግ ወይም ሕገ መንግሥት ማንም በማንም ላይ ያልጫነው ነው ማለትን የመሰለ ወግ ለመቀዳጀት፣ ከሁሉም በፊት ይህን ማድረግ የሚያስችለውን የጨዋታ ሜዳና የጨዋታ ሕግ ላይ መስማማት፣ ለዚህም መታመንና መገዛት ያስፈልጋል፡፡ ደጋግመን መጀመርያ ዴሞክራሲን እናደላድል፣ ‹‹መጀመርያ የመቀመጫችንን›› እሾህ እንንቀል የምንለው በዚህ ምክንያት ነው፡፡

ይህ ከወር ያነሰ ጊዜ ብቻ የቀረውና በየአቅጣጫው መሰናክል እየተደገሰለት ያለው ምርጫም፣ በሁሉም ኢትዮጵያ ለውጥና የሽግግር ኃይሎች ዘንድ መታየት ያለበት አንዱ ፓርቲ ሌላውን አሸንፎ ሥልጣን ይዞ፣ ይህንንም የሕዝብ ፈቃድ የባለቤትነት መታወቂያ አድርጎ ሕገ መንግሥትና ፌዴራላዊ አደረጃጀቱን እንዲቀይርበት፣ የፈለገውን ለውጥ እንዲያደርግበት ሳይሆን መጀመርያ የዴሞክራሲን ንጣፍ እንዲያደላድልበት ነው፡፡

መጀመርያ ምርጫው በተያያዝነው የኢትዮጵያ የተጨባጭ ሁኔታና በአገር የሕግ ማዕቀፍ ውስጥ ሰላማዊና ዴሞክራሲያዊ ሆኖ እንዲጠናቀቅ እንፈልጋለን፡፡ ምርጫችንን ከአሜሪካ ሴናተሮች ክፉ ዓይን፣ ከአውሮፓ ኅብረት ‹‹ታዛቢ››ዎች ስድ፣ ለከፋና ድፍረት እንዲሰውርልን ጠንክረን እንሠራለን፡፡ በዚህ ምርጫ ማንም አሸነፈ ማንም፣ አሸናፊው ወይም አሸናፊ ፓርቲዎች ከሌሎች የፖለቲካ ቡድኖችና ኃይሎች ጋር ተባብረውና ተረባርበው መጀመርያ ሽግግሩን ዘላቂ ማድረግና እንዲሰምር ማድረግ ነው፡፡ ሕገ መንግሥት ከማረምና ከመለወጥ ለኢትዮጵያ የሚያስፈልጋት ይኼኛው ወይም ያኛው ዓይነት አስተዳደር ነው ብለን ከመወሰናችን በፊት፣ መጀመርያ በዚህ ሽግግር ውስጥ በቅድያሚና ከማንኛውም ነገር በፊት ማከናወን የሚገባን የሁላችንም የጋራና የወል መነሻና መንደርደሪያ አለን፡፡ ይህንን ማደላደልና ከዚህ መነሳትም ለሁላችንም፣ ለፓርቲዎች ሁሉ የሚቀድም ሥራና አደራ ነው፡፡

መጀመርያ አሁን ያለውን የዴሞክራሲ ሽታ ተቋማዊ አድርገን ለመገንባት ተጋግዘን መረባረብ፣ ይህንም ዴሞክራሲያዊ አየር መዋቅራዊ መሠረት ለማስያዝ አብሮ መሥራት ያስፈልጋል፡፡ ምርጫ ውስጥ ገብቶ ‹‹እኔ እሻልሃለሁ›› ለማለት መጀመርያ የምንገኝበት የፖለቲካ አየር መጥራት፣ ትግሉም ወደ ሰከነ የፖለቲካ ኃይሎች ሰላማዊ ግብግብ እንዲሸጋገር ማድረግ የመሰለ ቅድሚያ ሥራ አለብን፡፡ ይህ ምርጫ የዚህ መለማመጃና መዘጋጃ መሆን አለበት፡፡

ከዚህ አኳያ ለምሳሌ በዚህ ምርጫ የሚወዳደሩትንም (አንወዳደርም ያሉትንም) በኩራትና የሲቪክ ግዴታ ላይ በተመሠረተ የልበ ሙሉነት ስሜት ለምንጠይቃቸው፣ ለመሆኑ እናንተ ራሳችሁ በእውነተኛ የሕዝብ ድምፅ ለመለካት ተዘጋጅታችኋል? እውነተኛ የሕዝብ ድምፅ መለኪያንስ አደላድላችኋል? የየራሳችሁን ፓርቲ/ድርጅት ወደ ሰላማዊ የፖለቲካ ተፎካካሪነት ለውጣችኋል? ይህስ የሚጠይቀውን አስተሳሰብና ምግባር ይዛችኋል? ዕውን እናንተ ራሳችሁና እያንዳንዳችሁ የተደራጃችሁት በዴሞክራሲያዊ መርህ መሠረት ነው? ይህ ማለት ‹‹የፓርቲያችን ተግባራት የሚከናወኑት በቀጥታም ሆነ በተወካዮቻቸው አማይነት እኩል መብትና ድምፅ ባላቸው በጠቅላላው የፓርቲው አባላት ነው፡፡ የፓርቲ መሪዎች፣ የአመራር አካላትና የፓርቲ ተቋማት በሙላ በምርጫ ይቋቋማሉ፡፡ ለመራጫቸውም ተጠያቂና በሌሎችም ሊተኩ የሚችሉ ናቸው፤›› ማለት ቤታችሁ ውስጥ በወሬም በተግባርም አለ?

ኢትዮጵያ አገራችን የተደገሰላትን አደጋ በአሸናፊነት መወጣት የምችለው፣ የመጠፋፋት ዕድልንም አምክና ዴሞክራሲን የመቀዳጀት ሥራ ውስጥ የምትገባው፣ መጀመርያ ተደጋግሞ የተገለጸውን አስተማማኝ ጎዳና ስትይዝ ነው፡፡ የአገሪቱ የመከላከያ ኃይል ከመናጋትና ከመፍረስ አደጋ ጋር ሳይገናኝ ወይም ከዚያ ድኖና አገግሞ፣ የአገር የመረጃና የደኅንነት አውታርም የአገርን የልማት ሀብቶች የሕዝቦችን ደኅንነትና ሰላም ነቅቶ ከመጠበቅ ለአንድ ጊዜም ሳይዘናጋና ሳይቋረጥ ከገዥ የፖለቲካ ቡድን ታማኝነትና ደባል አገልጋይነት እንዲላቀቅ፣ በጠቅላላው የተክለ መንግሥቱ ወይም የስቴቱ አውታራት ይበልጥ ገለልተኛ ባህርይን እንዲጎናፀፍ በማድረግ ነው፡፡ ይህንን ከበላዩ ሌላ የሚበልጠው የሌለበትን የአገር ከፍተኛ አደራና ግዳጅ መፈጸም የሚቻለው፣ ብልፅግናና የተቃውሞ ወገኖች በሙሉ በዚህ ምርጫ ዙሪያ ገጥመው አብሮ ለመሥራትና የተክለ መንግሥቱን ድኩምነትና መንሻፈፍ ለመፈወስና ለማቃናት (ዴሞክራሲን ለማደላደል) የተስማሙ፣ ተስማምተውም ለዚህ ግብ የሠሩ እንደሆነ ብቻ ነው፡፡

የትኛውንም ዓይነት ሕገ መንግሥትና ሥርዓት በተግባር እንዲሠራ ለማድረግ (አሁን ያለው ሕገ መንግሥትና ፌዴራላዊ ሥርዓት ሲሠራና ተግባራዊ ሲሆን ለመመስከር፣ እንዲሁም ለመቀየር ጭጭር) ዴሞክራሲንና የሕግ የበላይነትን በአግባቡ ማቋቋም አለብን፡፡ ዴሞክራሲንና የሕግ የበላይነትን መጀመርያ ማደላደል በአግባቡ ማቋቋም አለብን ማለት ውስጥ በርካታ ቁም ነገሮች ተካትተዋል፣ ታዝለዋል፡፡ የሥርዓተ  መንግሥቱ ወታደራዊና ሲቪል ቢሮክራሲ ከፓርቲ ማጠንትና ሰንሰለት መለያየት አለባቸው፡፡ ፓርቲዎች ከባለ ጠመንጃነት መቆራረጥ ይኖባቸዋል፡፡ ፓርቲዎች ከአግላይነት መውጣትና ከዴሞክራሲ አሠራርና እሴቶች ጋር የሚተዋወቁ ሊሆኑ ይገባል፡፡ ፓርቲዎች ወደ ሥልጣን የሚወጡበት ብቸኛው ሕጋዊ መንገድ የፖለቲካና የኢኮኖሚ ፖሊሲያቸውን በነፃነት አወዳድረው በተዓማኒ የምርጫ ሒደት በሚገኝ የድምፅ ውጤት መሆኑን ቅድሚያ ማረጋገጥና ለዚህ መሰናዳት ዝግጅቱንም ማደላደል አለባቸው፡፡

ኢትዮጵያ ወደዚህ ሥርዓት ለመግባት ጉዞውን ጀምራለች፡፡ ግርግር፣ ጥቃት፣ ክህደት፣ የውስጥ ወረራ፣ የውጭ ከበባና ሴራ እየተረባረበ ደንበር ገተር፣  ደፋ ቀና ማለት ቢኖርም፣ ‹‹ለውጡ በትምክህተኞች ተጠልፏል››፣ የለም ‹‹በጽንፈኛ ብሔርተኞች ተጠልፏል›› በሚል የንጭንጭና የጭቅጭቅ፣ እንዲሁም የጥቃት ደባና ሴራ ዓይን ውስጥ ቢወድቅም እንደ ምንም ወደፊት መጓዛችን ገና አልቆመም፡፡ ይህን ምርጫ በሰላምና በሚገባ ማጠናቀቅ፣ ለውጡንና ሽግግሩን ከቅልበሳ ማዳን ኢትዮጵያ አዲስ በተፈጠረው እየከፋም በመጣው የከበባና የሴራ ፖለቲካችን ውስጥ አስቸኳይና የማያወላውል ምላሽ ሊሰጠው የሚገባ የእናት አገር ጥሪ ነው፡፡  

ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊዋን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እንገልጻለን፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የመቃወም ነፃነት ውዝግብ በኢትዮጵያ

ስሟ እንዳይገለጽ የጠየቀችው በአዲስ አበባ ከተማ በተለምዶ የሾላ አካባቢ...

የሲሚንቶን እጥረትና ችግር ታሪክ ለማድረግ የተጀመረው አጓጊ ጥረት

በኢትዮጵያ በገበያ ውስጥ ለዓመታት ከፍተኛ ተግዳሮት በመሆን ከሚጠቀሱ ምርቶች...

የብሔር ፖለቲካው ጡዘት የእርስ በርስ ግጭት እንዳያባብስ ጥንቃቄ ይደረግ

በያሲን ባህሩ በሪፖርተር የኅዳር 9 ቀን 2016 ዓ.ም. ዕትም “እኔ...