Wednesday, March 29, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

የከበሩ ማዕድናትን በምርት ገበያ

- ማስታወቂያ -

ተዛማጅ ፅሁፎች

በዘመናዊ የግብይት ሥርዓት ዕጦት በዘፈቀደ የሚደረግ ግብይት አገርን በተለይም አምራቾችን እንደሚጎዳና አጠቃላይ የግብይት ሥርዓቱን የሚበረዝ ስለመሆኑ ይታመናል፡፡ የአገራችን የግብይት ሥርዓት ብዙ የሚቀረው፣ በአብዛኛው በዘልማድ የሚካሄድ በመሆኑም በየትኛውም ዘርፍ የሚመረት ምርት በሚገባው ዋጋ ተለክቶ ለገበያ እንዳይቀርብ እያደረገ ነው፡፡ ይህ አካሄድ አምራቾች ማግኘት ያለባቸውን ያህል ጥቅም እንዳያገኙና አገርም ከእነዚህ ምርቶች እንዳትጠቀም አድርጓል፡፡ በግብይት ሥርዓት ውስጥ አልፎ የሚካሄድ ገበያ መኖር ደግሞ ከፍተኛ ጠቀሜታ እንዳለው የሌሎች አገሮችን ልምድ ማየት ይቻላል፡፡

የኢትዮጵያ ምርት ገበያ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ወንድምአገኝ ነገራ እንደሚገልጹትም፣ በአገራችን ግብይት ሥርዓት ተበጅቶላቸው በሚገበያዩ ምርቶችና በዘፈቀደ ግብይታቸው በሚካሄዱ ምርቶች መካከል ትልቅ ልዩነት ያለ መሆኑን ነው፡፡ የግብይት ሥርዓት የተበጀላቸው ምርቶች በትክክለኛ የገበያ ዋጋ እንዲሸጡ ከማስቻሉም በላይ እያንዳንዱ ምርት በየደረጃው ዋጋ ወጥቶለት እንዲሸጥ ያስችላል፡፡ ምርትና ምርታማነት እንዲያድግም የራሱ አበርክቶ አለው፡፡ ከሁሉም በላይ ደግሞ ሻጭና ገዥ በዘመናዊ የክፍያ ሥርዓት ታግዘው ግብይት እንዲፈጸሙም ያስችላል፡፡

ከወጪ ንግድ አንፃርም የግብይት ሥርዓት የተዘረጋላቸው ምርቶች በተሻለ ዋጋ እንዲገበያዩ ማስቻሉም የግብይት ሥርዓቱ በበጎ ከሚገለጽበት መካከል የሚጠቀስ ነው፡፡  

በአገር ደረጃ ለሚፈጠር የዋጋ ንረት የግብይት ሥርዓቱ በሥርዓት አለመመራት፣ የተንዛዛ የግብይት ሰንሰለትና በደላሎች መያዙ በመሆኑ የኢትዮጵያ የግብይት ሥርዓት ብዙ ሊሠራበት እንደሚገባ ያሳያል፡፡ በተለይ እንደ ምርት ገበያ ያሉ ተቋማት አሁን ከሚያገበያዩት የግብርና ምርቶች ባሻገር ሌሎችንም ምርቶች በማካተት የግብይት ሥርዓቱን በማዘመን ረገድ ትልቅ ድርሻ ስለሚኖራቸው በዚሁ መንገድ ሊሠሩ እንደሚገባ ታምኖ ጅምር ሥራዎች እየታዩ ነው፡፡

የአገር ምርት በገበያ ዋጋ እንዳይሸጥ ሸማቾችም በተመጣጠነ ዋጋ ምርት እንዲያገኙ ይህ በዘልማድ የሚደረግ ግብይት ኢኮኖሚው ላይ የራሱ የሆነ ተፅዕኖ ያለው በመሆኑ ምርቶቹ በግብይት ሥርዓት እንዲመሩ ማድረግ የግድ እየሆነ ነው፡፡

እንደ አቶ ወንድማገኝ ገለጻ፣ በእነዚህ የግብይት ማዕከላት የግብርና ምርቶች ብቻ ሳይሆኑ ማንኛውንም ምርት ማገበያየት ይቻላል፡፡ የኢንዱስትሪ ምርቶች፣ የማዕድንና ሌሎች ሸቀጣ ሸቀጦች ሁሉ ይገበያያሉ፡፡ የቀንድ ከብት ሳይቀር በእነዚህ ማዕከላት መገበያየት የሚቻል በመሆኑም በኢትዮጵያም ይህ መተግባር ይኖርበታል ብለዋል፡፡  

አሁን በምርት ገበያው ከቡና፣ ሰሊጥና ከመሳሰሉት ምርቶች ሌላ የወጪ ንግድ ምርቶች በዘመናዊ የግብይት ማዕከላት የማያልፉ መሆናቸው ከምርቶቹ ሊገኝ የሚችለውን አገራዊ ጥቅም ከማሳጣቱም በላይ በሕገወጥ መንገድ ከአገር እንዲወጡ እያደረገ መሆኑ ለአገር ትልቅ ጉዳት ነው፡፡

በዚህ ረገድ ኢትዮጵያ በእጅጉ እየተጎዳችበትና መጠቀም እየቻለች የገበያ ሥርዓት ባለመዘርጋቱ ካልተጠቀመችባቸው ዘርፎች መካከል ከሚጠቀሱት መካከል የከበሩ የማዕድን ምርቶች በዋናነት ይጠቀሳሉ፡፡ በተለይ እንደ ኦፓል፣ ኢሜራልድ፣ ሳፋየርና የመሳሰሉ የጌጣጌጥ የማዕድን ምርቶች በሕጋዊ መንገድ ወደ ውጪ ከሚላከው በላይ በሕገወጥ መንገድ ከአገር የሚወጣው ልቆ ይገኛል፡፡

እነዚህ የጌጣጌጥ የማዕድን ምርቶች  በአብዛኛው ግብይታቸው የሚፈጸመው በሕገወጥ መንገድ ነው፡፡ የማዕድናቱን ደረጃ የሚለካ አሠራርም የለም፡፡ ይህ ከታች ብዙ ለፍተው ማዕድናቱን የሚያወጡ አምራቾችን ጨምሮ አገርንም እየጎዳ ስለመሆኑ የኢትዮጵያ ምርት ገበያና የማዕድንና ኢነርጂ ሚኒስቴር ባለሙያዎች ያመለክታሉ፡፡ የማዕድንና ነዳጅ ሚኒስትሩ ታከለ ኡማ (ኢንጂነር) እንደሚገልጹትም፣ በእነዚህ ማዕድናት ግብይት ዙሪያ አሁን ያለው ነባራዊ ሁኔታ አምራቾችን የሚጎዳ፣ አገርም ማግኘት ያለባትን ያህል ጥቅም እንዳታገኝ ያደረገ ነው፡፡

 ሕገወጥ አሠራር የሚጎላበትና ሕጋዊ ያልሆኑ የውጭ ዜጎች ጭምር ማዕድናቱ ወደሚወጡበት ቦታ በመሄድ ከአምራቹ በዝቅተኛ ዋጋ ገዝተው እነርሱ በከፍተኛ ዋጋ እየሸጡ የሚጠቀሙበት እንደነበር አመልክተዋል፡፡

ይህ ብቻ ሳይሆን ከአምራቾች በዱቤ የሚወስዱትን የከበሩ ማዕድናት ሳይከፍሉ የሚቀሩበትም ወቅት በመኖሩ የዘርፉ የግብይት ሥርዓት በብዙ ችግሮች የተፈተነ መሆኑንም ተናግረዋል፡፡

የአገሪቱን የከበሩ ማዕድናት ግብይት በቅርብ የሚከታተሉ ወገኖች ደግሞ እንደ ኦፓል ያሉ ምርቶች እስካሁን ድረስ በዘፈቀደ የሚገበያዩ መሆናቸው እያሳጣ ያለው ጥቅም ከዚህም በላይ የሚገለጽ ነው ይላሉ፡፡

ለዓመታት እንደ ህንድ ያሉ አገሮች የኢትዮጵያን ኦፓል እየወሰዱ በዓለም ቀዳሚ ኤክስፖርተሮች ሆነው መገኘታቸው በኢትዮጵያ በዘርፉ የተደራጀ የግብይት ሥርዓትና ቁጥጥር ያለመኖሩ ነው በማለት ይሞግታሉ፡፡  

እንዲህ ያለውን ትልቅ የገበያ ችግር ለመፍታት ግን አሁን ዓይን የተገለጠ ይመስላል፡፡ የማዕድን ምርቶች ልክ እንደ ቡናና ሰሊጥ እንደ ቦሎቄና አኩሪ አተር፣ በኢትዮጵያ ምርት ገበያ በኩል እንዲያልፉና የማዕድን ግብይቱን መደበኛ ለማድረግ ሲሠራ የነበረው ዝግጅት ተጠናቅቆ ወደ ተግባር ለመሸጋገር የሚያስችል ስምምነት በኢትዮጵያ ምርት ገበያና በማዕድንና ነዳጅ ሚኒስቴር በኩል የመግባቢያ ሰነድ ዓርብ ሚያዝያ 29 ቀን 2013 ዓ.ም. ተፈርሟል፡፡  

የኢትዮጵያ ምርት ገበያ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ወንድማገኝ ነገራና የማዕድንና ነዳጅ ሚኒስትሩ ታከለ ኡማ (ኢነጂነር) በፈረሙት በዚህ የመግባቢያ ሰነድ መሠረት፣ ከዚህ በኋላ ስትራቴጂክ የሚባሉት የከበሩ ማዕድናት ግብይት በኢትዮጵያ ምርት ገበያ በኩል ግብይታቸው እንዲፈጸም የሚያስችል ነው፡፡

የአገሪቱን የማዕድናት ምርት በጥራት በማምረት ለአገር ውስጥ፣ አኅጉራዊና ለዓለም አቀፍ ገበያዎች በስፋት ለማቅረብ እንዲቻል ግብይቱን በዘመናዊ የግብይት ሥርዓት ለማካሄድ የሚያስችል መሆኑን አቶ ወንድማገኝ ገልጸዋል፡፡

የመግባቢያ ሰነዱ ዋና ዓላማ የኢትዮጵያ ምርት ገበያ በዘመናዊ የምርቶች ግብይት ሥርዓት፣ በግብይት ሰንሰለት ቅንጅት፣ በኤሌክትሮኒክ ግብይት ጥራትና በመጋዘን ኦፕሬሽን ያካበተውን ሰፊ ልምድ የማዕድንና ነዳጅ ሚኒስቴር የአገራችንን የማዕድን ዘርፍ በመምራት ካለው ጥልቅ ተሞክሮ ጋር በማጣመር በኢትዮጵያ ዘመናዊ የማዕድናት ግብይት ማዕከልና ሥርዓት መዘርጋት መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡

ይህም በዘርፉ ለተሰማሩ ባለሀብቶችና ኢትዮጵያውያን አምራቾች ግልጽ የሆነ አሠራርን በማስፈን እኩል ተጠቃሚነትን የሚያስገኝና እስካሁን በዘፈቀደ የሚደረገውን የማዕድን ግብይት ወደ ሕጋዊ መስመር የሚያስገባ ነው፡፡

በመግባቢያ ሰነዱ መሠረት ሁለቱ ተቋማት በጋራ የሚያከናውኗቸውን ተግባራት ለተለያዩ ኢትዮጵያ ማዕድናት ለምሳሌ እንደ ኦፓል፣ ኢመራልድ፣ ሳፋየር፣ ታንታለም፣ ሊቲየም፣ ፖታሽ፣ ብረትና ለመሳሰሉት በዓለም አቀፍ ደረጃ ተቀባይነት ያለው የምርት ደረጃ ውሎችን ማዘጋጅት ቅድሚያ ተሰጥቶ የሚሠራ ይሆናል፡፡ ለብሔራዊ የማዕድን ግብይት የሁለቱንም ተቋማት የሰው ኃይል፣ ላቦራቶሪዎችና ተቋማዊ አቅም በመጠቀም የግብይት አሠራሮችን፣ ሞዴሎችን፣ የሥራ ሒደቶችን፣ ደንብና መመርያዎችን መቅረፅም የስምምነቱ አንድ አካል ነው ተብሏል፡፡

በምርት ገበያው የሚከናወነውን የማዕድን ግብይት በቀላሉ ለመቆጣጠር እንዲቻል የማዕድንና ነዳጅ ሚኒስቴርን የቁጥጥር ማዕቀፍ የመከለስ ሥራ እንደሚሠራ የተገለጸ ሲሆን፣ ለዚህ ግብይት በሚስማማ ደረጃ የተለያዩ ፖሊሲዎች ይቀረፃሉ፡፡ የማዕድን ግብይትም ዲጂታላይዝ የማድረግና የኢትዮጵያ ምርት ገበያ የግብይት መድረክን በመጠቀም የኢትዮጵያ ማዕድናት እንደ ምሥራቅ አፍሪካና የአፍሪካ ነፃ ገበያ የመሳሰሉ ገበያዎች ላይ በቀላሉ እንዲገቡና ተወዳዳሪ እንዲሆኑ የሚያስችል ስለመሆኑ አቶ ወንድማገኝ ገልጸዋል፡፡

በማዕድን ዘርፍ ውስጥ ያሉ ተጠቃሚዎችን በጥራት ደረጃ አጠባበቅና ስለዓለም አቀፍ ግብይት ደረጃ አቅማቸውን ለመገንባት ሥልጠና መስጠትና አገር ውስጥና ዓለም አቀፍ የማዕድናት ዋጋና ሌሎችንም መረጃዎች መሰብሰብ፣ መተንተንና ለተጠቃሚዎች ማሠራጨት የመሳሰሉ ተግባራት እንዲከናወኑ በማድረግ ግብይቱን ለማስጀመር ታቅዷል፡፡

በስምምነቱ መሠረት አስፈላጊው ዝግጅት ከተደረገ በኋላ በወራት ውስጥ ወደ ሥራ ይገባል ተብሎ የሚጠበቀው ይህ የግብይት ሥርዓት ዘርፍ ብዙ ጠቀሜታ ይኖረዋል፡፡

የግብይት ሥርዓቱ በዋናነት ተፈጻሚ የሚሆነው ስትራቴጂ ተብለው በተለዩት ኦፓል፣ ኢመራልድ፣ ሳፋየር፣ ታንታለምና የመሳሰሉት ላይ ነው፡፡

በማዕድን ሚኒስቴር የክልሎች ባለድርሻ አካላት ኢንዱስትሪ ትስስር ዳይሬክተር አቶ ጅክሳ ኪዳኔ እንደገለጹት ደግሞ፣ ስትራቴጂካል ተብለው ከተለዩት ከእነዚህ የከበሩ ማዕድናት ሌላ ወደፊት የሚያስገኙት ጠቀሜታ ታይቶ መንግሥት በመመርያ ሌሎች ማዕድናትንም በምርት ገበያው በኩል እንዲገበያዩ ያደርጋል፡፡

‹‹ይህንን ግብይት በዓለም አቀፍ ደረጃ ተቀባይነት ባለው አሠራር ለመተግበር ኢትዮጵያ ምርት ገበያ በቂና አስተማማኝ ተቋማዊ አቅም አለው፤›› ያሉት አቶ ወንድማገኝ፣ በተለያዩ የኢትዮጵያ አካባቢዎች የተሟላ የምርት ጥራት መፈተሽና ደረጃ መስጫ ላቦራቶሪና አደረጃጀት ያላቸው 25 የምርት መቀበያ ቅርንጫፎች እንዲሁም በዋናው መሥሪያ ቤትና በቅርቡ የሚከፈቱትን ጨምሮ አምስት ክላላዊ የኤሌክትሮኒክ ግብይት ማዕከላትን የሚጠቀም መሆኑ ተገልጿል፡፡

ኢንጂነር ታከለ በበኩላቸው፣ የኢትዮጵያ ምርት ገበያ የማዕድን ምርቶቹ ያለባቸው አካባቢዎች ምርቶቹን ለመቀበል የሚያስችሉ ማዕከላት የሚገነቡ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ እነዚህ ማዕድናት በተለይ እንደ ኦፓልና ሳፋየር ማዕድናት በሚመረቱበት አካባቢዎች ምርት ገበያው ቅርንጫፍ ለመክፈት የሚያስችለውን ግንባታ ሥራዎች ስለመጀመሩ ገልጸዋል፡፡

ግብይቱ ከተጀመረ በኋላ ያለ ችግር እንዲቀጥል በቂ የኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ አጠቃቀም፣ ለ13 ዓመታት የተደራጀ አስተማማኝ የመረጃ ቋት፣ የገበያ መረጃ ሥርጭት፣ ከሁሉም የንግድ ባንኮች ጋር በመረጃ መረብ የተሳሰረ የክፍያና ርክክብ ሥርዓት አለን ያሉት አቶ ወንድማገኝ፣ የሠለጠነ የሰው ኃይል አደረጃጀትም ሥራውን በወራት ውስጥ ለመጀመር ያስችለናል ይላሉ፡፡

ለረዥም ዓመታት ልምድ ያላቸው አሜሪካና የእስያ አገሮች ምርት በገበያዎች ያደጉት ጥቂት የግብርና ምርቶችን ከማገበያየት ተነስተው እንደሆነ የገለጹት አቶ ወንድማገኝ፣ የኢትዮጵያ ምርት ገበያም የማቋቋሚያ አዋጁን ለማሻሻል በወጣው አዋጅ 1050/2009 መሠረት ከግብርና ምርቶች ውጪ ያሉ ውሎችን በማጥናት ሊያገበያይ እንደሚችል ተናግረዋል፡፡

የማዕድናት ግብይት በዘመናዊ የግብይት ሥርዓት ሲከናወን ተጨማሪ የሥራ ዕድል ለመፍጠር፣ በጥራት የሚያመርቱ አምራቾች የተሻለ ገቢ እንዲያገኙ ለማድረግ፣ ውጭ ምንዛሪ ለመጨመርና በሕግና በዕውቀት የሠለጠነ ተገበያይ አፍርቶ ተወዳዳሪነቱን ለማሳደግ ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንደሚኖረው ገልጸዋል፡፡

የአገሪቱን የማዕድን ምርት እንዲህ ባለው ሁኔታ እንዲገበያይ ማድረጉ ከፍተኛ ጠቀሜታ የሚሰጥ ስለመሆኑ ተጨማሪ ማብራሪያ የሰጡት ኢንጂነር ታከለ፣ በተለይ ግብይቱን ከኢ-መደበኛ ወደ መደበኛ ማምጣት አንዱ እንደሆነና ምርት ገበያው ጋር በቅንጅት የሚሠራው ሥራ የንግድ ሰንሰለቱን የተሻለ ከማድረጉም በላይ አምራቾች የተሻለ ዋጋ እንዲያገኙ ያስችላል ብለዋል፡፡

ይህ ብቻ ሳይሆን ሕጋዊ የግብይት ሥርዓት በመፍጠር ግብይቱን መፈጸሙ እንደአገር ከዘርፉ የሚገኘውን የውጭ ምንዛሪ ከፍ በማድረግ ጉልህ አስተዋጽኦ እንደሚኖረው ኢንጂነር ታከለ አክለዋል፡፡

ከወርቅ ከሚገኘው የውጭ ምንዛሪ በላይ የሚገኝበት እንደሚሆንም ጠቁመዋል፡፡ በአነስተኛ ግራም ከወርቅ የበለጠ ዋጋ ያላቸው ምርቶች በመሆናቸው አሁን ከሚመረተው ወርቅ መጠን በግማሽ ያህል እነዚህ የከበሩ ምርቶች ተመርተው በግብይት ውስጥ ቢያልፉ በአጭር ጊዜ ከዘርፉ የሚገኘውን የውጭ ምንዛሪ 40 በመቶ እና 50 በመቶ ማሳደግ የሚያስችል እንደሆነም ኢንጂነር ታከለ ገልጸዋል፡፡  

አቶ ጅክሳ ደግሞ ይህ ስምምነት ያስገኛል ብለው ከጠቀሱት ይገኝበታል፡፡ የማዕድንና ጌጣጌጥ ግብይት ረዥምና በጣም ውስብስብ የሆነ የማዕድን አምራቾችን ተጠቃሚ ያላደረገ ስለሆነ ይህንን የተወሳሰበ ግብይት ግልጽ በሆነ ገበያ እንዲካሄድ ያስችላል፡፡

ከዚህም ሌላ ማዕድናቱ የት ነው የተመረቱት፣ ማነው ያመረተው፣ ግብይቱ በማን ነበር ሲያካሂድ የነበረው የሚለውንና ሌሎችንም በግልጽ በማስቀመጥ መንግሥትም ተጠቃሚ እንዲሆን የስምምነት ሰነዱ ያግዛል፡፡ በተለይ በከበሩ የጌጣጌጥ ማዕድናት የግብይት ሥርዓት ሕገወጥነት የሚበዛበት ነው፡፡ ኮንትሮባንድ ያለበት ነው፡፡ የውጭ ዜጎች ሳይቀሩ ቀጥታ ሄደው ማዕድኑን ይዘው የሚንቀሳቀሱበት ስለሆነ እንደዚህ ያለውን ሕገወጥ አሠራር እንደሚያስቀር አቶ ጅክሳ ተናግረዋል፡፡

የዚህ ግብይት ሥርዓት መፈጠር አምራቾች የተሻለ እንዲያመርቱ በማድረግም ይጠቅማል፡፡ አምራቾች እስካሁን ዋጋ ተቀባይ እንጂ ወሳኞች ያልሆኑበት በመሆኑ የዚህ ገበያ መፈጠር የድርድር አቅማቸውን ይጨምራልም ብለዋል፡፡

የእነዚህ ስትራቴጂካዊ ማዕድናት ወደ ምርት ገበያው መግባት መንግሥት በአገር ውስጥ የሚገኘውን ገበያ በአግባቡ ለመሰብሰብ ያስችለዋል፡፡ ምክንያም የግብይቱ ተዋንያኖች የት ቦታና እንዴት ማዕድናቱን እንደተገበያዩ ስለሚታወቅ መንግሥት ከዘርፉ የሚያገኘውን ገቢ ያሳድግለታል፡፡

የከበሩ ማዕድናትን በምርት ገበያው በኩል ለማገበያየት የተደረሰበት ስምምነት ላይ ያነጋገርናቸው በዘርፉ የተሰማሩ ተዋንያን ማዕድናት ልክ እንደ ሰብል ምርቶች አይደሉም፡፡ ቅንጣት የምታህል ማዕድን በሚሊዮን የሚቆጠር ዋጋ አላት፡፡ ስለዚህ ይህንን በእምነት እንዴት ማስረከብ ይቻላል የሚል ጥያቄ ያነሳሉ፡፡

በዚህ ጥያቄ ከምርት ገበያ የተገኘው መረጃ፣ እያንዳንዱ ማዕድናት ደረጃ የሚወጣለትና በወጣለት ደረጃ መሠረት ደረሰኝ የሚሰጥ ሲሆን፣ በደረሰኙ መሠረት ግብይቱ ተፈጽሞ ሻጭ ተገቢውን ዋጋ የሚያገኝበት አሠራር እንደሚኖር ጠቅሰዋል፡፡ የማዕድናቱን ደረጃ የሚወስነው ራሱን የቻለ ላቦራቶሪ የሚኖር ሲሆን፣ ይህንን ሊሠራ የሚችል የግልም ተቋም ሊፈጠር የሚችልበት ዕድል እንዳለም ተጠቅሷል፡፡ ይህ የመንግሥት ውሳኔ ግን አጠቃላይ የከበሩ ማዕድናት ግብይትን የሚቀይር ሲሆን፣ ወሳኙ ግን ይህንን የግብይት ሥርዓት ለመፍጠር የሚወጡ አዳዲስ መመርያዎች ይዘት እንደሚወስናቸው የገለጹ አስተያየት ሰጪዎችም አሉ፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች