Sunday, January 29, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -

የተመረጡ ፅሑፎች

‹‹ሥጋ ብርቁ›› እንዳንሆን!

የዋጋ ንረቱ ጉዳይ አሁንም መልሰን መላልሰን እንድንነጋገርበት ግድ ይላል፡፡ ኑሮ ተወዷል፡፡ ገበያ ወጥቶ ለመሸመት ከባድ ሆኗል፡፡ ያልጨመረ ዕቃና የምርት ዓይነት የለም፡፡ ያው እንደተለመደው አብዛኛው ዕቃና ምርት ጭማሪ የታከለበት በዘልማድ ነው ማለት ይቻላል፡፡ አንዳንድ ምርቶች ዋጋ ለመጨመራቸው በተወሰነ ደረጃም ቢሆን ምክንያት ሊኖራቸው ቢችልም፣ ብዙዎቹ ግን ማን ከልካይ አለ? ተብሎ ጭማሪ የተደረገባቸው ናቸው፡፡

በዓሉን ተንተርሰው ጭማሪ የተደረገባቸው ምርቶች መኖራቸው እርግጥ ቢሆንም፣ ለበዓል ተብሎ የተደረገ ጭማሪ ይኼው ሰሞኑንም መቀጠሉን እያየን ነው፡፡ የሥጋ ዋጋን በተለይ ልናይ እንችላለን፡፡

ከዚህ በፊት እጅግ ብዙ ሲባልለት የነበረው የሥጋ ዋጋ አሁን ላይ ዋጋው ተሰቅሎ ወጥቷል፡፡ ባለፈው ሳምንት ቅቤ ያላግባብ ዋጋ ተጨምሮበት ገበያው የጋለው  እጥረት ተፈጥሮ ሳይሆን፣ ተቆጣጣሪ የሌላቸው ደላሎችና ከልክ በላይ ለማትረፍ ይሉኝታ የሌላቸው ነጋዴዎች የፈጠሩት መሆኑን ልብ ይሏል፡፡

አንዱ ቦታ አንድ ኪሎ ቅቤ በ350 ብር ሲሸጥ፣ ሌላ ቦታ ደግሞ እስከ 600 ብር ዋጋ የተጠራበት ምክንያት ይኼው በገበያ ውስጥ ያለከልካይ የማትረፍ ውንብድና ውጤት ነው፡፡ እንደዚሁ ሁሉ አሁንም የሥጋ ዋጋ በዓመት በዓሉ ዋዜማ በነበረ የ‹ከብት ዋጋ ተወደደ› ሰበብ ሁሉም ባለልኳንዳዎች ያሻቸውን ዋጋ ጨምረው ሸጠዋል፡፡ አንድ ኪሎ ሥጋ 700 ብር ድረስ የተቸበቸበበት እንዳለም ስንሰማ ምን እየተሆነ ነው? ማለታችን አልቀረም፡፡ በዚህ ዋጋ አቅሙ ያለው ሊገዛ ይችል ይሆናል፡፡ ምናልባትም በዓል ነውና ግማሽ ኪሎም ገዝቶ ቤቱን ማሽተት የፈለገ አድርጎት ይሆናል፡፡ ከበዓል በኋላ ባሉት ቀናት ግን በዓውደ ዓመት ከብት ተወደደ ተብሎ የተጨመረ የሥጋ ዋጋ በዚያው ቀጥሏል፡፡

እያንዳንዱ ልኳንዳ ቤት በአንድ ኪሎ ሥጋ ላይ በትንሹ አንድ መቶ ብር ጨምሯል፡፡ በአብዛኛው ከ150 ብር እስከ 200 ብር የዋጋ ጭማሪ በማድረግ እየሸጡ ያሉ መኖራቸው ሲታሰብ በአንድ ኪሎ ላይ ይህንን ያህል የዋጋ ጭማሪ መደረጉ ፈጽሞ አግባብ አይሆንም፡፡  

ከሥጋ ግብይት ጋር በተያያዘ ሁሌም እንደሚሆነው ትንሳዔ በዓል በሚደርስበት ጊዜ በዓሉን አስታኮ የዋጋ ጭማሪ ይደረጋል፡፡ ልኳንዳ ቤቶችም ከሁለት ወራት በፊት ሲሸጡበት በነበረው ዋጋ ለመሸጥ ፍላጎት የሌላቸው መሆኑ ከልምድ ይታወቃል፡፡ የአሁኑ የዋጋ ጭማሪ ግን በጣም የበዛና ሠፈር ውስጥ ያሉ በተመጣጣኝ ዋጋ ያቀርባሉ የተባሉ ልኳንዳ ቤቶች ሳይቀሩ ተመካክረው ያደረጉት ይመስል በአንድ ኪሎ ላይ 100 ብር ጨምረው መገኘታቸው ብዙዎችን አስደንግጧል፡፡

የዋጋ ጭማሪያቸው ዋነኛ ምክንያት ከብት ተወደደ ነው፡፡ አዎ በከብት ዋጋ ላይ የተደረገው ጭማሪ ዓመት በዓሉን ምክንያት አድርጎ ነው፡፡ የዋጋ ጭማሪ መኖሩ እርግጥ ነው፡፡ የዋጋ ጭማሪው ግን የተጋነነ አልነበረም፡፡ በከተማው፣ ‹‹አንድ ሰንጋ 150 ሺሕ ብር ተሸጠ›› የምትለዋ ወሬ ሁሉም ጋር ተዳርሳ እንዲህ ከሆነማ እየተባለ ገበያው እንዲግል ሆኗል፡፡

በተባራሪ ወሬ የሚደራው ገበያ የተጋነነውን የሥጋ ዋጋ ተክሎ በዚያው እንዲቀጥል አድርጓል፡፡ የሚፈለገው ይህ ነበርና ተደረገ፡፡ ከበዓሉ በኋላም ይኼው የተጋነነ ዋጋ ቀጠለ፡፡ እንግዲህ አንድ ኪሎ ሥጋ ከተማ ውስጥ ብትዞሩ በአብዛኛው ልኳንዳ ቤቶች ከ350 ብር በታች ማግኘት አይቻልም፡፡ የከብት ዋጋ ከቀደመው ጊዜ  በምን ያህል ጨመረ ተብሎ ቢመረመር ደግሞ አሁን በሥጋ ላይ እየተደረገ ያለውን ያህል የዋጋ ጭማሪ ማድረግ ፈጽሞ የሚገባ አይሆንም፡፡

ከበዓል በኋላ የከብት ዋጋ መቀነሱ እርግጥ ቢሆንም፣ ይህንን ታሳቢ አድርጎ ዋጋ ለማስተካከል ያልተቻለበት ምክንያት ማናለብኝነት ነው፡፡ የልኳንዳ ቤቶችን የተጋነነ ዋጋ በደንብ ለመረዳት ጥሩ ምሳሌ የሚሆነን ሥጋ የሚሸጥባቸው ሱፐር ማርኬቶች ውስጥ አንድ ኪሎ ሥጋ ያውም በተሻለ ልኬት ከ300 ብር በታች እንዲያውም እስከ 250 ብር ድረስ መግዛት የሚቻል መሆኑን ነው፡፡ ይህ የሚያሳየን የልኳንዳ ቤቶች የዋጋ ጭማሪ የተጋነነ ከመሆኑም በላይ አሁንም ጥብቅ ዕርምጃ የማወሰድ ከሆነ በልክ አትርፈው መሥራት የሚሹትን ሁሉ የሚበርዝ መሆኑን ነው፡፡ ይህም ተጠቃሚዎች አቅም ላይ በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ ይሆናል፡፡

አሁንም ተቆጣጣሪ ካለ የልኳንዳ ቤቶችን ያላግባብ ጭማሪ እንዲያስቆምና የገበያውን ሁኔታ እንዲፈትሽ ማሳወቅ ተገቢ ይሆናል፡፡

ከዚህ ጎን ለጎን በብርቱ ሊሠራበት የሚገባውና ከዚህ ቀደምም ተተግብሮ ውጤት የታየባቸውን የሸማቾች ሥጋ ቤቶች ማጠናከር ነው፡፡ ኅብረተሰቡ በአቅሙ ገዝቶ እንዲጠቀም እነዚህ የሸማች ማኅበራት ሥጋ ቤቶች የበለጠ እንዲሠሩ ማድረግ ካልተቻለ አሁን በተያዘው ሁኔታ ብዙው የኅብረተሰብ ክፍል ሥጋ ብርቁ ይሆናል፡፡  

ከዚህም ሌላ ኅብረተሰቡ ከልኳንዳ ቤት ባነሰ ወደሚሸጡ ሱፐር ማርኬቶች በመሄድ የመገብየት ልምዱን ማዳበር ሌላው መፍትሔ ሲሆን፣ ቁርጥ ዋጋ ማውጣትም ሌላ መፍትሔ ሊሆን ካልቻለ ገበያው የጉልበተኞች መጠቀሚያ ሆኖ ይቀጥላል፡፡   

Latest Posts

- Advertisement -

ወቅታዊ ፅሑፎች

ትኩስ ዜናዎች ለማግኘት