Tuesday, November 28, 2023

አሸባሪ ተብሎ የተፈረጀው ‹‹ሸኔ›› ማንነትና የፍረጃውን አፈጻጸም አስፈሪ ያደረጉ ኢሰብዓዊ ጥሰቶች

- Advertisement -spot_img

በብዛት የተነበቡ

የሚኒስትሮች ምክር ቤት ሚያዚያ 23 ቀን 2013 ዓ.ም. ባሳለፈው የውሳኔ ሐሳብ ሕወሓትና ሸኔ የተባሉ የፖለቲካ ድርጅቶች የፖለቲካ ዓላማቸውን ለማሳካት ተደጋጋሚ ጥቃቶችን በንፁኃን ላይ በመፈጸም የሞት የአካልና የሕዝብ ሀብት ማውደማቸውን፣ በዚህም ሳቢያ ማኅበረሰቡ እንዲሸበርና በመንግሥት ላይ እምነት እንዲያጣ አድርገዋል በማለት በፀረ ሽብር አዋጁ ድንጋጌ መሠረት የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በአሸባሪነት እንዲፈርጃቸው ጠይቋል።

የሚኒስትሮች ምክር ቤት ባቀረበው የውሳኔ ሐሳብ ላይ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ሐሙስ ሚያዚያ 28 ቀን 2013 ዓ.ም. ተወያይቶ የቀረበውን የውሳኔ ሐሳብ በአንድ ድምፀ ተአቅቦ ያፀደቀው ቢሆንም፣ የውሳኔ ሐሳቡን በማፅደቅ ሒደት ውስጥ ግን አንድ ጥያቄ ተነስቷል። 

ጥያቄውም በአሸባሪነት እንዲፈረጁ ከተባሉት ድርጅቶች ውስጥ ‹‹ሸኔ›› የተባለው ድርጅት ማን ነው የሚል ጥያቄ ቀርቧል።

ለዚህ ጥያቄ መነሻ የሆነው ከዚህ ቀደም በተደጋጋሚ ለተከሰቱ ግጭቶችና የንፁኃን ሞት መንግሥት ኦነግ ሸኔ የተባለ የታጠቀ ቡድንን ተጠያቂ በማድረጉ፣ የዚህ ቡድን ማንነት አወዛጋቢ በመሆኑና በአሸባሪነት እንዲፈረጅ የተጠየቀው ድርጅት ‹‹ሸኔ›› በሚል ስያሜ መገለጹ በምክር ቤቱ አባላት ላይ ቀደም ሲል በሚያውቁት፣ ‹‹ኦነግ ሸኔ›› ስያሜ እና ‹‹ሸኔ›› ተብሎ በተገለጸው ድርጅት መካከል መደናገር መፈጠሩ ነው።

‹‹ሸኔ›› ማነው በሚል ከምክር ቤቱ ለተነሳው ጥያቄና ሌሎች ጉዳዮች የፌዴራል ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ ጌዲዮን ጢሞቲዎስ (/) ምላሽና ማብራሪያ ሰጥተዋል። 

በሰጡት ማብራሪያም፣ ‹‹‘ሸኔየሚባል ድርጅት ከዚህ በፊት ሕጋዊ ሰውነት ኖሮት የተመዘገበ ቡድን አይደለም። ነገር ግን በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች በተለይም በምዕራብ ኦሮሚያ እንቅስቃሴ እያደረገ ንፁኃን ዜጎች ላይ ጥቃት የሚፈጽም ራሱንየኦሮሞ ነፃነት ሠራዊትብሎ የሚጠራ ታጣቂ ቡድን እንዳለ ይታወቃል፤›› ሲሉ ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ ጌዲዮን (ዶ/ር) የድርጅቱን ማንነት ገልጸዋል።

ይህ ከሆነ ድርጅቱ ራሱን በሚጠራበት ስያሜ በአሸባሪነት እንዲፈረጅ መጠየቅ አልነበረበትምን? የሚል ጥያቄ ተያይዞ መነሳቱ አይቀሬ በመሆኑ ጠቅላይ ዓቃቤ ሕጉም ምላሽ ሰጥተውበታል።

‹‹አንድን ሽብርተኛ ቡድን የግድ ራሱን በሚጠራበት ስም መጥራት የለብህም። አንዳንዴ ራሱን የሚጠራበትን ስም ዕውቅና ስትሰጠው ለእሱ ሌላ ያልሆነውን ማድረግ፣ ወይም ማግዘፍ ሊሆን ይችላል። ስለዚህ በተለምዶሸኔእየተባለ ስለሚጠራ ያንን ተለምዷዊ አጠራሩን መጠቀም የተሻለ ሆኖ ስላገኘነው በዚያ መንገድ እንዲሰየም የውሳኔ ሐሳቡ ቀርቧል፤›› ሲሉ ጌዲዮን (/) ገልጸዋል።

ምክር ቤቱ የቀረበለትን የውሳኔ ሐሳብ ካፀደቀ በኋላ ተመሳሳይ ጥያቄ ከመገናኛ ብዙኃን ባለሙያዎች የቀረበላቸው ጠቅላይ ዓቃቤ ሕጉ በሰጡት ምላሽ፣ በምክር ቤቱ አሸባሪ ተብሎ የተፈረጀው ድርጅት ራሱን ‹‹የኦሮሞ ነፃነት ሠራዊት›› በሚል የሚጠራውና በምዕራብ ኦሮሚያና ሌሎች አካባቢዎች የሚንቀሳቀሰው ቡድን እንደሆነ ተናግረዋል።

ይህ ድርጅት ራሱን በሚጠራበት ስያሜ እንዲፈረጅ ማድረግ ስያሜውን ማፅደቅ በመሆኑ፣ ድርጅቱ በተለምዶ በማኅበረሰቡ ዘንድ በስፋት በሚታወቅበት ‹‹ኦነግ ሸኔ›› የሚል መጠሪያ ውስጥ ‹‹ሸኔ›› የሚለውን በመምረጥ እንዲፈረጅ ማድረጉ የተሻለ ሆኖ መገኘቱን አስረድተዋል።

ይህ ድርጅት በተለምዶ ከሚታወቅበት ‹‹ኦነግ ሸኔ›› የሚለው መጠሪያ ውስጥ ‹‹ኦነግ›› የሚለው ስያሜ በሕግ አግባብ በምርጫ ቦርድ ተመዝግቦ ከሚንቀሳቀስ የፖለቲካ ድርጅት ጋር የሚመሳሰል በመሆኑ፣ ‹‹ሸኔ›› የሚለውን መጠሪያ መመረጡን ጠቅላይ ዓቃቤ ሕጉ ገልጸዋል።

በፀረ ሽብር አዋጁ መሠረት አሸባሪ ተብሎ የተፈረጀ አንድ ድርጅት ስያሜውን ቢለዋውጥም፣ ስብስቡ ወይም ቡድኑ ያው እስከሆነ ድረስ የስም መለዋወጥ አሸባሪነት በሚለው ፍረጃ ላይ ለውጥ እንደማያመጣ ተናግረዋል።

ይህ ድርጅት ‹‹ኦነግ ሸኔ›› ወይም ‹‹ሸኔ›› አልያም ‹‹የኦሮሞ ነፃነት ሠራዊት›› በሚሉ መጠሪያዎች ይታወቅ እንጂ፣ የድርጅቱ አባላት ማንነት በማኅበረሰቡ ዘንድ በግልጽ የሚታወቅ አለመሆኑን፣ የድርጅቱ በአሸባሪነት መፈረጅን ተከትሎ ከዚህ ድርጅት የማይታወቁ አባላት ጋር መገናኘት ወይም በፀረ ሽብር ሕጉ የሚከለከሉ ተግባራትን መፈጸም፣ የወንጀል ተጠያቂነት የሚያስከትል በመሆኑ ነዋሪዎች ላይ ሥጋት ፈጥሯል።

ይኼው ሥጋት በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አንድ አባል ተነስቶ የነበረ ከመሆኑ በተጨማሪምክር ቤቱ ሁለቱን ድርጅቶች በአሸባሪነት ከፈረጀ ከሰዓታት በኋላ የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን በኦሮሚያ ክልል በሕግ ጥላ ሥር የሚገኙ ሰዎች ሰብዓዊ አያያዝን አስመልክቶ ያደረገውን ምርመራ አስመልክቶ ባወጣው ሪፖርት፣ ሸኔ ከተባለው ድርጅት ጋር በተገናኘ በኦሮሚያ ክልል እየተፈጸሙ ያሉ ሰብዓዊ ጥሰቶች ጉዳይ ሥጋቱን እጅግ አሳሳቢ ያደርገዋል ብሏል።

በሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን የምርመራ ሪፖርት ሰቆቃዎች

የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን በኦሮሚያ ክልል 21 የተመረጡ ፖሊስ ጣቢያዎች ላይ ያደረገውን ክትትልና ግኝቶቹን የተመለከተ ሪፖርት ሐሙስ ሚያዚያ 28 ቀን 2013 ዓ.ም. ይፋ አድርጓል።

ምርመራው በተደረገባቸው የኦሮሚያ ክልል የፖሊስ ጣቢያዎች የሚገኙ በርካታ እስረኞች ባልፈጸሙት ወንጀል ተይዘውፍርድ ቤት ሳይቀርቡ ጭምር እየማቀቁ መሆኑን የኮሚሽኑ ሪፖርት ያስረዳል።

‹‹በወንጀል ተጠርጥረው የሚፈለጉ ልጆቻችሁን አምጡ›› በሚል አባት ወይም እናትን ማሰር፣ እንዲሁም ‹‹ባልሽን አምጪ›› በማለት ሚስትን የማሰር ሁኔታዎች መኖራቸውን የሚገልጸው የምርመራ ሪፖርቱ፣ ይህ ተግባር ለወንጀል ድርጊት የግል ተጠያቂነት መርህን (Principle of Individual Responsibility) በመፃረር እየተፈጸመ መሆኑን አመልክቷል።

ከላይ በተገለጸው ሁኔታ የታሰሩ መሆናቸው የገለጹና ጨቅላ ሕፃናትን የሚያጠቡ እናቶችና ነፍሰ ጡር ሴቶችን፣ የሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን የክትትል ቡድን መመልከቱን ሪፖርቱ ይገልጻል። 

በአወዳይ ከተማ ሦስት ሴቶች በወንጀል የሚፈለጉ (በፖሊስ አመራሮቹ አገላለጽ ‹‹የኦነግ ሸኔ›› አባላት) ልጆቻችሁን አቅርቡ በሚል የታሰሩ መሆናቸውን፣ አንዲት ሴት ባልሽን አቅርቢ ተብላ ከሕፃን ልጇ ጋር በእስር ላይ እንደምትገኝ የኮሚሽኑ ሪፖርት ለአብነት ይጠቅሳል።

በተመሳሳይ በአዳባ ፖሊስ ጣቢያ ‹‹በኦነግ ሸኔ›› አባልነት ተጠርጥሮ የሚፈለግ ባሏ ከፖሊሶች በመሰወሩ ምክንያት የታሰረች መሆኑን የገለጸች አንዲት ነፍሰ ጡር፣ ሕፃን ልጇን ይዛ በእስር ላይ እንደነበረች የክትትል ቡድኑ መመልከቱም በሪፖርቱ ተገልጿል። 

በአንዳንድ ፖሊስ ጣቢያዎች (ለምሳሌ ዶዶላ) ‹‹በወቅታዊ ሁኔታ›› የተጠረጠሩ ናቸው የተባሉ ባልና ሚስት ሕፃናት ልጆቻቸውን ይዘው በእስር ላይ እንደነበሩ የኮሚሽኑ ሪፖርት ያመለክታል።

‹‹ወቅታዊ ሁኔታ›› መጠርጠር ማለትከኦነግ ሸኔ ጋር አልያም ከሕወሓት ጋር የተገናኘ መሆኑን ኮሚሽኑ በምርመራው ወቅት ማረጋገጡን በሪፖርቱ ያስረዳል።

‹‹በግንደበረት ፖሊስ ጣቢያ በ’ኦነግ ሸኔ’ አባልነት ተጠርጥረው የሚፈለጉ ልጆቻችሁን አቅርቡ ተብለው የታሰሩ መሆናቸውን የገለጹ ባልና ሚስት የሆኑ ወላጆችን ጨምሮ፣ አራት አባቶችና ሁለት እናቶች በእስር ላይ ነበሩ፤›› የሚለው ይኸው ሪፖርትይህንን ጉዳይ በተመለከተ የክትትል ቡድኑ አንዳንድ የክልሉ የፖሊስ ጣቢያ አመራሮችን እንዳነጋገረ ይገልጻል።

ካነጋገራቸው የፖሊስ ጣቢያ አመራሮችም ተጠርጣሪዎችን ለመያዝ ይኼንን ዘዴ መጠቀም አስፈላጊ ሆኖ መገኘቱን የሚገልጽ ምላሽ ከተወሰኑት እንዳገኘከተወሰኑት ደግሞ የተለየ ምላሽ ማግኘቱን ይጠቁማል።

ለምሳሌ በአዳባ ፖሊስ ጣቢያ በተለይም በወንጀል ተጠርጥረው ከሚፈለጉ ልጆቻቸው ወይም ባሎቻቸው ጋር በተያያዘ የታሰሩ እናቶችን ወይም ባለትዳር ሴቶችን በተመለከተ የፖሊስ ጣቢያው አዛዦች፣ ‹‹ልጆቻቸው ወይም ባሎቻቸው በወንጀል የሚፈለጉ ቢሆኑም፣ ግለሰቦቹ የታሰሩት በወንጀሉ ተሳትፎ ስላላቸውና በግል ስለሚጠየቁም ጭምር ነው፤›› የሚል ምለሽ መስጠታቸውን ሪፖርቱ ያመለክታል።

ይህንን ያልተገባ አያያዝ አስመልክቶ ከተያዙ ሰዎች ለተነሳው ቅሬታ የኦሮሚያ ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ በሰጠው ምላሽየተጠርጣሪዎች ቤተሰቦች ተጠርጣሪዎችን አቅርቡ ተብለው ይታሰራሉ የተባለው ትክክል እንዳልሆነና በምሳሌነት በተጠቀሱት ፖሊስ ጣቢያዎች ያሉት ሰዎች የታሰሩት ራሳቸው ወንጀል ፈጽመዋል በሚል እንጂ፣ ተጠርጣሪዎችን አምጡ በሚል እንዳልሆነ ፖሊስ ጣቢያዎቹ በመገኘት ማረጋገጡን ለኮሚሽኑ እንደገለጸ ሪፖርቱ ያመለክታል።

ይህ ቅሬታ በክትትሉ ወቅት በተለያዩ ፖሊስ ጣቢያዎች በሚገኙ እስረኞች በተደጋጋሚ የተነሳ ጉዳይ እንደ መሆኑና አንዳንድ የፖሊስ ጣቢያዎች ኃላፊዎች (ተወካዮች) ጭምር ዋናዎቹን ተጠርጣሪዎች ለመያዝ ይህንን ዘዴ መጠቀም አስፈላጊ መሆኑን በመጥቀስ አሠራሩን ደግፈው የተናገሩ በመኖራቸው፣ ኮሚሽኑ አሁንም ቢሆን ጉዳዩን በጥልቀት ማጣራት እንደሚያስፈልግ በማመን ምክረ ሐሳቡን አቅርቧል።

ኮሚሽኑ አክሎም፣ ‹‹ይህ አሠራር ሕገወጥ ከመሆኑም ባሻገር ለመብት ጥሰት ተጋላጭ በሆኑ ሴቶችና ሕፃናት ላይ ከፍተኛ አሉታዊ ተፅዕኖ ያለው እንደ መሆኑ በአንክሮ ሊመረመር ይገባዋል፤›› ብሏል።  

‹‹ሸኔ ማነው?›› የሚለውን ጥያቄ የሚያጎላው የኮሚሽኑ ግኝት 

ሁለቱ የፖለቲካ ድርጅቶች በአሸባሪነት እንዲፈረጁ የቀረበው የውሳኔ ሐሳብ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በቀረበበት ወቅት፣ አንድ የምክር ቤቱ አባል ‹‹ሸኔ ማነው?›› በማለት ላቀረቡት ጥያቄ በጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ ጌዲዮን (/) ምላሽ የተሰጠበት ቢሆንምበዚሁ ቀን ተጠሪነቱ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የሆነው የኢትዮጵያ የሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን ያወጣው ሪፖርት ውስጥ፣ ከላይ የተጠቀሰውን ጥያቄ የበለጠ የሚያጎላና ሥጋት የመጫር አንድምታ ያለው ሆኖ ይታያል።

ኮሚሽኑ ባቀረበው ሪፖርት ምርመራ በተደረገባቸው ኦሮሚያ ክልል ፖሊስ ጣቢያዎች ታስረው የሚገኙ ግለሰቦችን ሰብዓዊ መብት የሚጥስ ከመሆኑም ባለፈ፣ ኦነግ ሸኔ ስለሚባለው ድርጅት እውነተኛ ማንነት መደናገርን ሊፈጥር የሚችል እንደሆነ ከታች የተመለከተው የኮሚሽኑ የምርመራ ማሳያ ሊሆን ይችላል።

‹‹ኮሚሽኑ ክትትል ካደረገባቸው የፖሊስ ጣቢያዎች መካከል በሦስቱ (በገደብ አሳሳ ሦስት ሰዎች፣ በዶዶላ ሦስት ሰዎችና በአዳባ አራት ሰዎች) በድምሩ አሥር ተጠርጣሪዎች ያለ ፍላጎታቸው ወደ ሻሸመኔ ከተማ ተወስደው የታጣቂ ወይም የወታደር ልብስ እንዲለብሱ፣ አርቲፊሻል ፀጉር እንዲያደርጉና የተለያዩ የጦር መሣሪያዎችን እንዲይዙ ተደርገው ከዚያ በፊት ከማያውቋቸው ሰዎች ጋር በቪዲዮ ካሜራ መቀረፃቸውን ይናገራሉ፤›› በማለት ኮሚሽኑ ግኝቱን በሪፖርት አቅርቧል

ስለሁኔታው የተጠየቁ የሁለት ፖሊስ ጣቢያዎች ኃላፊዎች እስረኞቹ ወደ ሻሸመኔ መወሰዳቸውን ያረጋገጡ ቢሆንም፣ በካሜራ ስለመቀረፃቸው እንደማያውቁ ለኮሚሽኑ ቡድን መናገራቸውም በሪፖርቱ ተገልጿል። 

የአንድ ፖሊስ ጣቢያ ኃላፊ በበኩላቸው፣ ተጠርጣሪዎቹ መቀረፃቸውን ያመኑ ቢሆንም፣ በቪዲዮ የተቀረፁት ግን የጦር መሣሪያ በመያዝ ሳይሆን፣ ቀደም ሲል በሌላ ቦታ ወንጀል ፈጽመው አሁን ወደሚገኙበት ወረዳ የመጡ በመሆናቸው በፊት ከነበሩበት ወረዳ ጋር በቪዲዮ ኮንፈረንስ በማገናኘት መረጃ ለመሰብሰብ መሆኑን፣ ለኮሚሽኑ የምርመራ ቡድን መግለጻቸውን ሪፖርቱ ያስረዳል።

‹‹በአንዳንድ ፖሊስ ጣቢያዎች በተለይም በገደብ አሳሳ ወረዳ የሚገኙ እስረኞች አንዳንድ የፖሊስ አባላት (በተለይም የልዩ ኃይል አባላት) ሰዎችንለጥያቄ ትፈለጋላችሁበሚል በሌሊት ጭምር ከቤት በመውሰድ በቁጥጥር ሥር ካዋሉ በኋላ ገንዘብ የሚጠይቁ መሆናቸውን፣ የሰጡትን በመልቀቅ ይህንን የማይፈጽሙ ሰዎችን ደግሞየኦነግ ሸኔአባል ወይም ደጋፊ ናችሁ በማለት እንከሳችኋለን በማለት ዛቻና ማስፈራሪያ የሚያደርሱባቸው መሆኑን ያስረዳሉ፤›› ይላል የኮሚሽኑ ሪፖርት።

የኮሚሽኑ የክትትል ቡድኑ ይህንን ቅሬታ በሌላ ገለልተኛ ማስረጃ ማረጋገጥ እንዳልቻለም በሪፖርቱ ተመልክቷል።  የኦሮሚያ ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ ይህንን ጉዳይ በማስመልከት በሰጠው ምላሽ፣ ይህ ሁኔታ እንዳይፈጠር የሚያስችል ጥብቅ የቁጥጥር ሥርዓት መኖሩን በማመልከት ቅሬታው ‹‹ከእውነት የራቀ›› እንደሆነ፣ ያም ሆኖ ቅሬታው በማስረጃ ተደግፎ ከቀረበ ፈጻሚዎችን ለሕግ ለማቅረብ ዝግጁ መሆኑን የሚገልጽ ምላሽ መስጠቱም በሪፖርቱ ተጠቅሷል።

የኮሚሽኑ የክትትል ቡድን ከተለያዩ የፖሊስ ጣቢያ ኃላፊዎች ጋር ባደረገው ውይይት፣ ‹‹በወቅታዊ ሁኔታ›› የተጠረጠሩ ሰዎችን ጉዳይ በተመለከተ ውሳኔ የመስጠት ሥልጣን ያላቸው በዞንና በወረዳ ደረጃ የተቋቋሙ ‹‹የፀጥታ ምክር ቤቶች›› (Mana Maree Nageenyaa) መሆናቸውን መረዳት እንደተቻለም ሪፖርቱ ይገልጻል።

‹‹የፀጥታ ምክር ቤት›› አምስት አባላት ያሉት ሲሆን፣ እነሱም የዞን ወይም የወረዳ አስተዳዳሪ ወይም የከተማ ከንቲባ (ሰብሳቢ) የዞን ወይም የወረዳ የብልፅግና ፓርቲ ሕፈት ቤት ኃላፊ (ምክትል ሰብሳቢ) የዞን ወይም የወረዳ የአስተዳደርናፀጥታ ቢሮ ኃላፊ (አባል) የዞን ወይም የወረዳ ፖሊስ መምርያ ኃላፊ (አባል) የዞን ወይም የወረዳ የዓቃቤ ሕግ ቢሮ ኃላፊ (አባል) መሆናቸውንም ሪፖርቱ ያስረዳል። 

‹‹የፀጥታ ምክር ቤቱ የአካባቢውን ወቅታዊ የሰላም ሁኔታ በመገምገም መወሰድ ስላለባቸው ዕርምጃዎች አቅጣጫ ከማስቀመጥ በተጨማሪ፣ በቁጥጥር ሥር መዋል ያለባቸው ተጠርጣሪዎችን ይወስናል፣ እንዲሁም ከእስር መለቀቅ ያለባቸው ተጠርጣሪዎችን በመለየት ውሳኔ ይሰጣል። በመሆኑም ‹‹በወቅታዊ ሁኔታ›› የተጠረጠሩ ሰዎችን በሚመለከት በፍርድ ቤቶችም ሆነ በዓቃቤ ሕግ የሚሰጡ ውሳኔዎች ተፈጻሚ ለመሆን የምክር ቤቱን ይሁንታ ማግኘት ያለባቸው መሆኑን ከኃላፊዎቹ ገለጻ ለመረዳት ተችሏል፤›› በማለት የሚገልጸው የኮሚሽኑ ሪፖርትይህ አሠራር ከሕግ የሚጣረስ እንደሆነም አመልክቷል። 

ይህ አሠራር ተጠርጣሪዎች ያለ ፍርድ ቤት ትዕዛዝ በቁጥጥር ሥር እንዲውሉ፣ ከታሰሩም በኋላ በሕግ በተቀመጠው ጊዜ ውስጥ ፍርድ ቤት ቀርበው ጉዳያቸው በገለልተኛ ፍርድ ቤት ታይቶ የተፋጠነ ፍትሕ እንዳያገኙ፣ እንዲሁም በፍርድ ቤቶች የሚሰጡ ውሳኔዎች ተፈጻሚ እንዳይሆኑ በማድረግ ሰዎችን በሕግ ከመዳኘት ይልቅ የፖለቲካ ውሳኔዎች ሰለባ እንዲሆኑ ያደርጋል፤›› በማለት ድርጊቱን ይኮንናል።

የኮሚሽኑ የክትትል ቡድን አባላት በተለያዩ ፖሊስ ጣቢያዎች በመገኘት ያነጋገሯቸው እስረኞች በፍርድ ቤት ያገኙት ውሳኔ በፀጥታ ምክር ቤቱ እንዳይፈጸም በመደረጉ፣ ለወራት በእስር ላይ እንዲቆዩ መገደዳቸውንና በዚህም ምክንያት ተጠርጣሪዎች በፍትሕ ሥርዓቱ ተዓማኒነት ላይ ሰፊ ጥያቄ እንዲያነሱ ማድረጉን ሪፖርቱ ይገልጻል። 

‹‹የክልሉ መንግሥት የሕዝብን ሰላምና ደኅንነት የማስጠበቅ ከፍተኛ ኃላፊነት ያለበት መሆኑ ባይዘነጋም፣ ይኼንኑ ኃላፊነት ለመወጣት የሚወሰዱ ዕርምጃዎች በሕገ መንግሥቱ የተቋቋሙ የፍትሕ ተቋማትን ሥልጣንና ተግባርን ያከበሩ መሆን አለባቸው፤›› ሲልሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን በሪፖርቱ አሳስቧል። 

ኮሚሽኑ ይህንን የምርመራ ሪፖርቱን ለኦሮሚያ ክልላዊ መንግሥት የላከ ሲሆንየሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤትም ክትትል እንዲያደርግበት ሪፖርቱ ለሕዝብ ይፋ ከመሆኑ አስቀድሞ እንደላከ ለማወቅ ተችሏል።

የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ሁለቱን ድርጅቶች በአሸባሪነት ለመፈረጅ ባለፈው ሐሙስ ባደረገው ውይይት ላይ አንድ የምክር ቤቱ አባልየድርጅቶቹ በአሸባሪነት መፈረጅን ተከትሎ የሚከናወነው የሕግ ማስከበር ከፍተኛ ጥንቃቄ ካልተደረገበት ንፁኃን ሊጎዱ እንደሚችሉና የድርጅቶቹ መፈረጅ ንፁኃን ዜጎች ላይ ማስፈራሪያ እንዳይሆን ጥንቃቄ መደረግ አለበት የሚል ጥያቄና አስተያየት ሰንዝረዋል።

ለዚህ ጉዳይ ምላሽ የሰጡት ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ ጌዲዮን (ዶ/ር) በሰጡት ምላሽ፣ ይህ የአሸባሪነት ፍረጃ ከተካሄደ በኋላ አፈጻፈሙ በጥንቃቄ ካልተከናወነ በንፁኃን ላይ ጉዳት ሊያደርስ ይችላል የሚለው ሥጋት ተገቢነት ያለው መሆኑን አመልክተውከዚህ አንፃር የዓቃቤ ሕግ ተቋም ጥንቃቄ እንደሚያደርግና ለሕግ አስፈጻሚ አካላትም ስለአፈጻጸሙ ሥልጠና እንደሚሰጥ ተናግረዋል።

spot_img
- Advertisement -

ትኩስ ጽሑፎች

ተዛማጅ ጽሑፎች

- Advertisement -
- Advertisement -