በታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብና በሌሎች አገራዊ ጉዳዮች ላይ ለመምከር አዲስ አበባ የገቡት የአሜሪካ የአፍሪካ ቀንድ ልዩ መልዕክተኛ ጀፈሪ ፊልትማንና የአፍሪካ ኅብረት የወቅቱ ሊቀመንበርና የዴሞክራቲክ ኮንጎ ሪፐብሊክ ፕሬዚዳንት ፊሊስክ ሽስኬዲ ጉብኝት፣ ኢትዮጵያ በግድቡ ድርድር ላይ የያዘችውን አቋም የሚያስቀይር አይሆንም ሲል የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡
የሚኒስቴሩ ቃል አቀባይ ዲና መፍቲ (አምባሳደር) በሳምንታዊ ጋዜጣዊ መግለጫቸው የሁለቱ ከፍተኛ ልዑካን ጉብኝት የድርድሩን አካሄድ በተሻለ መንገድ ሊያፈጥነው ይችላል እንጂ፣ በኢትዮጵያ በኩል ምንም ዓይነት የአቋም ለውጥ አይኖርም ብለዋል፡፡
ማክሰኞ ግንቦት 2 ቀን 2013 ዓ.ም. ማለዳ ወደ አዲስ አበባ የገቡት የዴሞክራቲክ ኮንጎ ሪፐብሊክ ፕሬዚዳንት፣ ከጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድና (ዶ/ር) እና ከፕሬዚዳንት ሳህለ ወርቅ ዘውዴ ጋር ውይይት አካሂደዋል፡፡
በግብፅ፣ በሱዳንና በኤርትራ የነበራቸውን ጉብኝት አጠናቀው ኢትዮጵያ የገቡት የአሜሪካ የአፍሪካ ቀንድ ልዩ መልዕክተኛ ፊልትማን እሑድ አመሻሽ ላይ አዲስ አበባ የገቡ ሲሆን፣ በቆይታቸው የህዳሴ ግድቡን ድርድር በተመለከተ ከምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳዩ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን፣ ከውኃ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስትር ኢንጂነር ስለሺ በቀለ (ዶ/ር)፣ እንዲሁም ከህዳሴ ግድብ ተደራዳሪ ቡድን አባላት ጋር ውይይት አድርገዋል፡፡
ከሦስት ከሳምንታት በፊት የአሜሪካና የአፍሪካ ቀንድ ልዩ መልዕክተኛ ሆነው የተሾሙት ፊልትማን፣ ከአፍሪካ ኅብረትና ከሰብዓዊ ድጋፍ አቅራቢ ድርጅቶች ጋር ይወያያሉ ተብሏል፡፡
ቃል አቀባዩ ኢትዮጵያ ግድቡን በተመለከተ እየተከተለችው ያለውን ‹‹የአፍሪካን ችግር በአፍሪካውያን መፍታት›› የሚለውን አቋም በሚገባ በማንፀባረቅ፣ ‹‹አቋማችንን ይቀበሉታል ብለን እናምናለን፡፡ ይህ አቋማችንም ሁሉንም አሸናፊ የሚያደርግና ሊተገበር የሚችል ነው ብለን እናምናለን፤›› ብለዋል፡፡
ሱዳንና ግብፅ ባለፉት ሳምንታት በከፍተኛ ባለሥልጣኖቻቸው አማካይነት በተደረጉ ጉብኝቶች፣ ኢትዮጵያ ቀጣዩን ዙር የግድቡን ውኃ ሙሌት ከማከናወኗ በፊት በሦስቱ አገሮች መካከል ከስምምነት መደረስ አለበት ማለታቸው ይታወሳል።
በተጨማሪም ክረምቱ እየተቃረበ በመምጣቱ ውኃ የሚያዝበት ወቅት በመሆኑና ውኃ ለመያዝ ከአንድ ወር ያነሰ በቀረበት በዚህ አጭር ጊዜ ውስጥ፣ የማይሆን ድርድር ውስጥ መግባትና ሌላ ነገር ማድረግ እንደማይቻል ቃል አቀባዩ ገልጸዋል፡፡
ይህ በዚህ እንዳለ የአውሮፓ ኅብረት የዘንድሮ ጠቅላላ ምርጫ እንደማይታዘብ ማስታወቁ አይዘነጋም፡፡
ይሁን እንጂ የአውሮፓ ኅብረት የምርጫ ኮሚሽን ባለፈው ሳምንት መጨረሻ፣ በድጋሚ ስድስት አባላት ያሉት የታዛቢ ቡድን ለመላክ መስማማቱን ቃል አቀባዩ ገልጸዋል፡፡
በተጨማሪም ምርጫውን በታዛቢነት ለመሳተፍ ከአሜሪካ ሁለት፣ ከሩሲያ አንድ እንደሚመጡ፣ ከአፍሪካ ኅብረትና ከሌሎችም ለታዛቢነት ወደ ኢትዮጵያ ለመምጣት ማቀዳቸውን ቃል አቀባዩ አስታውቀዋል፡፡