ኢትዮጵያ ሕዝበ ሙስሊሙና ሕዝበ ክርስቲያኑ በጋራ እዚህ ያደረሷት አገር መሆኗ፣ እንደ አዲስ የሚነገር ዜና ወይም ታሪክ አይደለም፡፡ የኢትዮጵያ ሕዝብ የሃይማኖት ልዩነት ሳይበግረው ተጋብቶና ተዋልዶ በፍቅር መኖሩ፣ እንዲሁም በርካታ ዘመናትን የተሻገረ ዕፁብ ድንቅ ፀጋ ባለቤት መሆኑም አዲስ ነገር አይደለም፡፡ ምናልባት ሕዝቡን ለመከፋፈል የሚደረግ ሙከራ አካል ሆኖ መርዝ ለመርጨት ካልሆነ በስተቀር፣ የሕዝቡ የዘመናት ፍላጎት በፍቅር አብሮ የመኖር የጋራ እሴት እንደ አዲስ ነጋሪ የሚያስፈልገውም አይደለም፡፡ ሰሞኑን ሕዝበ ሙስሊሙ በመስቀል አደባባይ የአፍጥር ሥነ ሥርዓት እንደተያዘለት በተለያዩ የመገናኛ ዘዴዎች ሲነገር ሰንብቷል፡፡ ሥነ ሥርዓቱን ለማካሄድ ችግር ማጋጠሙና የኃይል ዕርምጃ እስከ መውሰድ የተፈጠረው ክስተት አሳዛኝ ነው፡፡ የአደባባዩ አለመጠናቀቅ ወይም የፀጥታ ሥጋት እንደ ምክንያት ሲቀርብ፣ የሚመለከተው የመንግሥት አካልና የሥነ ሥርዓቱ አስተባባሪዎች አንድ ዓይነት አቋም በመያዝ መግባባት መፍጠር ነበረባቸው፡፡ ኢትዮጵያዊያን የየትኛውም እምነት አራማጅ ይሁኑ፣ በመስቀል አደባባይም ሆነ በሌላ የሕዝብ የጋራ ሥፍራ ሕግና ሥርዓት አክብረው የመስተናገድ መብታቸው የተከበረ መሆን አለበት፡፡ በአንድ ሥፍራ ሊካሄድ የታሰበ ሥነ ሥርዓት በተለያዩ ምክንያቶች ሳንካ ሲገጥመው፣ ሁሉንም ወገን በሚያግባባ መንገድ ሌላ መፍትሔ መፈለግ የግድ ነው፡፡ ከዚህ ውጪ አንደኛው አካል የተፈጠረውን ችግር ሲያድበሰብስ፣ ሌላኛው ደግሞ በከፍተኛ ብስጭት ውስጥ ሆኖ ሲራገም ለአገር የሚተርፈው ቀውስ ነው፡፡ ቅንነትና መግባባት ካለ ግን የተበላሸውን በይቅርታ በማረም፣ የሰዎችን ደስታ በቀላሉ መፍጠር ይቻላል፡፡ ኢትዮጵያዊያን በገዛ አገራቸው ሲደሰቱ ለታሪካዊ ጠላቶች ክፍተት አይፈጠርም፡፡ የሃይማኖት እኩልነትና ነፃነት በሕግ ዋስትና ማግኘቱ ብቻ ሳይሆን፣ ተቋማዊ ሆኖ በተግባር መረጋገጡ የሚጠቅመው ለአገር ህልውና ነው፡፡
በዚህ ዘመን እያስቸገረ ያለ አንድ ነገር ከሚያግባቡ ጉዳዮች ይልቅ የሚለያዩ ጉዳዮች ላይ ማተኮር በስፋት መለመዱ ነው፡፡ መንግሥት በቀላሉ ሊፈታው የሚችለውን ችግር ራሱ ያወሳስብና ለንትርክ በር ይከፍታል፡፡ ኃላፊነት ይሰማቸዋል ተብለው የሚታሰቡ ወገኖችም ችግሮችን ያለዝባሉ ሲባል፣ እነሱ ራሳቸው ብሶባቸው አቧራ ያስነሳሉ፡፡ የተለያዩ ፍላጎቶች ባሉባት አገር ውስጥ ሁሉም ዜጎች በየትኛውም ሥፍራ እኩል መስተናገድ እንዳለባቸው ግልጽ ሆኖ ሳለ፣ ይህንን ዘመን ተሻጋሪ እውነት ለመካድ የሚፈልጉና አጋጣሚውን ደግሞ ለክፉ ዓላማ ለመጠቀም የሚቅበዘበዙ መብዛታቸው ያሳስባል፡፡ ይህን ጊዜ ነው እንግዲህ ኢትዮጵያዊያን ማስተዋል ያለባቸው፡፡ ትክክለኛውን ነባራዊ ሁኔታ ባለመገንዘብ ልዩነትን የሚያጦዙ ኃይሎችን ማንነት መረዳት አለመቻል፣ አገርን ለታሪካዊ ጠላቶች ቀላል ዒላማ ማድረግ ነው፡፡ በዚህ ጊዜ እንደሚታወቀው ታሪካዊ ጠላቶች ከየአቅጣጫው ተነስተዋል፡፡ ለዚህ እኩይ ፍላጎታቸው አንዴ የብሔር ማንነትን፣ ሌላ ጊዜ ደግሞ ሃይማኖትን እየታከኩ ቀውስ ይፈጥራሉ፡፡ ኢትዮጵያዊያንን እርስ በርስ ለማጣላት ሃይማኖትን መሣሪያ የሚያደርጉ ኃይሎች ሲነሱ፣ ኢትዮጵያዊያን ደግሞ በእኩልነትና በመተሳሰብ አገራቸውን በጋራ መከላከል ይጠበቅባቸዋል፡፡
ልዩነት ሊከበርና ዕውቅና ሊሰጠው የሚገባ የሰብዓዊ ፍጡራን ፀጋ ነው፡፡ ነፃነት ከሚገለጽባቸው ባህርያት መካከል አንዱ ለልዩነት አክብሮት መስጠት ነው፡፡ የሌሎችን ነፃነት ሳያከብሩ ስለራስ ነፃነት መናገር አይቻልም፡፡ አገር የምትገነባውም በዚህ መርህ መሆን አለበት፡፡ ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች እንዲከበሩ የሚወተውቱ ሁሉ፣ ሁሉም እምነቶች በእኩልነት እንዲከበሩ አርዓያ መሆን ይጠበቅባቸዋል፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ ተከባብሮና ተፋቅሮ መኖር አዲስ ነገር አይደለም፡፡ ኢትዮጵያዊያን ከጥንት ጀምሮ ዘመናትን የተሻገሩባቸው የጋራ ማኅበራዊ እሴቶቻቸው የተገኙት፣ በልዩነት ውስጥ በተፈጠሩ የጋራ መስተጋብሮች አማካይነት መሆኑን ማንም አይስተውም፡፡ እነዚህ መስተጋብሮች ልዩነቶች መኖራቸው እስኪዘነጋ ድረስ፣ የኢትዮጵያን ሕዝብ አንድ ላይ አኑረዋል፡፡ በዚህ በሠለጠነ ዘመን የበለጠ የማስቀጠል ኃላፊነት አሁን ያለው ትውልድ ነው፡፡ ትውልዱ የጥንት ኢትዮጵያዊያን ያስተላለፉለትን አኩሪ ቅርስ መጠበቅ ካቃተው፣ የመጪው ትውልድና የታሪክ ተወቃሽ ይሆናል፡፡ ከተወቃሽነት ራሱን መከላከል የሚችለው ለሰላም፣ ለሕግ የበላይነትና ለአብሮነት ራሱን ሲያስገዛ ነው፡፡ ሕዝበ ክርስቲያኑና ሕዝበ ሙስሊሙም በማስተዋል ይመሩ፡፡ ለዚህም ነው ለኢትዮጵያ የሚያስፈልጋት በሰላምና በእኩልነት አብሮ መኖር ነው የሚባለው፡፡
ኢትዮጵያዊያን ልዩነቶቻቸውን በአግባቡ እያስተናገዱ በአንድነት አገራቸውን መገንባት ይችላሉ፡፡ የታሪክ ጠባሳዎችን እያከኩ በማድማት እርስ በርስ ለመተናነቅ ከማድባት ይልቅ፣ ያለፉትን ስህተቶች በጋራ እያረሙና እያስተካከሉ በወንድማማችነትና በእህትማማችነት አብረው መኖር አይሳናቸውም፡፡ ኢትዮጵያዊያን ሃይማኖትን ጨምሮ የየራሳቸው የሆኑ መገለጫዎች ቢኖሩዋቸውም፣ ሁሉንም በእኩልነት የምታስተናግድ ኅብረ ብሔራዊት አገር ለመገንባት አያቅታቸውም፡፡ ለዘመናት እምነት ሳይገድባቸው ተጋብተውና ተዋልደው ታላላቅ ማኅበራዊ እሴቶችን ያፈሩ ኢትዮጵያዊያን፣ ‹ከራስ በላይ ንፋስ› በሚሉ የግጭት ነጋዴዎች ሊበለጡ አይገባም፡፡ ኢትዮጵያን የአንድ ወገን የበላይነት የሚታይባት አገር ለማስመሰል ማሰብም ሆነ መሞከር በዚህ ዘመን አይታሰብም፡፡ ሀቀኛ ኢትዮጵያውያን ይህንን ዘመን ያለፈበት አስተሳሰብም መስማት አይፈልጉም፡፡ ኢትዮጵያ ሁሉም ሃይማኖቶች በእኩልነት የሚስተናገዱባት አገር መሆን እንዳለባት ይታመናልና፡፡ የአንድ ወገን የበላይነት የተጫጫናቸውን አጓጉልና ኋላቀር ትርክቶች በማስወገድ፣ የወደፊቱን የጋራ ብሩህ ሕይወት አመላካች ጉዳዮች ላይ ማተኮር ይገባል፡፡ በታሪክ አንፀባራቂ የሚባሉ ክንውኖችን ብቻ ሳይሆን አስከፊ የሚባሉትንም በጋራ በመቀበል፣ የወደፊቷ ኢትዮጵያን በጋራ ሊገነቡ የሚያስችሉ የመሠረት ድንጋዮችን ማኖር ተገቢ ነው፡፡
ኢትዮጵያ ውስጥ ተቆጥረው የማያልቁ በርካታ ችግሮች እንዳሉ ለማንም እንግዳ ነገር አይደለም፡፡ እነዚህን ችግሮች የሚረዳ ማንኛውም ቅን ዜጋ ባሉት ላይ ሌላ ከመጨመር ይልቅ፣ ችግሮቹ ደረጃ በደረጃ እንዴት ቢፈቱ ይሻላል በማለት ለመፍትሔ የሚረዱ ሐሳቦችን ነው የሚያቀርበው፡፡ ይህ ኃላፊነት የሚሰማው ሰብዓዊ ፍጡር የሚያደርገው ነው፡፡ በሌላ በኩል ግን ከዚህ በተቃራኒ ባሉት ችግሮች ላይ ተጨማሪ ችግሮችን እየቀፈቀፉ፣ አገርን ቁምስቅሏን የሚያበዙ በመበርከታቸው ከግጭት አዙሪት ውስጥ መውጣት አልተቻለም፡፡ ለአገርና ለሕዝብ የሚጠቅሙ አጀንዳዎች የሌሉዋቸው ግለሰቦችና ስብስቦች፣ በቀላሉ ሊፈቱ የሚችሉ ችግሮችን እያጦዙ አገር ያምሳሉ፡፡ በዚህ ጦስም ንፁኃን ሕይወታቸውን ይገብራሉ፡፡ የደሃ አገርና የምስኪን ዜጎች አንጡራ ሀብት ይወድማል፡፡ በኢትዮጵያ ምድር ሁከት፣ ጥቃት፣ ግድያና ማፈናቀል የዘወትር ተግባር እየሆኑ ያሉት፣ ጽንፈኞችና ተባባሪዎቻቸው የግጭት ነጋዴዎች ስለሆኑ ነው፡፡ እንወክለዋለን ለሚሉት ማኅበረሰብ የሚጠቅም ተግባር ከማከናወን ይልቅ፣ በስሙ እየነገዱ ሕይወቱን ያመሰቃቅላሉ፡፡ አማኞችን በማጣላት አገር ለማፍረስ ያሴራሉ፡፡ የዘመኑ ትውልድ በማስተዋል መራመድ ይኖርበታል፡፡ በጠንካራ ተቋማት አማካይነት የሃይማኖት እኩልነት የተረጋገጠባት አገር መገንባት አለበት፡፡
አንድ ችግር ሲያጋጥም እንዴት ተደርጎ ነው መፈታት ያለበት ማለት እንጂ፣ ጠላቶች በቀደዱት ቦይ ውስጥ እየፈሰሱ አገር ማተራመስ ዋጋ ያስከፍላል፡፡ በተለይ የጋራ አገር ለመገንባት በአንድነት መሠለፍ ያለበትን ሕዝብ በእምነት በመከፋፈል ለማባላት የሚሸረበው ሴራ፣ ደመ ፍሉ ወጣቶችን በገዛ ወገኖቻቸው ላይ እጃቸውን እንዲያነሱ ለማድረግ ነው፡፡ በሰላማዊ መንገድ ሊፈቱ የሚችሉ መናኛ ችግሮችን ሰበብ በማድረግ፣ አገር የማፍረሱን ሴራ በሃይማኖት ግጭት ለማሳካት መዶለቱን ማወቅ ያስፈልጋል፡፡ ከዚህ ቀደም የፈሰሰው የንፁኃን ደምና የወደመው ንብረት አልበቃ ብሎ ዛሬም ሌላ ዙር ክተት የሚታወጀው፣ ኢትዮጵያን በማተራመስ ለማፈራረስ ነው፡፡ ሕዝቡን በብሔር የማተራመስ ፕሮጀክት ዓላማ አልፈጥን ሲል፣ ወቅቱን ጠብቆ በዚህ ጊዜ ቀውስ መፍጠር ለምን እንደተፈለገ መንቃት ይገባል፡፡ ሙስሊም ክርስቲያኑ ለዘመናት አንድ ላይ መኖራቸው የማይታወቅ ይመስል፣ ልዩነት በመፍጠር ለማጋጨት ለምን ተፈለገ መባል አለበት፡፡ በዚህ አጋጣሚ የተስተጓጎለው የመስቀል አደባባይ የአፍጥር ሥነ ሥርዓት መከናወኑ በጣም የሚደገፍ ነው፡፡ ኢትዮጵያዊያን የሚያምርባቸው ለአገራቸው በፍቅር አንድ ሲሆኑ ብቻ ነው፡፡ የሃይማኖት እኩልነት ፀጋ እንጂ ፍርጃ መሆን የለበትም!